በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ላይ እየቀረቡ ያሉ የሙስና እና ብልሹ አሠራር አቤቱታዎችን አጣርቶ የሚያቀርብ ኮሚቴ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተቋቋመ፡፡

  • የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተወካዮች አሉበት
  • የሀ/ስብከቱ የአስተዳደርና የፋይናንስ ችግሮች፤የቀረቡ አቤቱታዎች ይጣራሉ፤
  • አቤት ባዮችና ግፉዓን ኹሉ ጉዳያቸውን ለኮሚቴው እንዲያቀርቡ ይበረታታሉ፤
  • በአንዳንድ ብፁዓን አባቶች ምልጃ ማምለጥ የለመዱ ሓላፊዎች ዋጋ ይከፍላሉ
  • በርምጃው የተደናገጡ የአጥቢያ ሌቦች ሒደቱን ለማደናቀፍ እየተሯሯጡ ነው፤
  • ለኮሚቴው አባልነት ከተጠሩ በኋላ ራሳቸውን ያገለሉ ሓላፊ ምልክት ናቸው፤
  • “የማጣራቱ አስፈላጊነት ሌቦቹን በአንድነት ለመመንጠር ነው፤”/ፓትርያርኩ/

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ላይ እየቀረቡ ያሉ የሙስና እና ብልሹ አሠራር አቤቱታዎችን አጣርቶ የሚያቀርብ ኮሚቴ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተቋቋመ፡፡

ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት እና ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እንዲሁም ለተለያዩ የመንግሥት አካላት ሲቀርቡ የቆዩ አቤቱታዎችን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱን የአስተዳደርና የፋይናንስ ችግሮች ያካተተ ማጣራት ሲኾን፣ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ እንዲቀርብላቸው፣ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ትላንት ማምሻውን ለኮሚቴው አባላት በሰጡት መመሪያ አዝዘዋል፡፡

“በአቤቱታ የቀረቡትንና የምናውቀውን ነገር በይፋ እንድታጣሩልን ነው የምንፈልገው፤ ኹለት ነገር ነው የምትሠሩት፤ አንደኛው፡- በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደረጃ የተፈጸሙ ዝውውሮች፤ በየመሥሪያ ቤቱ እየሔዱ የሚከሡ ሰዎች ጉዳያቸው ምን እንደኾነ፤ በአስተዳደሩና በፋይናንሱ ረገድ በአጠቃላይ ያለውን ችግር በመልክ በመልክ አድርጋችሁ እንድታቀርቡ፤ ኹለተኛው፣ መፍትሔውን ጭምር በአጭር ጊዜ እንድታቀርቡ ነው፤” ብለዋል ቅዱስነታቸው በመመሪያቸው፡፡

የፓትርያርኩን ልዩ ጸሐፊ ጨምሮ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ልዩ ልዩ መምሪያዎች የተውጣጡ አምስት አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚቴው፣ ከፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሚወከሉ ኹለት አባላት እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡

የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የካህናት አስተዳደር መመሪያ ዋና ሓላፊ መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም በሰብሳቢነትና የፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ መጋቤ ሠናያት አሰፋ ሥዩም በጸሐፊነት የሚመሩት ኮሚቴው፣ የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ አእላፍ ያዝ ዓለም ገሠሠ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የበጀትና ሒሳብ መምሪያ ምክትል ሓላፊ መጋቤ ምሥጢር ጌራ ወርቅ ገብረ ጻድቅ እንዲሁም የመንበረ ፓትርያርክ ውጭ ግንኙነት መምሪያ ጸሐፊ መጋቤ ሀብታት ቃለ ወንጌል ታደሰ በአባልነት እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡

የማጣራት ሒደቱን መንግሥት በቅርበት እንደሚከታተለው የጠቆሙ ምንጮች፣ቀደም ብሎም በአቤቱታ የቀረቡለት ጉዳዮች አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ሲያሳስብ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በርምጃው የተደናገጡ የአጥቢያ አማሳኞች ሒደቱን ለማስተጓጎል፣ የኮሚቴው አባላት በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ከተጠሩበት ከትላንት በስቲያ ጀምረው እየተሯሯጡ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ለኮሚቴው አባልነት ከተመረጡት አንዱ፣ ቀርበው መመሪያውን ካዳመጡ በኋላ በሕመም ሰበብ ራሳቸውን ማግለላቸው ከዚሁ የቀንደኛ አማሳኞች ተጽዕኖ ጋራ ሳይያዝ እንደማይቀር ተገምቷል፡፡ ገለጻውን ካዳመጡ በኋላ ለብቻቸው ወደ ፓትርያርኩ ቀርበው፣“አባታችን፣ ታምሜያለሁ፤ ሕመም ላይ ነኝ እኔ፤ ክፉኛ ታምሜያለሁ፤” ያሉት የመምሪያ ሓላፊው እንደማይቻላቸው በመግለጻቸው በሌላ ተተክተዋል፡፡ “ይኼ አቋም የለሽ፤ በጥቅም ተገናኝቶ ይኾናል ይኼኔ፤”በማለት እንዳዘኑባቸው ተገልጿል፡፡ አለመቻላቸውን መመሪያው ከመሰጠቱ በፊት አስቀድመው ተናግረው እንዲወጡ በኮሚቴው አባላት በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ተጠቁሟል፤“ባይመጣ ነበር የሚሻለው፤መጥቶ የቅዱስነታቸውን ገለጻ ካዳመጠ በኋላ ነገሩ በጥብቅ የተያዘ ጉዳይ መኾኑን ሲረዳ፣‘አልችልም’ ማለቱ፣ የሚባለውን አዳምጠህ ውጣ ተብሎ የተላከ አስመስሎበታል፤” ሲሉ የኮሚቴው አባላት ትዝብታቸውን ተናግረዋል፡፡

ተመሳሳይ የማስተካከያና የለውጥ ርምጃዎችን በማስተጓጎል የተካኑ የአጥቢያ ቀንደኛ ሌቦች፣ የሌብነት ድራቸውን በመጠቀም የማጣራት ሒደቱን ለማሰናከል ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ ከወዲሁ በቂ ምልክት የሰጠ መኾኑ ተሠምሮበታል፡፡ “በቂ ማስረጃዎችና ማሳያዎች አሉ፤ የሚታወቅና ያፈጠጠ ጉዳይ ነው፤ እንደብቅህ ቢሉት ሊደበቅ አይችልም፤ መደለል፣ መደራደር፣ በጥቅም መያዝ አይቻልም፤” ያሉት የጉዳዩ ተከታታዮች፣ መንግሥት ለማጣራቱ ይኹንታ በመስጠት የኮሚቴውን እንቅስቃሴ በቅርበት ክትትል እንደሚያደርግበት ተናግረዋል፡፡ ለአንዳንድ ብፁዓን አባቶች የተዛቡ መረጃዎችን እየሰጡ ጫና በመፍጠርና ሽምግልና በመላክ ማምለጥ የለመዱ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ሓላፊዎች እንዳሉና በአሁኑ ማጣራት ግን ይህ መሠሪነታቸው እንደማይሳካላቸው ተጠቁሟል – “የጳጳሳት ምልጃና ሽምግልና ኹሉ መኖሩን መንግሥት አውቆታል፤ በጥቅም እንደልላለን የሚሉ ኹሉ ዋጋ ይከፍላሉ፤” ተብሏል፡፡

አጣሪ ኮሚቴው፣ ከመጪው ረቡዕ አንሥቶ ሥራውን የሚጀምር ሲኾን፣ በላያችን ተገቢ ያልኾነ ምደባና አላስፈላጊ ዝውውር ተፈጽሞብናል፤ ከደረጃ ዝቅ ተደርገናል፤ መብታችንና ጥቅማችን አልተጠበቀልንም፤ የሚሉ አቤት ባዮችን እያነጋገረ ሪፖርቱን የሚያጠናቅር ይኾናል፡፡ ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ ከስድስት ያላነሱ የዋና ክፍል ሓላፊዎች የጥቅም ትስስር የሚጋለጥበት ሲኾን፣ አላግባብ የተሰናበቱ፣ የታገዱ፣ ከደረጃ ዝቅ የተደረጉ፤ ጉቦ የተጠየቁና ተገደው የሰጡም ጭምር በአካል ቀርበው እንደሚያስረዱ ይጠበቃል – “እርሱን[ሥራ አስኪያጁ] ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ ሒድ ማለት ቀላል ነው፤ ከሥሩ አሉ የተባሉት ሌቦች ኹሉ አብረው ተጣርተው ይቅረብልን፤ ከተመነጠሩም በአንድነት ይመነጠራሉ፤ ኮሚቴውን የማቋቋሙ አስፈላጊነትም ይኸው ነው፤” ብለዋል ፓትርያርኩ በመመሪያቸው፡፡

ምንጭ ሃራ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *