” የሰውየው አካሄድ ይገርማል” ይላል። ነዋሪነቱ አሜሪካ የሆነው ወጣት ” ሰውየው” ሲል የሚጠራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ መሪነት ማማ ከመጡ በሁዋላ ለሕዝብ የሚሰጡት ክብር ኢህአዴግን ቢጠላም እሳቸውን ለይቶ እንዲወድ አድርጎታል።

abiy-ahmed-pm-e1527298627127-948x474

ኢህአዴግና ዳያስፖራው ፊትለፊት የሚነጋገሩበት ጊዜ ገና እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። በተቃራኒው ደግሞ መቀራረቡ ወደፊት ለሚታሰበው እርቅ በር ከፋች መሆኑንን በመጠቆም ድጋፍ የሚሰጡ አሉ። ገለልተኛ ሆነው ምክር የሚሰነዝሩም አሉ። በድፍን ተቃውሞ አይሆንም በሚል ዘመቻ የከፈቱም አሉ። ልክ እንደ ቅንጅት ዘመን ” ፓርላማ ተገቡና ዋ!!” መፈክር ” ዋ” የሚሉ አሉ። ሁሉም በየፊናው የተሰማውን ቢልም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ህዝቤን” ላናግር በሚል ያቀረቡት ጥያቄ ነገ በአሜሪካኖቹ ሰዓት ፬ ፒኤም ላይ ውሳኔ ያገኛል። ፌዴሬሽኑ ጥያቄውን ይቀበለዋል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ለዛጎል ተናግረዋል።

ዛጎል ያነጋገራቸው በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምንጮች ድብዳቤ መጻፉን አረጋግጠዋል። ድብዳቤው የተጻፈውና ተፈርሞ የወጣው በአምባሳደሩ ነው። ድብዳቤው ጁላይ ስድስት በሚደረገው የኢትዮጵያ ቀን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተገኝተው ንግግር እንዲያደርጉ የሰሜን አሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፈቃድ እንዲሰጥ የሚጠይቅ ነው።

በአገር ውስጥ የተጀመረውን የማቀራረብ ስራ በውጭ አገርም ለማስቀጠል እንዲቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበአሉ ላይ እንዲገኙ የቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ መተራመስ ተፈጥሯል። በየአቅጣጫው መልከ ብዙ ሩጫ ተጀምሯል። የዲሲ ግብረሃይል በሚል የሚታወቀው ክፍል ፌዴሬሽኑ ጥያቄውን ውድቅ እንዲያደርገ በይፋ ዘመቻውን እያጣደፈ ነው። የፌዴሬሽኑንን የቦርድ አስፈጻሚዎች ሞባይል ይፋ በማድረግ በስልክ ጫና የመፍጠር ስራም ተግባራዊ ሆኗል።

“ከአንድ ሳምንት በፊት ESFNA ዝግጅቱን ሊያደርግ ባቀደበት ቦታ አቅራቢያ ካለ ሆቴል ይዣለሁ። መልካም ጊዜ ከመላዉ ሀገር አፍቃሪ ጋር እንደሚኖረኝ በመገመት በጉጉት እየጠበኩ ነዉ። እድለኛ ከሆንኩም ጀግናዉን እስክንድር….. ማንያዉቃል መሪዬን አንዳርጋቸዉንም እመለከት ይሆናል ……ቴዲም አይጠፋም፤ ይሁን እና ESFNA እርሶን ይምጡ ብሎ ቢወሰን ግን እኔ እቅዴን እሰርዛለሁ። በእርሶ ላይ ቂም የለኝም ….ይልቁንም አክብሮት!!…ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ወዳጅ የሚያሰኘን  በቂ ትስስር የለንም ” ሲሉ ዶክተር መኮንን ሃብተጊዮርጊስ የተባሉ ሰው አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

“በህዝብ ባይመረጡም የአንድ አገር መሪ በእንዲህ መሰሉ ዝግጅት ላይ ወገኖቼ ፌት ቆሜ ንግግር ላድርግ ብሎ ሲጠይቅ አለመቀበል ወንጀል ነው። በኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያ በአል ላይ አትገኙም ማለት ኢትዮጵያዊ አይደሉም በሚል ዜግነትን የመንሳት ያህል ነው። ምንም ይሁን ምን  ፌዴሬሽኑ ጥያቄውን የማይቀበል ከሆነ የተቋቋመበትን ዓላማ መዘንጋት ይሆንበታል። በግሌ ፌዴሬሽኑ ይህንን ጥያቄ የማይቀበል ከሆነ ከነቤተሰቤ በዝግጅቱ ላይ አልገኝም። አግራችን አሁን የሚያስፈልጋት መቀራረብ እንጂ ወደሁዋላ ተመልሶ ቂም እየቆጠሩ መናቆር አይደልማና ” ስትል የሲያትል ነዋሪ ለዛጎል ተናግራለች።

Image may contain: 1 person, sitting and text

ጎልጉል የተሰኘው የድረ ገጽ ጋዜጣ “የጠቅላዩን ጉዞ በአዎንታዊ መልኩ የሚመለከቱ ወገኖች ጉብኝቱን እንደ አንድ መልካም ዕድል  ለበጎ ውጤት እንጠቀምበት በማለት ይመክራሉ። ጠቅላይ ሚ/ር ዓቢይ አህመድ የዳያስፖራውን ኃይል በሚገባ የተገነዘቡና ይህንንም በአደባባይ የተናገሩ መሆናቸውን የሚጠቅሱ ክፍሎች፣ ዳያስፖራው ካለው ሙሉ የመናገር መብት አኳያ አገር ቤት ያለው ኢትዮጵያዊ በድፍረት ሊናገር የማይችለውን በማንሳት ለወገኑ ያለውን ተቆርቋሪነት ማሳየት ይገባል ይላሉ። ከዚህ በፊት የህወሓት ኃላፊዎች በድብቅ መጥተው በድብቅ መሄዳቸው አግባብነት የለውም በሚል ትልቅ ተቃውሞ ይደርስባቸው እንደነበር የሚያስታውሱ ወገኖች በገሃድ እንወያይ የሚል መሪ ሲመጣ በጭፍን ከመቃወም ይልቅ “እኛም የምንፈልገው ይህንን ነበር” በሚል በሰከነ መንፈስ የጉብኝቱ አካል መሆን ይገባቸዋል በማለት ሃሳብ ይሰጣሉ” ሲል የበኩሉን አስተያየት ሰንዝሯል።

በ “ሰላማዊ ሽግግር ” ስያሜ ጥገናዊ ለውጥ እያደረገ ያለው ኢህአዴግ በመሪዎቹ ታሪክ እንዲህ ባለ መድረክ  ህዝብ መሃል ለመገኘት ጥያቄ ሲያቀርብ ይህ የመጀመሪያው ነው። ቀደም ባሉት ዓመታት የስፖርት ፌዴሬሽኑንን ለማፍረስ ከፈተኛ በጀት በመመደብ ሲተጉ የነበሩትን መሪዎች ለሚያስቡ፣ የነበረውን ተራና ከአንድ አገር እመራለሁ ከሚል ድርጅት የማይጠበቅ ተግባር ለሚያውቁ፣ እነ አብነትና ወዳጆቻቸው ለዚህ ተግባር ተላላኪ ሆነው የገቡበትን ተራና እውቀት አልባ አምባ ጓሮ በውል ለተከታተሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አካሄድ አስገርሟቸዋል።

ሰላሙ አያሌው ” የሰውየው አካሄድ ይገርማል” ይላል። ነዋሪነቱ አሜሪካ የሆነው ወጣት ” ሰውየው” ሲል የሚጠራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ መሪነት ማማ ከመጡ በሁዋላ ለሕዝብ የሚሰጡት ክብር ኢህአዴግን ቢጠላም እሳቸውን ለይቶ እንዲወድ አድርጎታል። እናም በኢትዮጵያ ቀን ቢገኙ ደስተኛ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ጥያቄ ግን አለው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አድርገው ብቻ መሄድ የለባቸውም። ይህ ከሆነ የፖለቲካ ትርፍ ከማግኘት የዘለለ ትርጉም አይኖረውም። 

እንደ ሰላሙ አባባል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ጋር ስርዓት በተሞላበት መንገድ የሚነጋገሩበት የውይይት መድረክ አሰቅድሞ ቢደረግ እጅግ ውብ ይሆናል። ከበአሉ አስቀድሞ ግልጽ የጥያቄና መልስ ውይይት ቢደረግና በኢትዮጵያ ቀን ላይ ቢገኙ የሚፈጥረው ስሜት እጅግ ያማረ ይሆናል። 

በሌላ በኩል ለስር ነቀል ለውጥ ዝግጁ መሆኑንን ያላሳየው ኢህአዴግ የኤች አር ፩፪፰ ህግን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች የገባበትን አጣብቂኝ ለመወጣት ይጠቀምበታል የሚሉ ወገኖች ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዝግጅቱ ላይ እንዲገኙ መፈቀድ የለበትም” ባይ ናቸው። ፌዴሬሽኑ በምን መልኩ ጥያቄውን ውድቅ እንደሚያደርገው ግን አልጠቆሙም።

ከእነዚህ ወገኖች መካከል ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እንዲጋበዙ የሚጥይቁ አሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ በዝግጅቱ ላይ መገኘት ፖለቲካዊ ሽንፈት አድርገው የሚወስዱት ክፍሎች የብርሃኑ ነጋ መገኘት ጉዳዩን ያመጣጥነዋል ባይ ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ ከሁሉም ይልቅ ጃዋር መሃመድ ቢገኝ የተሻለ ነው ሲሉ ከእነ ዶክተር ብርሃኑ የላቀና የሚታይ ስራ መስራቱን ይጠቁማሉ። የእስክንድር ነጋ መገኘት ሁሉንም ለማመጣጠን በቂ ስለሆነ ሁሉም ወገኖች ጎን ለጎን ተቀምጠው መታየታቸው ለጊዜው በቂ ይሆናል በሚል ጉዳዩን ዳር ሆነው የሚያዩም አሉ። 

በተዛማጅ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን አሰባስቦ ለማወያየት በኤምባሲው አማካይነት እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ይሁን እንጂ ቁጥሩ ከመብዛቱ አንጻር አስቸጋሪ ስለሚሆን የተወሰኑ ቁልፍ የሚባሉ ሰዎችን መርጦ ለማነጋገር ቢሞከርም ” እኔ እኔ ካልሄድኩ” በሚል ሊሳካ አልተቻለም ተብሏል።

በሌላ ተመሳሳይ በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን  የእግር ኳስ ውድድር ላይም በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲገኙ ለፌዴሬሽኑ ጥያቄ ቀርቧል። የፌዴሬሽኑ አመራሮች የአሜሪካኑንን ውሳኔ አይተው ምላሽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

በቆይታቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ በተለይ በሰላማዊ መንገድ ትግል ከሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ጋር በግልና በቡድን በመገናኘት ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።
 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *