አቶ በቀለ ገርባ ሆነ ተብሎ በተሰራ የትርጉም ስህተት ዘመቻ ተካሄደብኝ ሲሉ ማስተባበያ መስጠታቸው ፣ የፈለጉትን ዓላማ የማራመድ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ይቅርታ እንዲጠየቁ እንጋብዛቸዋለን። በፈሰሰ ደም ልክ አለመጠቀምን አጀንዳ አድርገው መናገራቸው በራሱ አሳንሷቸዋልና ተመልሰው ሙሉ ሰው እንዲሆኑ እንማጸናቸዋለን። 

አቶ በቀለ አስተዋይና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰው ናቸው ወይም ነበሩ። የአሜሪካን ምድር ከረገጡ በሁዋላ፣ በተለይም ሚኖስታ ወለው ካደሩ በሁዋላ አንዳርጋቸው ጽጌን በስም ባይጠቅሱም ለንፅፅር መጠቀማቸው አስደንጋጭ ሆኗል። ፖለቲካውን ወደዚያ እንተወውና ቢያንስ የአንዳርጋቸው ጽጌ ልጆች ” ዳድ አንተ የለህም” ብለው ያሰራጩትን የቪዲዮ መልዕክት አላዩትም። የልጆቻቸውን ጣር አላስተዋሉም 

አቶ በቀለ በእስር ላይ ላሉት መቆርቆራቸው የሚደገፍ ሆኖ ሳለ፣ “ባፈሰነው ደምና በከፈልነው መስዋዕት መጠን አልተጠቀምንም” በሚል የደም ካሳ አይነት ጥያቄ መጠየቃቸው እጅግ የከፋ ጥፋት ነውና አሁንም ደግመን ደጋግመን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ እንመክራለን። ካልሆነም አቋማቸውን ግልጽ ያድርጉና እንዳሻቸው ይናገሩ። እኛም እንተዋቸዋለን፣ እሳቸውም ቅርቃራቸው ውስጥ ይገባሉ። አለቀ።

በሚቀጥለው ምርጫ ኢትዮጵያ ብሎ የተነሳውን ኦህዴድን በምርጫ የማሸኘነፉና ስልጠና የመያዙ ጉዳይ አሳሳቢ ከሆነብዎ አሁን የጀመሩት መንገድ ሃሳብዎን ይበልጥ ያጣምመዋል እንጂ አያቀናውም። እንዲያውም በክብር ባነገሰዎት አዳማ ለቀበሌም ላይመረጡ ይችላሉ። ተገፍተውም ይሁን ሳያስቡት ለሰሩት ስህተት ይቅርታ ጠይቀው አንድ የኦሮሞ ልጅ ብሄራዊ ጀግናችን ይሁኑ። ምርጫው የራስዎና የራስዎ ነው።

ዛሬ ጊዜው ተቀይሯል። በዘፈቀደ ለፍልፎ ማደር አይቻልም። ሁሉም የሚዲያ ባለቤት ነው። ቀደም ሲል እነ መለስ ሲሞላፈጡ የኖሩበት ዘመን ላይመለስ አክትሟል። ዓለም በመረጃ መረብ አንድ ሆናለች። እርስዎ የተናገሩትን ተከትሎ የተሰጠው አስተያየትና ቁጣ የዚሁ ውጤት ነው። ኦነግ ሮጦ ሮጦ የዛለበትን የሞተ አካሄድ አዝለው ከሚንከላወሱ ጽንፈኞች ዘንድ ክብረት የለም። አሁንም እባክዎን ብሄራዊ ጀግናችን ሁኑ። ከእነ አቶ ለማ ልምድ ይውሰዱ። ያለዎትን ኩታ ገጠም ዝናና ክብር ዳግም ይልበሱት። እንዳማረብዎ እንይዎት። የበርካቶች የፍቅር ልባቸው አሁንም ክፍት ነውና አቶ በቀለ ወደ ማማዎት ይውጡ። ዛሬም ክብራችን ከእርስዎ ጋር ነው። ለታላቅ ይቅርታ ይመጥናሉና። ያለን ክብር ስህተቶትን ለመደምሰስ አቅሙ እጅግ ከፍ ያለ ነው።

ጎልጉል የጻፈውን ተመሳሳይ ሃሳብ እንደሚከተለው አትመነዋል።

Tank Man 1989

የዛሬ 29 ዓመት በቻይና የታይናንመን አደባባይ የሆነውን ታሪክ ስናስብ “ታንክ ማን” ወይም በግልቡ የአማርኛ ትርጉም “ታንክ ሰው”ን እናስባለን። እናያለን። የወቅቱን ገድሉን እናስባለን። ወደ አገራችን ስንመለስ ምንም እንኳን ምንም ያልተባለላቸው ጀግኖች ያለመታወሳቸው ሊያሳዝነን ሲገባ፣ አሉ የሚባሉት ላይ መማማል መመረጡ በቃላት ሊገለጽ የማይችል የሃዘን አዙሪት ውስጥ ይከተናል።

ከሁሉም በላይ ደም ሰፍረን ትርፍ እንሻለን። ለአገር ክብርና ልዕልና ያለፉትን የማይተኩ ዜጎች የግብር ማወራረጃ ለማድረግ ይዳዳናል። ህወሓት “በሞተብኝ መጠን ልዝረፍ” በሚል ቀረርቶ ል27 ዓመታት ያደነቆረንና ለዚሁ ግልብ ዓላማው የጨፈጨፈን፣ የደገንብን ታንክና አፈሙዝ፣ ያሰረን፣ ያቆሰለን፣ የገረፈን ሳያንስ ዛሬም በተመሳሳይ “የእኛ ደም” በሚል ክፍያ ሲጠየቅ ሰምተናል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ አሳዛኙና አስገራሚው ስህተትን ከመቀበልና ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ ማስተባበያ በመስጠት በአንድ ጀንበር ስህተት በስህተት ሲሞሸር ማየት ነው። በርካቶች ተመሳሳይ ስህተት ቢሰሩም የሰሞኑ የአቶ በቀለ ገርባ አካሄድ ጎልቶ የሚወጣ ነው።

አቶ በቀለ በበርካቶች የሚመሰገኑ፣ የሚወደዱ ናቸው። ትንሽ ትልቅ ሳይባል፣ ክልልና አድራሻ ሳይለይ ሁሉም አልቅሶላቸዋል። ዘምሮላቸዋል። ጮሆላቸዋል። እሳቸውም ከእስር ሲወጡ ይህንኑ የሕዝብ እሪታና መስዋዕትነት በወጉ አክብረው ምስጋና አቅርበዋል።

ዋሽንግቶን ዲሲ ስለኢትዮጵያ ለአሜሪካኖቹ ሲናገሩ ከቆዩ በኋላ ሚኖሶታን ሲረግጡ ቋንቋቸው ተቀየረ። ቀጥሎም አንዱን ከሌላው ስለማወዳደር እንዴት ሊያስቡና እንዴት እዚያ ጉሮኖ ውስጥ ሊገቡ እንደቻሉ ግራ በሚያጋባ ደረጃ “ተጠቃሚነትን” በኦሮሞ ልጆች ደም ሰፍረው መናገራቸው፤ “ፍቱኝ ብዬ አልጠይቃችሁም አብሬያችሁ የሠራሁበትን ጊዜ እንደውለታ ቆጥራችሁ የሞት ፍርዱን ተግባራዊ አድርጉ፤ “ሰው እየሳቀ መሞት እንደሚችል አሳያችኋለሁ” ብሎ የተናገረን ታጋይ ለንፅፅር ማቅረብን ምን አመጣው? እንዴትስ ታሰበ? አሳዛኝ፣ አስደንጋጭ፣ ለማመን የሚያስቸግር! “እነሱ”ና “እኛ” ብሎ ማስላት!! ሰው “ውለታ ቆጥራችሁ ግደሉኝ” ሲል ደም በመስፈር ውለታን መናፈቅ!!

የትርጉም ስህተት እንደተሠራና እንዲስተባበል ቢሞከርም፣ የተባለው የትርጉም ስህተት ተፈጽሞ ቢሆንም፣ የተኬደበት የንፅፅር መንገድ አቶ በቀለን ከተቀመጡበት የክብር ማማ እንዳወረዳቸው አያጠራጥርም። ከምንም በላይ ሊገሩ የሚገባቸውን ከመግራት ይልቅ እሳቸው “የሚገሩ” ሆነው መገኘታቸው አስደምሞናል። ከአንድ የፊደል አባት፣ ከአንድ ፈጣሪውን እንደሚያምን ከሚናገር ሰው፣ ከአንድ ብሩክ ቤተስብ መውጣቱን ከሚናገር ሰው፣ አንድ አገሪቱን አሁን ከገባችበት ቀውስ አሻግራለሁ ከሚል የተፈተነ ታጋይና አታጋይ … የማይጠበቅ ተግባር በመስማታችን ማዘናችንን አጠንክረን ስንገልጽ በቂ ምክንያት አለን።

በርካታ ፖለቲከኛና አክትቪስት ነን የሚሉ ስህተት ውስጥ ገብተው ሲንቦጫረቁ ለይተን አልተናገርንም። በኦሮሚያ የተከፈለውን ዋጋ ብናውቅም በጋምቤላ፣ በአማራ፣ በኦጋዴን፣ በደቡብ፣ በሁሉም አቅጣጫ ደም መፈሰሱን፣ ግፍ መፈጸሙን፣ አሁንም ድረስ እየተፈጸመ መሆኑንን የሚከራከር ባይኖርም ደምን ለክቶና ሰፍሮ በደም የነገደ የምናውቀው ወያኔን ብቻ በመሆኑ አቶ በቀለን በግልጽ ይቅርታ እንዲጠይቁ ማበረታታት ግድ ሆኖብናል፤ “ትሳስቻለሁ” ብሎ ይቅርታ መጠየቅ ቀላልና የሰላማዊ ታጋይ መለያው ነው። ምክንያቱም ለአገራችን የሚያስፈልጉ ሰው ናቸውና! ከፈለጉ! እስኪ ወደ “ታንክ ሰው” ታሪክ እንመለስ!

በተለያዩ ስሞች ይጠራል፤ ታንክ ሰው፣ ያልታወቀው ተቃዋሚ፣ ያልታወቀው ዓማጺ፣ ወዘተ። ስሙን ያገኘው የዛሬ 29 ዓመት ነበር።

በወቅቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ቻይናን እየናጣት ነበር። ተማሪዎቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም ዋንኛዎቹ ግን ከውሱን የፖለቲካ ተሳትፎ፣ ከዋጋ ንረት፣ ከኢኮኖሚ ተሃድሶ፣ ከፖለቲካ ሙስና፣ ከወገንተኝነት፣ ወዘተ ጋር የተጣመረ ነበር። በመሆኑም ዴሞክራሲ፣ ተጠያቂነት፣ የፕሬስና የመናገር ነጻነት፣ ወዘተ በቻይና እንዲሰፍን በተማሪዎቹ ጥያቄዎች ውስጥ የተካተቱ ነበር።

ለበርካታ ወራት በተቃውሞ ጥያቄያቸውን ሲያሰሙ የነበሩት ተማሪዎች የተሰበሰቡት በቤይጅንግ በሚገኘው የታይናንመን አደባባይ ነበር። አደባባዩ በተቃውሞ ሲናጥ ከከረመ በኋላ የቻይና ኮሙኒስታዊ አገዛዝ 200,000 የጦር ሠራዊቱን ወደ ወደዚያው ላከ። በዚያም በጥይት እሩምታ በርካታዎችን ገደለ፤ አቆሰለ። የሞቱትን ቁጥር እስካሁን ለማወቅ ካለመቻሉ የተነሳ የሚሰጠው ግምትም የዚያኑ ያህል በጣም የሰፋ ነው፤ ከ180 – 10,454!

ይህ እጅግ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከተካሄደ በኋላ በነጋታው ጁን ፭ ቀን ተጨማሪ በርካታ ታንኮች ወደ አደባባዩ ይላካሉ። አንድ ነጭ ሸሚዝ የለበሰና በሁለት እጆቹ ፌስታል ላስቲኮች የያዘ ሰው ቀዳሚው ታንክ ፊት ይቆማል። ከፊት ለፊቱ ሲደርስ ታንኩ ይቆማል። በቪዲዮው ላይ በግልጽ እንደሚታየው ታንኩ ወደ ግራና ቀኝ ብሎ ለማለፍ በሁለቱም አቅጣጫ ሲሞክር ሰውየው ይከላከላል። በእጁም ከዚህ ሂዱ በሚመስል ሁኔታ ተቃውሞ ያሳያል። በመቀጠልም ታንኩ ላይ ይወጣል፤ ውስጥ ካሉት ጋር የሚነጋገር በሚመስል ሁኔታ ትንሽ ከቆየ በኋላ ይወርዳል።

በመቀጠል ፊት መሪው ታንክ ለመሄድ ሲያኮበኩብ ሰውየው አሁንም በፊት ለፊት በመቆም ታንኩን ይጋፈጣል። በመጨረሻ ሁለት ሰዎች እየሮጡ ሄደው ከመንገድ ካወጡት በኋላ ታንኮቹ ጉዟቸውን ቀጠሉ። ከዚያ ወዲህ የዚህ ታንክ ያስደገደገ፤ ለብቻው ብረት ለበስ የተገዳደረ ሰው መጨረሻ አልታወቀም። አንዳንዶች በቻይና አገዛዝ ተገድሏል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ አምልጦ ወደ ታይዋን ሄዷል ሲሉ ይህንን የማይቀበሉ ደግሞ እስካሁን የት እንዳለ አለመታወቁ እዚያው ቻይና ውስጥ ድምጹን አጥፍቶ እየኖረ በመሆኑ ነው ይላሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየታየ ለሚገኘው ለውጥ እጅግ በርካታ ታንክ ያንበረከኩ ወገኖቻችን ተሰውተዋል። ክቡርና መልሶ የማይገኝ ህይወታቸውን ሰውተዋል። ዘር፣ ቋንቋ፣ ቀለም፣ አካባቢ፣ የትውልድ ሐረግ፣ ወዘተ ሳይለይ የህወሓትን አግአዚ ፊትለፊት በመጋፈጥ ደማቸውን አፍስሰዋል፤ አጥንታቸውን ከስክሰዋል።

ሰልፍ የማይወጣላቸውና ያልተወጣላቸው፤ መዝሙር ያልተዘመረላቸውና የማይዘመርላቸው፤ በመስዋዕትነታቸው ምንም ያልተጠቀሙና ወደፊትም የማይጠቀሙ፤ ከነጻነት በስተቀር ለሚያራምዱት የፖለቲካ ርዕዮትም ወይም ወገኔ ለሚሉት ዘር ያልኖሩ፣ ያልሞቱ፤ ለዚህች ታላቅ አገር ግን የማይመለሰውን ህይወታቸውን የገበሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፤ አሁንም አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። ኢትዮጵያ እስካለች ድረስ ሁልጊዜ መስዋዕትነታቸው ሲታሰብ ይኖራል። እነዚህ የኢትዮጵያ “ታንክ ሰዎች” ናቸው! ከታንክም በላይ!! ደም ሰፍረው ጥቅምን በንፅፅር የማይጠይቁ!!

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ህወሓት፤ የኢትዮጵያና ኤርትራ የጋራ ጠላት!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *