“Our true nationality is mankind.”H.G.

የዓለማየሁ ገላጋይ ‹ወሪሳ›፤ ሒሳዊ ንባብ

የ‹ወሪሳ› ታሪክ የሚከናወንባቸው መቼቶች የዘራፊዎቹ ምድር ወሪሳ እና የፀበኞቹ ምድር እሪ በከንቱ እና በጠላትነት የሚተያዩ ተጎራባች መንደሮች ሲሆኑ፣ ሁለቱም የተሠሩባቸው እና ነዋሪዎቻቸውን የሚያስተዳድሩባቸው የየራሳቸው ደንቦች አሏቸው፡፡

ቴዎድሮስ አጥላው – የሥነ-ጽሑፍ ባለሙያና ሐያሲ The Black Lion
‹ወሪሳ› ከዓለማየሁ ገላጋይ የልቦለድ ሥራዎች በአጻጻፍ ስልቱም በዘይቤያዊ ልቀቱም የተለየ የረጅም ልቦለድ ሥራው ነው፡፡ በ1999 ዓ.ም ምናባዊ ተረክን ከምናባዊ ደብዳቤዎች ጋር አዋሕዶ ረጅም ልቦለድ የማዋቀርን ቴክኒክ (Epistolary writing) ተጠቅሞ ‹አጥቢያ›ን አሳትሟል፡፡ በዚህ ድርሰቱ ነቢይ አከል ደራሲ መሆኑን አሳይቷል፡፡

በ2001 ያሳተመው ‹ቅበላ› ደግሞ ዓለማየሁ የድኅረ ዘመናዊ ልቦለዶች መገለጫዎች ተደርገው ከሚጠቀሱት ባሕርያት ሜታፊክሽን (ምናልባት “ዲብ” የሚለውን የግዕዝ ቃል ከልቦለድ ጋር አቀናጅተን “ዲበ-ልቦለድ” ልንለው እንችላለን) የሚባለውን ስልት በልቦለድ ውስጥ ሌላ ልቦለድን በመተረክ አቅርቧል፤ ይኽ ድርሰቱ የዲበ-ልቦለድ ቤተ ሙከራው ነው ማለትም ይቻላል፡፡ ድርሰቱ እኛ ጋር የሚደርሰው ሁለት ምናባዊ ዓለማትን አነባብሮ ነው፡፡ አንደኛው ዓለም ራሱን እውናዊ አስመስሎ ውስጡ ያለውን ዓለም ደግሞ ምናባዊ ሊያደርግብን ይሞክራል፡፡ በልቦለዱ ሆድ ውስጥ የምናገኘውን ልቦለድ የሚተርክልን በአቃፊው ልቦለድ ውስጥ በደራሲነት የምናገኘው ማቴዎስ የተባለ ገፀባህርይ የሁለት ዓለማት ገፀባሕርይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ድርሰቱ በታቃፊው (inscribed) ልቦለድ ያሉትን ገፀባሕርያት፣ ታሪካቸውን እና ዓለማቸውን በአቃፊው ልቦለድ ውስጥ በማምጣት፣ ታቃፊውን እንደ ልቦለድ፣ አቃፊውን ደግሞ እንደ እውናዊ ተረክ እንድንቆጥረው ይታገለናል፡፡

ወደዚህ ትንታኔ የሚገፋፋን ይኼ ዲበልቦለዳዊነት ብቻም አይደለም፡፡ ልቦለዱ በግልፅ ልቦለድነቱን ሲክድ እናገኘዋለን፡፡ በዘመን አይሽሬ ድንቅ ሥራነቱ ሐያሲያንም አንባቢያንም በመሠከሩለት የሳሊንገር ‹The Catcher in the Rye› ውስጥ እንደምናየው የምናባዊነትን ድንበር ተሻግሮ ወደ እውናዊነት የመግባት አመጽ ‹ቅበላ›ም ውስጥ ያጋጥመናል፡፡ ለእዚሁ ድርሰት ውስጥ ከዋና ገፀባሕርያቱ አንዱ “ይኼ ሕይወት ባይሆንና ድርሰት ቢሆን ኖሮ…” ብሎ አበክሮ ይሞግተናል፡፡ (ገፅ 88) ይኸው ገፀባሕርይ ቀደም ባለ የመጽሐፉ ክፍል ድርሰትን እና ደራሲን በመተቸት፣ አንባቢውን ማመንታት ውስጥ ይከታል፡፡ በትረካው ውስጥ ገንኖ የሚሰማው የእሱ ሐሳብ እንደመሆኑ፣ ወይም ትረካው ከዚሁ መንክር ከተባለ ገፀባሕርይ አንፃር እንደመተረኩ ትችቱን የሚሞግት ሐሳብ አናገኝም፡፡ “ደራሲ ሥራው መፍጠር ነው፡፡ ሌላ አይደለም የሚፈጥረው፤ የተቀናበረ ውሸት፣ የተደራጀ ቅጥፈት ነው የሚፈጥረው፡፡ … ደራሲ ትልቅ ቆርጦ ቀጥል ነው፡፡ የቅጥፈት ስልቱ ያልገባው ተራ ሰው ውሸታም፣ ወሬኛ እየተባለ ክብሩ ሲገፈፍ የተሳካለትና በስልት የዋሸው ግን ‘ደራሲ’ ተብሎ ይወደሳል፣” ይላል (ገፅ 61)፡፡

ዓለማየሁ ገላጋይ የአጫጭር ታሪኮች ስብስቡን ‹ኩርቢት› በሚል ገዢ ርዕስ ካሳተመ በኋላ ሦስተኛውን እና በገፅ ካየነው ትልቁን የልቦለድ ሥራውን ‹የብርሃን ፈለጎች›ን አሳትሟል፡፡ እንግዲህ በዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነችንን ድርሰቱን ያቀበለን ከእነዚህ መጻሕፍቱ በኋላ ነበር፡፡

ስለ ‹ወሪሳ› – ማስተዋወቂያ

በህትመት ዘመን ቅደም ተከተል ለደራሲው (ለጊዜውም ቢሆን) የመጨረሻ የሆነው ልቦለዱ፣ ‹ወሪሳ› (የውድቅት ፈለጎች) (2007 ዓ.ም.) በሁለት በጊዜ እና በሥፍራ (በመቼት) በተከፈሉ ክፍሎች፣ በስምንት ምዕራፎች እና በአርባ ንኡሳን ምዕራፎች የተከፈለ፤ ባለ 240 ገፅ መጽሐፍ ነው፡፡ ድርሰቱ ሙሉውን በአንደኛ መደብ ተራኪ የቀረበ ሲሆን፣ ወሪሳ እና እሪ በከንቱ (በዚህ ስም የሚታወቅ ሠፈር የነበረ ቢሆንም ይኽኛው የተለየ ነው) በሚባሉ ምናባዊ መንደሮች ውስጥ፣ በእውናዊውን ዘመን ምናባዊነቱ የጓነውን ታሪክ የሚነግረን ደግሞ፣ የአክስቱን ቤት ሊጠብቅ ድንገት ወሪሳ ወደተባለው ዘራፊነትን መገለጫው ወዳደረገ መንደር የሚገባው እና መውጫ የሚያጣው የአማርኛ መምህር ነው፡፡

የ‹ወሪሳ› ታሪክ የሚከናወንባቸው መቼቶች የዘራፊዎቹ ምድር ወሪሳ እና የፀበኞቹ ምድር እሪ በከንቱ እና በጠላትነት የሚተያዩ ተጎራባች መንደሮች ሲሆኑ፣ ሁለቱም የተሠሩባቸው እና ነዋሪዎቻቸውን የሚያስተዳድሩባቸው የየራሳቸው ደንቦች አሏቸው፡፡ የእነዚህ ዓለማት እውነታ ከምንኖርበት ዓለም (mundane world) እውነታ የተቀዳም ቢሆን፣ የአንድ ማኅበረሰብ መለያ ሆኖ ሲመጣ ግን ቢያንስ የኛ እውነታ ነው ብለን ከምናምነው ጋር ይማታብናል፡፡ ወሪሳዎች የሌብነትን፣ ነጣቂነትን፣ የዘራፊነትን ትክክለኛ ማኅበራዊ እሴትነት እያጠየቁ፣ እሪ በከንቱዎች ደግሞ ወንድ ልጅ ካልተጣላ፣ ካልገደለ፣ ካልተካሰሰ … ምኑን ወንድ ሆነው የሚል ማኅበራዊ እሴት እያወደሱ የሚኖሩ ናቸው፡፡

ተረት ስንቁ የሆነው መምህር ተራኪያችን መጀመሪያ ወደዘራፊዎቹ ወደ ወሪሳዎች ምድር የሚገባው፣ ከአርሲ ወደ አዲስ አበባ ዝውውር ጠይቆ እንደመጣ ነው፡፡ ከዚያም በሕልሙም በውኑም ሲያስበረግገው በሚኖር መላተም ከአካባቢዎቹ እውነታ፣ ታሪክ፣ እና አኗኗር ጋር ተዋውቆ፣ በፍርሃቱ ምክንያት ከአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ጋር እየተመሳሰለም እየተጋጨም ሲኖር ያሳየናል፡፡

ዓለማየሁ ገላጋይ በሁሉም የፈጠራ ሥራዎቹ ከእሱ ዘመን ደራሲዎች በተለየ ለሚጽፍበት ቋንቋ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ትረካውንም ገለጻውንም ለአንባቢው ማሳየት የሚችል ደራሲ ነው፡፡ ወሪሳ ላይ ይህ ችሎታው እና የቋንቋ ትኩረቱ ላቅ ብሎ ታይቷል፡፡ በአማርኛ ልቦለድ ውስጥ ተረት እና ምሳሌዎች የተለያዩ ተግባራት ተሰጥቷቸው ጥቅም ላይ ሲውሉ እናያለን፤ ነገር ግን በወሪሳ ደረጃ የገፀባህርያት ምልልስ እና የተራኪም ማሰላሰል ማድመቂያ እና ሐሳብን እና ስሜትን አጉልቶ ማቅረቢያ መሣሪያዎች ሆነው በስፋት የቀረቡባቸው መጻሕፍት አላጋጠሙኝም፡፡ ዓለማየሁ በተረት እና ምሳሌዎች አማካይነት አንባቢው የድርሰቱን ስለምን እንዲረዳለት ከማገዝ፣ በአገባባቸውም አማካይነት ከማዝናናት ባሻገር ተራኪውን አሰልቺ ለማድረግም ይሆነኝ ብሎ ተጠቅሞበታል፡፡ (ይኼ ምናልባትም ዋና ገፀባሕርይውን ተሸናፊ በማድረግ ለልቦለዱ በአንባቢዎች የሚወደድ፣ የሚደነቅ፣ የሚታዘንለት፣ አርአያ የሚሆን ተጋዳሊ (fictional hero) በመፍጠር ፈንታ ሆነ ብሎ ‹anti-hero› ከመፍጠር ፍላጎት የመነጨ ይሆናል፡፡ ለነገሩ ደራሲው በየትኞቹም የረጅም ልቦለድ ሥራዎቹ አንድን ገፀባሕርይ ለይቶ ለአርአያነት ሲያበቃው አናይም፡፡

በዚህ ጽሑፍ ‹ወሪሳ› በአቀራረቡ የተለየ ሆኖ እንደመምጣቱ እንዲህስ ብናነበው በሚል ከእኔ ንባብ ያገኘኋቸውን ነጥቦች አቀርባሁ፡፡ የዚህ ንባብ ዋነኛ ዓላማውም መጽሐፉ ሊነበብ እና ሊደነቅ (ካስፈለገም ሊተች) ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱን ለአንባቢያን መጠቆም ነው፡፡

ወሪሳ ተቀጣጣቢው (Parodist) ድርሰት
***
በሥነ-ጽሑፍ ትንተና ውስጥ አስቀድሞ ባነሳነው እና ድንበር ሊበጅለት አስቸጋሪ መሆኑ በሚነገርለት የሥነ-ጽሑፍ ድኅረ ዘመናዊነት/ድኅረ-መዋቅራዊነት ምርምር፣ የትኛውም ድርሰት ብቻውን አይቆምም የሚባል ሐሳብ አለ፡፡ ድርሰቶች የሌሎች የተጻፉም ያልተጻፉም ቴክስቶች በይነንባቦች (inter-texts) ናቸው፤ ምልዑ የሚሆኑት አንዳቸው ከሌሎቹ ጋር ሲናበቡ ነው ተብሎ ይነገራል፡፡ አንድ ድርሰት ከሌሎች ቴክስቶች ጋር ከሚዛመዱባቸው መንገዶች አንዱ ቅጥጥብ (Parody) የሚባለውእና ደራሲው የነባር የኢ/ልቦለዳዊ ታሪክን፣ የማኅበረሰብ መዋቅርን፣ የእሴቶችን፣ የድርሰቶችን፣ የተቋማትን፣… ቅርፅ ተውሶ በምናቡ ያመነጫቸውን ትረካ፣ እሴት፣ እውነት፣ ስሜት… የሚያቀርብበት መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ በዓለም ታላላቅ የግጥም ሥራዎች፣ የልቦለድ ድርሰቶች፣ የሃይማኖት እና የታሪክ ጽሑፎች በተቀጣጣቢ ደራሲያን አማካይነት ተለውጠው ይቀርባሉ፡፡ ደራሲያኑ ከሚቀጣጠቡት ቴክስት ጋር ለመቃረን፣ ለቴክስቱ ተውላጠ ቴክስት ለመፍጠር፣ የቴክስቱን ሐሳብ ለመተቸት ወይም ለመሞገት ይሞክራሉ፡፡ ድኅረ ዘመናዊው ቅጥጥብ ሊንዳ ሐቺዎን እንደምትለው ተቀጣጣቢው ድርሰት ቀዳሚውን ድርሰት እያስቀጠለ፣ በምፀቱ ከመንገድ ያስቀረዋል፣ አምሳያው እየመሰለ ልዩነቱን በማሳየት ይገለጣል፡፡

በእኛ አገር፣ ጥናቱ ታትሞ ባላገኘውም፣ አቶ ወንድወሰን አዳነ በግራፊቲ ላይ ባካሔዱት ጥናት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መማሪያ ክፍሎች፣ መፀዳጃ ቤቶች እና ዶርሞች ግድግዳ ላይ የሚጻፉት ጽሑፎች በሚታወቁ አባባሎች፣ ግጥሞች እና የመሳሰሉት ላይ በማሾፍ ሐሳብ የተገለጠባቸው ቅጥጥቦች ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ቅጥጥብ የሚለው ስያሜም የ‹parody› አቻ ሆኖ ሲቀርብ የሰማሁት ከዚሁ ጥናት ነበር፡፡ በዚህ ረገድ በርካታ የአማርኛ ግጥሞች፣ አጫጭር እና ረጃጅም ልቦለዶች ውስጥ ቅጥጥቦችን ልናገኝ እንችላለን፡፡

‹ወሪሳ› ከዳር እስከዳር ለማመን በሚከብዱ፣ ነገር ግን ደራሲው በገነባላቸው አሳማኝ መቼት፣ እና በመቼቱም ደንብ ምክንያት አምነን በምንቀበላቸው ድርጊቶች እና ምልልሶች የተሞላ ትረካ ነው፡፡ የድርሰቱ ገፀባሕርያት አቋመ ቢሱን ተራኪ ብንተወው፣ በሁለት ወገን የቆሙ ናቸው፡፡ አስቀድሞ እንደጠቀስኩት ወሪሳዎች እና እሪ በከንቱዎች ይባላሉ፡፡

እነዚህ ወገኖች ምንም እንኳን በአደባባይ የምንኮንናቸውን፣ በህግም የተከለከልናቸውን፣ ሃይማኖትም የሚያወግዛቸውን ድርጊቶች እንደማኅበራዊ እሴት ይዘው የሚኖሩ ተደርገው ተገልፀዋል፡፡ በየተራ ብናያቸው፡-

‹ወሪሳ›፤ ከስሙ ብንነሳ በራሱ በመጽሐፉ ውስጥ እንደተበየነው “ወረረ፣ ዘረፈ፣ በዘበዘ” ማለት ነው፡፡ መምህሩ መጀመሪያ የሚያገኛቸውን ባልቴት፣ “ይኼ ምኑ ስም ይሆናል? የፌዝ ስም ነው?” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ የአሰያየሙን የፌዝ አለመሆን ገልፀው፣ አካባቢው ወሪሳ የተባለው “የወንዶች ሠፈር ሆኖ” ነው ይሉታል፤ ወዲያውም ነጥቆ መብላት የወንድነት መገለጫ መሆኑን ይነግሩታል:: በወሪሳ ሌብነት ማኅበራዊም ኢኮኖሚያዊም ግዴታ ነው፤ ሌብነት ሕፃናት ከፊደል ጋር የሚያጠኑት፣ ሲያድጉ ሊካኑበት የሚያልሙት፣ ወጣቶች እና አዛውንት እንደሥራ የሚሰማሩበት፣ ዕድሜ እና ጾታ የማይለይ ተግባር ነው፡፡ ጎበዝ ሌባ ይወደሳል፤ ደካማው በወሬ መሃል እንኳን ይረሳል፡፡ በዚህ ማኅበራዊ ሥርዓት ውስጥ ሌብነትን መቃረንም ሆነ በለዘብተኝነት እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ይነወራል፤ ከእኛ ጋር ካልሆናችሁ፣ ከእነሱ ጋር ናችሁ ዐይነት ፅንፈኝነት! ለሚዛናዊነት የሚተው አማካይ ሥፍራ የለም፡፡

እሪ በከንቱዎች፤ መለያቸው ጸብ፣ ግድያ፣ ክስ ነው፡፡ ገድሎቻቸው የግድያ ገድሎች ናቸው፤ ሰላም እረፍት የሚነሳቸው ተደርገው ነው የተቀረፁት፡፡ ስሞቻቸው ሁሉ አምጰርጵር፣ መርጌ፣ ሺ-ትርገጥ፣ አምባጓሮ ጠጅ ቤት፣ ደምስሰውን የመሳሰሉ የጠብ ያለሽ የሚሉ ስሞች ናቸው፡፡ ገዳይነት ከፖሊስ ጣቢያ እንኳን ነፃ ያወጣል፡፡ የእሪ በከንቱዎች ዓለም ጠበኝነት መከበሪያ፣ መታፈሪያ የሚሆንበት ዓለም ነው፡፡

እነዚህ ሁለት ሕዝቦች የሚኖሩባቸውን እሴቶች በአፈታሪኮቻቸው፣ በተረቶቻቸው እና በኬትመጣ ተረኮቻቸው ሲያፀኑ እናያለን፡፡ ለምሳሌ እማማ ጉዶ የሚባሉት ወሪሳዊት መምህሩን አካባቢውን (አገሬውን?) እንዲመስል ሲያበረታቱት ዘመኑን በመተቸት ወሪሳዊውን ፍልስፍና ይነግሩታል፡- “በዛሬ ዘበን ሰው ሁሉ የሰው ፈላጊ ሆኗል፡፡ አሁን ገበያ ሄደህ ለምንድነው ዋጋ አውርድ አታውርድ የምትከራከረው? ብትችል በነፃ ይዘህ ለመምጣት ነው፡፡ ሌላ’ኮ አይደለም፤ ሌብነት በነፃ ገዝቶ መምጣት ነው፡፡ ንግድ ደግሞ ከተቻለ በእጥፍ ሸጦ፣ ስንጥቅ በማትረፍ አስማምቶ መስረቅ ነው፡፡…” (ገፅ 17) እማማ ጉዶ ሌብነት ያገር ነው፤ የወሪሳዊ ብቻ አይደለም የሚሉት ይመስላሉ፡፡

እዚህ የእማማ ጉዶ ንግግር ውስጥ የምናገኘው የራሳችንን እውነት ነው፤ የምንኖርበትን የግብይት ሥርዓት ነው፡፡ እኒሁ ሴት መንደሩ በአያታቸው የፈረስ ስም ስለ መሰየሙ ሲናገሩ፣ አያታቸውን “የፈረስ ስሙን ያገኘው ተዋግቶ አይደለም፤ ዘርፎ ነው፤” ይሉና፣ ዝርፊያን ከውጊያ ጋር ያስተካክላሉ፡፡ የተዋጋ ይዘርፋል፣ የዘረፈ ይዋጋል፤ ሁለቱም የጀግና ሥራ ነው ብለው ያፀናሉ፡፡ (በነገራችን ላይ ደራሲው በተለያዩ የጋዜጣ እና የመጽሔት መጣጥፎቹ፣ በኢትዮጵያ የጦርነት፣ የማስገበር ታሪክ ውስጥ በየጊዜው ቤቱን፣ ከብቱን ሚስቱን ሳይቀር ታሪክ በሚያጀግናቸው ያፄ ጦረኞች የሚዘረፈው ገበሬ እንደሚያሳስበው በተደጋጋሚ አይቻለሁ፡፡ ምናልባት ተዋጊን ከዘራፊ ጋር የማስተካከሉ ሐሳብ የተሰነዘረው ከዚሁ ገደድ በመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡)

በሥነ-ቃል ምርምር፣ ሰዎች “ማኅበራዊ ድርጅቶቻቸውን እና ልዩ ልዩ ባህሎቻቸውን በስነቃል አማካይነት ያጠናክራሉ፡፡ ከልደት እስከ ሞት የሚያከናውኗቸውን ድርጊቶች አስፈላጊነትና ተገቢነት እያሳመኑ ክንዋኔዎቹ እንዳይከስሙ፣ ቀጣይነት እንዲኖራቸው፤” (ፈቃደ፣ ገፅ 18) ለማድረግ በተረትና ምሳሌዎቻቸው፣ በአፈታሪኮቻቸው፣ በቃላዊ ግጥሞቻቸው እና በሌሎቹም ስነቃሎቻቸው አማካይነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላልፏቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በዚህ ረገድ መልካም ሥነ-ምግባሮቻችንን ለማጽናት፣ መጥፎዎቹን ለማረቅ፣ ጀግኖቻችንን ለማወደስ፣ ፈሪዎችን እና ምግባረ ብልሹዎችን ለመገሰፅ፣ ባህላዊ እሴቶችን ለማቆየት በተረቶቻችን፣ በአፈታሪኮቻችን፣ በቃል ግጥሞቻችን፣ በቀረርቷችን ስንጠቀም ኖረናል፡፡ ወሪሳ ይኽንን መዋቅር ወስዶ እሴቶቻችንን ይጠይቃል፡፡

ፊደልን ከመልካም ምግባር ጋር ተምረን የምንወጣበትን ማኅበራዊ ተቋም፣ የቄስ ትምህርት ቤትን የሌቦች መፈልፈያ ጎሬ ያደርግብናል፡፡ በቋንቋችን ውስጥ የኖሩ ተረትና ምሳሌዎቻችን ሳይቀይር እዚሁ የቄስ ትምህርት ቤት አውድ ውስጥ አስገብቶ ራሳችንን እንድንፈትሽ ይገፋፋናል፡፡ ለካ የምንትነታችን መገለጫ የሆነው ሥነ-ቃላችን መልካም ምግባርን ማነጫችን ነው ማለት ጎዶሎ ሐሳብ ነው፤ ተቃራኒውንም ነው፡፡ አያያዙን አይተው ጭብጦውን ቀሙት፣ የዘነጋ ተወጋ፣ ቤታቸውን ሳይዘጉ ሰውን ሌባ ይላሉ፣ አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ … እነዚህ ሁሉ እና መሠሎቻቸው ንጥቂያን ማበረታቻዎቻችንም ናቸው፡፡

ደራሲው የመጣጥፍ ስብስቦቹን ባሳተመበት ‹ኢሕአዴግን እከሳለሁ› መጽሐፉ መጨረሻ ላይ እንዲህ የሚል መላምት አስፍሯል፡- “የማይተዛዘን፣ እርስ በእርስ በጠላትነት የሚጠባበቅ፣ ጨዋነት ያጣ፣ ኢትዮጵያዊ ክብር ያልገባው … ኅብረተሰብ መፍጠር የዚህ ዘመን የሥልጣን ማስጠበቂያ ዘዴ የሆነ ይመስላል፡፡” (ገፅ፣ 231) የቄስ ትምህርት ቤቱ ነጣቂ ትውልድ የማፍራት ትዕይንት ይኽንን ከመሳሰሉ የደራሲው ስጋቶች የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡

የ‹ወሪሳ› ታሪክ ከተረትና ምሳሌዎቹ ጎን ለጎን በተውላጠ ታሪክም (Alternate History) ነው የተገነባው፡፡ ወሪሳዎች እና እሪ በከንቱዎች አያት ቅድመ አያቶቻቸውን ጀግኖች አድርገው ለማሳየት፣ እና የራሳቸውን የጀግና ዘርነት ለማጠየቅ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ በጀግንነት ከሚጠሩ ሰዎች ተርታ ያሰልፏቸዋል፡፡ ነገር ግን ልክ በእውኒቱ ኢትዮጵያ እንደምናየው የሁለቱ መንደሮች ነዋሪዎች በታሪክ ሽሚያ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሁሉም የየራሳቸውን እውነት ይነግሩናል፡፡ አንዱ ታሪክ ቢያንስ አንድ ሌላ ሞክሼ ይኖረዋል፡፡ በአጠቃላይ ታሪካችንን የዝርፊያ ታሪክ የሚያስመስሉ ተውላጠ ታሪኮችን ይሰጡናል፤ በዚህም ወሪሳ ታሪካችንን ይቀጣጠባል፡፡

በርግጥ ደራሲው የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የሰው ልጅ ታሪክ የመናጠቅ ታሪክ ነው የሚል አቋም ያለውም ይመስላል፡፡ በ‹ቅበላ› ልቦለዱ ውስጥ እንዲህ ይላል፡- “የሰው ልጅ በፍቅር እዚህ አልደረሰም፡፡ ዘሩን ያተረፈው በመተሳሰብ አይደለም፡፡ በመናጠቅ፣ በመናቆር፣ በመናቸፍ፣ በራስ ወዳድነት፣ በጥላቻ፣ በመዋጋት፣ በመጋደል፣ በጭካኔ ነው እዚህ የደረሰው፤” (ገፅ 51)፡፡

ለዚህ የእሴቶች መዝቀጥ ደራሲው በቀጥታ ማንንም ተጠያቂ ባያደርግም (ለነገሩ ድርሰቱ በቀጥታ የሚናገረው የለውም)፣ በየዘመኑ የተነሱትን የኢትዮጵያን መንግሥታት በተራዛሚ ሳይተች አላለፈም፡፡ ነገሥታቱን የዘራፊዎቹ አጋሮች አድርጎ የሚተርክልን ለጨዋታ ብቻም አይመስልም፡፡ ዝርዝሩ ውስጥ ላለመግባት ለቅጥጥቡ ግልፅ ምሳሌ የሚሆኑኝን ክፍሎች ልጠቃቅስ፡፡ አሁን ያለውን የፓርቲዎች አመሠራረት ሂደት እና የአሠራር መዋቅር ተጠቅሞ ለዘራፊዎቹም ለጸኞበቹም ከመንግሥት ጋር በአጋር ድርጅትነት የሚሠሩ ፓርቲዎችን ያቋቁምላቸዋል፡፡ “ወህዴድ”፣ “አባር ድርጅት”፣ “መጪው ጊዜ ከወህዴድ ጋር ፍሰሐ ነው” የሚሉትን የፖለቲካ ቃላት፣ የፓርቲዎቹን ድርጅታዊ አሠራር ስናይ የደራሲው ዓላማ ያለሌላ ነጋሪ ይገባናል፡፡ ፖለቲካዊው ቅጥጥብ ራሱን ችሎ በስፋት ሊተነተን የሚገባው ጉዳይ በመሆኑ በዚሁ እንተወው፡፡

እንደ መቋጠሪያ
***
‹ወሪሳ› እንደ ግጥም እምቅ ድርሰት ነው፤ ማኅበራዊውን ሂስ፣ ኢኮኖሚያዊውን ሥጋት፣ ፖለቲካዊውን ትችት በውስጡ አምቆ ይዟል፡፡ በመጽሔት መጣጥፍ ቁመት መጽሐፉን አስተንትኖ መጨረስ አይቻልም፡፡ ይኽ ጽሑፍ መጽሐፉ እንዲነበብ መገፋፊያ ያህል ከሆነ ግቡን እንደመታ እቆጥረዋለሁ፡፡ ጽሑፉን እንደ ጅምር ስፌት እንዲሁ ከምተወው አጠቃላይ ሐሳቦችን ጨምሬ ሁለት ሦስት ቦታ ቋጠር ቋጠር ላድርገው፡፡

ወሪሳ የዓለማየሁ ገላጋይ ቀልድ አዋቂነት፣ በቋንቋ እንዳሻው የመጫወት ብቃት፣ የተረት (የተውላጠ ታሪክም ጭምር) ፈጣሪነት (እንደ ኤዞፕም፣ እንደ ሀዲስ ዓለማየሁም) አቅም የታየበት ድርሰት ነው፡፡ ደራሲው ምስላቸው አንባቢው ዓይነ ልቡና ውስጥ በአካል ገዝፎ የሚመጣ ገፀባሕርያትን የመቅረፅ ችሎታው ይበልጥ ጎልቶ ታይቷል፡፡

በ‹ወሪሳ› አንባቢው አርአያ የሚያደርገው ልቦለዳዊ ተጋዳሊ (fictional hero) ወይም አንባቢው የሚያምነው የተረጋገጠ እውነት የለም፡፡ ዋናው ገፀባሕርይ አንባቢውን የሚያበሳጭ እንጂ የሚወደድም የሚታዘንለትም አይደለም፤ የተተረኩት ልዋጭ ታሪኮችም ሆኑ ተረቶች እንደየተራኪያቸው/ እንደተራቻቸው የተለያዩ መሆናቸውና የድርሰቱ ተራኪም አመዛዝኖ የሚፈርድ አለመሆኑ አንባቢውን ማመንታት ውስጥ ይጥሉታል፡፡

ደራሲው በሌሎቹ ልቦለዶች ውስጥ እንዳደረገው ጊዜን በተምሳሌታዊነቱ ከመጠቀሙ ባሻገር፣ ‹ወሪሳ›ን በምሽቶች እና በውድቅቶች ብቻ መተረኩ የጭብጥ ጥቆማ መስጠቱ ይመስላል፡፡ እንዲያውም ለመጽሐፉ በአማራጭነት በቅንፍ የሰጠው ርዕስ “የውድቅት ፈለጎች” መባሉም ወደ ጭብጡ የሚመራን ፈለግ ነው፡፡

በመጨረሻም፣ ‹ወሪሳ› እንደ ግጥም ተደጋግሞ በተነበበ ቁጥር ሲያነቡት ትርጉሙ እየተስፋፋ የሚሔድ፣ የሚያጫውት፣ የሚያስደንቅ፣ የሚያበሳጭ፣ የሚያሰጋ፣ የሚያስቆጭ… ድርሰት ከመሆኑም በላይ በዘመንኛ የሥነ-ጽሑፍ ጽንሰ ሐሳቦች እና መቅረቢያ ዘዴዎች በስፋት እንዲተነተን የሚጋብዝ ነው፡፡

………………………………………………………………………….
የዋቢ መጻሕፍት ዝርዝር
ዓለማየሁ ገላጋይ፡፡ ቅበላ፡፡ አዲስ አበባ፣ ማኅሌት አሳታሚ፣ 2001 ዓ.ም.፡፡
አጥቢያ፡፡ አዲስ አበባ፣ 1999 ዓ.ም.፡፡
ኢህአዴግን እከሳለሁ፡፡ አዲስ አበባ፣ 2004 ዓ.ም.፡፡
ኩርቢት፡፡ አዲስ አበባ፣ 2004 ዓ.ም.፡፡
ወሪሳ፡፡ አዲስ አበባ፣ 2007 ዓ.ም.፡፡
የብርሃን ፈለጎች፡፡ አዲስ አበባ፣ 2005 ዓ.ም.፡፡
ፈቃደ አዘዘ፡፡ የስነቃል መምሪያ፡፡ አዲስ አበባ፣ 1991 ዓ.ም.፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0