ይልቁንም የጠ/ሚ አብይ የመቀሌ ማብራሪያ ትላንት በጎንደር፣ በደብረታቦር፣ በባህርዳር፣ በወሎና፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ብሎ አደባባይ በመውጣት ውድ ህይወቱን የሰዋውን የአማራ ወጣት ክቡር መስዋዕትነት ማራከስ ነው።

የወልቃይት ህዝብ ትግል መነሻው የፍሽስት ህወሃት ወረራና ተስፋፊነት ሲሆን የተጀመረውም የባንዳው ቡድን ታጣቂዎች የተከዜን ወንዝ ተሻግረው የጎንደርን/ወልቃይትን መሬት ከረገጡበት ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ይህ ህወሃት አቅዶና ተዘጋጅቶ የቆሰቆሰውና ለብዙ ንጹሃን ወገኖቻችን ደም መፍሰስ ምክንያት የሆነው ግጭት ለአለፉት 40 ዓመታት የቀጠለና እኛም በግፍ የተነጠቅነውን የአባቶቻችን ዕርስት እስክናስመልስ ድረስ ትላንት፣ ዛሬና፣ ወደ ፊትም “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” እያልን በታላቅ ክብርና ኩራት የምንሰዋለት ማንነትን የማስጠበቅና ህልውናን የማስቀጠል ትግል ነው።

Welkait Tsegede

እኛ ጎንደሬዎች! የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምት፣ የሁመራ… ባለዕርስቶች እያል ያለነው “ድንበራችን ተከዜ ነው!” ነው!

“ድንበራችን ተከዜ ነው!” ማለት የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር የጎንደር/አማራ መሬት ውስጥ ምን ይሰራል ማለት ነው!

“ድንበራችን ተከዜ ነው!” ማለት ጎንደሬ/አማራዎች እንጂ ትግሬዎች አይደለንም ማለት ነው!

“ድንበራችን ተከዜ ነው!” ማለት አንድም ኢትዮጵያን በቋንቋ ሸንሽኖ ህዝቧን እርስ በእርስ የማባላት የወያኔ ሴራ እናከሽፋለን ማለት ነው!

“ድንበራችን ተከዜ ነው!” ማለት በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ የምትገነባውን የትግራይንና የትግሬዎችን የበላይነት አንቀበልም ማለት ነው!

“ድንበራችን ተከዜ ነው!” ማለት ህወሃት በሃገራችን ኢትዮጵያና በህዝቧ ላይ ያነገበውን ፋሽስታዊ ተልዕኮ እናኮላሻለን ማለት ነው!

መጋቢት 24/2010 ዓ.ም የጠቅላይ ሚንስትርነት ቃለ ማህላ የፈፀሙትና በ10ኛው የስራ ቀናቸው ሚያዚያ 5 በመቀሌ ከተማ ተገኝተው ከትግራይ ህዝብ ጋር የተመካከሩት ጠ/ሚ አብይ አህመድ፣ በዚህ መድረክ ስለ ጎንደር ህዝብ በተለይም ስለ ወልቃይትና የአርማጭሆ ህዝብ ትግል የያዙት አቋምና ያስተላለፉት መልእክት ድርጅታችን በአንክሮና በፅሞና ተከታትሎታል። ጠ/ሚንስትሩ የህዝባችንን ጥያቄ አስመልክተው የሰጡት ማብራሪያ ተጨባጩን እውነት በእጅጉ የደፈቀ፣ ሃሰተኛና፣ ከህዝባችን ጥያቄና ብሶት በተቃራኒው የቆመ ሆኖ አግኝተነዋል። ይልቁንም የማንነትና የህልውና ጥያቄዎቻችንን በማኮሰስ ተራ የመሰረተ ልማት ጥያቄ ማድረጋቸው ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን፣ አባላቶቻችንና፣ መላው ህዝባችንን በእጅጉ ያስቆጣና የጠ/ሚኒስትሩን ጅማሮ በእንጭጩ ያጨነገፈ ሆኖ አግኝተነዋል።

የቀደመውን ህዝባዊ ትግል ይቆየንና የ2008ቱን “ወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ” ብቻ እንኳ ብንመለከት መነሻው በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚኖሩ ከ50 ሺ በላይ የወልቃይት ተወላጆች ፊርማቸውን ያሰፈሩበትና ህጋዊ ኮሚቴ መርጠው በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ያቀረቡት ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ የአማራ ማንነታችን ይጠበቅልን የሚለው ጥያቄ ህዝባዊ መሰረት ያለውና ከወያኔው የፌደሬሽን ምክር ቤት እስከ አሜሪካ መንግስት ድረስ እውቅና የተሰጠው ሆኖ እያለ፤ ነገር ግን ይህን የህዝብ ብሶት ወደ ጎን በመግፋት ጥያቄውን የመብራት፣ የውሃና፣ የመንገድ ማደረግ የአዲሱ ጠ/ሚ ትልቅና ታሪካዊ ስህተት ነው ብለን እናምናለን።

የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ሊያቃልሉ እንደሞከሩት የዲያስፖራው የተሳሳተ ጭንቀት፣ የፌስቡክ ጫጫታ፣ የውሃና የመብራት ጥያቄ ሳይሆን፤ እጅግ የገዘፈና ፅኑ የህዝብ መሰረት ያለው የህልውና ጥያቄ ነው! ጥያቄው የመኖርና ያለመኖር  ነው! ጥያቄው አማራዊ ማንነትን ለማዳንና በትግሪያዊነት ላለመዋጥ የሚደረግ ፍትሃዊ ትግል ነው! ጥያቄው እራስንና መጭውን ትውልዳችን  ከተጋረጠበት የዘር ማፅዳት ወንጀል የመታደግ ጥያቄ ነው! ጥያቄው በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ንጹህ ደም የተገበረበት ነው!

ይልቁንም የጠ/ሚ አብይ የመቀሌ ማብራሪያ ትላንት በጎንደር፣ በደብረታቦር፣ በባህርዳር፣ በወሎና፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ብሎ አደባባይ በመውጣት ውድ ህይወቱን የሰዋውን የአማራ ወጣት ክቡር መስዋዕትነት ማራከስ ነው። ይህ የአማራ ልጆችን መስዋዕትነት ማራከስ ኤርትራን ለማስገንጠልና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የትግራይን ወጣት ደም በከንቱ ያፈሰሰውን የህወሃት መሪዎች ለማስደሰትና የስልጣን እድሜውንም ለማራዘም የተደረገ የሃሰት ምስክርነት እንደሆነ እንረዳለን።

የህዝብን ጥያቄና ትግል በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ አለመስጠትና አፍኖ የህዝብና የሃገር ስልጣን ላይ ለመቆየት መሞከር የሚያመጣውን ውርደትና ውድቀት ከህወሃት በላይ አስረጂ ይኖራል ብለን አናምንም። ይሁን እንጂ ዛሬም ህወሃት በአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር በኩል የሚረጨው ውሸት ትላንት የኢትዮጵያን ወጣት ዳር እስከዳር ያስቆጣውን የመብት ጥያቄ ዛሬም “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብሎ በማለፍ እድሜውን ለማራዘም እየዳከረ እንደሆነ አመላካችን ሆኖ አግኝተነዋል።

ከሁሉም በላይ ግን የጠ/ሚ አብይ በሃሰት የታጨቀ ማብራሪያ ያረጋገጠልን ነገር ቢኖር ህወሃት ሳይወገድ የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ምንም መፍትሄ እንደማያገኘና ህዝብ በተስፋ የሚጠብቀው ለውጥ ከቶውንም እንደማይመጣ ነው። ስለሆነም በህወሃት የጭቆና መዳፍ ስር ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ለውጥ የሚታሰብ ባለመሆኑ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምት፣ የአርማጭሆ፣ የጎንደር፣ የአማራና፣ መላው የኢትዮጵያ ልጆች የጀመርነውንና በብዙ ዋጋ እዚህ ያደረስነውን ህወሃትን የማስወገድ ትግል ለአፍታም ሳንዘናጋ ከምንግዜውም በላይ አጠናክረን እንድንቀጥል አበክረን እናሳስባለን!

ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ !

ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!

ሚያዚያ 6, 20101 ዓ.ም
ልሳነ ግፉዓን ድርጅት

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *