የዳኞቹ መልስ እጅግ አስገራሚ ነበር። “አንተ የተከሰስክበትን መዝገብ መሥራት አቁመን ሌላ መዝገብ እየሠራን ስለሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ መስጠት አንችልም። ብይኑ ሳያልቅ ወደ ውጭ ሀገር ሄደህ መታከም አትችልም። ሰው እንደመሆናችን ችግርህ ያሳዝነናል። ቢሆንም ግን ፍትህን አናዛባም።”


ሰለሞን ከበደ

ኑሪ ሙዘይን የመርካቶ ባተሌ ነው። ጠዋት ተነስቶ ሦስት ሕጻናት ልጆቹን ወደ ትምህርት አድርሶ መርካቶ ወደሚገኘው ሱቁ ያመራል። አመሻሹ ላይ የመርካቶ ሁካታና ወከባ ጋብ ሲል ዓለም ባንክ አካባቢ ወደሚገኘው ቤቱ ያዘግማል። አብዛኛውን ጊዜውን በሩጫ ስለሚያሳልፍ ወደ ቤቱ የሚገባው ተዳክሞ ነው። ጥር 21/ 2005 ግን ሩጫውን የሚገታ ጥሪ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል ደረሰው። ከወራት የማዕከላዊ ቆይታ በኋላም በእነ አማን አሰፋ መዝገብ ክስ ተመስርቶበት ወደ ቃሊቲ ማሰሪያ ቤት ወረደ።

አንድ ዓመት ከስምንት ወራት በእስር ከቆየ በኋላ የተከሰሰበት አንቀጽ በብይን ተለወጠ። የተለወጠው አንቀጽ የሚያስቀጣው ከ10 ቀን እስከ 6 ወር ነው። ኑሪ ግን አንድ ዓመት ከ8 ወር ታስሯል። አንቀጹ ከተለወጠ በኋላ “የዋስትና መብቴ ይከበርልኝ” ሲል ጠየቀ። “ጥፋተኛ” ቢባል እንኳ መታሰር ካለበት በላይ ሦስት እጥፍ እንደታሰረ እየታወቀ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱን ለማክበር አንገራገረ። ዓቃቤ ሕግም “ዋስትና ሊከበርለት አይገባም” ሲል ተከራከረ። በመጨረሻም ከሦስት ጊዜ ቀጠሮ ክርክርና ሙግት በኋላ ፓስፖርት ማሳደስም ሆነ ማውጣት እንዳይችል እና ከሀገር እንዳይወጣ የሚያደርጉ ከህጉ መንፈስ ጋር የሚቃረኑ እገዳዎች ተጥለውበት በ30 ሺህ ብር ዋስትና ተለቀቀ።

ከተለቀቀ በኋላ የመከላከያ ማስረጃ አሰምቶ እንደጨረሰ ከፍተኛ የልብ ህመም ስላጋጠመው ሆስፒታል ገባ። ሀገር ውስጥ ያሉ ሆስፒታሎች ወደ ውጭ ሄዶ ካልታከመ ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አረዱት። ላንድማርክ፣ አዳማ ጀነራል ሆስፒታልና ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ ሐኪሞች በሙሉ በአፋጣኝ ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ መታከም እንዳለበት ወስነዋል። በዚህም መሠረት የሐኪሞች ቦርድ ውሳኔውን ይዞ ወደ ፍርድ ቤት አመራ።

መከላከያ ማስረጃ ከተጠናቀቀና ለብይን ከተቀጠረ አራት ወራት አልፏል። ያለሕክምና የምታልፈው እያንዳንዷ ቀን ደግሞ የኑሪን ሕይወት አደጋ ላይ ትጥለዋለች። “በአጭር ጊዜ ውስጥ ብይን እንዲሰጠው፣ ይህ የማይቻል ከሆነ ደግሞ ጥፋተኛ ቢባል እንኳ ከሦስት እጥፍ በላይ መታሰሩን” ጠቅሶ “ይጠፋል” ተብሎ ስለማይታሰብ ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ መታከም እንዲችል ዳኞቹን ፍቃድ ጠየቀ።

የዳኞቹ መልስ እጅግ አስገራሚ ነበር። “አንተ የተከሰስክበትን መዝገብ መሥራት አቁመን ሌላ መዝገብ እየሠራን ስለሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ መስጠት አንችልም። ብይኑ ሳያልቅ ወደ ውጭ ሀገር ሄደህ መታከም አትችልም። ሰው እንደመሆናችን ችግርህ ያሳዝነናል። ቢሆንም ግን ፍትህን አናዛባም።”

መታሰር ካለበት ሦስት እጥፍ በላይ የታሰረን ሰው መልቀቅ የትኛውን ፍትህ ነው የሚያዛባው? ከሌሎች ተከሳሾች ተነጥሎ ብይኑ ቢሠራለትስ ችግሩ ምንድን ነው? በነገራችን ላይ ኑሪ ያቀረበው የመከላከያ ማስረጃ የዓቃቤ ሕግን ክስ በአግባቡ መከላከል በመቻሉ “ነጻ ነው” ተብሎ በመጨረሻ ተለቋል። – ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ yefteh-kulkulet

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *