“Our true nationality is mankind.”H.G.

ኢትዮጵያዊነት ሲባል?

ታሪካዊት ኢትዮጵያ (Historic Ethiopia)
ታሪካዊት ኢትዮጵያ የምንለው ክፍል ከ1ኛው መቶ ዓመተ ምሕረት እስከ 19ኛው ምዕት አጋማሽ ገደማ ያለውን ሲሆን፣ ከሞላ ጎደል የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ይዘትና ቅርጽ የተወሰነበት ረዥም ዘመን ነው፡፡

ታሪካዊት ኢትዮጵያ ጥንታዊነቷን ሙሉ በሙሉ ሳትረሳ፣ በአዲስ ሃይማኖት፣ በአዲስ ልሣን፣ አዲስ ሥልጣኔ ለብሳ የታደሰችበት የታሪክ ወቅት ነው፡፡ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ግንዛቤ ገዥ ርዕዮት ሆኖ ወደ ገሃዳዊ ታሪክነት የተተገበረበት ዘመን ነው፡፡ አልፎ አልፎ መሳሳትና ክፍተት ቢያጋጥመንም፣ ኢትዮጵያዊነት በታሪክ ማስረጃዎች በአስተማማኝ የተከተበበት በመሆኑ ስለታሪካዊት ኢትዮጵያ ማንነት ከሞላ ጎደል የጠራ ግንዛቤ አለን፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ በጥንታዊትና ታሪካዊት ኢትዮጵያ ግዛተ መንግሥት መካከል ያለውን ቀጣይነት የሚያረጋግጡልን ማስረጃዎችን ከዘመኑ መባቻ አንስቶ እናገኛለን፡፡ ሄሮዶቱስ ስለ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ከዘገበ ከአራት መቶ ዓመታት በኋላ ግሪካዊው የታሪክ ሊቅ ዲኦዶሮስ ሲኩለስ (ከ90 – 21 ዓ.ዓ) ‹የዓለም ታሪክ› በተሰኘው ዝነኛ መጽሐፉ፣ የኢትዮጵያ አንዱ ክፍል ከግብፅ እስከ መረዌ፣ ሁለተኛው ደግሞ ከመረዌ በስተደቡብ ምሥራቅ የተዘረጋ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ሌላው ግሪካዊ የመልክዓምድርና የታሪክ ሊቅ ስትራቦ (ከ63 ዓ.ዓ – 24 ዓ.ም)፣ ራሱ ግብጽ መጥቶ ሽቅብ በዓባይ ወንዝ ሸለቆ ተጉዞ የኢትዮጵያን አቀማመጥ በተመሳሳይ ሁኔታ ከኤሌፋንታይን እስከ ሕንድ ውቅያኖስ መዳረሻ መሆኑን አስተማማኝ ምስክርነት ሰጥቷል፡፡ ሦስቱም ጸሐፍት ዓባይ ከአንድ የኢትዮጵያ ሐይቅ እንደሚመነጭ ጽፈዋል፡፡

የታሪክና መልክዓምድር ሊቃውንቶቹ ሮማዊያኑ ፕሊኒም (ከ23 – 79 ዓ.ም) ሆነ ክላውዲዎስ በጥሊሞስ (ከ100 – 170 ዓ.ም) ኢትዮጵያን በተመለከተ ድምዳሜያቸው ከግሪካውያኑ ያልተለየ ነበር፡፡ እንዲያውም በጥሊሞስ የኢትዮጵያን ከተሞች አዱሊስንና አክሱምን በካርታ ላይ ጭምር አስፍሯል፡፡ ራሱ የአክሱም ንጉሥ የነበረው ዞስካለስ (1ኛው ክፍለ ዘመን)፣ ጥርት ያለ ግሪክኛ ተናጋሪ እንደነበር በዘመኑ ከተገኘው ‹ፐረፕለስ ኦቭ ዘኤርትራን ሲ› መረዳት ይቻላል፡፡ ከብሉይ ኪዳን በንጽጽር ሲታይ አዲስ ኪዳን የተጻፈው የኋልዮሽ ባለመሆኑ (ከ50-150 ዓ.ም.)፣ ‹ወርጅናሌ› ግሪኩ ነባራዊ ታሪኮችን የሚጠቅስ ነው፡፡

በዚህ ዘመን መርዌ ተዳክማ በምትኳ አክሱም የመንግሥቱ መቀመጫ በመሆኗ፣ ኢትዮጵያ የሚለው የኩሽ ምትክ ነው ብሎ መከራከር አይቻልም፡፡ ልማዳዊውና ዘመናዊው የኢትዮጵያ የታሪክ ጥናት አክሱም የኢትዮጵያዊነት እምብርት መሆኗን ቢስማሙም፣ የሁለቱ አክሱም የትየለሌ ናቸው፡፡ “ሳባዊት” አክሱም የጥንታዊት ኢትዮጵያ መናገሻ ስትሆን፤ የኋለኛዋ ታሪካዊት አክሱም ግን ቢበዛ ከ2ኛው ምዕተ ዓለም የሚቀድም ዕድሜ የሌላት፣ የታሪካዊት ኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት፡፡ በጥንታዊትና ታሪካዊት አክሱም ብቻ ሳይሆን፣ በታሪካዊት አክሱምና በኢትዮጵያ መሃል ያለው እንቆቅልሽ ገና አልተፈታም፡፡

በዘመናዊ ታሪክ ጥናት ለኢትዮጵያዊነት የመጀመሪያው አገራዊ ፍንጭ ተደርጎ የሚወሰደው፣ “ኢትዮጵያ” እና “ሐበሻ” የሚሉት ስያሜዎች የጽሑፍ ማስረጃ የተገኘላቸው በዘመነ ኤዛና አክሱም በአራተኛው መቶ ዓ.ም. ነበር፡፡ አክሱማውያን እንዲያው በድንገት በዚህ ዘመን ራሳቸውን ኢትዮጵያውያን ብለው መጥራት አልጀመሩም፡፡ ሌላው ዓለምም ቀድሞም በሚያውቃቸው መጠሪያቸው እንጂ፣ ኢትዮጵያውያን ነን ስላሉ ብቻ አልተቀበላቸውም፡፡ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያና የቀድሞዋ ኢትዮጵያ አንድነትም በግልጽ የታወቀ ነበር፡፡ የኤዛና የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሦስት መቶ ዓመታት ውስጥ የተገኘ ብቸኛው አገራዊ ሰነድ ነው፡፡ በአካባቢው ዓለም ስለዚያን ዘመን ኢትዮጵያ የሚገኘውን የማያወላዳ የግሪክ፣ ላቲንና ዐረብኛ ማስረጃ ስናጤን፣ ችግሩ የሰነድ እንጂ የታሪክ መቋረጥ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡

ለምሳሌ ክርስትና በመንግሥተ ኢትዮጵያ ተቀባይነት ያገኘው ገና በዘመነ ሐዋርያት ለመሆኑ እማኞች አሉ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ክርስትናን የተቀበለው ከነብዩ ማቴዎስ ነበር፡፡ በዚሁ ዘመን ማቴዎስ ያጠመቃት ኢትዮጵያዊቷ ልዕልት ኢፌጂኒያ (1ኛው ክ.ዘ) ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቅድስና የሰጣት የመጀመሪያዋ (የመጨረሻዋም?) ጥቁር ሴት ናት፡፡ የዚህችን ቅድስት ኢትዮጵያዊነቷን እንዳንጠራጠር፣ በተደራቢ “ሐበሻዊቷ” ተብላ ትለያለች፡፡ የሚደንቀው ነገር ይኽች በካቶሊኩ ዓለም ዕለተ ቀኗ (ሴፕቴምበር 21) የሚታሰበው ኢትዮጵያዊት፣ ከኢትዮጵያ በቀር በአፍሪካውያንም ዘንድ ስመጥር ናት፡፡ የሥራ ባልደረባዬ ዶ/ር ዳንኤል ወልደጻድቅ እንዳጫወተኝ፣ በሴኔጋል የቀድሞው የባሪያ ንግድ ማዕከል በነበረው በጎሬ ደሴት ላይ በምትገኝ ቤተክርስቲያን፣ ምስለ ኢትዮጵያዊት ኢፌጂኒያ የአገር ልብሷንና ጥቁር የወይዛዝር ካባዋን እንደለበሰች በመሥራች እናትነት ለጎብኝዎች በክብር ትታያለች፡፡

ነገር ግን አራተኛው መቶ ለታሪካዊ ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ መሠረት የጣሉ በርካታ ክስተቶች በስለው የታዩበት ነበር፡፡ ለምሳሌ በሮም እንደተስተዋለው ክርስትና በኢትዮጵያም በመንግሥታዊ ኃይማኖትነት የተተከለው በዚሁ ክፍለ ዘመን ነበር፡፡ የግዕዝ ፊደል አናባቢው ተሟልቶለት ከንግግር ወደ ብሔራዊ የሥነ-ጽሑፍና የሥነ-አምልኮ ልሳንነት ያደገው በዚህ ወቅት ነበር፡፡ “ያለም ቋንቋ ሁሉ በየነገዱ ስም ሲጠራ፣ ግዕዝ ብቻ በማንም ነገድ ስም አልተጠራም፤ በራሱ በገንዘቡ እንጂ” ይላሉ አለቃ ኪዳነወልደ ክፍሌ (1948፤ 10)፡፡

ተከታዮቹ ሁለት ምዕተ ዓመታት ደግሞ ቤተ ክህነት በፍጥነት የተስፋፋችበት፤ ገዳማት በአገሪቱ ወርድና ቁመት የተተከሉበት፤ መጽሐፍ ቅዱስ ወደግዕዝ የተተረጎመበት፤ የዜማ፣ ቅኔ፣ ጽሑፍ፣ ሥዕል፣ ወዘተ ሥነ-ጥበባዊ ባህል ያበበት ዘመን ነበር፡፡ ይኽንን ከይሁዲነት ወደ ክርስትና፣ ከሳባ ወደ ግዕዝ የተደረገ ሽግግር፣ እንደ ሁለተኛው የተሳካ የባህል ማወራረስ ሂደት አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡ ዘመኑ መንግሥተ ኢትዮጵያ ወደ ሁለገብ ሥልጣኔና ገናናነት የተሸጋገረበት ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ታሪካዊና ባህላዊ እትብታቸውን በማሰብ፣ የጥንቱ ግዛታቸውን መረዌን የወረሩበት፣ ባሕር ተሻግረውም በደቡብ ዐረብያ የተስፋፉበት ነበር፡፡

እዚህ ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ የተተከለው የኢትዮጵያ ግዛተ አፄ በ6ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ተዳክሞ ወደ እናት ምድሩ ሲያፈገፍግ ኢትዮጵያም አንድ ተጨማሪ ብሔራዊ ቀለሟን እስልምናን ወረሰች፡፡ እስልምና በ7ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ገደማ በምድረ ኢትዮጵያ መሠረት ሳይጥል እንዳልቀረ ይገመታል፡፡ ነገር ግን በሚቀጥሉት ሁለት ክፍለ ዘመናት ከሰሜናዊው ጠረፋማ ስፍራዎች መሃል ለመሃል እየሰነጠቀ፣ እስከ ማዕከላዊው ምድረ ሸዋ ድረስ ለማበብ ችሏል፡፡

ክርስትና በተወሰነ መልኩ የይሁዲነት ቀጣይ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ከመጤነት ወደነባርነት ያደረገው ሽግግር አስቸጋሪ አይመስልም፡፡ እስልምና ግን ከነባሩ የኢትዮጵያዊነት ርዕዮት ጋር የማይጣጣምና ሥር ነቀላዊ ባዕድነት ስለነበረው፣ አንዱ ሌላውን ለመዋጥ የሚሞክርበት ሁኔታ መፈጠሩ አልቀረም፡፡ ነገር ግን ይኽ ፍፁም መሸናነፍ ያልተቻለበት ረዥም ትግል፣ የታሪካዊት ኢትዮጵያን ብሔራዊና ነባራዊ ሕልውና ቋሚ ተጽዕኖ አሳደረበት፡፡ እስልምና በሂደት ከባላንጣነት ወደ አዎንታዊ የኢትዮጵያ ኃይልነት መሻገሩ አይቀሬ ነበር፡፡ ነባርነትና መጤነት የጊዜም ጉዳይ በመሆኑ፣ ቀዳማዩ ደኃራዩን እያለመደ፣ እየገራና እየተቻቻለ አብሮ የሚኖርበት የኢትዮጵያዊነት ገዥ መንፈስ ተጠናከረ፡፡

ታሪካዊት ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ የስፋትና ጥልቀት እንጂ ሥርነቀል የይዘት ለውጥ አልታየባትም፡፡ ብሔረ ኢትዮጵያ ከ8ኛው ምዕት ጀምሮ ገናናነቷ ፈተና ውስጥ ሲወድቅ፣ የባሕር ማዶ ግዛቶቿን ስታጣ፣ የንግድ መናኸሪያዎቿ ሲራቆቱና ኤኮኖሚዋ ሲያቆለቁል፣ መንግሥቷ በአካባቢያዊ፣ ተፈጥሯዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ክንዱ ሲዝል አመጾች እዚህም እዚያም ተቀሰቀሱ፡፡ በተከታዩ ምዕት አክሱም ከናካቴው በዮዲት ጉዲት ስለወደመችና መንግሥቱም ሙሉ በሙሉ ስለፈራረሰ፣ መናገሻውን ወደ ደቡባዊው ክፍል ለማንፏቀቅ ተገደደ፡፡ ምናልባትም በመንግሥተ ኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን ውድመት ጽናት የሚያመለክተው፣ በተከታዮቹ ሁለት ምዕት ዓመታት ስለ አገሪቱ እጣ ፈንታ እንኳን ለመናገር የሚያስችሉ አገራዊ ማስረጃዎች መጥፋታቸው ነው፡፡

ከዚህ የጭለማ ዘመን በኋላ ብሔረ ኢትዮጵያ በ12ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በአዲስ መልክና ቁመና በላስታው የዛግዌ ሥርወ መንግሥት (1140-1268) ብቅ አለች፡፡ የዛግዌ መንግሥት በኃይማኖት፣ በቋንቋ፣ ባህል፣ ሥነ ሕንጻ፣ ሥነ ጽሑፍና መንግሥታዊ ወግ የብሔረ ኢትዮጵያን ቁልፍ ዘርፎች አስቀጠለ፣ አሻሻለ፣ አዳዲስ ፈጠራዎችንም አከለበት፡፡ በተለይ ደግሞ የብሔረ ኢትዮጵያን ሃይማኖታዊ ርዕዮተ-ዓለም ልዕልናውን አረጋገጠ፡፡ ዛጉዌዎች ከሰለሞናዊያኑ የተነሳባቸውን የሥልጣን ትግል የመከቱት ከብሔረ ኢትዮጵያ ርዕዮተ-ዓለም በመጋፈጥ ሳይሆን፣ ራሳቸውን በዚያው ማዕቀፍ ውስጥ ሁነኛ ሥፍራ በማስያዝ ነበር፡፡ የፍልስፍናው ማዕከል የነበረውን ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት በማጥበቅና ከቤተ ክህነት ጋር ፍጹም አንድነት በመፍጠር ነበር፡፡ አስደናቂዎቹ የአለት ቤተ ክርስትያናት የተፈለፈሉባት ላሊበላ፣ የአክሱም ፅዮንን ብሔራዊ የእምነትና የፖለቲካ ማዕከልነት ለመገዳደር የበቃችው በዋናዋ ፅዮን ተምሳሌት በመገንባት ነበር፡፡

ዛጉዌዎች የአክሱም ቀጣይ ብቻ ሳይሆኑ፣ የመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያም መሥራቾች ነበሩ፡፡ የቤተ መንግሥቱና ቤተ ክህነቱን ክንዶች በጥብቅ አቆራኝተዋል፡፡ አማርኛን በልሳነ መንግሥትነት ቆርቁረዋል፡፡ የነገሥታቱን ተዘዋዋሪ አስተዳደር ብልሃት አስተዋውቀዋል፡፡ በተለይ በተለይ በፖለቲካ ድርድር መንግሥታዊ ሥልጣን “ለባለመብቶቹ” በመመለስ ብሔረ ኢትዮጵያን ያፀኑ አስተዋይ ገዥዎች ነበሩ፡፡ የዚህ ሰላማዊ አፈታት በአገር ግንባታው ጥረት በቤተመንግሥትና በቤተ ክህነት መካከል የነበረውን የዓላማ አንድነት በማረጋገጡ፣ በሚቀጥሉት ሦስት ክፍለ ዘመናት (ከ13ኛው እስከ 16ኛው መቶ) ሁለቱ ተቋማት በእጅና ጓንትነት ብሔራዊ ግዛቱንና ብሔራዊ ሃይማኖቱን በከፍተኛ ሁኔታ ለማስፋፋት ችለዋል፡፡

የታሪካዊት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰነድ የሆነው ክብረ ነገሥት የብሔረ ኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሽግግር መደምደሚያ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ክብረ ነገሥት ከመቼቱ ሁለት ሺሕ ዓመታት ገደማ ዘግይቶ የተደራጀ ሰነድ ቢሆንም፣ ዋና ዋና ትረካዎቹ ቀደም ባሉት ክፍለ ዘመናት በኢትዮጵያና በአካባቢው ሲነገሩ የኖሩ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ ይኽ ሰነድ የአገሪቱን መሠረታዊ ሕግጋት፣ ግዛቷንና የውጭ ግንኙነቷን፤ የመንግሥትን ሥልጣን ምንጭ፣ ለአገራዊ ኃላፊነት መመረጫ መስፈርቶች፣ በተለያዩ ተቋማት መካከል የሚኖረውን የሥልጣንና ኃላፊነት ክፍፍል፤ የሕዝብን መብቶችና ግዴታዎች፣ በገዥና ተገዥ መካከል የሚኖረውን ግንኙነት፤ እንዲሁም ፅላተ ሙሴ ለኢትዮጵያዊነት ያላትን ቁልፍ ጠቀሜታ በዝርዝር ያትታል፡፡ ስለዚህም ክብረ ነገሥት ኢትዮጵያዊነትን ደምና ስጋ በመስጠት ሙሉ ብሔራዊ ፍልስፍና አድርጎ ከመቅረጹም በላይ፣ በጥንታዊት ኢትዮጵያና በታሪካዊት ኢትዮጵያ መካከል ርዕዮታዊ ቀጣይነትና ተወራራሽነት አረጋግጧል፡፡

ከ16ኛው ምዕት ለጥቆ የነበሩት ሦስት ምዕታት የኢትዮጵያ ባህላዊና ፖለቲካዊ መልክዐ ምድርን እንዳይመለስ የለዋወጡ፣ ነባሩን ብሔራዊ ርዕዮትና መንግሥት ያዳከሙና ከሞላ ጎደል የዘመናዊት ኢትዮጵያን መጪ ገፅታ የቀረፁ ዐበይት ሂደቶች ነበሩ፡፡ የግራኝ አሕመድ ጦርነት እስልምና ወደ ማዕከላዊው ደጋማ ክፍል እንዲቆናጠጥ ከማስቻሉም በላይ፣ ከዚህ የላቀ ተጽዕኖ ላሳደረው የኦሮሞ ሕዝብ መስፋፋት በር በመክፈት፣ በታሪካዊት ኢትዮጵያ ባህላዊና ፖለቲካዊ ቀመር ላይ ዘላቂ ለውጥ አስከትሏል፡፡ ከ1625 እስከ 1761 ዓ.ም. የነበረው የጎንደር መንግሥት የእነዚህን ጥምር ኃይሎች ግስጋሴ በማስተናገድ ለማለዘብ ከመሞከር በዘለለ፣ ማዕከላዊ ሥልጣኑን መልሶ ለማጥበቅ፣ ቤተ ክህነትንና ጦር ሠራዊቱን ለማጎልበት አልቻለም፡፡

ዘመነ መሣፍንት (1770-1847 ዓ.ም.) ተብሎ የሚጠራው ቀጣዩ የታሪክ አንጓ ይኽ ሂደት በብሔራዊ ማዕከሉ መንኮታኮት የተደመደመበትና፣ እስልምናና ኦሮሞነትን ያጣመሩ የየጁ የጦር አበጋዞች ሥልጣኑን በስመ ኢትዮጵያ የተቆጣጠሩበት ዘመን ነበር፡፡ የዚህ ዘመን ዋነኛ ባሕሪው በሥነ-ልቡናዊ ውዥንብርና ግራ መጋባት የሚገለጽ ነበር፡፡ ማዕከላዊ መንግሥቱ በአውራጃዊ ኃይሎች የተከፋፈለበት፣ ዘውዱ ለትዕምርታዊ ዋጋው ሲባል ብቻ ተዋርዶ የተጠበቀበት፣ ቤተ ክህነት በጽኑ አንጃዎች እየተናጠች ሰላም ያጣችበት ዘመነ አፀባ ተደርጎ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን ከታሪካዊት ኢትዮጵያ ህልውና አኳያ ያን ያህል መሠረታዊና ሥር-ነቀል ለውጥ አልታየበትም፡፡ የየጁ መሳፍንት ከብሔረ ኢትዮጵያ ቀጣይነት እሳቤ አላፈነገጡም፡፡ በፊውዳላዊው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ራሳቸውን በማደላደል፣ በዋነኝነት ክርስትናን በመቀበልና አማርኛንም በመንግሥታቸው ይፋዊ መግባቢያነት በማስቀጠል አገሪቱን ከመበታተን አደጋ ታድገዋል፡፡ በተለይ በመጪዋ ኢትዮጵያ የኦሮሞና አማራ ሕዝቦችን ምሰሶነት በማያዳግም ማሕተም አረጋግጠዋል፡፡

(ሐ.) ዘመናዊት ኢትዮጵያ (Modern Ethiopia)
***
ከአፄ ቴዎድሮስ ንግሥ የምትነሳው ዘመናዊት ኢትዮጵያ ከመቼውም የላቀ ፈጣንና ተለዋዋጭ ፈተናዎች የተደቀኑባት ነበረች፡፡ ቋረኛው ካሣ ኃይሉ የየጁዎችን አገዛዝ የገለበጡት፣ የአገሪቱን ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ አንድነት፣ የዘውዱን ሥልጣንና ግርማ፣ እንዲሁም የታሪካዊውን ብሔረ ኢትዮጵያ መልሶ ለማቆም ቃል በመግባት ነበር፡፡ ቴዎድሮስ የሚለው ስመ መንግሥታቸው ራሱ ይኽንን ሕልማቸውን የሚያትት ስያሜ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ቴዎድሮስ ለአገራቸው አዲስ ፈር ለመቅደድ የታጠቁ ባለራዕይ ንጉሥ ነበሩ፡፡ የዘመናቸውን የአንድነት ፍላጎት ያዋለዱ፣ ተሸንፈውና ሞተው የኢትዮጵያን አባትነት ድል የተቀዳጁ፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ የመጀመሪያው ብሔራዊ ጀግና ናቸው፡፡

ሆኖም የቴዎድሮስ ሕልም ፈር የያዘው እርሳቸውን በተከተሉት ሦስት ነገሥታት ነበር፡፡ አፄዎቹ ዮሐንስ፣ ምኒልክና ኃይለሥላሴ በወቅቱ የተደቀነውን የአውሮፓ ቅኝ ገዥነት አደጋ የተገነዘቡ፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ህልውና አብነቱ የአውሮፓን ሥልጣኔ የታጠቀች አንዲት አገር ናት ብለው የሚያምኑ ነበሩ፡፡ እውነትም አገሪቱ በታሪኳ አይታው የማታወቀው ተደጋጋሚ ዓለም ዐቀፍ ጦርነት በመቅደላ፣ ጉንደት፣ ጉራዕ፣ ዶጋሊ፣ መተማ፣ አድዋ፣ ማይጨው ብሔራዊ ህልውናዋን ክፉኛ ፈትኗታል፡፡ ስለዚህ ዘመናዊነት የውዴታ ምርጫ ጉዳይ ብቻ አልነበረም፡፡

በደምሳሳው ከ1850ዎቹ እስከ 1950ዎቹ የነበረው መቶ ዓመት፣ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንደገና የለመለመበት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ አገራዊ ወዝ እያጣ በባሕር ማዶ ኩረጃ ላይ በመመካቱ፣ የአውሮፓን ታሪክ ዘግይቶ የመድገም ደነዝ ሂደት ሆነ፡፡ የአውሮፓዊነት ሕልም እየበረታና ኢትዮጵያዊነት እያደር ከመንግሥታዊው ርዕዮት ማዕከልነት እየራቀ መጣ፡፡ በውጤቱም ሁለት መልክና መንፈስ ያለው ፖለቲካዊ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ ተከሰተ፡፡

በአንድ በኩል በድኅረ አድዋ (1888 ዓ.ም.) የተፀነሰው ለዘብተኛ አገራዊ ብሔርተኝነት አመለካከት፣ የብሔረ ኢትዮጵያን መደባዊና እምነታዊ ቅጥሮች አሻሽሎና አድሶ፣ ኢትዮጵያዊነትን ሰፋ ባለ ሕዝባዊ ሉዓላዊነት መርህ ላይ ለመመሥረት ያለመ ነበር፡፡ ሆኖም ይኽ ተራማጅ አገራዊ ንቅናቄ መልክ ሳይዝ በፋሽስት ጣልያን ወረራ (1928-1933 ዓ.ም) በእንጭጩ ተቀጨ፡፡ ወራሪዋ ጣልያን ከራሷም ብሔራዊ አንድነት ተመክሮ የብሔርተኝነትን ኃይል በሚገባ የተገነዘበች ስለነበረች፣ ኢትዮጵያዊነትን ዋነኛ ጠላት አድርጋ ዘመተችበት፡፡ በተለይም ኦርቶዶክሱን፣ አማራውን፣ ሸዌውን፣ ምሁሩን፣ ካህኑን በደመኝነት ፈጀችው፡፡ ከሁሉም በላይ ከፊሉን ኢትዮጵያዊ (በኤርትራና በትግራይ) ከእትብቱ በማቆራረጥና በገዛ ማንነቱ ላይ እንዲዘምት በማባበል ኅሊናውን በፀፀት የማናወጡ ሴራ ተሳካላት፡፡ እንደፈራችው ኢትዮጵያዊነት በድጋሚ ሃፍረት ቢያከናንባትም፣ በሰሜኑም በደቡቡም የአገሪቱ ክፍል ጠላቱን ዘውጌ ብሔርተኝነትን ተክላ ሄደች፡፡

ዘውጌ ብሔርተኝነት በድኅረ ጣልያን በአዲስ መንፈስ ማቆጥቆጥ ለጀመረው ኢትዮጵያዊነት ፈተና ለመሆን የበቃው፣ ከብሔረ ኢትዮጵያ እሳቤ ይልቅ ለፋሽስታዊው “ተሃደስቲ ኢትዮጵያ” ግንዛቤ ልቡናው የቀረበ፣ በባዕድ ወግ ለአዲስ ተልዕኮ የታጨ የአስኳላ መደብ በማግኘቱ ነበር፡፡ ይኽ ጣልያን ወለድ እትብታዊ እሳቤ ብሔርን በደምና ዘር በተዛመደ ደመነፍሳዊ ማኅበረሰብነት በመገደብ፣ በተለይም ቋንቋ የዝምድናው ዋነኛ ማረጋገጫ፣ የአንድ ሕዝብነት አልፋና ኦሜጋ ያደርጋል፡፡ ዘውጌ ብሔርተኝነት አገር፣ መንግሥትና ሕዝብ የተሰኙትን አዕማዶች በአዲስ መልክ በመተርጎም ሳይወሰን፣ አገራዊ ብሔርተኝነትን በባላንጣነት ያጠቃል፣ ያዳክማል፣ ከናካቴውም ህልውናውን ይክዳል፡፡

ከ1950ዎቹ የተነሳሳውን የተማሪዎች ንቅናቄን እውነተኛ ባሕሪ ለመረዳት የምንችለው፣ ከፍ አድርጎ ያነገበውን የብሔረሰቦች ጥያቄን ምንነት ስንመረምር ነው፡፡ ተደጋግሞ እንደሚነገረው ይኽ ንቅናቄ ከትውልዳዊ እምቢተኝነት ቢነሳም፣ አገራዊ ችግርን በአገራዊ መላ ለመፍታት የረባ ጥረት አላደረገም፡፡ ብሔረ ኢትዮጵያ የቆመችበትን ታሪካዊ መሠረት በቅጡ አልመረመረም፡፡ አዲሲቱ ኢትዮጵያ የምትወጠንበትን አገር በቀል ፍልስፍና አላፈለቀም፡፡ በእውነቱ ኢትዮጵያዊነት ምንድነው? ብሎ ለመተንተን እንኳን አልሞከረም፡፡ ከዚህ ይልቅ እውነታውን በአብዮታዊ ርዕዮተ-ዓለም ድሪቶ ለመጠቅለል ተግደረደረ፡፡

ዋለልኝና ደቀመዛሙርቱ ከማርክስ፣ ከማኦ፣ ከሌኒን፣ ከስታሊን፣ ከፋኖን እንዳሻቸው እየቆነፃፀሉ “ኢትዮጵያዊነት የሚባል ነገር የለም”፣ “ኢትዮጵያ የሚባል ብሔር የለም”፣ “የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንጂ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሎ ነገር የለም”፣ “የኢትዮጵያ ባህል ብሎ ነገር የለም” የሚል መናፍቃዊነት ለትውልዳቸው ሰበኩ፡፡ ከዘውጎች ጥርቃሞ የዘለለ ብሔራዊ አገር አልታይ አላቸው፡፡ እገሌ ትምክህተኛ፣ እንቶኔ ጠባብ፣ እገሌ ቅኝ ገዥ፣ እንቶኔ ተገዥ እያሉ በመፈረጅ፣ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ያላንዳች ፀፀት ዘመቱ፡፡ ከጥራዝ ነጠቅነትም ይኹን ከቀቢፀ ተስፋ፣ ከመሰሪነት ወይም ከሌላ ክፉ መንፈስ ይፍለቅ፣ ይኽ ስብከታቸው በኢትዮጵያ ሠራ አካላት የጎሰኝነት መርዙን ረጨ፡፡

የኢትዮጵያን አብዮት ከዳር ያደረሰው ወታደራዊ ደርግ፣ የተማሪውን ቅጥያጣ ጎሰኝነት ወደጎን በመተው በአንድ ኅብረተሰባዊ ፍልስፍና የምትመራ አገር ለመፍጠር ሞከረ፡፡ ይሁን እንጂ “የኢትዮጵያ ኅብረተሰባዊነት” የሚል ሙከራው ከሲቪሉ ክፍል ስላቅ ስላተረፈለት ሊገፋበት አልቻለም፡፡ የብሔረ ኢትዮጵያን አሮጌ ተቋማትና መዋቅር ጠራርጎ ቢገረስስም፣ ከቶም የዘውጌ ቡድኖችን ጠባብ ፍላጎት ሊመልስ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ወቅት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከሲቪሉ ርዕዮት ሙሉ በሙሉ ተወግደው ነበርና፡፡ የወታደራዊው አገዛዝ 17 ዓመታት፣ ሶሻሊስታዊው ብሔርተኝነትና ደመነፍሳዊው ዘውገኝነት የሞት ሽረት ትንቅንቅ ያደረጉበት ነበር፡፡ ነገር ግን ሶሻሊስት ኢትዮጵያዊነት ጥብቅ አገር በቀል መሰረትና ይዘት ስላልነበረው፣ ዕድሜው ከሶሻሊስቱ ጎራ አልዘለለም፡፡

እንግዲህ በታሪክ ግጥምጥሞሽ ወደ ኢትዮጵያ መንበር የመጣው ኢትዮጵያዊነትን ለ17 ዓመታት ሲዋጋ የነበረው ዘውገኛው ሕወሓት ነበር፡፡ ይኽ ቡድን ቀድሞውንም በጦር ግንባር ሲያደማት የነበረችውን አገር ለመምራት አልተሠራም፡፡ በዚህ ላይ ዘውጋዊ ርዕዮቶች በዓለም ዐቀፍ መድረክ እያንሰራሩ የነበረበት ወቅት በመሆኑ ታላቅ የሚና መምታታት አጋጠመው፡፡ አንዳንድ እውነት ከውሸት በላይ ያስፈራል፡፡ ሕወሓት በኢሕአዴግነት የኢትዮጵያን መንበረ ሥልጣን በተቆናጠጠበት የ26 ዓመታት ዕድሜ በራሱ አንደበት ደጋግሞ ቢነግረን ልናምነው ያልቻልነው ሃቅ ፀረ-ኢትዮጵያዊነቱን ነው፡፡ ታሪክ ሲከልስ፣ ሰንደቅ ዓላማ ሲረግጥ፣ ቅርስ ሲያጠፋ፣ ሕዝብ ሲያዋርድ፣ ሉዓላዊነት ሲያስገስስ፣ ድንበር ሲያስደፍር፣ ጥቅም አሳልፎ ለባእድ ሲሰጥ፣ ከብሔራዊ ጠላቶች ሲያብር ብናይም፣ ችግሩን ለመመርመር አልደፈርንም፡፡

የኢሕአዴግ አገዛዝ የዘውጌ ሕልሞች እናት ከሆነችው ጣልያን ተሞክሮና ከሌኒናዊ – ስታሊናዊ ንድፈ ሐሳብ የተቀመመመ መርዙን ይዞ፣ ኢትዮጵያዊነት የሚባለውን ብሔራዊ ማንነት ክፉኛ ተገዳደረው፡፡ በአገር ፈንታ ክልሎች፣ በሕዝብ ፋንታ ሕዝቦች፣ በመንግሥት ላይ መንግሥታት፣ በባንዲራ ላይ ባንዲራዎች ቀፈቀፈ፡፡ በአዋጅ ደንግጎ በብሔራዊ ምልክቶች፣ እሴቶች፣ ባህሎች፣ ተቋማትና ማኅበረሰቦች ላይ ያለርህራሄ ዘመተባቸው፡፡ ይኽ መንግሥት በየትም አገር ባልታየና ከቅኝ ገዥ ባልተለየ ሁኔታ፣ ከብሔራዊ ጥቅምና ከሕዝብ ስሜት መራቁና አንዳንዴም ተቃርኖ መቆሙ ጉድ የሚያሰኘን፣ በደመነፍስ የሚነዳውን አክራሪ ዘውጌ ብሔርተኝነት ባሕሪውን በቅጡ ባለመረዳት ይመስለኛል፡፡

(፬.) ኢትዮጵያዊነትን እንዴት እናጠናክር?
***

አንዳንድ ጊዜ አብሮ መኖር የፍፁም ውዴታ ጉዳይ ብቻ የሚመስለን የዋሃን አንጠፋም፡፡ አብሮ መኖር ታሪካዊም ነባራዊም ምክንያቶች ያሉት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ በዚህ መጣጥፍ በዝርዝር ለማየት እንደሞከርነው፣ ኢትዮጵያዊነት በፍላጎትና በራስ ምርጫ ብቻ የተገነባ ማንነት አይደለም፡፡ እንደማንኛውም ብሔራዊ መንግሥት በረዥምና አባጣ ጎርባጣ ቅብብሎሽ የወረስነው ታሪካዊ ቤተሰብነት ነው፡፡ ይኽ ብሔራዊ ቤተሰብ በቀላሉ በማይበጠሱ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ግዴታዎች የተሳሰረ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነትን አስገዳጅ የሚያደርጉ ተጨማሪ ውጫዊ ምክንያቶችም አሉ፡፡ ብሔራዊ ማንነት ከአገራዊ መንግሥታት ህልውና ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ግንዛቤ በመሆኑ፣ ብሔረሰባዊ ወይም ሌላ ንዑስ ማንነት በዓለም ዐቀፋዊ ሕግና ተግባር ተጨባጭ ትርጉም የለውም፡፡ ብሔራዊ መንግሥት እዚህም እዚያም ተግዳሮቶች ይግጠሙት እንጂ፣ ሉላዊው የፖለቲካ አወቃቀር ወደ ዘውጌ ሥርዓት የሚቀየርበት ዕድል የለም፡፡ ዘጠና በመቶው የዓለም መንግሥታት ኅብረ ብሔራዊ እስከሆኑ ድረስ፣ በዘውግ ላይ የተመሠረተ የመነጣጠል ጥያቄ በበጎ ዓይን አይታይም፡፡ በተግባርም ብዙ ሺሕ ንዑስና ጥቃቅን መንግሥታትን መፈልፈል ሊከናወን የማይችል ጉዳይ ነው፡፡

ነገር ግን ከሁሉ የላቀው አብሮ የመኖር ግዴታ የጋራ ጥቅም ይባላል፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለአገራችን ዝንጉርጉር ቁመና የሚስማማ ብቻ ሳይሆን፣ ለማኅበራዊ ሰላም፣ ጥንካሬና ብልጽግና ከሁሉ የተሻለው አማራጭ ነው፡፡ የራሳችን ተሞክሮም ታሪክም ደጋግሞ እንዳስተማረን ከመነጣጠል አትራፊ የሆነ አንድም አገር የለም፡፡ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለው ብሂል መቼም ቢሆን አያልፍበትም፡፡ ስለዚህ በአንድ ብሔራዊ መንግሥት ጥላ ሥር የመኖር ግዴታው እስካለ ድረስ፣ ትዳሩ የሰመረ እንዲሆን በመፈቃቀድና በመተሳሰብ ላይ የቆመ መሆን ይገባዋል፡፡

በጋራ የምንኖረው የጋራ ራዕይ ሲኖረን ነው፡፡ ከሁሉ በፊት ስለብሔራዊ ማንነታችን የጠራ ግንዛቤ እንዲኖረን ያሻል፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚባል ኅብረ ብሔረሰባዊ ማንነት እንዳለን ብቻ ሳይሆን፣ ባይኖር እንኳን ልንፈጥረው የሚገባን የአብሮነት እሴት መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ ኢትዮጵያዊነት አንድ ቤተሰብነት እንጂ ደባልነት አይደለም፡፡ አንድ ቤተሰብ የሚቆመው በመላ አባላቱ ፍፁም የአካልና የባሕርይ ወጥነት ሳይሆን፣ በውሱን የወል ተመሳስሎና በተለይም አብሮነት በሚፈጥረው መተሳሰብና ተስፋ መሆኑን አንሳት፡፡

ታሪክን በቅንነት ለጋራ ራዕያችን ተሞክሮነት ለማዋል እንነሳ፡፡ የየትኛውም አገር ታሪክ ከስህተት፣ ከመከራ፣ ከኢ-ፍትሐዊነት የጠራ አይደለም፡፡ ሕይወት ራሷ የሌላትን ምሉዕነት ከየት ያመጣዋል? እንደ አሜሪካ ያሉ ትናንትና የተፈጠሩ አገሮች እንኳን ከሙግትና ከብዥታ የጠራ ታሪክ የላቸውም፡፡ ስለዚህ ወደኋላ መለስ ብለን ታሪካችንን ስንቃኝ፣ ትናንትን ለመኮነን ሳይሆን ከትናንት ለመማር መሆኑን አንሳት፡፡ ከታሪክ ሽሚያ፣ ብረዛ፣ ተበቃይነትና አልቃሻነት ተላቅቀን፣ ተመክሯችንን ለበጎ ዓላማ እናውል፡፡ የዘውገኝነት ምንጭ የትናንት ቁስል ብቻ ሳይሆን የወደፊት ስጋት በመሆኑ፣ በማኅበረሰቦች መካከል ፍርሃትንና ጥርጣሬን ለማስወገድና ለጋራ ህልውናችን ዋስትና ለመስጠት ጠንክረን እንሥራ፡፡

ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት አውደ ሰፊና ለመለወጥ ክፍት በመሆኑ እያደር የሚያበለጽግ ሂደት ነው፡፡ ይኽ ማለት ግን ለአምባገነኖችና የሥልጣን ጥመኞች መሣሪያነት ሊጣመም አይችልም ማለት አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ፍሬ ነውና እንከን እንደማያጣው ከቅርብ ታሪካችን ተምረናል፡፡ ቁምነገሩ ኢትዮጵያዊነት ያለቀለት ጉዳይ ሳይሆን፣ ሁልጊዜም የሚያድግና የሚሻሻል ሂደት መሆኑን እንገንዘብ፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የጎደለውን እያሟላ፣ ያጋደለውን እያቀና፣ የየጊዜውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ እሴቶችን ሊያክልበትና የራሱን አሻራ ሊያትምበት ይችላል ይገባልም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ትርጉሙ የተሟላ የሚሆነው በየዘመኑ ሚዛን መሆኑን አንሳት፡፡

ኢትዮጵያዊነት በየዘመኑ ጥንታዊነቱን በሚያድስበት ሂደት፣ ዘላቂም ተለዋዋጭም ባሕሪያት አዳብሯል፡፡ ጠጋኝም ሥር ነቀልም ለውጦችን አስተናግዷል፡፡ ሆኖም የለውጡ ሞገድ ፅናት ከናካቴው እንዳያጠፋው፣ ታሪካዊ ውኃ ልኩን አልሳተም፡፡ ብሔርተኝነት ታሪካዊ ርዕዮት በመሆኑ ነባሩን ከመጤው አስማምቶ መኖር አለበትና፡፡ ታሪካዊት ኢትዮጵያና አዲሲቱ ኢትዮጵያ ይኽን በሁለት አቅጣጫ የተዘረጋ ቀጣይነት ያመለክታሉ፡፡ ከብሔረ ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊት ኢትዮጵያ በተደረገው ሽግግር፣ በሥር ነቀሎቹ የ1966 ሕዝባዊ አብዮትም ሆነ በ1983ቱ ዘውጋዊ ድል፣ ኢትዮጵያዊነት በየትኛውም ወቅት ፍጹም ከአልቦ አልተነሳም፡፡

ኢትዮጵያዊነትን በቅርጽም በይዘትም እያሻሻልን፣ ተራማጅ እሴቶችን እያጎለበትን፣ በቀድሞው ቅጥር ውስጥ የማያካትታቸውንና ዳር የገፋቸውን ማኅበረሰቦችና ባህሎችን እንዲያካትት ማድረግ እንጂ መካድ፣ ማፍረስ ወይም መነጠል መፍትሔ አይሆንም፡፡ ካለማወቅም ይሁን በተሳሳተ አገር ፍቅር ኢትዮጵያዊነትን ከአንድ ብሔረሰብና ሃይማኖት ጋር ለማጣበቅ መሞከርም አያስኬድም፡፡ ትናንትም ዛሬም በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተው የሚኖሩ፣ በመከራም በደስታም አንድነታቸውን ያተሙ በርካታ ብሔረሰቦችንና ማኅበረሰቦችን ውለታ መንፈግ ጤናማ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ክፉም ሆነ ደግ የመላ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ነው፡፡ ማንም በኢትዮጵያዊነት ላይ ብቸኛ ባለርስት አይደለም፡፡ ዛሬ “የአንድነት ኃይሎች” ማለት የአማራ ሽሙጥ ስም አድርገው የሚጠቀሙ የራሳቸው መሰሪ ተልዕኮ ያላቸው ናቸው፡፡ አማራነት ከኢትዮጵያዊነት መሳ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት በተፈጥሮው ከዘውጋዊ ማንነቶች ኅብረት የተገመደና የማይቃረን ላዕላዊ መቋጠሪያ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት አማራነትን ወይም ኦሮሞነትን አይከለክልም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያዊነት መኖር ለብሔረሰባዊ ማንነታችን አደጋ አይደለም፡፡ ግልባጩም እንዲሁ፡፡ ይልቁንስ በወጉ ከተያዙ ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት መልኮች፣ ተደጋጋፊዎችና የየፊናቸው ሚናና ደረጃ ያላቸው የማንነታችን እርከኖች ናቸው፡፡

ይኽን ውዥንብር ለመቅረፍ በብሔራዊው ማንነትና በብሔረሰባዊው ማንነት መካከል ተደጋጋፊነትና ሚዛን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይበልጥ የሚያስተሳስሩን የጋራ እሴቶችን፣ ባህሎችን ታሪኮችን በመለየት ብሔራዊ ማንነታችንን ማበልፀግ የግድ ይላል፡፡ በየማኅበረሰቦች ቅጥር የሚካተቱ ጉዳዮችን በግልጽ አንጥረን ዋስትና መስጠትም ይኖርብናል፡፡ በጎንዮሽም በንዑስ ማኅበረሰቦች፣ እምነቶች፣ መደቦች፣ ወዘተ. መካከል ዘርፈ ብዙ ድልድይ መፍጠር ለብሔራዊ ህልውናችን ዋስትና ነው፡፡ የኅብረ ባህላዊነት አስኳል እሳቤ በዚህ ላይ የተመሠረተ ነውና፡፡

ካለፈው ሩብ ምዕት ተሞክሯችን በግልጽ እንዳየነው፣ ዘውጋዊ ብሔርተኝነት በተፈጥሮው ግትርና ግለኛ ነው፡፡ በአግባቡ ካልተያዘና መረን ከተለቀቀ፣ በመቻቻል ፋንታ ቂምና ቁርሾን የሚሰብክ፣ አብሮነትን የሚያጠወልግ አደጋ አለው፡፡ ዘውጋዊነት መድረሻ ዓላማው ፖለቲካዊ ነፃነት በመሆኑ፣ ከራሱ በላይ ማናቸውንም ዓይነት ብሔርተኝነት ለመቀበል አይሻም፡፡ ስለዚህም አገራዊ ብሔርተኝነትን በብሔረሰቡ ልክ ያጠበዋል፣ ወይም በባላንጣነት ፈርጆ ይቦረቡራል፤ ያዳክማል፡፡ ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ እንዳረጋገጠልን ዘውጌ ብሔርተኝነት በማዕከላዊነት የሚያቀነቅነው የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚባለው መርህ ራሱ ከፍትሕ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲ ይልቅ በበቀለኝነት፣ በበታችነትና በራስወዳድነት መንፈስ የተሳከረ ነው፡፡

በአጠቃላይ የቱም አገር በአንድ ጀንበር አልተገነባም፡፡ ብሔራዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ትዕግስት፣ አስተዋይነት፣ ራዕይ፣ ከፍተኛ ደምና ላብ ይጠይቃል፡፡ በትውልዶች ቅብብሎሽ በዘመናት ሂደት የሚከናወን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ከምንገኝበት ብሔራዊ አዘቅት ለመውጣት፣ ይኽን ቅብብሎሽ በጥንቃቄ የሚመራ አዎንታዊ፣ የሰከነና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ መቅረጽ ግዴታችን ነው፡፡ በማንነቱ የሚኮራ ልበ ሙሉ ትውልድ ልንፈጥር የምንችለው፣ ኢትዮጵያዊነትን ከብዥታ አውጥተን በግልጽ መሠረት ላይ ስንገነባው ብቻ ነው፡፡

The Black Lion page
ቴዎድሮስ ኃይለማርያም (ዶ/ር) – የታሪክ ምሁር

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ
0Shares
0