በተለያዩ ክልሎች በሚያስተላልፏቸው ተራማጅ ሀሳቦች የኢትዮጵያ ህዝብ የናፈቀውን የለውጥ ፍላጎት ሲያንፀባርቁ ስለነበር ነው። ስለሆነም በእኔ እምነት ህዝቡ ድጋፍ እየሰጠዎት ያለው በለውጥ ፈላጊነትዎ ምክንያት መሆኑን ላስምርልዎት እፈልጋለሁ።

ክቡር ዶክተር ዓብይ አህመድ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር፣  ክቡራን ሚኒስትሮች፣ የአማራ ክልል አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ክቡራን የታሪካዊቷ ጎንደርና የአካባቢዋ ነዋሪዎች፣  ክቡራንና ክቡራት የዚህ ስነ ስርዓት ታዳሚዎች፣

ከሁሉ አስቀድሜ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችንን እንዲህ በደመቀና በአማራ ስነ ስርዓት ስለተቀበላችሁልን ያለኝን ላቅ ያለ አክብሮት ለጎንደር ህዝብ እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ፣
ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ እንኳን ወደ አማራ ክልልና ጥንታዊቷ ጎንደር በደህና መጡ እያልኩ የተሰማኝ ደስታ በአማራ ክልል ህዝብና መንግስት ስም ልባዊ አክብሮት ላቅ ባለ ሁኔታ አቀርብልዎታለው።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣

እርስዎ የአገራችን ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ መላው የክልላችን ህዝብ የተቀበለዎት ከዳር እስከ ዳር በደስታ፤በከፍተኛ የፍቅር የተስፋ ስሜትነው ።
የአማራ ህዝብ በአጠቀላይ በተለይም የክልላችን ህዝብ እርስዎ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሲሆኑ ለምን ዳር እስከ ዳር በደስታ ሃሴት ተሞላ?

ለምንስ ከሞላ ጎደል ይህን ያህል ከጫፍ ጫፍ በአንድ ጊዜ የሚበዛው ህዝብ በሚያስደንቅ ሁኔታ የእርስዎን መመረጥ ተቀበለው? መልሱ፣ ይህ ህዝብ ለውጥ በመፈለጉ እርስዎን የለውጥ ምልክትና ተስፋ አድርጎ በመመልከቱ ነው። እርስዎ ህዝቡ ለውጥ በፈለገ ወቅት ለኦሮሞ ህዝብ በሚያደርጓቸው ንግግሮች፣ በልዩ ልዩ አገር አቀፍ እና በተለያዩ ክልሎች በሚያስተላልፏቸው ተራማጅ ሀሳቦች የኢትዮጵያ ህዝብ የናፈቀውን የለውጥ ፍላጎት ሲያንፀባርቁ ስለነበር ነው። ስለሆነም በእኔ እምነት ህዝቡ ድጋፍ እየሰጠዎት ያለው በለውጥ ፈላጊነትዎ ምክንያት መሆኑን ላስምርልዎት እፈልጋለሁ።

የአማራ ህዝብ ፍላጎት አገራችን ኢትዮጵያ ከዳር እስከ ዳር ሁሉም ህዝቦች ያለስጋትና መሸማቀቅ በነፃነት የሚኖሩባት፣ በሁሉም መስክ መንግስት ለዜጎችና ህዝቦች የሚሰጠውን አገልግሎት ግልፅነትና ፍትሃዊነት የሰፈነበት እንዲሆን እና የኢትዮጵያ ህዝቦች የመቻቻልና የአብሮነት እሴት ተጠብቆ በፅኑ አንድነትና በፍቅር መኖርን ነው። እንዲሁም በአገራችን የሚታየውን መልካም የልማት ጅመር ሰፍቶ አሁንም በድህነትና በኋላቀርነት የሚሰቃዩ ዜጎች ከዚህ አስከፊ አኗኗር ተላቀው አልፎላቸው ማየት ነው።

በአሁኑ ወቅት ከላይ እንደገለፅኩት የህዝባችን የለውጥ ፍላጎት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑ እንደተጠቃ ሆኖ በሌላ መልኩ ይህ ለውጥ በአንድ ጊዜ ወይም በአንድ ግለሰብ እንዳይመጣ ህዝባችን ይገነዘባል። ህዝቡ ያሳደረው የለውጥ ተስፋ የራሱ የሆነ ጊዜ የሚጠይቅና የብዙ አካላትን ትብብር እና በቁርጠኝነት መንቀሳቀስን የሚጠይቅ መሆኑና ህዝቡ እራሱ የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም ያምናል።
ከሁሉም በላይ መሪ ድርጅቱና መንግስታዊ መዋቅሩ ለለውጥ አደናቃፊ ሳይሆን የህዝባችንን የንቃት ደረጃ በሚመጥን መልኩ የለውጥ ሞተር እንዲሆኑ ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ግንባር ቀደም የለውጥ አቀጣጣይ ሆኖ በመሰለፍ እርስዎ እንዲመሩት የሚጠበቀውን የለውጥ ተስፋ እውን እንዲሆን የበኩሉን እንደሚወጣ በግልፅ በመገንዘብ ነው።

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገውን ጤናማ፣ የበለፀገና ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት ህብረተሰብ የመገንባት አንገብጋቢ ጥያቄን እውን ለማድረግ በሚያደርጉት ሃቀኛ ጥረት ሁሉ የአማራ ህዝብና መንግስት ሁልጊዜም ከጎንዎ የሚሰለፍ መሆኑን ከዚህ ባመነበት አቋሙ ጠንካራ እና ቃሉን አክባሪ የጎንደር ህዝብ ፊት ቆሜ በእውነት አረጋግጥልዎታለሁ፡፡

በሁሉም መስክ ለውጥ ለማምጣት የድርሻችን ለመወጣት በቁርጠኝነት የምንንቀሳቀስ መሆናችንን በሙሉ ልብ እገልፅዎታለሁ።
ይህ ዛሬ በደመቀ ሁኔታ በአክብሮት የተቀበለዎት የጎንደር ህዝብ ከጥንት እስከ ዛሬ ለፍትህ መስዋዕትነት እየከፈለ የመጣ ህዝብ ነው ። ለፍትህ ሺዎችን የገበረ ህዝብ ነው ። አሁንም እርስዎ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህና ነፃነትን ለማስፈን በሚያደርጉት ትግል የጎንደር ህዝብ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የማያቅማማ መሆኑን በሙሉ እምነት በታላቅ ኢትዮጵያዊ አክብሮትና ኩራትም ጭምር ነው ፡፡
በመጨረሻም የስራ ዘመንዎ የተሳካ በተለይም የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍቅርና አንድነት እንዲጎለብት፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት ባለቤቶች እንዲሆኑ ሰላምና ፍትህ በአገራችን እንዲሰፍን፣ ድህነትና ኋላቀርነት ከስር መሰረቱ እንዲነቀል፣ አገራችን በጎረቤቶችና በአለም ህብረተሰብ ፊት የታፈረችና የተከበረች እንድትሆን የሚያደርጎት የመሪነት ጥረት እንዲሳካና በኢትዮጵያ ህዝቦች ስምዎና ታሪክ ሁልጊዜ የሚታወሱ መሪ የሚያደርግዎትን ስኬትና ውጤት እንዲያስመዘግቡ መልካሙን ሁሉ በራሴና በአማራ ክልል መንግስትና ህዝብ ስም እመኛለሁ፡፡

በመቀጠልም በዚህ አደባባይ እርስዎን ለመቀበል የታደመውን እንግዳ ተቀባዩን እና አክባሪ ህዝብ መልዕክት እንዲያስተላልፍልኝ በታላቅ አክብሮት እጠይቅዎታለሁ።
አመሰግናለሁ!

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *