ሳዑዲ አረቢያ በሙስና ወንጀልና በሌላ ግልጽ ያለወጣ ጉዳይ እስር ቤት የሚገኙት ሼኽ መሐመድ አላሙዲ ላለፉት ሃያ ዓመታት በባለቤትነት የያዙት የለገደንቢ ሚድሮክ የወርቅ ማምረቻ ከማምረት ስራው መታገዱን የማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ይፋ አደረገ። ፋብሪካው በሰውና በተፈጥሮ ሃብት ላይ ላደረሰው ጉዳት ስለመጠይቁ ያለው ነገር የለም።

ከሽያጩ ጀምሮ በውል በማይታወቅ የማስፋፊያ ስምምነት ችግር እንዳለበት ለዓመታት ምሬት ሲቀርብበት የነበረው የለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ በሰው ልጆች ላይ ላደረሰው ጉዳት ተጠያቂ እንዲሆን ባለቤቱ ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅት መደረጉን የዛጎል ምንጭ አስታውቀዋል።

የክስ ሂደቱን ለማስጀመር ስራ የጀመሩት ክፍሎች እንዳሉት ” ከፋብሪካው በሚለቀቅ ተረፈ ምርት የደረሰው አስከፊ አደጋ በየትኛውም መስፈርት፣ በማንኛውም አገር፣ በየትኛውም የፍርድ አካሄድ ወንጀል ነው” ወንጀሉ እስር ቤት ያሉትን ” ባለሃብት” ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሃላፊነት ደረጃዎች  ላይ ያሉትን በሙሉ እንደሚያካክትት ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ተናግረዋል። 

ሚድሮክ የወርቅ ማምረት ስራውን እንዲያከናውን ለተጨማሪ አስር ዓመት ፈቃድ መውሰዱን ተከትሎ የተነሳውን የሕዝብ ተቃውሞ ተከትሎ እግዱ መወሰኑን የገዢው ፓሪቲ ልሳኖች እንደሚከተለው ዘግበውታል።

የሚድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ ከዛሬ ጀምሮ መታገዱን የኢፌዴሪ የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በኦሮሚያ ክልል ጉጅ ዞን ሚድሮክ ጎልድ በለገደምቢ በሚያካሂደው የወርቅ ማዕድን ልማት ስራ ላይ የአካባቢው ነዋሪ፥ የኩባንያው የምርት ሂደት የአካባቢ ብክለት እያስከተለ ነው የሚል ቅሬታ ማንሳቱን ተከትሎ ነው ፍቃዱን ያገደው።

በገለልተኛ አካል ጥልቀት ያለው ጥናት እስከሚጠና ድረስ የኩባንያው ወርቅ የማምረት ስራው መታገዱንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ጥናቱ በገለልተኛ አካል ከፌደራል እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮችን እና ባለ ድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እንደሚካሄድ፥ የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ባጫ ፋጂ ተናግረዋል። የኩባንያው ወርቅ የማምረት ሂደት መቀጠል ያለመቀጠል ሂደትም በጥናቱ ውጤት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አዲስ ጥናት ሲሰራም የጥናቱ ወሰን ከዚህ በፊት ከተደረገው እንዲሰፋ እንደሚደረግ ጠቅሰው፥ የሚወሰዱ ናሙናዎች ቁጥርም ከፍ ይደረጋል ብለዋል። የነበረው አዋጅ የሚድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ እድሳት እንዲደረግ እንደሚፈቅድ ያነሱት ዳይሬክተሩ፥ የኩባንያው የወርቅ አመራረት ሂደት በአካባቢው ችግር እየፈጠረ መሆኑን ሚኒስቴሩ እንዳመነበት አንስተዋል።

ይህን ተከትሎም የኩባንያው የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ ከዛሬ ጀምሮ መታገዱን አስረድተዋል። አሁን የተወሰደው እርምጃም ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል። ከሚድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ጋር በተያያዘ በገለልተኛ አካል የሚደረገው የጥናት ሂደትም ዛሬ ተጀምሯል። የጥናቱ አጠቃላይ ውጤት ምን ያክል ጊዜ እንደሚወስድና መቸ እንደሚጠናቀቅ ግን የተባለ ነገር የለም።

በካሳዬ ወልዴ እና ባሃሩ ይድነቃቸው

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *