ዶ/ር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊት በተለያዩ የአመራር ቦታዎች ላይ በነበሩ ጊዜ ካደረጓቸው ንግግሮች ምርጥ የተባሉት ጥቂቶችን በኢትዮ ኤፍ.ኤም. ተቀንጭቦ ሲተላለፍ ሰምቻለሁ። በአስተዳደር ረሃብ ላይ ያተኮረ ነው። 


ሴትዮዋ ልጇ ታሞባት ማሳከም ትፈልጋለች። አለቆች ሦስት ዓይነት ርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። አንዱ ቦታ ያለው አለቃ (የሰው ኃይል ሹመኛ) «አሁን ሥራሽን ሥሪ ሌላ ጊዜ ታሳክሚያለሽ ይላል። ሌላው አለቃ ደግሞ «ሂጂ! አሳክመሽ የሀኪም ወረቀት አምጪ ይላል» ሌላኛው ደግሞ ዝም ብሎ ሂጂ ይላል ሦስቱም ዋጋ የላቸውም ሴትዮዋ የታመመባት ልጇ ነው። ሹመኞች ጥቂት እንኳ ርህራሄ ሊኖራቸው ይገባል። «ማሳከሚያ ገንዘብ ይዘሻል? መኪና ይታዘዝልሽ? እንዲያው ለመሆኑ ልጅሽን ምን አገኘብሽ? አይዞሽ! … እግዜር ከአንቺ ጋር ይሁን የሚል ዓይነት የሀዘኔታ ቃል ሊያሰሟትና ሊያጽናኗት ይገባል። 
ሠራተኛውን እንዲህ አድርገን ከያዝነው እንደ ሠራተኛ ብቻ ሳይሆን እንደባሪያም ጭምር ያገለግላል። መስሪያ ቤቱን ይወዳል! ሥራውን አድምቶ ይሰራል! ውጤታማ ይሆናል! ሹመኞች እዚያ ማዶ እላይ ተቀምጠው የታችኛውን ሠራተኛ ቁልቁል የሚያዩበት መነጽር ከተንሸዋረረ አስተዳደራችን ልክ አይመጣም፡፡ የሚል ዓይነት ንግግር ነው። ቃል – በቃል አልያዝኩትም አማርኛውንም እንደ እርሳቸው አላሳመርኩትም ሰውየው ኃይለኛ ንግግር አዋቂ ናቸው። መሪ ስለሆነ «እርስዎ» አልኳቸው እንጂ በዕድሜ ከሆነ በሃያ ዓመት እበልጣቸዋለሁ።
የሃያ ዓመት ታናሼ ናቸው ማለት ነው። ይሁን እንጂ መሪ «አንተ» አይባልም ነውር ይመስለኛል። በነገራችን ላይ ስለመሪዎች መጠሪያ የሕግ ማዕቀፍ አለን ይሆን? መሪ ሲጠራ ምን ተብሎ ነው። ዶክተርነቱ አይነካበትም። በሁሉም አጋጣሚ ዶ/ር መባል አለበት። ከዚያ በፊት የሚለጠፈው የመጠሪያ ድሪቶ ብዛት ያስፈልጋል? ወይም አያስፈልግም? «የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች የበላይ ጠባቂ ወዘተ… ተብሎ እንዲጠራ የሚያመለክት ሕግ ያለ አይመስለኝም። ስም ይወጣል ከቤት ይከተል ጐረቤት እየሆነ የተወሰኑ አጫፋሪዎች አንድ መጠሪያ ይፈጥሩና በሚዲያ ይለቃሉ። ሕዝቡ በዚያው መሠረት «ጓድ ሊቀመንበር ወዘተ … እያለ ሲተረትር ይውላል እንጂ «እንዲህ ብለህ ካልጠራህ ዋጋህን ታገኛለህ የሚል የተፃፈ ሕግ ስለመኖሩ አላውቅም። ታጂኪስታን የምትባል አገር ውስጥ ግን አለ፡፡ የታጂኪስታን ፕሬዚዳንት ስሙ ሁለት ቃላት ብቻ ናት ከስሙ በፊት ያለው የመጠሪያ ቅጥያ ለመጥራት ብቻ ከ15 ሴኮንድ በላይ ይፈጃል። ከቴሌቪዥን ዜና በስተግርጌ የሚፃፈው የመሪ መጠሪያን አንብቦ ለመጨረስ የሚችል የለም። በተለይ የመንግሥት ሚዲያዎች (ጋዜጦች፣ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ) ይህን ስም አስተካክለው መፃፍ ወይም ማንበብ ግዴታቸው ነው። ያለበለዚያ የእስርና ከሥራ የመባረር ቅጣት አለባቸው። የእኛ አገር መሪ በስንት ጣዕሙ!
ወደ ዶ/ር አብይ አህመድ ንግግር እንመለስና ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑ ዕለት በፓርላማ ፊት ያደረጉትን ንግግር እንዴት አገኛችሁት? ጉድ አይደለም እንዴ! የጉድ ጉድ! መረጃ ለማደራጀት ሳይሆን ወሬ ለመቃረም ዞር ዞር ብዬ ነበር። በንግግራቸው፣ በቃላት አመራረጣቸውና አሰዳደራቸው፣ ከድምጽ አወራረዳቸው፣ ከማራኪነታቸውና ከቁም ነገራቸው አንፃር ወደር የሌላቸው መሆናቸውን ነው ሰዎች ሲናገሩ የሰማሁት፡፡ አንድም ሰው ተቃውሞ የሰነዘረ የለም። ንግግራቸው በሰዎች ዘንድ ያሳደረው ስሜት ሲገለጽ፡-
– ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው ሰው የሚል ንግግር ሰማሁ፤ 
– ብሔራዊ ትንሣኤን ያበሰረ ንግግር ሰማሁ፤ 
– ኢትዮጵያዊነት ብቻ ሲሰበክበት የዋለ የማይሰለች ንግግር ነው፤ 
– በሰው ልብ ውስጥ የነገን ተስፋ የሰነቀ ንግግር ነበር፤ 
– አንድም ውሸት/ሀሰት/ የሌለበት ንግግር ነበር፤ 
– ሰውየው ያላቸውን በራስ መተማመን ያሳየ ንግግር ነበር፤ 
– የአንድነትን ተስፋ በውስጣችን የጫረ፤ 
– መለኮታዊ መስህብ ያለው ወንጌላዊ ቃና የተላበሰ ንግግር ግሩም ድንቅ፤ 
– የነፍስ ጥም ቆራጭ፤ 
– ምድራዊ የማይመስል ስሜታዊ መልዕክት ነው፤ 
– የአዕምሮ ፍካት ብርሃን የፈነጠቀ ነው፤ 
– የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ስሜት የነካ ነው፤ 
– የኢትዮጵያዊነትን ፍቅርና አክብሮት የተላበሰ ነው፤ 
– ከስድብና ከጥላቻ የፀዳ ንግግር ነው፤
– ጐጠኝነት ቀርቶ ኢትዮጵያዊነት የተሰበከበት መድረክ ነበር፤ ወዘተ… ያልተባለ ነገር የለም። በእርግጥ ንግግሩ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል። የአንድነት ስሜት ፈጥሯል። ይህ የሆነው ግን በተናጋሪው የንግግር ጥበብ (ዕውቀት) ብቻ ይሆን በሕዝቡ ልብ ውስጥ ባለው የመሰማት ዝግጁነት ነው። ንግግሩ በጆሮዬ ውስጥ ላለው ጆሮ የተናገረ በመሆኑ ምንጊዜም ከውስጤ አይጠፋም። እንደማለት ነው። በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ሥልጣን ላይ የነበሩ መሪዎች ንግግር ሕዝቡን አስመርሯል። ፋሽናቸው ስድብ ብቻ ነበር። «ያለፈው ሥርዓት ናፋቂ … የሻዕቢያ ተላላኪ … ጠባብ …ትምክተኛ … ሕዝበኛ … ኪራይ ሰብሳቢ … ሽብርተኛ ወዘተ… »የሚሉ ሞራል ነኪ አዋራጅና ክብረነክ ፀያፍ ቃላቶችን እየፈበረከ በሚያከ ፋፍላቸው የፖለቲካ ኩባንያ በኩል የሚያገኙትን ስድብ እንደወረደ ሕዝብ ላይ የሚደፉ ስለነበሩ የሰውን ጆሮና በጆሮውም በኩል ልቡን ሊያገኙ አልቻሉም።
ንግግራቸው ሁሉ ውሸት ይበዛበታል። የማይጨበጥ ተስፋ ያዘለ ላም አለኝ በሰማይ ዓይነት ንግግር ነወ። ከመሀከላቸው ደፍሮ የሚናገር የለም፡፡ በተለይ ታች ያሉ ትናንሽ አባላት የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ሲነሳ ይሸሻሉ፡፡ ምክንያቱም ቢናገሩ ያለችሎታቸው ያገኙትን ሥራና ከአቅም በላይ የሚከፈላቸውን ደመወዝ ያጣሉ። ስለዚህም ተሸማቅቀው ይኖራሉ። ወሬ አመላላሽ የበዛበትና የፍርሃት ቆፈን የጠነከረበት በረት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። በመንግሥትና በሕዝብ መሃል ድልድይ ሆነው መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር አይሰሩም። መንግሥት የሚለውንም ቢሆን በትክክል ሰምተውና ተረድተው ለሕዝቡ ማድረስ አይችሉም። ከላይ የመጣው መመሪያ ወደ ታች በወረደ ቁጥር እየዘቀጠና እየተጣመመ ይሄድና የሕዝቡን ሆድ የሚያሸክር ይሆናል። የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር ይህን የተዛባ አካሄድ ለማረም በአርአያነት የሚጠቀስ ነው።
የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር ለማድነቅ (ለማሞካሸት) ዜጐች ያላሉት ቃል የለም። አንዳንዶቹ ይሄኛውን በማሞገስ በሌላኛው ላይ ያላቸውን ቂም የተወጡ አስመስሎባቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ንግግሩን እስከጠርዝ ድረስ ለጥጠውታል። ሌሎቹ በበኩላቸው እስከ ፊደል ቆጠራ ድረስ ገብተውበታል። «በ2500 ቃላት … በ12ሺ ፊደላት… በምንትሴ ዓረፍተ ነገራት… በቅብርጥሴ መስመራት …» እያሉ የገለፁም አሉ። አንዳንዶቹ ከንግግሩ ውስጥ አንዳንዱን አባባል ወደ ስላቅ ወስደውታል። «… ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን…» የሚለውን የዶሮ ካርቱን መፈክር አስይዘው «… ስንኖር ዶሮ ስንሞት ዶሮ ወጥ ነን» ዓይነት ፌዝ አይተናል። የቀራቸው ንግግሩ በኪስ በሚያዝ መጠን ታትሞ ይሰጠንና እሱኑ ጧትና ማታ እንደ እምነት መጽሃፍት ስናነበንብ እናርፍድ ማለት ብቻ ነው ።
ዋናው ነገር ንግግሩ ጥሩ ቢሆንም በውዳሴ ብዛት ተበልጠን እንዳንዘናጋ መጠንቀቁ ላይ ነው። «ቧንቧ ውስጥ ውሃ መኖሩን (መምጣቱን) ሳታረጋግጥ እቤትህ (ባልዲህ) ውስጥ ያለውን ውሃ አትድፋ» በኋላ ጉድ ትሆናለህ። የቤትህን ውሃ ደፍተህ የገንዳውንም አጥተህ አትችለውም፡፡ በተግባር እስክናይ ድረስ እንረጋጋ! ውዳሴያችንና አድናቆታችን ደርዝ ይኑረው፡፡ «ፍቅሬ ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም…» የተባለው ዘፈን በከንቱ አይደለም።
ከንግግሩ በኋላ ያሉትን ቀናት አገራዊ አከራረም ስንመለከተው እጅግ በጣም ሰላም የሰፈነበት ሕዝቡ ሁከት ስለመኖሩ ለማሰብ ደቂቃ የማያባክንበትና ከስጋት ነፃ የሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው። የተሻለ ቀን እየመጣ መሆኑ ተሰምቶታል። ተማሪው፣ ወጣቱ፣ ሴቱ፣ አጠቃላይ ኅብረተሰቡ ደስ በሚል መንፈስ ውስጥ ነው ያለው። ድንጋይ መወርወር፣ ጐማ ማቃጠል፣ ትራንስፖርቶችና ንግድ ማስተጓጐል ቆሟል። ከፀጥታ ኃይሎች ጋር መጐነታተል የለም። እፎይታ ተገኝቷል። በፊት ጊዜ እፎይታ የሚታ ወቀው «እፎይታ መጽሔትና እፎይታ ገበያ» ብቻ ነበር። ዛሬ በተፈጠረው ሰላም ውስጥ እፎይታ ከነሙሉ ክብሩና ጥቅሙ ጋር በየቤታችን ገብቷል። ልጆቻችን በደስታ ወጥተው በደስታ ወደቤታቸው እንደሚመለሱ እርግጠኞች ነን ። የሚያሰጋን ነገር የለም። የፋሲካ ዶሮ ሺህ ብር እንደሚገባ ጠብቆ የነበረው ሕዝብ በ4 እና 5 መቶ ብር ጥሩ ዶሮ እየገዛ ገብቷል። በዓሉ ያለአንዳች ረብሻና ሁከት መከበሩ በራሱ ብቻ ትልቅ ደስታን ፈጥሯል፡፡ አገራችን ሰላም መሆኗን መስክረናል። ሰላሙ ከየት መጣ? ከሰውየው ከራሱ ስብዕና ነው? ወይስ ከንግግሩ መሳጭነት ነው? ወይስ ከኮማንድ ፖስቱ ብቃት ነው? ወይስ ከሕዝቡ ዝግጁነት ነው? ጥቂት ጥናት ሊፈልግ ይችላል። ያም ሆነ ይህ አገሩ ሰላም ነው። የምንፈልገውም ሰላም ነው። የምንፈልገውን አግኝተናል። ያዝልቅልን! ከግለሰብ አምልኮና ከንግግር ጥገኝነት ያውጣን! መጪው ጊዜ ከሰውየው ጋር ብሩህ ይሆናል።

አዲስ ዘመን

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *