ከ55ቱ የአፍሪቃ ኅብረት አባል አገራት መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ 44ቱ ከ1.2 ቢሊዮን በላይ ሸማቾች የሚኖረውን ነፃ የገበያ ቀጠና ለመመሥረት ሥምምነት ፈርመዋል። ሥምምነቱ ለአፍሪቃ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ግብይት ወጥ ገበያ ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። 

የአፍሪቃን የርስ በርስ ንግድ ያበረታታል ተብሎ ይጠበቃል

ከኒጀር ዋና ከተማ ኒያሜይ እስከ አዲስ አበባ፣ ከቱኒያዝያዋ ቱኒስ እስከ ሌሴቶዋ ማሴሩ ከ1.2 ቢሊዮን በላይ ለሚሆኑ አፍሪቃውያን ወጥ አኅጉራዊ ገበያ ሊመሰርቱ 44 የአፍሪቃ አገሮች ከሥምምነት ደርሰዋል። መጋቢት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በርዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ሰነዱን ከፈረሙ አባል አገራት መካከል 22ቱ በየአገሮቻቸው ምክር ቤት ካጸደቁት ተግባራዊ ይሆናል። 

ሀገራቱ ስምምነቱን ለማፅደቅ ሰነዱን ከፈረሙበት ጀምሮ 120 ቀናት ተሰጥቷቸዋል። ኪጋሊ ላይ መጋቢት 21 ቀን በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ታዳሚያን ዘንድ ትልቅ ደስታ እና ፈንጠዝያ እንደነበር ፕሮፌሰር መላኩ ጎብዬ ያስታውሳሉ። በዩናይትድ ኪንግደም የሌስተር ደ ሞንትፎርት ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ኤኮኖሚና የሕግ ፕሮፌሰሩ የሥምምነት ሰነዱንም ካረቀቁ የኤኮኖሚ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ፕሮፌሰሩ “አብዛኞቻችን በጣም ትንንሽ አገሮች ነን። አብዛኞቻችን ትንንሽ ገበያዎች ነን። አገራቱ ውስጥ ያለው ኤኮኖሚ ባነሰ እና ገበያው በጠበበ ቁጥር ኩባንያዎቻችን አምርተው የሚሸጡበት የገበያ መድረክ እየጠበበ ለማደግ ያላቸው ዕድል በዛው ልክ እየቀጨጨ ይሔዳል። እኛ ተከፋፍለን በምንቀጥልበት ጊዜ ልክ እስካሁን ሲሆን እንደነበረው የተሻለ ማምረት የሚችሉት ከእኛ ቀድመው በተሻለ መንገድ ማስኬድ በቻሉ አገሮች እንደ ቻይና እንደነ ሕንድ በመሳሰሉት አገሮች የእነሱ የሸቀጥ ማራገፊያ እንሆንና አሁን ሆነን እንዳለንው ማለት ነው አፍሪቃ ውስጥ ያሉ የአምራች ድርጅቶች ከነዛ ጋ መወዳደር ስለማይችሉ ከገበያ የሚወጡበት ሁኔታ ስንፈጥር ነው የቆየንው” ሲሉ ይናገራሉ። 

Afrikanischen Union Fahne (picture alliance/dpa/S. Stache)

ፕሮፌሰር መላኩ”አሁን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በራችንን ለሌሎቹ ከፍተን ከመስጠታችን በፊት መጀመሪያ ከእኛው ውስጥ ለተመረቱ እቃዎች በራችንን እንክፈተው ሌሎቹ ላይ ቀረጥ የምንጥል ከሆነ ከአንድ የአፍሪቃ አገር ወደ ሌላ የአፍሪቃ አገር ስንናገድ እስኪ ያለ ቀረጥ የሚገቡበት ሁኔታ እንፍጠርላቸው፤ ያለ ቀረጥ መግባት ቻሉ ማለት የአፍሪቃ አገሮች ውስጥ ብዙ እቃ ይመረታል ማለት ነው። ብዙ እቃ ተመረተ ማለት ብዙ ሰዎች ሥራ አገኙ ማለት ነው። አንድ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ኩባንያ ካለ፤ ያ ኩባንያ ማምረት እስከቻለ ድረስ 1.2 ቢሊዮን የሚጠጋ ገዢ ሊኖረው ይችላል ማለት ነው።”  ሲሉ ፋይዳውን ያስረዳሉ። 

የአፍሪቃ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመዋዕለ-ንዋይ እና ነጋዴዎች ነፃ እንቅስቃሴን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። የአፍሪቃ ኅብረት የንግድ ቀጠናውን እውን ለማድረግ ከወሰነ ስድስት አመታት ቢያልፉትም ፖለቲከኞቹ ስምንት ዙር ድርድር አስፈልጓቸዋል። የአፍሪቃ ኅብረት እና አባል አገራቱ አኅጉራዊ ትሥሥርን ያቀላጥፋል፤ የክፍለ-አኅጉራዊ የኤኮኖሚ ትብብር ማዕቀፎችንም ሚና ይለያል የሚል ተስፋ አሳድረዋል። 

አኅጉራዊ የንግድ ቀጠና የመመስረቱ ሐሳብ የተበታተነ ገበያ ያላቸው የአፍሪቃ አገራት ረዘም ላሉ አመታት ሲያመነዥኩት የቆየ እንደሆነ በሉክዘምበርግ የማክስ ፕላንክ ማዕከል የጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሔኖክ ብርሐኑ ይናገራሉ። አቶ ሔኖክ በዓለም አቀፍ ሕግ እና ኤኮኖሚ የዶክትሬት ጥናታቸውን በጣልያን ሀገር በሚገኘው ቦኮኒ ዩኒቨርሲቲ እያከናወኑ ይገኛሉ። አብዛኞቹ የአፍሪቃ አገሮች በኤኮኖሚ ለመተሳሰር ያደረጉት ጥረት እስካሁን ሳይሰምር ቆይቷል የሚሉት አቶ ሔኖክ አፍሪቃውያን ተመሳሳይ ምርት ስላላቸው የደራ ግብይት አይኖራቸውም በሚለው አመክንዮ አይስማሙም። የንግድ ቀጠናው እውን ሲሆን 90 ከመቶ በሚሆነው የአፍሪቃ ንግድ ላይ ያለውን ቀረጥ እንደሚቀንስም ይናገራሉ።

Symbolbild Afrika Markt Bunt (P. U. Ekpei/AFP/Getty Images)

የአፍሪቃ አገራት የተለያየ የንግድ ሕግጋት አላቸው። ወደ አገራቸው በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጥሉት ገደብም ሆነ ቀረጥ ወጥነት የለውም። ይኸን ማጣጣም 44 አገራት የፈረሙት የንግድ ቀጠና አንድ ውጥን ነው። የአፍሪቃ አገሮችን የርስ በርስ ግብይት በማሳደግ ይኸ የንግድ ቀጠና የአምራች ዘርፉን ተወዳዳሪ ያደርጋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል። ዛምቢያ፣ ቦትስዋና እና ናሚቢያ ከመፈረም ተቆጥበዋል። ትልቁ ጉድለት ግን የደቡብ አፍሪቃ እና ናይጄሪያ ተዓቅቦ ነው። ሁለቱ አገራት ሥምምነቱን እንዲፈርሙ ማግባባት ቀጣዩ የቤት ሥራ ነው።  ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪቃ የግሉን ዘርፍ ማማከር አለብን የሚል ምክንያት አቅርበዋል።

የአፍሪቃ አገራት የርስ በርስ ንግድ ከአኅጉሪቱ ገበያ 10 ከመቶ ብቻ ድርሻ አለው። አገራቱ ተሳክቶላቸው የንግድ ቀጠናው ከተመሰረተ የአውሮጳ ኅብረትን መንገድ መከተል ይሻሉ። በገቢ እቃዎች ላይ ተመሳሳይ ግብር የማስከፈል፣ የጋራ ገበያ የመመሥረት ግፋ ሲልም አንድ የመገበያያ ገንዘብ የመጠቀም ውጥን አላቸው። ከዛ በፊት ግን አንዳቸው ከሌላቸው ለመገበያየት ጥብቅ ድርድር ማድረግ ያሻቸዋል። ፕሮፌሰር መላኩ እንደሚሉት ድርድሩ እልህ አስጨራሽ እና ውስብስብ ሊሆን ይችላል።

Ruanda Kigali Unterzeichnung Afrikanisches Freihandelsabkommen (Imago/Xinhua/G. Dusabe)

በነገራችን ላይ ባለፈው ወር በኪጋሊው ስብሰባ ለአፍሪቃውያኑ አገሮች የቀረቡት ሶስት ሰነዶች ነበሩ። አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመመስረት የቀረበውን ሰነድ 44 አገሮች ፈርመውታል። በነፃ የመንቀሳቀስ መብትን ለአፍሪቃውያን የሚሰጠውን ሁለተኛ ሰነድ የፈረሙት ግን 30 አገሮች ብቻ ናቸው። ሶስተኛው የኪጋሊ ፕሮቶኮል ሲሆን የ47 አገሮችን ድጋፍ አግኝቷል። አቶ ሔኖክ የነፃ ንግድ ቀጣናው መመሥረት የአፍሪቃ አገሮች መዋዕለ-ንዋይን ለማበረታታት እንደሚያግዛቸው ይናገራሉ። ባለሙያው እንደሚሉት ስምምነቱ የማምረቻ ወጪን ይቀንሳል፤ ከተመረተበት አገር ባሻገር በተመሳሳይ የቀረጥ ክፍያ ተጨማሪ ገበያም ይፈጥራል። የንግድ ቀጠና መመስረቱ ብቻውን ግን ፋይዳ አይኖረውም።
አጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠናቸው 3.4 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ የሚገመተው 55 የአፍሪቃ ኅብረት አባል አገራት የሚመሰርቱት የንግድ ቀጠና ከዓለም ግዙፍ ይሆናል። የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) እንዳለው የንግድ ቀጠናው የአኅጉሪቱን የርስ በርስ ግብይት በ52.3 በመቶ ያሳድጋል። አፍሪቃውያን ውጤቱን ለማየት ፕሮፌሰር መላኩ እንዳሉት ረዘም ላለ ጊዜ መታገስ ይጠበቅባቸዋል። 
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *