በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ የደረሰው ጉዳት ገለልተኛ አጣሪ የሚያስፈልገው፣ በሕዝብ ላይ የተፈጸመ ወንጀልና ግፍ ነው። በአበባ እርሻዎች ኬሚካል ቆዳቸውንና የሰውነታቸውን ያጠፋባቸው ወገኖች ጥቂት አይደሉም። ሚድሮክ ወርቅ በሚዝቅበት አካባቢም የደረሰው ጉዳት በተመሳሳይ አሳዛኝ ነው።

በተለያዩ ወቅቶች የወጡ መረጃዎች ይፋ እንዳደረጉት በክቡር የሰዎች ልጆች ጤንነት ላይ፣ በከብቶች ላይ፣ በአካባቢው የተፈጥሮ ሃብት ላይ፣ በመጠጥ ወሃና በግጦሽ ቦታዎች ላይ የደረሰው ጉዳት በተባራሪ ከሚሰማው በስተቀር ወገኖቹን ባለ አካል በጥብቅ ምርመራ አልተደረገበትም።

Image may contain: sky, outdoor and nature
 

አንዳንዶች በማህበራዊ ገጾች፣ ለሰው ስሜት ቅርብ በሆኑ ጋዜጠኞችና ተቆርቋሪ ዜጎች በወፍ በረር ከሚሰማውና ከሚታየው አሳዛኝ የኬሚካል ሰለባዎች የጣር ድምጽ በቀር ጉዳዩ በአገር ደረጃ ቁብ የከተተው አካል ያለ አይመስልም። እንዲህ ያለው ደንታ ማጣት በአገር ደረጃ ክሽፈት ነው።

ድህነትን እና ራስን አለመቻልን እንደ ምክንያት በማቅረብ የሰው ልጆች በመርዝ ሲበከሉ ለዓመታት እጅን አጣጥፎ መመልከት፣ አይቶም ዝምታን መምረጥ፣ ሰምቶም ጆሮ ዳባ ማለት፣ ከጉዳቱ በላይ በአገር ደረጃ አገሪቱን የሚሾፍሩ ሰዎች፣ ይህንን ጉድ እያዩ ለባለሃብቶች ማጎብደድን የመረጡ ዜጎችን ማስብ ልብን የሚሰብር ጉዳይ ነው።

guji 1

” ደግ” እየተባሉ የሚዘፈንላቸው ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲና ወኪል የሚባለው ሰውም ሆነ በውል የሚታወቁ ተቀጣሪ ሰራተኞቻቸው፣ ወርቅ በሚዛቅበት ስፍራ የደረሰውን በደልና ጉዳት አያውቁትም? ህጻናት ጎዶሎ ሆነው ሲወለዱ አላዩም፣ መራመድ ያቃታቸው ህጻናት አዋራ ላይ እየተጎተቱና እየተንፏቀቁ ሲድሁ አላዩም? ይህንን ሁሉ ጉድ ተሸክመው ህዝብ ፊት ቆመው ሲቀጥፉና ቅጥፈታቸው ሲራገብላቸው ማየት…

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

አንዳንድ “ለህዝብ ተቆርቋሪ ነን” የሚሉ ወገኖችም ተመሳስለው በጨቅላ ሕጽናት ስቃይ ላይ እየደነሱ የውዳሴ ሪፖርት ሲያቀርቡ ማየት አደጋውን የከፋ ያደርገዋል። ለዚህም ነው መሰል ህዝብ አምርሮ ከጠመንጃ ፊት ለመቆም የተገደደው። ከጅምሩ ጤናማ ባልሆነ ጨረታ ወደ ግል ንብርተነት የዞረው የወርቅ ማምረቻ  ሚደሮክ እጅ ከወደቀ ጀምሮ በርካታ መረጃ ቢወጣም ሰሚ አላገኘም።

የማዕድን ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሞቱማ ገና የኦሮሚያ ወሃ ቢሮ ሃላፊ ሳሉ ችግሩን እንደሚያውቁት ተናገረው ነበር። በአዲሱ ካቢኔ ወደ መከላከያ ሚኒስትርነት የዞሩት አቶ ሞቱማ ይህንን ሁሉ ጉዳይ እያወቁ የሚድሮክ ወርቅን ውል እንዲራዘም ማድረጋቸው ዞሮ እንደሚያስጠይቃቸው እየተነገረ ነው። ቀደም ሲል ከህዝብ በቀረበና በክልሉ ውስን ሃላፊዎች በተሰጠ ምስክርነት የሚድሮክ ወርቅ  ውል እንደማይታደስ ይፋ ሆኖ ነበር። ዳሩ ግን ባለፈው ሳምንት ለተጨማሪ 10 ዓመታት ያለ አንዳች ለውጥና ግዴታ መራዘሙ ይፋ ሆኗል። ይህንኑም ተከትሎ  ተቃውሞ ተቀስቅሷል።

” ባለሃብቱ” ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን ከሙስና እና በውል ባልተገለጸ ጉዳይ በሳዑዲ እስር ላይ ናቸው። አብረዋቸው ከታሰሩት መካከል አብዛኞቹ የተጠየቁትን ገንዘብ ከፍለው ሲለቀቁ እሳቸው ለምን እንደሆነ በውል በማይታወቅ ምክንያት አሁንም ዘብጥያ ናቸው። የቅርብ ሰዎች ነን የሚሉ ዛሬ ይፈታሉ። ነገ አገር ቤት ይገባሉ በሚል በተለያዩ መገናኛዎች ቢናገሩም አሁን ድረስ እሳቸው አልተለቀቁም። አሁን ሚድሮክ ወርቅ አዲስ ተቃውሞ የገጠመው እሳቸው በሌሉበት ነው። አባዱላ ኦሮሚያን በሚያስተዳድሩበት ወቅት በስፍራው በመገኘት ላህዝብ የገቡትን የመሰረተ ልማት ግንባታ ምን ያህል ተግባራዊ ድደረጋቸው በሪፖርት ደረጃ አልቀረበም። ይህ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የንተነሳውን ተቃውሞ አስመልክቶ የኦህዴድ አቋም በይፋ አልተገለጸም።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

ኢሳት የሚከተለውን ዝግቧል

በጉጂ ዞን ሻኪሶና ፊንጫ ከተማ ከጠዋት ጀምሮ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።

ሜድሮክ ኢትዮጵያ የወርቅ ማእድን የማውጣት ስራውን እንዲያቆም ከተደረገ ከ1 ዓመት በኋላ በድጋሚ ፈቃድ በማግኘቱ የአካባቢው ህዝብ በተቃውሞ አደባባይ ወጥቷል። ተቃዋሚዎች ከፌደራል ፖሊስ ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው በፊንጫ እስካሁን 3 ሰዎች በአስለቃሽ ጭስ ተጎድተው ወደ ህክምና ማዕከል መወሰዳቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ሻኪሶና አካባቢው በወርቅ ምርት የበለጸገ ምድር አለው። ከዚህ አንጡራ ሀብት ግን የአካባቢው ህዝብ መጠቀም አልቻለም። ወርቅ ተሸክሞ በድህነት የሚማቅቅ፣ ሆስፒታል አጥቶ የሚሰቃይ፣ትምህርት ተነፍጎት ድንቁርና የተፈረደበት ህዝብ ሆኗል።

ሜድሮክ ኢትዮጵያ የተሰኘው የሼህ ሁሴን አላሙዲን የወርቅ ቁፋሮ ኩባንያ በአካባቢው ትምህርትና ጤና አስፋፋለሁ የሚል የተስፋ ቃል ሰጥቶ በአካባቢው ወርቅ ማፈስ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። እንደሰጠው ተስፋ ግን ለአካባቢው ህዝብ አንዳችም የመሰረተ ልማት ሳያከናውን ቆይቷል። የዚህ ኩባንያ ጉዳይ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናትን በብርቱ ሲፈታተን ቆይቷል።

በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን የህዝ ንቅናቄን ተከትሎ የሻኪሶና አካባቢዋ ህዝብም በሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ ላይ ተቃውሞውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

ከዚህ ቀደም የሚደረገውን ተቃውሞ በአጋዚና በፌደራል ፖሊስ የሃይል ርምጃ ሲያፍን የዘለቀው የህወሃት አገዛዝ በመላው ኦሮሚያ ህዝባዊ አመጽ ሲቀጣጠል የሻኪሶን ህዝብ ተቃውሞ መግፋት ከማይችልበት ጊዜ ላይ ደረሰ።

ይህን ተከትሎም ለ10 ዓመት ኮንትራት የወሰደው የሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ ለተጨማሪ 10 ዓመት እንዳይራዘምለት ተደረገ።

ግን ብዙም አልቆየም። የህዝብ ንቅናቄ ጋብ ማለቱን ተከትሎ ከሰሞኑ የሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ የጠየቀውና ለተጨማሪ 10 ዓመታት ወርቅ እያፈሰ እንዲወስድ የሚፈቅድለት ኮንትራት መሰጠቱ ተገለጸ። ይህም ቆሞ የነበረውን የህዝብ ተቃውሞ ዳግም እንዲቀሰቀስ አደረገው።

ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንዳመለከተው የሜድሮክ ኩባንያ ኮንትራቱ መራዘሙ የሻኪሶንና አካባቢውን ህዝብ አስቆጥቷል። ዛሬ ሻኪሶን ጨምሮ በ5 ከተሞች ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል። በፊንጫም እንዲሁ ህዝብ አደባባይ በመውጣት የወርቅ ዘረፋውን አጥብቆ እንደሚያወግዝ ገልጿል።

ተቃውሞ ከሻኪሶ ሌላ በ4 ከተሞች የተካሄደ ሲሆን በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ቁጣውን በመግለጽ ሜድሮክ በአስቸኳይ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ጠይቋል። በፊንጫው ተቃውሞ የአገዛዙ ታጣቂዎች አስለቃሽ ጢስ በመተኮስ 3 ሰዎችን መጉዳቱንም ለማወቅ ተችሏል።

ነገ ተቃውሞው በሌሎች በርካታ ከተሞች ሊካሄድ እንደሚችል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በሌላ በኩል በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሚማርሩ የኦሮሞ ተወላጆች በዛሬው ዕለት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። በባለፈው ህዝባዊ ንቅናቄ ወቅት የታሰሩ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ባለተፈቱበት ሁኔታ መማር አንችልም በማለት ያሰሙትን ተቃውሞ ሌሎች የዩኒቨርስቲው ተማሪዎችም መሳተፋቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *