“…ለድንበርህ ዝመት በማለት ጦርነቱን በበላይነት የመራ የኢሕአዴግ መንግሥት ከድሉ በኋላ ወደ ድርድር መግባትና የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቅ መሠረት መደራደር ሲችል፤ ከብዙ የሰው ሕይወት እልቂት በኋላ ሔግ ኔዘርላንድ በሚገኘው ቋሚ የግልግል ሕጋዊ አካል በመሄድ ቦታው ለኤርትራ ይገባል ብሎ ፍ/ቤቱ በኢትዮጵያ በኩል ምንም አይነት የታሪክ ሰነድ ሳይቀርብና ኢትዮጵያ ጥቅሟን የሚያስከብር ልዑክ ሳይወክላት ተሸናፊ ሁና እንድትወጣ ተደርጓል…”

ለክብር ዶ/ር አብይ አህመድ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ
መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ/ም

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣

በቅድሚያ ከጥቂት ወራት በፊት የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንዲያገለግሉ በመመረጥዎ የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰማውን ደስታ ልንገልጥልዎት እንወዳለን።

ሥልጣን ላይ ከወጡበት ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና እያንዳንዱ ዜጋ በኢትዮጵያዊነቱ እንዲኮራ በመወሰድ ላይ ያሉትን ታሪካዊ እርምጃዎች ኮሚቴው በእጅጉ ያደንቃል። የበለጠ ድል ለማስመዝገብ ጥበቡንና ጽናቱን ኃያሉ ፈጣሪ እንዲቸርዎ ምኞታችን ነው። ዛሬም ቢሆን ሕዝብን የሚያፈናቅሉና የዜጎችን በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ሠርቶ መኖርን የሚጋፉ፣ የሕዝብ በሰላም አብሮ መኖርን የሚፃረሩ ተግባራት በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ተቀምጠው ወንጀል ሲሰሩ ያታያሉ። በእነዚህና በሌሎች ለአገራችን እና ለሕዝባችን ሰላም፣ አብሮ መኖርን ጠንቅ የሆኑትን ሁሉ አስተዳደርዎ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት መፍትሔ እንዲፈለግለት እንደሚያደርጉ ከፍተኛ እምነት አለን።

እርሶ ጠንቅቀው እንደሚያውቁት ውዷ አገራችን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ጠብቃ ለዘመናት የኖረች አገር በመሆኗ፣ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ወድቀው ለነበሩ አንዳንድ አገራት የበኩሏን ድርሻ በማበርከት ለአብዛኞቹ ነጻ መውጣት በአደረገችው አስተዋፅዖ ከፍተኛ የታሪክ ሥፍራ ይዛ የቆየች አገር ናት።

በአገራችን የተፈጥሮ አቀማመጥ በተለይም በአባይ ወንዝና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በነበራት የባሕር በር ባለቤትነት ሳቢያ፤ ከኦቶማን ቱርክ፣ ከግብጽ፣ ከድርቡሽና ከጣሊያን ወራሪዎች ጋር በየዘመናቱ በተደጋጋሚ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለባቸው በርካታ ጦርነቶች ተከሂደዋል። ሁሉንም በድል አድራጊነት ተወጥታለች።

በዚህ ረገድ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከመያዙ በፊት፤ አገራችንን ያስተዳድሩ የነበሩት መንግሥታት፤ በአስተዳደር ብልሹነት ይወቀሱና ይጠየቁ እንደሆነ እንጂ፤ የአገራቸውን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በማስከበር የኢትዮጵያን ኅልውና በማስጠበቅ ረገድ ታግለው ያታገሉ መሆናቸውን የታሪክ ገድላቸው ሕያው ምስክር ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ በሺ ዓመታት ለሚቆጠሩ የረዥም የታሪክ ዘመኗ የግዛቷ ስፋት አሁን ካለው እጅግ በጣም ትልቅ እንደነበር በአገራችን የታሪክ ፀሐፊዎች ብቻ ሳይሆን በውጭ አገር ጠበብቶችም ጭምር የመዘገቡለት የታሪክ ሃቅ ነው።

ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የአገራችንን የግዛት አንድነት የተዳፈሩና የኢትዮጵያን ካርታ የቀየሩ እምርጃዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ባልመከረበት ሁኔታ ለሌላ አገር አሳልፎ ተሰቷል። ኢትዮጵያ የባሕር በሯን እና ሰሜናዊ ክፍሏን አስረክባ ዛሬ የባዕድ አገር ወደብ ተጠቃሚ ከሆነች 27 ዓመታት ተቆጥረዋል።

በኢትዮጵያና በሱዳን መንግሥታት መሃከል በድብቅ ለረዥም ዓመታት ይካሄድ የነበረው የድንበር ክለላ ስምምነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዳጋጠመው  የሚያውቁት ጉዳይ እንደሆነ እንገነዘባለን።

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት አደጋ ላይ የጣሉ የድንበር ውይይትና ስምምነቶች ያለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ እውቅናና ተሳትፎ የሚካሄዱ በመሆናቸው፤ እየተከታተለ በትክክለኛ መረጃ ሴራውን ሲቃወምና ለኢትዮጵያ ሕዝብ መረጃ በመስጠት ለበርካታ ዓመታት ሲታገልና አሁንም በመታገል ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር አስመልክቶ የሚካሄደውን ሕገ-ወጥ ውይይትና ስምምነት የፈጠረውና ለወደፊት የሚፈጥረው ችግር ገና እልባት ባላገኘበት በአሁኑ ወቅት “በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” እንዲሉ በቅርቡ በእርስዎ የሚመራው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተሰብስቦ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሠላም ለመፍጠር በሚል የአልጀርሱን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመቀበልና ባድሜና ዛለአንበሳን የመሳሰሉ የድንበር አካባቢዎችን ለኤርትራ ለማስረከብ መወሰኑን የሰማነው እጅግ በከፍተኛ ሃዘን ነው።

ክቡርነትዎ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ኃላፊነት ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ ስለ አገር ደህንነትና ሉዓላዊነት አንድ ሆነን በጋራ ስለመኖር የሚያሰሙት ንግግር፣ ይህም በጫረው ከፍተኛ ተስፋ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በደስታ በተዋጠበት በዚህ ወቅት፤ የአገራችን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የመሰለ ግዙፍ ብሔራዊ አጀንዳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይመክርበትና ይሁንታውን ሳይሰጥበት እናስረክባለን ማለት ከዳር እስከ ዳር ሙሉ ድጋፉን የቸርዎ የኢትዮጵያ ሕዝብ አመኔታ እንዲያጡ የሚያደርግ መሆኑን መገንዘቡ ብልህነት ነው።

የኢትዮጵያ የድንበር ጉዳይ ኮሚቴ እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ባተኮሩ የድንበር ስምምነቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳያውቀውና ሳይመክርበት፣ የአገራችን ጥቅምና የፀጥታ ጉዳይ ሳይገመገም፣ የታሪክና የባለቤትነት ሰነዶች በአግባቡ በመረጃነት ሳይቀርቡ የሚደረጉ በመሆናቸው ስንቃወም እንደቆየነው ሁሉ፤ ዛሬም ገና ከጅምሩ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ባልተመሰረተና በተሳሳተ የቅኝ ግዛት ሰነድ መነሻነት በተወሰነ የአልጀርስ የድንበር ስምምነት ውሳኔ መሠረት ያደረገ የድንበር መሬት የማስረከብ ሂደት በከፍተኛ ደረጃ እንቃወማለን።

እንደሚታወቀው ከ 1998-2000 ዓ/ም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተደረገው አስከፊ ጦርነት፣ በሁለቱም ወገን ቁጥሩ 100 ሺ የማያንስ ወታደሮች ውድ የሆነ ሕይወታቸውን እንዳጡ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። አገርህ ተደፍራለች፣ ለድንበርህ ዝመት በማለት ጦርነቱን በበላይነት የመራ የኢሕአዴግ መንግሥት ከድሉ በኋላ ወደ ድርድር መግባትና የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቅ መሠረት መደራደር ሲችል፤ ከብዙ የሰው ሕይወት እልቂት በኋላ ሔግ ኔዘርላንድ በሚገኘው ቋሚ የግልግል ሕጋዊ አካል በመሄድ ቦታው ለኤርትራ ይገባል ብሎ ፍ/ቤቱ በኢትዮጵያ በኩል ምንም አይነት የታሪክ ሰነድ ሳይቀርብና ኢትዮጵያ ጥቅሟን የሚያስከብር ልዑክ ሳይወክላት ተሸናፊ ሁና እንድትወጣ ተደርጓል።

ስለዚህ፣ የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ዛሬ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርነትዎ የሚያቀርበው ተቃውሞ እንደሚመለከተው ነው፤

1ኛ. ኢትዮጵያ በሔግ የድንበር ኮምሽን የፍርድ ሂደት በበቂ ደረጃ ያልተወከለች በመሆኑና ተደራዳሪዎቹ በቂ እውቀት የሌላቸውና በቂ የሠነድ ማስረጃዎች እያሉ ሆን ተብሎ ባለመያዛቸው፤

2ኛ. ኤርትራን ይጠቅማሉ ተብለው የቀረቡ ሠነዶች በቅኝ ግዛት ዘመን የነበሩ ማስረጃዎች በመሆናቸውና እነዚህ የቅኝ ግዛት ስምምነት የተባሉትም ሰነዶች በተለያዩ ወቅቶች የተሰረዙ መሆናቸው በቂ ማስረጃዎች በኢትዮጵያ በኩል ማቅረብ እየተቻለ ሳይቀርቡ በመቅረቱ፤

3ኛ. የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚመለከቱ ከሌላ አገር ጋር የሚደረጉ ማንኛውም የድንበር ስምምነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ መቅረብ የሚገባውና በጉዳዩም ላይ ውሳኔ መስጠት ሲገባው ያለሕዝብ ፈቃድና ውሳኔ የተደረገ በመሆኑ፤

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣

የኢትዮጵያን ካርታ የቀያየሩ በርካታ እርምጃዎች በኢሕአዴግ በኩል ሲወሰዱ አንድም ቀን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲወስን አይደለም እንዲያውቀው እንኳ ተደርጎ አይታወቅም። ከአጎራባች አገሮች ጋር በጋራ ተባብሮ ለመኖር የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት እያደነቅን፤ ኢትዮጵያ ከአጎራባች አገራት ጋር በሰላም ለመኖር የራስዋን ጥቅም አሳልፋ መስጠት አይጠበቅባትም ብለን እናምናለን። ሰላም አንድ ወገን ስለፈለገው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ለሰላም ሲቆሙ ብቻ ነው ውጤታማ የሚሆነው።

በራሳችን አገር ውስጥ በትውልድ ሥፍራቸው ባሕላቸውንና ማንነታቸውን አስከብረው መኖር የተሳናቸውና ሕወሓት በፈጠረው በጠባብነት ላይ የተመሠረተ ተስፋፊነት በመከራና ስቃይ ላይ ያሉ የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ራያናቆቦ፣ አላማጣ፣ ኮረምና አፋር ወገኖቻችን ጩኸት ሰሚ ሳያገኝ፤ ከሌላው ጋር ሰላም ለመፍጠር መሮጥ “የራሷ ሲያርባት የሰውን ታማስላለች” አበው እንዳሉት የሚያስቆጥር እርምጃ ነው። በመጀመሪያ በሕወሓት የውስጥ ሰላማችውን የሚነሳና በማንነታቸው ላይ ያነፃጸረ ዘረኛ እርምጃ መፍትሄ ለመስጠት ማሰብ ክብሩነትዎ ደጋግመው የሚናገሩለትን ተደማምሮና አንድ ሆኖ መኖር ይፈጥራል ብለን እናምናለን።

የብዙ ወገኖቻችን ሕይወት የቀጠፈው፣ ንብረት ያወደመው፣ ከቀያቸው ያፈናቀለውና አሳዛኝ ፍልሰት የፈጠረው በኦሮሞና በሱማሊ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰው በደል ገና ዘላቂ መፍትሔ አላገኘም። ዛሬም አልፎ አልፎ የሚታዩ ግጭቶች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህንን የአገር ውስጥ ጸጥታና የሕዝብ በሰላም አብሮ መኖርን የሚጻረሩ እርምጃዎች በቅድሚያ መፍትሔ የሚሹ ናቸው። ስለሆነም፣ ለአገር ውስጥ ችግሮቻችን ቅድሚያ እንዲሰጥና የሕዝብ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ እንዲያደርጉ በአክብሮት እንጠይቃለን።

የአልጀርስ ስምምነት ያለቅድመ ሁኔታ ተቀብለን ተግባራዊ እናደርጋለን የሚለው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ በኢትዮጵያዊነታችው የሚኮሩት በአንድ ቋንቋና ባሕል የተሳሰሩ የኢሮብ ሕዝብ ያለፍላጎታቸውና ምንም ታሪካዊና ሕጋዊ መሠረት በሌለው እርምጃ ለሁለት ተከፍለው ግማሹ ወደ ኤርትራ እንዲገቡ ማድረግ፤ በወገንና በአገር ላይ የተቃጣ አደገኛ እርምጃ መሆኑን እንዲታወቅ በጥብቅ ለማስገንዘብ እንወዳለን። ለትግራይ ሕዝብ ቁሜአለሁ በሚል የውሸት አባዜ የተጠናወተው ሕወሓት፤ ትላንት በኢትዮጵያ ኅልውና ላይ እንደፈጸመው በደል ሁሉ፤ ዛሬም ጠዋትና ማታ እየማለ የሚገዘትበትን እወክለዋለሁ ያለውን የትግራይ ሕዝብ በገሀድ ሲክድ ታይቷል። እየታየም ነው።

ይህ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ያስነሳው የአልጀርስ የድንበር ስምምነት ውሳኔ አፈጻጸም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ በሚያውቀውና በሚወስንበት ሁኔታ እንዲሆን አጥብቀን እንጠይቃለን።

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በቆራጥ ጀግና ልጆቿ ይጠበቃል!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *