ግራ በመጋባት የዶክተር ብርሃኑንን ምላሽ የሚጠብቁ ግን በርካታ ናቸው፤ እነ አቶ ሌንጮ በግል እንደ ፓርቲ የፈለጉትን አቋም ማራመድ የራሳቸው ጉዳይ ቢሆንም የአርበኞች ግንቦት ሰባትን ቀለም አያሳምረውም፤


የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በአቶ ሌንጮ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር / ኦዲኤፍ/ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ እንደሚያቀና ይፋ አድርጓል፤ ቀደም ሲል ድርጅቱ መግለጫ አውጥቶ ድርድር ማድረጉን ይፋ አድርጎ ነበር፤
የዜናውን ይፋ መሆን ተከትሎ መነጋገሪያ የሆነው አቶ ሌንጮ ለታና ድርጅታቸው ወደ አዲስ አበባ የማቅናታቸው ጉዳይ ሳይሆን “ከዛስ?” የሚለው ጉዳይ ነው፤ ከየአቅጣጫው የተለያየ አስተያየት ቢወረወርም ፣ ለአቶ መለስ ቅርብ እንደነበሩ የሚነገርላቸው አቶ ሌንጮ አገር ቤት ገብተው “ህገ መንግሥቱንና ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ተቀብዬ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ተስማምቼና ወድጄ ወደ አገር ቤት ለመግባት ችያለሁ ፤ያሳዘነውን መንግስትና ህዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን” በማለት ከአጋሮቻቸው ጋር ሆነው በቲቪ መግለጫ የሚሰጡበት ቀን ነው ፤

Bilderesultat for dr berhanu nega and lencho leta
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ አቶ ሌንጮ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር ውህደት ሲፈጽሙ በጎን አዲስ አበባ ለመግባት ድርድር እያደረጉ መሆኑንን ዘግቦ ነበር፤ ዛሬ ላይ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ምን እንደሚሉ ባይታወቅም እነ አቶ ሌንጮና ዲማ ነገዎ ሱዳን ላይ ከሕወሃት ሰዎች ጋር ድርድር ማድረጋቸው መሰማቱን አስመልክተው አርበኛ ብርሃኑ ነጋ “እንዲህ ያለ እቃ እቃ ይጫወታሉ ብዬ አላስብም” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት፤
በወቅቱ ዶክተር ዲማ ነገዎ ወደ ሱዳን ያቀኑት ለስራ እንደነበርና ከሕወሃት ሰዎች ጋር አለመገናኘታቸውን ይፋ አድርገው ነበር፤ እሳቸውም ሆኑ አብረዋቸው ወደ ሱዳን ያቀኑት ቢያስተባብሉም ጎልጉል ምንጮቹን ጠቅሶ ኦዲኤፍ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ አዲስ አበባ ሊያገባ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጦ ነበር፤ ይሁን እንጂ የቀድሞው የአክራሪነት ጉዞና የአርባ ዓመቱ የትግል ታሪክ በስተርጅና የተገለጸላቸው አቶ ሌንጮ ኦስሎ ከዶክተር ብርሃኑ ጋር ተቀምጠው የሚከተለውን ሲሉ ጭብጨባ ይወርድላቸው ነበር፤

“በኢትዮጵያ ታሪክ ማንም ንጉስ ከእዚአብሔር የመጣሁ ነኝ ብሎ አያውቅም። በኢትዮጵያም ጨቋኝ የሚባል ብሔር የለም።የጨቆነ ከአንድ ብሔር የወጣ ቡድን ቢሆን ይህ ቡድን ብሄሩን ይወክላል ማለት አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።” … እኔ ኦሮሞም ኢትዮጵያዊም መሆን እፈልጋለሁ። ”    ጭብጨባው ጎረፈ።

“…ደርግ ሲመጣ ከደርግ የባሰ ሊመጣ አይችልም ብለን ስናስብ የባሰ መጣ። ሆኖም ግን ማሰብ የሚገባን ደርግ ሲገድል በቀጥታ የፍየል ወጠጤ እያለ ነበር። ስለሆነም የገደለውን ቁጥር መገመት ይቻላል። የአሁኖቹ ግን በስውር ነው። በስውር ያሰሩት፣የገደሉት እና የሰወሩት ሕዝብ ቁጥር አሁን መናገር አንችልም። ምክንያቱም ሁሉን በድብቅ ነው የሚያደርጉት”  አያይዘውም ኢትዮጵያን እስካሁን ጠብቆ ያኖራት የህዝቧ ጨዋነት እንጂ የመሪዎቿ ብቃት አይደልም ” ጭብጨባው ጎረፈ።

በማርች 27, 2015 ጎልጉለ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደጻፈው እነ አቶ ሌንጮ ለታ አዲስ አበባ ደረሰው የሚያናግራቸው አጥተው ተመልሰዋል፤ “አረና እና ህወሃት መካከል ማንም ጣልቃ እንደማይገባ ሁሉ ኦዴግ እና ኦህዴድ መካከልም ይህ ሊከበር ይገባል” በሚል መቃወሚያ ኦህዴድ ድርድሩን እንደማይቀበል በማሳወቁ ነበር ድርድሩ ሳይደረግ የቀረው። ጎልጉል አያይዞ እንዳለው እነ አቶ ሌንጮ በግል አቶ ስብሃትን ማግኘታቸውንና ከአምስት ዓመት በኋላ በ2012 በሚካሄደው ምርጫ እንዲሳተፉ ድጋፍ እንደሚስጣቸው ማረጋገጫ አግኝተዋል። የአዲስ አበባው ጉዞ ከመከነ በሁዋላ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ የጀመረውን መንገድ እንደሚገፋበት ይፋ አድርጎም ነበር፤

እነ ሌንጮ ወደ አዲስ አበባ እንዲያቀኑ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅና ሚና ተጫውተው ነበር። በተለይም ፕሮፌሰሩ ኦስሎ በተደጋጋሚ በመምጣት ምክክር ማካሄዳቸውን እንደሚያውቁ የሚገልጹ ወገኖች ይናገራሉ

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

ይህ ከላይ የተባለው ለማሥታወሻ ያህል ሲሆን አሁን ” እጅግ አመርቂ እድል” ሲል ኦዲኤፍ ያቆላመጠው ድርድር ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል? የሚለው ነው፤ አብዛኞች እንደሚሉት አሁን በኦሮሚያ ምድር ያለው ትግል ያለው በወጣቶችና በተራማጅ ኦህዴዶች እጅ ነው፤ ወደ ሕዝብ ስሜት ራሱን በመጎተትና ውስጡን በማጥራት የሚገባውን ቦታ የያዘው ኦህዴድ ስር መግባትና ቀሪ የጡረታ ዘመንን በአገር ምድር መኖር ካልሆነ በስተቀር የእነ ሊንጮ ፓርቲ ኦሮሚያ ላይም ሆነ በአገሪቱ ደረጃ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ የሚያምኑ በርካታ ናቸው፤
ከኢህአዴግ አንጻር የተገፉ የሚባሉ ፓርቲዎችን ማሰባሰብና ” እርቅ” የተሃድሶው አካል መሆኑንን ለውጭው ማህበረሰብ ለማሳየት ከሚጠቀምበት በቀር አንዳችም ፋይዳ የለውም የሚሉ ያሉትን ያህል፣ መስማማት ክፋት እንደሌለው የሚጠቁሙም አሉ፤

ግራ በመጋባት የዶክተር ብርሃኑንን ምላሽ የሚጠብቁ ግን በርካታ ናቸው፤ እነ አቶ ሌንጮ በግል እንደ ፓርቲ የፈለጉትን አቋም ማራመድ የራሳቸው ጉዳይ ቢሆንም የአርበኞች ግንቦት ሰባትን ቀለም አያሳምረውም፤ በዚህ መነሻና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዶክተር ብርሃኑ ምን ይሉ ይሆን? የሚለው ለመስማት ያህልም ቢሆን የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፤

አርበኞች ግንቦት ሰባትን በስም ባይጠቅሱም የመጀመሪያውን ንግግር አድነቀውና ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር በያን አሶቦ ሁሉም ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲገቡ ፍላጎታቸው መሆኑንና ይህ አስፈላጊም እንደሆነ ከኦኤሜን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አመልክተዋል፤

 

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

“ወሬ አይደለም፤ አገር ቤት አንገባለን” ሌንጮ ለታ

የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር ከፍተኛ አመራርና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ አዲስ ያቋቋሙትን ድርጅት ይዘው አዲስ አበባ እንደሚገቡ አስረግጠው ተናገሩ። አቶ ሌንጮ ድርጅታቸው ኢትዮጵያ ገብቶ ለመታገል መወሰኑ ለምን ወሬ እንደሚባል እንዳልገባቸውም አመላክተዋል። በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ኢትዮጵያ መግባታቸውን ኦነግ እንደሚቀበለው ተጠይቀው “ኦነግን ጠይቅ” በሚል ጠበቅ ያለ መልስ ሰንዝረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እንደሌለው አመልክቷል።

ጥር 5 ቀን ከጀርመን ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት አቶ ሌንጮ “ኖርዌይ ተቀምጠን ምን እናደርጋለን? ሃገር ቤት ገብተን እንታገላለን” ሲሉ ወደ አገር ቤት ለመመለስ መወሰናቸውን ግልጽ አድርገዋል። “ይሳካል?” በማለት ጠያቂው ላቀረበው “ይሳካል አይሳካም ተብሎ ወደ ትግል አይገባም” በማለት አቶ ሌንጮ ማምረራቸውን በሚያሳብቅ ሁኔታ መልስ ሰጥተዋል።

ህወሃት የዘረጋውን የፌዴራል ሲስተም እንደሚቀበሉትና የኦሮሞ ህዝቦች ጥያቄም በዚያው ውስጥ ሊመለስ እንደሚችል ያመለከቱት አቶ ሌንጮ፣ “በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋ የተመሰረተ ሳይሆን በህግና በህገመንግሥት በተደነገገ የህዝቦች አንድነት እናምናለን” ብለዋል። የግለሰብ መብት ከብሔር መብት መቅደም አለበት፣ የብሔር መብት አስቀድሞ ሊከበር ይገባዋል በሚል ሁለት አቋም ከሚያራምዱት የተለየ ፕሮግራም እንዳላቸውም አቶ ሌንጮ አስታውቀዋል። የግለሰብም ሆነ የቡድን መብት መከበር አለበት የሚል ፕሮግራም ያለው አዲሱ ድርጅታቸው በዚህ አቋሙ ከሌሎች እንደሚለይ አመልክተዋል።

በምርጫ የመሳተፍን ጉዳይ አስመልክቶ የእሳቸው ድርጅት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ተቃዋሚ ሃይሎች ወደ ምርጫ ቢገቡ ፍላጎታቸው መሆኑንን አቶ ሌንጮ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ከምርጫ በፊት ብዙ ጥያቄዎች እንዳሉ አመልክተዋል። ዴሞክራሲን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፋፈት ምርጫ ብቻውን መፍትሔ እንዳልሆነም ጠቁመዋል። ህዝብን አገር ቤት ገብቶ ማስተማር፣ መቀስቀስና ማብቃት በዋናነት አስፈላጊ እንደሆነም አስምረውበታል።

ከኢህአዴግ ጋር ድርድር ስለማድረጋቸው ለተጠየቁት፣ እስካሁን የተደረገ ድርድር እንደሌለ አቶ ሌንጮ ጠቁመዋል። አያይዘውም ከኢህአዴግ ጋር ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋርም የመደራደር እቅድ እንዳላቸው አመልክተዋል። አቶ ሌንጮ በተደጋጋሚ አገር ቤት መሄዳቸው መገለጹንም በማንሳት አስተባብለውታል። አቶ ሌንጮ ድርድር ስለመደረጉ ባያምኑም በተለያዩ ጊዜያት በኖርዌይና በተለያዩ አገራት ከኢህአዴግ መልዕክተኞች ጋር አሁን ይፋ ባደረጉት ጉዳይ ዙሪያ መነጋገራቸው መዘገቡ ይታወሳል። ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣም በቅርቡ ኢህአዴግ ብሔር ተኮር ከሆኑ ድርጅቶች ጋር ድርድር እያደረገ መሆኑንና ከሌሎች ማናቸውም ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ሃሳብ እንደሌለው ምንጮቹን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል።

አቶ ሌንጮ የሚመሩት ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት መወሰኑን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ዲና ሙፍቲ “መረጃ የለኝም፤ የድርጅት ሰዎች ብትጠይቅ የተሻለ ነው” በማለት ዜናውን ይፋ ላደረገው የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ተናግረዋል። የሚመለከታቸውን አካላት ለማግኘትና በሪፖርቱ ለማካተት እንዳልተቻለ ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል። አብዛኛው የኦነግ ደጋፊዎች የነበሩ በድርጅቱ የትግል ጉዞና ውጤታማ አለመሆን መማረራቸውን የተለያዩ ድረገጾች በስፋት ይዘግቡ ነበር።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *