የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁራን አበክረው እንደሚያስተምሩት ከሁሉም በላይ በዜጎች መካከል በፖሊሲና በሕግ የተደነገገ ልዩነትን የሚፈጥር መዋቅራዊ መድልዎ በኅብረተሰብ ውስጥ ቅሬታን የሚያከርርና ለአመጽ የተመቻቸ ነው። በተለይ ደግሞ የግጭትና አመጽ መሠረታዊ መንስኤ የሀብት ቁጥጥርና ክፍፍል ኢፍትሐዊነት ነው። ማርክሳውያን በግልጽ እንዳስቀመጡት ነባራዊው ኅብረተሰባዊ መዋቅር የባለሀብቶችን ባለቤትነትና ጥቅም ለማስጠበቅ የተቀየሰ ከሆነ፣ በሌላ አነጋገር የማኅበራዊ ተቋማት፣ የፖለቲካና ኤኮኖሚው ሥርዓት ሥልጣን ያላቸው የሌላቸውን እንዲበዘብዙ የተመቻቸ ከሆነ፣ በገዥና ተገዥ፣ በሀብታምና ድኃ፣ ባለውና ባጣው መካከል መደባዊ ርቀት በመፍጠር፣ ተርታው የኅብረተሰብ ክፍል ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ሥነ ልቡናዊ ባይተዋርነት እንዲሰማው ያደርጋል። ሰፊ ማኅበራዊ ልዩነት በፊናው ድህነትን፣ ድንቁርናን፣ እርዛትን፣ ችጋርን፣ በሽታን፣ ወንጀልንና ብሎም አመጽን ማፈንዳቱ አይቀሬ ይሆናል።
ሁለተኛ ዕድገት ወይም ልማት በራሱ ተፈላጊ ነገር ቢሆንም፣ በአግባቡ ካልተያዘ የግጭት መንስኤ ይሆናል። በተለይም ልማቱ ፍትሐዊ ካልሆነ፣ ከፍተኛ ማኅበራዊ መድልዎ ወይም አንጻራዊ በደል ካስከተለ፣ ዜጎች የበይ ተመልካች መሆናቸው የሚሰማቸው፣ በገዛ አገራቸው የመሻሻል ሕልማቸውና ምኞታቸው የተጨናገፈና የመከነ፣ በዜግነታቸው በሚጠብቁትና በገሃድ በሚያገኙት መካከል ሊታገሱት የማይችል ክፍተት ካለ፣ ቅሬታ ሊፈጥርባቸውና ለአመጽ ሊያነሳሳቸው ይችላል።
ሦስተኛ መንግሥት ብሔራዊ እሴታዊ መግባባትን ሊፈጥር ካልቻለ፣ ራሱን ከአመጽ አዙሪት ሊያወጣና ዋነኛ ተግባራቱን ማከናወን ካቃተው፣ በዚህ ላይ ከአቅሙ በላይ የሆኑ አደጋዎች፣ ቀውሶችና ሴራዎች ውስጥ የተዘፈቀ ስለመሆኑ አጠቃላይ እምነት ካለ፣ ለቡድናዊ አመጽ የተመቻቸ ይሆናል።
አራተኛ በሕዝቦች መካከል የሚራገቡ እትብታዊና ደመነፍሳዊ ስሜቶች በማኅበረሰቦች መካከል አላስፈላጊ ፉክክሮችንና ከማን አንሼነትን በማጋጋልና መድልዎን በማባባስ የግጭቶችን አደገኝነት ይጨምራሉ። በሥልጣንና በሀብት የተፈጠሩ ልዩነቶችን ለማካካስና ብልጫ ለማግኘት የሚደረጉ መቀናቀኖችና ግጭቶች፣ በአንድ አገር ውስጥ ባሉ የተለያዩ ቡድኖች አጠቃላይ መስተጋብሮችና በማኅበራዊ ለውጥ ሒደቶች ውስጥ የሚንጸባረቁ የማያባሩ ጉዳዮች ይሆናሉ።
አምስተኛ ሠላማዊ ሙግት ለዘብተኛ የግጭት ዘይቤ ሲሆን፣ ቡድኖች በሠለጠነ መንገድ የሚፎካከሩበት፣ አንዱ የሌላውን ሐሳብ ለማስቀየር ወይም የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያገለግል፣ አመጽን የሚያመክን መላ ነው። ቅሬታን ለማስተንፈስ ወይም ለማስወገድ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ አማራጮች በተዘጉበት፣ ፖለቲካው በዜሮ ድምር ስሌት በሚካሄድበትና ተቃዋሚና ጠላት በተግባርም በቃልም ድንበራቸው በሚደበዝዝበት ሁኔታ፣ የአመጽ ቡድኖች ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም፣ ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ፣ ጥቅማቸውን ለማስከበርና አቅማቸውን ለማደርጀት የሚጠቀሙበት ብቸኛ ብልሐት ይሆናል።
ስለዚህም ኅብረተሰብ በዘፈቀደ በጥቂት ‹ጸረ-ሰላም ኃይሎች› ሰበካ የሚነዳ ሳይሆን፣ የራሱን ግላዊም ሆነ ቡድናዊ ጥቅም የሚያሰላ፣ ትእምርታዊና ባሕላዊ ወይም ሥነ-ልቡናዊ እሴቶቹን ለማስከበር የሚቆም አስተዋይ ኀይል ነው። ዜጎች በመንግሥት ላይ እምነት ሲያጡ ወይም አደጋ፣ ተግዳሮትና ውርደት የደረሰባቸው መሆኑን ካመኑ ያምጻሉ። ዓላማቸው መብታቸውን ለማስከበር፣ ክብራቸውን ለማደስ ወይም ራሳቸውን ለመከላከል ነው።
ሕወሓት/ኢሕአዴግና ተፈጥሮአዊ የአመጻ ባሕርያቱ
ግጭት ሕወሓት/ኢሕአዴግ የፈጠረው ጉዳይ አይደለም። አገዛዙ ራሱ በአመጽ ደርግን ገርስሶ ሥልጣን በተቆናጠጠበት ወቅት፣ የተረከበው ለሠላሳ ዓመታት ገደማ የክፍፍልና የጥላቻ መንፈስ የተዘራበት፣ ደም እንዲቃባና በጎሪጥ እንዲተያይ የተገደደ ሕዝብ ነበር። በእውነቱ በተለያዩ ውስጣዊና ዓለማቀፋዊ ክስተቶች ግጥምጥም ታሪክ የሥልጣን ሸክሞችን ያቃለለችለት፣ ሕዝብም እንደ ሙሴ ሊከተለው ተስፋ የጣለበት እንደ ኢሕአዴግ ያለ አገዛዝ በአገሪቱ ታይቶ የሚያውቅ አይመስለኝም። ትልቁ ምፀት ይህንን ሐቅ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ለመገንዘብ አለመቻሉና፣ ሠላም በተራበው አቅመቢስ ሕዝብ ላይ ራሱን በግጭት አራጋቢነትና ዳኝነት በመደልደል፣ ከእያንዳንዱ ማኅበራዊ ስንጥቅ ለማትረፍና ሥልጣኑን ለማስጠበቅ መሰለፉ ነው። በአጭሩ ክፍፍልን፣ ግጭትንና አመጽን የሕልውናው መሠረት ማድረጉ ማለት ነው።
ሕወሓት ያልጠበቀው አገራዊ ኃላፊነት ሲወድቅበት በከፍተኛ የኀይል መዛባት ላይ የተመሠረተ ያንድ ወገን የንዑሳን መንግሥት አቆመ። ለአገራዊ አደራው የሚመጥን ማኅበራዊ መሠረትም፣ ችሎታም ፍላጎትም ስላልነበረው፣ ሳይውል ሳያድር ያዋጣኛል ባለው በተንኮልና በሴራ ዘይቤ ተሰማራ። በአሸናፊ ማናለብኝነት ዋና ዋና ተፎካካሪ ብሔረሰቦችን፣ አገራዊ ራዕይ ያላቸውን ነባርና አዲስ ቡድኖችን በመከፋፈል፣ በማገድና በመምታት ከጨዋታ ውጭ አደረጋቸው። በጥቂት የጎሳ ምልምሎችና የሥልጣን ተስፈኞች ታጅቦ የከፋፍለህ ግዛው ዓላማውን የሚያስፈፅምበትን ሕገ መንግሥት በብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዘይቤ መጫኑ የሠላም ምልክት አልነበረም። ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊቱን አላጠቆረበትም።
ነገር ግን ኢሕአዴግ እያደር የአገሪቱን ብሔራዊ ጦር በጠላትነት ፈርጆ በመበተን፣ ነባር መንግሥታዊ መዋቅራትን በተጓዳኝ የፓርቲና ሕዝባዊ ማኅበራትን በማዳከም ሙሉ በሙሉ በአንድ የዘውግ ቡድን ሥር መቆጣጠሩ። የጦር ኀይሎችንና የደኅንነትን፣ የቁልፍ ሚኒስቴር ቦታዎችን፣ በትልልቅ ከተሞች ውስጥ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራንን፣ ከአገር ዐቀፍ እስከ ጎጥ ያሉ የቤተ እምነት ኀላፊዎችን እና ከዞን እስከ ቀበሌ ያሉ የአስተዳደርና ፖለቲካ እርከኖችን ያለ አንዳች ሐፍረት በአንድ ብሔረሰብ አባላት እጅ ሲጠቀልል፣ ለይስሙላ ጣል ጣል የተደረጉ ሹማምንትን በታማኝ የሕ.ወ.ሓ.ት. ታኮዎች እያሾረ ሲቀልድና፣ በግልጽ አገሪቱን ጡንቻው ፈጥርቆ ለመግዛት ሲደላደልም አንድ ቀን ልብ ይገዛ ይሆናል የሚሉ የዋኾች አልጠፉም።
ሆኖም በይስሙላ ፌዴራላዊነት በቀጥታ የተማከለ የፋይናንስና የፖለቲካ ቁጥርር በማድረግ፣ ብዙኃኑን የአገሪቱ ብሔረሰቦች መብቶች በመግፈፍና በምልምሎች በማስረገጥ ለንዑሳን ምርጦች ልዕልና የቆመ በመሆኑ፣ ዛሬ ኢሕአዴግ የብሔረሰቦች መብት ጠበቃ ነኝ ቢል ማንም አያምነውም። እሱም ጉዳዩን በዘፈንና በማስታወቂያ ሰሌዳ ሙግት ገድቦ፣ ልማታዊ መንግሥት ነኝ ወደሚል ዜማ ዞሯል። ብዝኃነት የምትለው ዘይቤ ሁልጊዜም በግጭትና በተቃርኖ በከፋፍለህ ግዛው ስልት ለመዝለቅ የመጣጣሩ መሪ ቃል ናት። ማኅበራዊ ጥርጣሬንና ሽኩቻን ለማራገብ፣ መቻቻልና አብሮነት ለማደፍረስ በተደጋጋሚ ግልጽና ስውር ደባዎች መፈፀሙ፣ በየተጎራባች ብሔረሰቦች መካከል መቃቃርና ጥላቻ ሲካረር፣ ዜጎች በማንነታቸው የተነሳ በገዛ አገራቸው ሲበደሉ፣ ሲጋዙ፣ ሲባረሩ፣ ሲገደሉ፣ ንብረታቸው ሲቀማና ሲወድም በቸልታ ማየቱ፣ በተደጋጋሚ በሕዝብ ደም የታጠቡ ታማኝ ወንጀለኞችን ከመቅጣት ይልቅ ለዕድገት ማጨቱ የስርዓቱን ማንነት ይመሰክራል።
የተለየ ሐሳብ ያላቸውን ዜጎች በጥርጣሬ ከማየት ባለፈ ጠባቦች፣ ትምክህተኞች፣ ፀረ-ሠላምና ፀረ-ልማት ኀይሎች፣ የሻዕብያ ተላላኪዎች፣ ሽብርተኞች እያለ በጠላትነት በመፈረጅ በሥራና በሕይወት፣ በግልጋሎትና በግብር ግልጽ አድልዎ በማድረግ አዋክቧል። በአጠቃላይ የማኅበራዊ ታጋዮችን፣ የመብት ተሟጋቾችን፣ የተቃዋሚ ኀይሎችን፣ የነጻው ጋዜጠኛ አባላትን በ“ሽብርተኝነት” በመፈረጅና በማንገላታት ግንባር ቀደም መሆኑ፣ እያንዳንዷን ማኅበራዊ ሕይወትና ተቋም ለመቆጣጠር ካልሆነለት ደግሞ ለማዳከምና ለማጥፋት ቀን ተሌት መትጋቱ፣ ፍትሕን የጉልበተኞች ደንገጡር ማድረጉ የስርዓቱ ዓመጻዊ የአስተዳደር ዘይቤ ማሳያ ነው።
የግንባሩ ዋነኛ ችግሩም አቅመ ደካማነት ሲሆን፣ ይህም በአፈፃፀም፣ በቅቡልነት፣ በማኅበራዊ መሠረት ወዘተ. ይገለጻል። ከሁሉም በላይ የንዑሳን መንግሥት በመሆኑ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት አለበት። ይህን የድካምና የማቅለሽለሽ ስሜት ለመሸፈን ያለው አማራጭ ጠንካራና አይበገሬ መስሎ መታየት ነው። ‹ፈሪ ቀድሞ አስፈራሪ› እንዲሉ፤ ኢሕአዴግ የጀግንነቱን ልክ በራሱ ለክቶታል፡፡ ስለዚህም ራሱን ‹የሕዳሴው ትውልድ› እያለ አለቅጥ በማቆላመጥና የአንድ ብሔረሰብ ጀግንነትን፣ የአንድ ግለሰብ ምልኪን በማራገብ አባዜ ተጠምዷል። ከዚህ በላቀ ግን የሥልጣኑ ምንጭ ከሕጋዊነት ይልቅ የደምና ጀግንነት ገድል በማድረግ ለሌሎች ከሁሉ የሚያዋጣው መንገድ ይህ መሆኑን ተምሳሌት በማኖሩ ኢሕአዴግ የሠላሙን አጀንዳ ዘግቶታል።
ስለዚህም በአስገራሚ ማናለብኝነት፣ ግትርነትና አምባገነንነት ከሕዝብ በመካረር፣ በማስፈራራትና በብረት አለንጋ በመግረፍ ሩብ ምዕት ዓመት ዘልቋል። መሠረታዊ ለውጦችን ለማስተናገድ አሻፈረኝ ማለቱ፣ የዜጎችን ሐሳብ መናቁ፣ ደማቸውን ደመ-ከልብ አድርጎ ማስቀረቱ፣ በአፈናና በአውጫጪኝ መተማመኑ፣ ኀይልን የመጀመሪያም መጨረሻም አማራጭ አድርጎ በመውሰዱ ነው። በኃይል የወጣ በኃይል ይወርዳል የሚል ይመስላል። ከስርዓቱ ተፈጥሮ የመጣና ‹ለሕዝብ ስንዝር ስትሰጠው ክንድ ይመኛል› በሚለው ሸውራራ ብሒል ላይ የተመሠረተ መሆኑም አያጠራጥርም።
ኢሕአዴግ ፓርላማውን በአሳፋሪ ሁኔታ መቶ ፐርሰንት ጠቅልሎ (ጆሴፍ ስታሊን እንኳን በ1934 እ.ኤ.አ በ17ኛው የፓርቲው ጉባኤ ላይ ያገኘው ድምጽ 99 በመቶ ነበር) በሌላ በኩል የሕፃናት ፓርላማ እያለ ብላቴናዎችን መስበኩ፣ ሥነ ዜጋ እያስተማረ መብቱን የጠየቀውን ወጣት በጥይት መቁላቱ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ምን ያህል ከጥበት ወደቧልታዊነት የመውረዱ መለኪያ ነው። አገሪቱ ሠላማዊ ሰልፍ እንኳን የማይፈቀድባት ብቸኛዋ የአፍሪካ አገር ሆናለች። ወኅኒ ቤቶች በፖለቲካ እስረኞች ተጣብበዋል፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ ከዓለም ጭራ አድርጎናል። በአጠቃላይ ብሔራዊ መግባባት የሚባለውን ሐሳብ በመጥላት ሕዝብን ደፍጥጬ ሐሳቤን አስፈፅማለሁ፣ በኔ ርዕዮ ተዓለም የታረቀ አዲስና ታዛዥ ትውልድ እፈጥራለሁ ብሎ መታከቱ የሚሳካ አይሆንም።
ሠላም ዝም ብሎ አይመጣም፤ ከፍተኛ አስተዋይነት፣ ታጋሽነት/ሆደሰፊነት፣ አርቆ ተመልካችነትና ቅንነት ይጠይቃል። በአገሪቱ ሠላምና ፍትሕን ለማምጣት ያለው የመጀመሪያ አማራጭ የራሱን ጎደሎ አስተዳደር መጠገን ቢሆንም፣ ለዚህ የሁሉንም ወገኖች የጋራ ተሳትፎ ለሚጠይቅ ግዳጅ ኢሕአዴግ ቀና አይደለም። የሚጠበቅበትን ቢያንስ ሦስት ዋና ዋና ግዳጆች ማለትም አመጽን ከምንጩ ለመከላከል የተሻለ ዕኩልነት ለማስፈንና፣ የላቀ ማኅበራዊና ባህላዊ መደጋገፍና መግባባት ለማበልፀግ በአግባቡ አልጣረም።
በአጭሩ ኢሕአዴግ ስህተትን በተሻለ ስህተት እያረመ ለመሄድ የሚሞክር መሆኑን የአገዛዝ ታሪኩ ያሳያናል። የተደቀኑበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከምር ገምግሞ የሰው ልጅን ተፈጥሮአዊ ባሕሪ በሠላማዊ እርምጃዎች በማሻሻል አመጽን ለመከላከልና ለማስቆም ይቻላል የሚል እምነት የለውም። በዚህ ፋንታ የያዘው ፈሊጥ የመቋቋሚያ ደኅንነትን ማጎልበትና እንዳስፈላጊነቱ ኀይልን ከጥቅም ቀይጦ በመጠቀም ንትርኮችን ለመፍታት መሞከር፣ አመጽ የሚከሰትበት ዕድል ለመቀነስና ከተነሳም ለማጥፋት ይበልጥ አስተማማኝ ነው የሚል ይመስላል። ዞሮ፣ ዞሮ ዓላማው ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሥርዓት መገንባት ሳይሆን፣ የድለላ እና የቁጥጥር አገዛዝ ለመመሥረት ነው። ይህ ነው ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ አገርና ሕዝብን ሲያደማ የቆየው አካሄድ፡፡