በመንግሥት የለውጥ መሪነት ከቀውስ ለመውጣት የተጀመረው ጥረት እየሰመረ፣ ነፍጥ አንስተው ሲፋለሙ የነበሩ ወገኖቻችን ሳይቀሩ የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለአገር ግንባታ መሰለፍ በጀመሩበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት የግል ጥቅምን ታሳቢ አድርገው ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚያደርጉትን ሩጫ መግታት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ወቅታዊ ተግባር መሆኑን መንግስትአጽንዖት በመስጠት ጥሪ አቅርቧል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመራው አዲሱ አስተዳደር ወደ ሃላፊነት ከመጣ ጀምሮ እየወሰደ ያለው እርምጃ ያላስደሰታቸው አካላት ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የማጋጨት ስራ ላይ መጠመዳቸው በተለያዩ ሚዲያዎችና አስተያየት ሰጪዎች፣ እንዲሁም የችግሩ ሰለባ በሆኑ ክፍሎች በተደጋጋሚ ሲገለጽ ሰንብቷል።

በተመሳሳይ እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች፣ ሕዝብ ” ምን እየሆነ ነው” በሚል ማመን እስከሚያቅተው ድረስ መገረሙን እየገለጸ ነው። ድጋፉንም እያሳየ ይገኛል። ይሁን እንጂ በተለያዩ አካባቢዎች ብልጭ ድርግም የሚሉ ግጭቶች፣ መፈናቀል እንዲሁም ኩርፊያ እያየለ መምጣቱ ለበርካቶች ስጋት እየሆነ ነው።

በተለይም ህወሃት ያወጣው መግለጫ ይህንኑ ችግር የሚያሳይና በተጀመረው ለውጥ ላይ ቅሬታ ስለመኖሩ ምስክር ሆኖ ታይቷል። ሌሎች አጋርና እህት ድርጅቶች አቋማቸውን እንደ ህወሃት ተገፋን በሚልም ሆነ በድጋፍ በግልጽ ባያሳውቁም የሃይል አሰላለፉ ብዙም ግር የሚል አልሆነም።

በተለይም ኦህዴድና ብአዴን የመደጋገፋቸው ጉዳይ ፈተና የሆነባቸው አካላት ይህንኑ ጥምረት ለመስበር እላይ ታች እያሉ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እየገለጹ ነው። በሌላም በኩል ሁለቱም ድርጅቶች ውስጥ ድርጅታቸውን እየገነቡ ነው። በተለይም ኦህዴድ ከስራ አስፈጻሚ ጀመሮ እስከ ታች ባለው መዋቅሩ ስር ነቀለ ለውጥ በማድረግ የጀመረውን አዲስ አካሄድ ግፍቶበታል። በማፈናቀል ተግባር ሆን ብለው የተሳተፉትንም ለይቶ ለፍርድ እንደሚያቀርብ ይፋ አድርጓል።

በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ላይ ተጫምጦ አዲስ አስተሳሰብ ላይ መሆኑንን ይፋ ያደረገው ኦህዴድ በጀመረው ተግባር እንደሚገፋ  ሳያቅማማ አሳውቋል። ” ስልጣን ከአገር አይበልጥም፣ የእኛ ስልጣን ጥንቅር ይበል” ሲል ይፋ ያደረገው ኦህዴድ ” ፓርቲ ከአገር ይበልጣል” የሚለውንም የቀነጨረ አስተሳሰብም አስወግዶታል። ለዚህም ይመስላል አቶ ለማ መገርሳ ” ኢትዮጵያን የማዳን ስራ ሰርተናል” ሲሉ ተደምጠዋል።

አዲሱ ምደባና የለውጥ አስተሳሰብ ” የአብዮታዊ ዴሞክራሲን መርሃ የሚጥስ ነው” በማለት ወደ ዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት አስተሳሰብ ስለመመለስ የሚወተውተው ህወሃት የመጨረሻ አቋሙ ምን እንደሚሆን የሚለይበት ጊዜ ደርሷል። በርካቶች እንደሚያምኑት ህወሃት በየትኛውም መስፈርት ካሁን በሁዋላ በአማራና ኦሮሚያ ክልል ተቀባይነት አያገኝም። እንደ መለአክ ክንፍ ቀጥሎ ቢመጣ እንኳን ጉዳዩ ያከተመ እንደሆነ የሚናገሩ እንደሚሉት ህወሃት ይህንን አምኗል።

ይህንን ቢያምንም ግን ቀጣይ አገሪቱ እያመራችበት ያለውን አካሄድ ለመቀበል አቅም ማግነት አልቻለም። ለዚህም ይመስላል ሮሮ እያሰማ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት ከሮሮም የዘለለ አቋም ለመያዝ እንደሚችል ይገምታሉ። ሌሎች ደግሞ ህወሃት የፈለገውን አቋም ቢይዝ ችግር የለውም ፣ ግን ጣጣውን ወደ ሌሎች እንዳያራባ ሊያስብ ይገባል ባይ ናቸው። አሁን የተጀመረው አካሄድ ያልጣመው ህወሃት ከኢህአዴግ ስብስብ ሊለቅ እንደሚችል የሚገምቱ ቢኖሩም፣ ሌሎች ከኤርትራ ጋር ስምምነት ሳያደርግ ይህንን እንደማያስብ ይናገራሉ። ሁሉም አካላት ግን የኢህአዴግ መፈረካከስ በደጅ ስለመሆኑ አይከራከሩም።

ኦህዴድም ሆነ ብአዴን ካሁን በሁዋላ ወደ ሁዋላ እንደማይሉ የሚስማሙ ክፍሎች፣ በህወሃት ውስጥ የተፈጠረውን ስጋት አስታሞ ለመቀጠል አሁን የሚያስፈልገው የህወሃት ቀናነት ብቻ ነው። ጊዜውን፣ ወቅቱንና የሕዝቡን ስሜት በማገናዘብ አገሪቱ ወደ ሁሉን አቀፍ እርቅ የምታመራበትን፣ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በፍቅር የሚኖርበትን፣ ቀደም ሲል የተሰሩ ስህተቶችን በጎ ጎኖችን በማየት ብቻ የሚከስሙበትን መንገድ መሻት!!

ገለልተኛ የሆኑ ወገኖች አስረግጠው እንደሚናገሩት በማህበራዊ ገጾችም ሆነ በተለያዩ ሚዲያዎች ግለስቦችን እጅግ በማጉላት ሌሎችን እልህ ውስጥ የመክተት አካሄዳቸው በፓርቲው ውስጥ ሰላም እንደሚያደፈርስ ያምናሉ። በፓርቲ ደረጃ የተወሰኑ ውሳኔውች ተግባራዊ ሲደረጉ ሙገሳውን ወደ ግለሰብ ባለመጎተት፣ ግለሰቦች ቢሰሩም ስራቸውን ስለሆነ ብዙም ባለማዳነቅ መጓዙ ለውጡን እንደሚያፋጥንና የተሳለጠ እንደሚያደርገው ያምናሉ።

የዴንማርክ ነዋሪ የዛጎል የዘወትር አስተያተ ሰጪ እንዳሉት አሁን ባለው ሁኔታ ስለ ማሸነፍና መሸነፍ መስበክ አገሪቱን ለኪሳራ ከመዳረግ ውጭ የሚያመጣው ነገር የለም። ሁሉም ወገኖች በሰከነ መንገድ ድጋፋቸውን ሊሰጡ እንደሚገባ የሚመክሩት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፤ የአገሪቱ ችግር የቆየ፣ የተወሳሰበ፣ አንዱን ሲነኩት ሌላው የሚመዘዝ አይነት በመሆኑ አርቆ አስተዋይነት ግድ መሆኑንን ይናገራሉ። አቶ መለስ የተበተቡት ትብትብ ሰላማዊ ዜጎችን ህሊና ያሳተ በመሆኑ ይህንን ለማረም አርቆ ማሰብና በሰከነ መንገድ መጓዝ ግድ ነው።

አስተያየት ሰጪው አያይዘውም አኩራፊዎች የነበራቸው የቀድሞው ሰንሰለት ሰሎ እስኪበጣጠስ ድረስ የሚያደሩት የተንኮል ድር በቀላሉ የሚታይ አንዳልሆነ ተናግረዋል። አሁን የሚታዩት ግርግሮችና ተቃውሞዎች የዚሁ ውጤት ናቸው። ስለሆነም ህዝብ ለውጡን በስሜታዊነት ሳይሆን በሰከነ መንፈስ ሊደግፍና ሊጠብቅ ይገባል። ይህ ካልሆነ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰና የማንወታው ሊሆን ይችላል። ወሃ ሲወስድ አሳስቆ እንዲሉ። … ባላቸው የዲፕሎማሲ መረጃ መነሻነት በአዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዙሪያ የተለየ ነገር ይፈጠራል የሚል ስጋት ባይኖራቸውም የመከላከያና የድህንነት ክፍሉ ለአገር፣ ለህዝብና ለቆሙለት ህገ መንግስት ብቻ ታማኝ በመሆን ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ባለፉት ወራቶች የተከሰቱትን አለመረጋግቶችና ቀውሶች አስመልክቶ መንግስት ያወጣውን መግለጫ ተንተርሶ ፋና የሚከተለውን ዘግቧል 

በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን አስመልክቶ የኢፌዴሪ መንግስት መግለጫ አውጥቷል። ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እና አገራዊ ድባብ ጠብቆ ማስቀጠል የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት መሆን አለበት ብሏል::

በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ እየሰፈነ ያለው ሰላምና መረጋጋት ብሎም እየታየ ያለው አገራዊ መግባባትና የህዝቦች አንድነት የአገራችንን ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት በአፍሪካ ደረጃ ብሎም በዓለም አቀፍ መድረኮች ውጤት እያስገኘ ያለ ስኬት ነው ብሏል መግለጫው።

በዚህም ሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን የምንገኝበትን የአፍሪካ ቀንድ እና የአካባቢውን ወቅታዊ ሁኔታ ከመሰረቱ የሚለውጥ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናችን ይታወቃል።

በዚህም ዓለምን ያስደመመ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት በማሰመዝገብ ላይ እንገኛለን ያለው መግለጫው፥ ይህም አገራዊ ጥቅማችንን ከማስጠበቅ አልፎ ቀጠናዊ ትስስር በመፍጠር ረገድ ያጋጠሙንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመቅረፍ የህዝቦቻችንን የተከማመሩ ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ሌት ተቀን እየተጋ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች ጊዜያዊ ግጭቶች ሲከሰቱ እየተስተዋለ ነው ብሏል።

አካባቢያዊ ወሰንና ሌሎች መሰል ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ ለዘመናት አብሮ በኖረው ህዝቦች መካከል ጥርጣሬን የሚፈጥሩ እና ለግጭት የሚያነሳሱ ሴራዎች መስተዋላቸውን አስታውቋል።

የተፈጠረው ግጭት በምንም መስፈርት ህብረተሰቡን የማይወክልና የተጀመረው የለውጥ ሂደት ባልተዋጠላቸው አካላት ጠንሳሽነት እየተመራ እንደሆነ ከወዲሁ መገንዘብ ይቻላል ነው ያለው።

ስለሆነም መንግሥት በግጭቱ ምክንያት ለደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ በማለት፥ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል። በድርጊቱ የተሳተፉትን አካላት መርምሮ አስተማሪ እርምጃ እንደሚወስድም አረጋግጧል።

ይህን መሰል ጥፋትና ግጭት ያቀነባበሩት እና ሁከቱን ያባበሱት አካላት ዓላማ አሁን በአገራችን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ማወክ፣ መንግሥት እየገነባው ያለውን አገራዊ አንድነት መናድና በአጠቃላይ አገራችን የጀመረችውን ውጤታማና ፈጣን የሪፎርም እንቅስቃሴ ማደናቀፍ መሆኑ አያጠያይቅም ብሏል መንግስት በመግለጫው።

በመሆኑም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አምርሮ ሊታገለው የሚገባ አደገኛ አዝማሚያ እና ተግባር መሆኑን ተገንዝቦ በጽናት ሊታገልና ሰላሙን መጠበቅ ይገባዋል ብሏል።
በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በክፉውም ይሁን በደግ አብረው በኖሩ ህዝቦቻችን መካከል ግጭት ሊፈጠር አይችልም ያለው መግጫው፥ ይህ በረጅሙ የታሪክ ጉዟችን የተረጋገጠ ሃቅ

ከመሆኑም ባሻገር የህዝቦች ፍላጎት ምንግዜም ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና እንጅ ብጥብጥና ውድመትአይደለም።

በመንግሥት የለውጥ መሪነት ከቀውስ ለመውጣት የተጀመረው ጥረት እየሰመረ፣ ነፍጥ አንስተው ሲፋለሙ የነበሩ ወገኖቻችን ሳይቀሩ የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለአገር ግንባታ መሰለፍ በጀመሩበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት የግል ጥቅምን ታሳቢ አድርገው ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚያደርጉትን ሩጫ መግታት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ወቅታዊ ተግባር ነው ብሏል።

በመሆኑም መላው ህዝባችን ለዘመናት ሲንከባከባቸው የኖሩትን የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመከባበርና የመረዳዳት እትዮጵያውያን እሴቶች በጥቂቶች ሴራ እንዳይሸረሸሩ ነቅተን እየጠበቅን በአገራችን ዘላቂ ሰላም፣ አስተማማኝ ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ልማትና ብልጽግና እንድሰፍንና የተጀመረው አገራዊ ትግል ለውጤት ይበቃ ዘንድ የጥፋት ሃይሎችን ዕኩይ ተግባር ነቅተን እናምክን የሚል ጥሪውን መንግስት በመግለጫው አስተላልፏል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *