ጠ/ሚ አቢይ አህመድ ወንበር ከያዙ 50 ቀናት አለፉ። የጫጉላ ሽርሽሩ ግማሽ ላይ ደርሰዋል ማለት ነው። በትረ ሥልጣኑን በጨበጡ ዕለት ያደረጉት ንግግር አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ አስደስቷል። ጣት እንቆርጣለን፤ የከፋው በሊማ ሊሞ ገደል ማቋረጥ ይችላል…፤  ወራዳ ….. ጨምላቃ… አይነት ጸያፍ ቃላት ሲደመጥበት በነበረው ፓርላማ እንዲያ ያለ በትህትና የተሞላ ፤ እራስን በወቀሰና ብሎም ለተፈጸመ በደል ይፋ ይቅርታ የጠየቀ ንግግር ማድመጥ በርግጥም ብርቅ ነው፡፡

ዶክተር አቢይ በንግግራቸው ሟቹ ጠ.ሚ በ21 ዓመት የስልጣን ዘመናቸው ስሟን ለመጥራት እየተጠየፉ “ሃገሪቷ” ሲሏት የነበረቺውን ኢትዮጵያን 39 ጊዜ ደጋግመው ጠርተዋታል። ይህም ኢትዮጵያዊውን ዜጋ ሁሉ አስደስቷል። የህዝባዊ ድጋፋቸው መነሻም ይኽው ታሪካዊ ንግግር ነው።

ዶ/ር አቢይ በ50 ቀናት የስልጣን ቆይታቸው ለበርካታ ዘመናት የናፈቅናቸውን ድንቅ ድንቅ ነገሮችን ነግረውናል። የዘር ፖለቲካ ጦስ ያስከተለውን የመበታተን አደጋ በፍቅርና በመቻቻል ልንመክት እንደሚገባ መክረውናል። ለዚህም እውንነት ተግተው እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል። በርግጥ የህዝብን ጥያቄ ሁሉ በአንድ ጀንበር መመለስ አለመቻሉም እውነት ነው። ህዝብ ግን ከሰናይ ቃላቸው በመነሳት ተስፋን ሰንቆ በተስፋ እየተከተላቸውና እየጠበቃቸው ነው።

በአሁኑ ወቅት የዶክተር አቢይን እንቅስቃሴ በተመለከተ የተለያዩ አመለካከቶች እየተንሸራሸሩ ይገኛሉ። ሱሪ ባንገት አይነት፦ ይህን አላደረገም፤ ይህን ችላ ብሏል…..ስለዚህ  ጉዳይ አልተናገርም …. የሚሉ ጥርጣሬን ማዕከል ያደረጉ ወቀሳዋች እንዳሉ ሁሉ፤ የዶር አቢይን ንግግር ከህውሃት የዘመናት ተንኮልና ሴራ አኳያ ብቻ እየመዘኑ ከወዲሁ እንደ መሲህ በመቁጠር ፍጹም የሆነ ድጋፍ በመስጠት ላይ ያሉም አሉ።

በኔ እይታ ሁለቱም ጫፎች ከቁንጽል ነገር ተነስተው ለድምዳሜ የቸኮሉ ኢ-ምክንያታዊ ናቸው።  ችኩል የሆነ “ፍጹም አይነኩብን” አይነት የድጋፍ ስሜት ተገቢ አይደለም። በዛው አንጻር ዶክተሩን ወያኔን በምናይበት መነጽር በማየት ብቻ ጭፍን ነቀፌታ መሰንዘርም ትክክል አይሆንም።  በኔ አተያይ በመጀመሪያ የህወሃትን የበላይነት በመታገል እዚህ ለደረሱበት ጉዞ እውቅናና አድናቆት መቸር ይገባናል። በመቀጠል ወደፊትም ቃል የገቡትን ነገር እንደሚተገብሩ በማመን ፤ ተገቢውን ጊዜና ድጋፍ መስጠት ያስፈልጋል። በዛው አኳያ  ጉልበታቸው ህዝብ መሆኑንና የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ ከመመለስ ሌላ ምንም የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸው የሚያስታውሱ ምክሮችን መሰንዘር፡ አቅጣጫ የሳቱ በመሰለን ግዜም ገንቢ ትችቶችን ማቅረብ ጠቃሚ ነው።

ዶር አቢይ ከመጋረጃው ጀርባ

ዶ/ር አቢይ በሹመት ቀናቸው ሊተገብሯቸው ቃል ከገቧቸው ጉዳዮች መካከል፦

  • ገለልተኛ የዲሞክራሲ ተቋማትን መገንባት
  • በየትኛውም የትግል ስልት ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ (በሳቸው አጠራር ተፎካካሪ) ድርጅቶች ጋር መነጋገር
  • ከመንግስት ተጽዕኖ ውጭ የሆነ የፍትህ ስርዓት መገንባት ዋና ዋናዎቹና ለመሰረታዊ ለውጥ መደላድል ናቸው የሚባሉ ተግባራት ይገኙበታል።

ይሁንና እነኚህ በዋናነት ለተግባራዊነታቸው ቃል የተገባላቸው ጉዳዮች እውን ከመሆናቸው በፊት የሚከተሉት ቅድመ ሁኔታዎች ማለትም

  • የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መነሳት፤
  • የፖለቲካ እስረኞች ሙሉ ለሙሉ መፈታት፤
  • በሽብርተኝነት የተፈረጁ ተፎካካሪ ድርጅቶችን እገዳ ማንሳት፤
  • የጸረ-ሽብር አዋጁን (ማንሳት ወይም ማስተካከል) የመሳሰሉት እርምጃዎች እንደሚተገበሩ ህዝብ ታሳቢ አድርጓል።

ይሁንና ዶክተር አቢይ የተጠቀሱትን የፖሊሲ ለውጥን የሚጠይቁ እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጅት ስለማድረጋቸው ቢቂ ፍንጭ እየሳዩ አይደለም። ይህ ለምን ሆነ ? ለሚለው ጥያቄ ተጨባጭ መልስ መስጠት ባይቻልም፤ ለህዝብ የገቡትን ቃል ለመፈጸም እንዳይችሉ የሚገዳደራቸው ኃይል እንዳለ መገመት ግን ከባድ አይሆንም።

ለዚህ ግምት ዋቢ መጥቀስ ካስፈለገ፦ በባህርዳር በነበራቸው ቆይታ ባህታዊያኑን ለማስፈታት የነበረባቸውን ችግር ጠቆም አድርገው ማለፋቸውን ማስታወስ ይቻላል።  እናም  ዶክተር አቢይ ከመጋረጃው ጀርባ በከፍተኛ ጉልበት እየታገሏቸው ያሉትን “የህወሃትን የበላይነት ናፋቂ” ወገኖች መጋረጃውን በጥቂቱ ገለጥ አድርገው ቢያሳዩ ውጥረታቸውን ህዝብ ተረድቶ አስፈላጊውን ጉልበትና እገዛ ሊያደርግላቸው የሚችል ይመስለኛል፡፡

እንደኔ ግምት ዶክተር አቢይ በሹመታቸው ቀን ያደረጉትን ንግግር የህወሃት ሰዎች እንደገና ኤዲት በማድረግ የሚፈጸሙና የማይፈጸሙ ጉዳዮችን በማንሳት ግብ ግብ ውስጥ ሳይገቡ አልቀሩም። ይህን ለማለት ያስገደደኝ ዶክተር አቢይ በሹመት ቀን ንግግራቸው “በማንኛውም መንገድ የምትታገሉ ” በማለት ለተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ያደረጉት የሰላም ጥሪ በቅርቡ የኢህአዴግ ጽቤት ባወጣው መግለጫ “በሰላማዊ ትግል ውስጥ ያላችሁ” በሚል መቀልበሱ ነው።

ይህን በማስረጃና በመረጃ መጥቀስ መቻሉ እንጂ ዶክተር አቢይና የህወሃት ባለስልጣናት ከመጋረጃው ጀርባ በሌሎችም በርካታ ጉዳዮች እየተሟገቱ እንደሆነ ፍንጭ የሚሰጡ ሁነቶች አሉ።

በተለያዩ ክልሎች፤ በተለይም በቅርቡ በደቡብ ክልል ሚዛን ተፈሪ የተከሰተው ብሄርን ከብሄር የማናቆር ተግባር በህወሃት የደህንነት አካላት እንደተመራ የክልሉ ነዋሪዎች መስክረዋል። ይህ ማለት ከቤተ መንግስቱ አካባቢ የራቀውና በየክልሉ የደህንነትና የመከላከያ መዋቅር ላይ የተንሰራፋው የህወሃት ክንፍ ለጠ/ሚ አቢይ እንቅስቃሴ እንቅፋት በመፍጠር በህዝብ ያገኙትን ተቀባይነት ለመናድ እየተጋ መሆኑን የሚያሳይ አንዱ የመጋረጃው ጀርባ ትግል መገለጫ ነው።

ዶ/ር አቢይ ዘርዓይ የተባለውን የብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ኃላፊ የነበረ ( ተወዳጇን ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩን የድሮ ሥርዓት ናፋቂ ብሎ የፈረጀ)  ጭፍን ዘረኛ ! ከስልጣን ካባረሩ በኋላ አጋጣሚ ጠብቀው ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩን ሙያዊ ብቃቷን አድንቀው ማወደሳቸው በራሱ ከመጋረጃው ጀርባ ከህወሃት ጋር የተያያዙትን ግብግብ በጭላንጭል የሚያሳይ ይመስለኛል።

ባጠቃላይ ከመጋረጃው ጀርባ ስላለው እሰጥ አገባ አለማወቃችን፤ በተለይም በህወሃት ስራ አስፈጻሚ ውስጥ ያለው የኃይል አሰላለፍ ምን ይመስላል? ምንያህልስ ለጠ/ሚ አቢይ ጉዞ አመቺ ነው ? ለሚሉት ጥያቄዎች በቂ መረጃ ባለማግኘታችን ዶክተሩን ከመጋረጃው ፊት ለፊት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብቻ እንድንገመግማቸው አስገድዶናል።

ለአብነት ያህል በአቶ አንዳርጋቸው መፈታት ዙሪያ እየተንሸራሸረ ያለውን ሃሳብ እንመልከት፦ አቶ አንዳርጋቸው ከእስር እንዲፈታ ውሳኔ ላይ ተደርሷል የሚለው መረጃ ከተሰማ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ነገር ግን ተግባራዊነቱ እስካሁን የዘገየበት ምክንያት በዶክተር አቢይና በህግ አስፈጻሚው መካከል ያለ አለመግባባት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምክንያት ማሰብ ይቸግራል።

ዶክተር አቢይ ራሳቸው ባዋቀሩት የሚንስትሮች ምክርቤት ውስጥ እጅ ጠምዛዥ ሃይል ያጋጥማቸዋል ባይባልም፤ በኢሃአዴግ ስራ አስፈጻሚ ውስጥ ያላቸው ጉልበት ግን ምን ያህል እንደሆነ መገመት አይቻልም።  የሥራ አስፈጻሚውን ይሁኔታ ቢያገኙ እንኳ ህግ አስፈጻሚው ሙሉ ለሙሉ በሚባል መጠን በህወሃት ሰዎች እጅ በመሆኑ ውሳኔያቸውን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ችግር እንደሚያጋጥማቸው አይጠረጠርም፡፤ ለዚህ ደግሞ መፍትሄው ከመጋረጃ ጀርባ ያለውን ግብ ግብ እያሾለኩ ለህዝብ ማሳየትና የህዝብን እገዛ መሻት ብቻ ነው። ይህ አሁንም በመጠኑ እየተከወነ መሆኑን ልብ ይሏል።

የህወሃትን የበላይነትን ናፋቂዎች

በነገራችን ላይ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ በደርግና በንጉሱ ዘመን የነበሩ ድንቅ የታሪክ ክስተቶችን መዘከር፤ አበው የሰሩትን ገድል ማውሳት በህወሃት ካድሬዎች እይታ “የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ” የሚያሰኝ ተግባር ነበር፡፤ ዛሬ ደግሞ በተራቸው የህወሃት ካድሬዎች የህወሃትን የ17 ዓመት የጦርነት ጉዞ እያነሱ ቅድመ ዶ/ር አቢይ የነበራቸውን የበላይነት ለመመለስ በሚያደርጉት ያልሞት ባይ ተጋዳይ ፍልሚያ ሳቢያ እነሱንም “የህወሃት የበላይነትን ናፋቂ “ ልንላቸው ተገደናል። ፌዝ በሚመስል መልክ ታሪክ እራሱን ደገመ ያለው ማን ነበር…? በቅርቡ አንድ የትግራይ(ህወሃት) ሴት በመቀሌ ደብረ ጺዮን በተገኘበት ስብስባ ላይ “አዲስ አበባ ውስጥ ሹሩባችንን ሸፍነን ለመሄድ ተገደናል እናንተ ምን እያደረጋችሁ ነው?” በሚል የበላይነታችንን አስመልሱ አይነት ጭንቀት የተጣባው ሮሮ ማሰማቷም የዚሁ ወቅታዊ የህወሃት ካድሬዎች ጭንቀት መገለጫ ነው።

ዶክተር አቢይ ከመጋረጃው ፊት ለፊት፤

ዶ/ር አቢይ ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ የፈጸሟቸው ነገሮች ባብዛኛው የህዝብን ስሜት በማረጋጋት ላይ ያተኮሩ ናቸው። በተለያዩ የሃገሪቷ ክፍሎች ያለውን ህዝብ በግንባር እያነጋገሩ መንግስታቸው ሊያደርግ ያሰበውን በመንገር ከህዝብም የሚጠበቀውን በመጠቆም አያይዘውም በአብሮነትና በመደመር መስራት ያለውን ጥቅም አንክሮ ሰጥቶ ማስረዳት ነው።

ከመጋረጃው ፊት ለፊት ካየነው የዶክተር አቢይ እንቅስቃሴዎች መካከል በተለይ በውጭ አገራት በእስር ላይ የነበሩ ዜጎቻችንን ማስፈታታቸው በ27 አመታት ለመጀመሪያ ግዜ መንግስት ዜጋውን ያሰበበት ታሪካዊ እርምጃ ነው። ይህን ማድረጋቸው በራሱ ህወሃት ለዜጎቹ የነበረውን ጥላቻ ያጋለጡበት፤ ሳይተኩሱ የገደሉበት ድንቅ ስትራተጂ ነው።

በነገራችን ላይ ዶ/ር አቢይ በእጃቸው ያለውን አንዳርጋቸውን ሳይፈቱ በውጭ ያሉትን ዜጎች ማስፈታታቸው አልገባንም ያሉ ወገኖች እንዳሉ በሶሻል ሚዲያ ከሚሰጡ አስተያየቶች ተረድቻለሁ። ይሁንና እነኚህ ወገኖች አንዳርጋቸው በዶክተር አቢይ እጅ አለመሆኑን ያስተዋሉ አልመሰለኝም፡፤ አንዳርጋቸው አሁንም በህወሃት እጅ ነው። ሊፈታ የሚችለውም ዶር አቢይ የህወሃትን እጅ መጠምዝ ከቻሉ ብቻ ነው። ይፈታ የሚለው ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን የቆየበት ምክንያት ከላይ ጠቆም ያደረኩት ከመጋርጃው ጀርባ ያለው ፍልሚያ አካል መሆኑን ልብ ይሏል።

በሌላ በኩል ከመጋረጃው ፊትለፊት የምናያቸው የዶክተር አቢይ እንቅስቃሴዎች በሲመተ-በዓላቸው ላይ ቃል ስለ ገቧቸው የመሰረታዊ ለውጥ ቅድመ ዝግጅቶች ገቢራዊነት ፍንጭ የሚሰጡ ያለመሆናቸውና በፖሊሲና በመዋቅር ረገድ ሊተገብሩ ስላሰቧቸው ነገሮች ያለመናገራቸው ብዝዎችን እያሳሰበ እንደሚገኝም እውነት ነው።

ዶ/ር አቢይ ሚንስትሮቻቸውን ሰብስበው የስራ አመራር ስልጠና በሰጡበት አጋጣሚ ሽርሽርና ንግግር አበዙ በሚል ከህዝብ የተሰነዘሩ አስተያየቶችን ተመርኩዘው በሰጡት ምላሽ “ ቃል ወደ ተግባር የሚወስድ ድልድይ ነው። መጀመሪያ ሃሳብክን ትናገራለህ፡፤ የተናገርከውን ደግሞ ትተገብራለህ። ቃል! ዳኛ ነው። የተናገርከውን ካልተገበርክ የምትዳኘው በቃልህ ነው። ይህን ብለህ ለምን አልተገበርክም ተብለህ የምትዳኘውም በቃልህ ነው”(ሃሳቡን እንጂ ቃል በቃል አይደለም) ብለዋል። ይህ ለኔ ዶክተሩ የተናገሩትን እንደሚተገብሩ በድጋሚ ቃል የገቡበት አጋጣሚ ነው፡፤ ከዚህ ተነስቼ ላስብ የምችለው ዶክተሩ ቃላቸውን ለመፈጸም ፍላጎት እንዳላቸው ነው። ይሁንና ፍላጎት ብቻ በቂ አይደለም። አቅም ያስፈልጋል። እናም አቅም አላቸው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የግድ ከመጋረጃው ጀርባ ስላለው እንቅስቃሴ ማወቅና መረጃ ማግኘትን ግድ ይላል።

ከመጋረጃው ጀርባ የተዶለተውን እየተገበሩ ይሆን?

ከመጋረጃው ጀርባ ስላለው ፍልሚያ በቂ መረጃ ባለመኖሩ ሳቢያ፤ ዶክተሩ ከፊት ለፊት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ቃል ገብተው ካልፈጸሟቸው ተግባራት ጋር በማነጻጸር እንዲገመገሙ ግድ ብሏል። ይህ ደግሞ ጥርጣሬን መሰረት አድርጎ ስጋትን ያረገዘ አመለካከት እንዲኖር ግድ ብሏል። በመሆኑም ዶክተር አቢይ ከመጋረጃው ፊት ለፊት እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ ድርጅታቸው ኢ.ህ.አ.ዴግ እድሜውን ለማራዘም ከመጋርጃው ጀርባ የዶለተው ወደ ጥገናዊ ለውጥ የሚደረግ ጉዞ ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ።

ለዚህም አመለካከታቸው እንደ መገለጫ ከሚጠቅሷቸው መካከል ፦ ያዋቀሩት ካቢኔ ከቀደመው ካቢኔ  የቅርጽም የይዘትም ለውጥ የሌለበት መሆኑ፤ ህወሃት ወሳኝ የሆኑትን የመከላከያና የድህንነት መዋቅሮች እንደያዘ መቆየቱ፤ አስቸኳይ ግዜ አዋጁን ያለማንሳታቸውን፤ተቃዋሚ ድርጅቶችን ለይፋዊ ድርድር አለመጋበዛቸው፤ ባጠቃላይ ወደ መሰረታዊ ለውጥ የሚያንደረድሩ ምንም አይነት ቅድመ ተግባራትን ለማከናወን ሃሳብ እንዳላቸው ፍንጭ ያለማሳየታቸውን ነው።

ከዚህ በመነሳትም ዶር አቢይ ለህዝብ ቁጣና አመጽ ምክንያት ናቸው የተባሉ ጉልህ የስርዓቱ እንከኖችን ብቻ በመቅረፍ  በጥገናዊ ለውጥና አዲስ አመራር በመታገዝ ድርጅታቸውን በስልጣን ለማስቀጠል እየሰሩ ነው ወደሚል ድምዳሜ ይደርሳሉ፡፡

እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ግዜው ገና ነው ሊባል ይቻል ይሆን እንጂ ጥርጣሬው ዕውን ሊሆን የሚችል አይደለም ብሎ መከራከር የሚቻል አይመስለኝም። ነገር ግን እንደ እኔ እይታ ዶ/ር አቢይ ይህን መንገድ ከመረጡ፤ በአሁኑ ወቅት የተጎናጸፉት ህዝባዊ ድጋፍና ክብር እንደ ጠዋት ጤዛ ረግፎ ታሪካቸው በጥቁር መዝገብ እንዲጻፍ ከማድረግ በስተቀር የ27 አመታት ግፍ የወለደውን  የህዝብን የመሰረታዊ ለውጥ ጥያቄ ሊያዳፍኑት እንደማይችሉ ከማንም በላይ እሳቸው የሚረዱት የመስለኛል። “ ስልጣን ላይ ሲወጣ ነገ መውረድ እንዳለ የማያስብ ሰው መጨረሻው አያምርም” በማለት ከቀናት በፊት በሚላንየም አዳራሽ የተናገሩትን ልብ ይሏል።

በመሆኑም የህዝብን ሙሉ ድጋፍና እገዛ ተጠቅመው ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱትን የመሰረታዊ ለውጥ መደላልድሎች በይፋ ይተገብሩ ዘንድ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በተስፋ እየጠበቃቸው እንደሆነ በቅጡ እንደሚረዱትም እምነቴ ነው።

ዶክተር አቢይ ኢህአዴግ ናቸው!

ዶክተር አቢይ ኢህአዴግ ናቸው። የሚሰሩትም ለኢህአዴግ ነው። በመሆኑም ኢሃዴግን በስልጣን ለማቆየት ቢፈልጉ ህዝብን እንደካዱ ሊቆጠር አይችልም። ነገር ግን ቃል በገቡት መሰረት የዲሞክራሲ መደላድሉን በማመቻቸት የህዝብ ወኪል ነኝ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ሁሉ ያለምንም ተጽዕኖና አግላይነት በነጻነት ተንቀሳቅሶና ተወዳድሮ፤ ሕዝብም የወደደውን መርጦ በመረጠው እንዲተዳደር መድረኩን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። ክህደት የሚሆነው እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አፋኝ የምርጫ ድራማ ሰርተው ድርጅታቸውን ያለህዝብ ይሁኔታ በስልጣን ለመቆየት ካሰቡ ብቻ ነው። ራሳቸው በአንድ መድረክ “እኛ ኢሃዴጎች በትግል የተፈተንን ነን! እኔም ድርጅቴ ኢህአዴግ በስልጣን እንዲቆይ እሰራለሁ፤ ከኛ የተሻለ አማራጭ አለኝ የሚል ተፎካካሪ ድርጅት ቀርቦ የህዝብን ይሁኔታ ካገኘ ግን በጸጋ ወንበሩን እንለቃለን “ ሲሉ ተናግረዋል። ህዝብም የሚጠብቀው ይህንኑ ብቻ ነው። ሜዳውን ያመቻቹ ግልቢያው ለሁሉም ክፍት ይሁን…።

በመጨረሻም የጀመሩት የለውጥ ጉዞ ፍጻሜ፦ ህዝቦች ተከባብረው የሚኖሩባት፤ ሰው በዜግነቱ እንጂ በዘሩ የማይታይበት፤ ዲሞክራሲ ፤ፍትህና ሰላም የነገሰባት ኢትዮጵያን እውን የሚያደርግ ፤ የስራ ግዜዎም የተቃና ይሆን ዘንድ መልካም ምኞቴን እየገለጽኩ በህዝብ ትግል የወጡበትን መንበረ ስልጣን በህዝብ ጉልበት አጠናክረው ራስዎን ከታሪክ ተወቃሽነት የለውጥ ጉዞውንም ከመጨናገፍ ይታደጉ ዘንድ ያብቃዎ እላለሁ።

አዜብ ጌታቸው: azebgeta@gmail.com

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *