“በሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ሌብነት አለ፤ ኦዲት አይደረጉም፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሙስና በፍትሕ ሥርዐት፣ በግዥ፣ በገቢ እና በፋይናንስ አስተዳደር ያለውን ትስስርና ጉድኝት በማጥናት የምናስተካክልበትን መንገድ መቀየስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

ሐራ ዘተዋሕዶ

  • መፍትሔ ካላበጀን፣ የፈራነው ጥላቻና ቁርሾ አጀንዳ ኾኖ የሚቀጥል ይኾናል፤
  • በጥላቻ ላይ የተመሠረተ አካሔድ መቆም አለበት፤አየነው፣ አየነው ኪሳራ ነው፤
  • ከጥላቻ ይልቅ ስለኢትዮጵያዊነትና ወንድማማችነት፤ከመፍረስ ይልቅ ስለመደመር፤
  • ተቋማቱ ኦዲት አይደረጉም፤ የምናስተካክልበትን መንገድ መከተል ያስፈልጋል

አገራችን ኢትዮጵያን ለውጥረት የዳረጋት በጥላቻ ላይ የተመሠረተ የፖሊቲካ አካሔድ፣በሃይማኖት ተቋማት ውስጥም ልዩነት መፍጠሩን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መከፈል ጀርባም መኖሩን የጠቆሙ ሲኾን፤የዘር እልቂት ከማስከተሉ በፊት መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፤ በሃይማኖት ተቋማት ሥር የሰደደው ሌብነትም፣ የእርስ በርስ ጥላቻንና ቁርሾን የሚያስቀጥል በመኾኑ ከመሠረቱ ተጠንቶ የሚስተካከልበትን መንገድ ማበጀት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ትላንት ሰኞ፣ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተገኝተው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ማብራሪያ ከሰጡባቸው የእንደራሴዎች ጥያቄዎች መካከል፣ የፀረ ሽብር እና የፀረ ሙስና ሕጎች በሥራ አስፈጻሚው አካል እየተተገበሩ ያለበትን ኹኔታ በተመለከተ የቀረበው ጥያቄ ይገኝበታል፡፡ የተፈረደባቸው ወንጀለኞች የሚፈቱበት አግባብ የሕግ ክፍተት የሌለበት እንደኾነ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሕግና በሕግ ብቻ ለማስተዳደር ሰዉ ጭንቅላቱ መቀየር አለበት፤ አገርን በይቅርታ የሞራል ልዕልና ለማቆምም ልባችንን ሰፋ እናድርግ፤ በማለት መክረዋል፡፡

ከተፈረደባቸው አንዳንዶቹ በይቅርታ የሚፈቱበት ምክንያት፣ በጥላቻ ላይ የተመሠረተውና ውጥረት የተመላ የፖሊቲካ አካሔድ፣ ከመባባሱና እልቂት ከማስከተሉ በፊት በማስቆም ለበሰለ የፖሊቲካ ውይይት ምኅዳሩን ለማስፋት በማሰብ እንደኾነ አመልክተዋል፡፡ ይህም፣ ኹሉም ኢትዮጵያዊ የብሔር ማንነቱ ተከብሮ ሲያበቃ ከግጭትና ከጥላቻ መንገድ ተጠብቆ ለሚወዳት አገሩ ዕድገትና ታላቅነት የሚቆረቆረውን ያህል ለመሥራት እንደሚያስችለው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጥላቻውና ውጥረቱ፣ በፖሊቲካው ያልተወሰነና በሃይማኖት ውስጥም መከሠቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ሲኖዶሳዊ አንድነት መከፈል በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ “አሜሪካ ያለው ሲኖዶስ እና እዚህ ያለው ሲኖዶስ ኦርቶዶክስ ብቻ አይደለም፤ ከኋላው ብሔር አለ፤” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፣ መለያየቱ ከጉዳት በስተቀር ያስገኘው ጥቅም ባለመኖሩ ሊፈታ እንደሚገባው በአጽንዖት አሳስበዋል – “መቆም አለበት ይኼ፤ አይጠቅመንም፤ አየነው፤ አየነው ኪሳራ ነው፤” ብለዋል፡፡

ለችግሩ መፈጠር የፖሊቲካው ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጫና የማይዘነጋ ቢኾንም፣ በማባባሱ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሡት “ብሔረተኝነት” ሊታበል እንደማይችል በብዙዎች ይታመናል፡፡ እንደተናገሩትም፣ ማዕከላዊ አስተዳደሯን በማናጋት ለተለያዩ ተጽዕኖዎች ከማጋለጡም በላይ ከወዲሁ እልባት ካላገኘ ወደ ከፋ ቀኖናዊ ልዩነትም እንዳይሰፋ ያሰጋል፡፡ አገራችን ለሚያስፈልጋት ይቅርታና ዕርቅ፣ የጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊ አንድነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው በተለያዩ አጋጣሚዎች የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ መንግሥታቸውና እርሳቸውም በግል፣ በተሻለ አያያዝ ለተጀመረው የሰላም ጥረት የበኩላቸውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁነታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የሰላምና አንድነት ዓለም አቀፍ ኮሚቴው፣ ልኡካን አባቶች የሚገናኙበትን ቦታና ጊዜ ወስኖ ሲዘጋጅ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍም፣ በስደት ያሉት አባቶች ወደ ሀገር ተመልሰው ለመኖር የሚያስችላቸውን ዋስትና ከመስጠት አንሥቶ፣ በአሜሪካ ያደርጉታል ተብሎ በሚጠበቀው ጉብኝት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን፣ “በይፋ አግባብቶ በተጓዙበት አውሮፕላን ይዞ እስከ መመለስ”ድረስ ያሰቡበት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡

በአገራችን የተፈራውን ጥላቻና ቁርሾ የሚያስቀጥለው ሌላው ችግር፣ የተደራጀ ሌብነት/ሙስና እንደኾነ የተናገሩት ዶ/ር ዐቢይ፣ በሃይማኖት ተቋማትም በከፍተኛ ደረጃ መንሰራፋቱን ገልጸዋል፡፡ መንሥኤው መዋቅራዊ እንደኾነና በየጊዜውም እየጨመረና እየሰፋ በመምጣቱ፣ ከመሠረቱ አጥንቶ መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

“በሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ሌብነት አለ፤ ኦዲት አይደረጉም፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሙስና በፍትሕ ሥርዐት፣ በግዥ፣ በገቢ እና በፋይናንስ አስተዳደር ያለውን ትስስርና ጉድኝት በማጥናት የምናስተካክልበትን መንገድ መቀየስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት፣ እንደ ሞራል አስተማሪነታቸው፣ በውስጣቸው የተሰገሰገውን የሌብነት ድር በመበጣጠስ ለመንግሥትና ለሕዝብ አርኣያ እንዲኾኑ በቀደሙ መድረኮች ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሚሰበስቡት መባ እና ዘካ የሕዝብ ሀብት እንደመኾኑ መንግሥት አጠቃቀሙን የመቆጣጠር ርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ለፓርላማው ያቀረቡትን አጭር ሪፖርትና የሰጡትን ማብራሪያ የተለያዩ አብያተ እምነት መሪዎች በምክር ቤቱ በተመልካችነት የተከታተሉት ሲኾን፤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ ተገኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ

በፀረ ሽብር እና የይቅርታ ሕጉ አፈጻጸም ዙሪያ(በከፊል)፤

ሰዉ ጭንቅላቱ መቀየር አለበት፤ ለዘለዓለም እንደማይኖር አውቆ በሕግና በሕግ ብቻ መግዛት፣ ማስተዳደር፣ መቀየር መቻል አለበት፡፡… ልባችንን ሰፋ እናድርግ፤ አንዳንዶቹን[በወንጀል የተፈረደባቸውን] የምንፈታበት ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያ ውጥረት የተመላ(TENSEFUL) በጥላቻ ላይ የተመሠረተ የፖሊቲካ አካሔድ የዘር እልቂት ሊያመጣ እየሔደ ነው፡፡ኹሉ በዘር ነው፡፡ ፖሊቲካ ብቻ አይደለም፤ ሃይማኖትም፡፡ አሜሪካ ያለው ሲኖዶስ እና እዚህ ያለው ሲኖዶስ ኦርቶዶክስ ብቻ አይደለም፤ ከኋላው ብሔር አለ፤ መቆም አለበት ይኼ፤ አይጠቅምም፡፡ አየነው፤ አየነው፤ ኪሳራ ነው፡፡አኹን የሚያዋጣው ነገር፣ ብሔር ማግኘት የሚገባውን ክብር ካገኘ በኋላ እንደ ሀገር አብሮ ለመኖር ግን የማይቸገር መኾን አለበት፡፡ ኹለተኛው ሰላም በሰላም ብቻ ነው የሚገኘው፡፡ ሰላም በማሰር፣ በማሳደድ አይገኝም፤ ያብሰዋል ጉዳዩን፡፡ይህ አገር የኹሉም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ያገባኛል፤ የእኔ ነው፤ ይኾነኛል፤ ብሎ እንዲሳተፍ መፍቀድ ያስፈልጋል፡፡ መንገዱ ይለያይ ይኾናል እንጅ፣ ኹሉም አገሩን የሚወድ፣ የአገሩን ዕድገት የሚመኝ፣ ለአገር ታላቅነት አልማለሁ ብሎ ለአገሩ የሚሠራ መኾኑን ማመን አለብን፡፡ እኛ ብቻ አይደለንም የምንቆረቆረው ለኢትዮጵያ፤ ኹሉም ይቆረቆራል፡፡ሲቆረቆር በስሕተት መንገድ እንዳይሔድ፤ በግጭት እንዳይሔድ፤ በጥላቻ እንዳይሔድ፣ ብሔርን ከብሔር በሚያጋጭ መንገድ እንዳይሔድ፤ ትላንት ተበድያለሁ፣ ነገም ስለምበደል አልፈልግም በሚል መንገድ እንዳይሔድ፤ የበሰለ(MATURED ያደረገ) የፖሊቲካ ውይይት ያስፈልጋል ብሎ ማሰብ ጥሩ ነው የሚኾነው፡፡ አኹን የእኛ ድርሻ ሜዳውን ማስፋት ነው፤ ኹሉም እንዲወዳደር፤ ኹሉም ሐሳቡ እንዲደመጥ ማስፋት ነው፡፡

በፀረ ሙስና ሕጉ አፈጻጸም ዙሪያ(በከፊል)፤

ሙስና የሚባለው ካንሰር ዋነኛ የጭቆና እና የዘረፋ መሣሪያ እየኾነ ነው፡፡ ሙስና አምስተኛ መንግሥት ነው የተባለበት ምክንያት፣ በተደራጀ መንገድ ያሻውን ነገር እጅን ጠምዝዞ ስለሚያስፈጽም ነው፡፡ ሰርቆ መብላት ብቻ አይደለም፤ ሰርቆ ከፍላጎቱ ዝንፍ ስትል አንቆ ወደ ፍላጎቱ ማምጣትን ጭምር እንደ መንግሥት መተግበር ስለሚችል ነው፡፡ እንደ እኛ ባላደገ አገር የኢኮኖሚ ውድቀት ብቻ ሳይኾን፣ መደለል የማይችሉ አቅም የሌላቸውን ድኾች በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ፍላጎታቸው በሌሎች ፍላጎቶች የተዋጠና የተገዛ ይኾናል፡፡ ይህን አይቶ ምላሽ መስጠት ተገቢና አስፈላጊ ይኾናል፡፡የሙስና መንሥኤ መዋቅራዊ መኾኑን ማየት ተገቢ ነው፡፡ ላለፉት ዐሥር ዓመታት የኾኑ የኾኑ ሰዎቸ ስናስር ሙስናው ለምንድን ነው እየጨመረ የሔደው? እየቀነሰ አልመጣም፤ እየጨመረ፣ እየሰፋ ነው የሔደው፤ ዋናውን ምንጩን በሚደፈጥጥ አግባብና አቅም እየሔድን አይደለም ማለት ነው፡፡…የፍትሕ ዕጦት፣ የፍትሕ ችግር፣ በገንዘብ ማሰር፣ በገንዘብ መፍታት የሚቻል ከኾነ ሙስና ይስፋፋል፡፡ ሙስና ፥ በፍትሕ ሥርዐት፣ በግዥ፣ በገቢ፣ በፋይናንስ አስተዳደር ምን ያህል ትስስርና ጉድኝት እንዳለው ማየት አስፈላጊ ይኾናል፡፡ ኹለተኛ፥ ሙስና ሲባል ለኾነ ግሩፕ የመስጠት ዝንባሌም አደገኛ በሽታ ነው፡፡ መጠኑ ይስፋ ይብዛ እንጅ፣ ሌብነት ከጫፍ ጫፍ ባህል ኾኗል፡፡ ይህንም በሚያስተካክል አግባብ የሙስናን ጉዳይ አይቶ፣ ከመሠረቱ አጥንቶ መፍትሔ ማበጀት ይገባል፡፡ ያን ማድረግ የማንችል ከኾነ፣ ቅድም የፈራነው ጥላቻ፣ ቅድም የፈራነው ቁርሾ፣ ይኼም አጀንዳ ኾኖ ልክ እንደ ሃይማኖት የሚቀጥል ይኾናል፡፡በሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ሌብነት አለ፤ ኦዲት አይደረጉም፤ በትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ሌብነት አለ፤ ግሬድን ጨምሮ፡፡ እነዚህን ኹሉ በጥቅሉ ፈትተን የምናስተካክልበት መንገድ መከተል ያስፈልጋል፡፡የመንግሥት ሓላፊዎች ደግሞ ተጨማሪ ሓላፊነት አለባቸው፡፡ በመንግሥት ሥልጣን የሕዝብን ሀብት መስረቅ ጸያፍ ወንጀል፣ ከወንጀልም በላይ አሳፋሪ ወንጀል ስለኾነ የመንግሥት ባለሥልጣናት መነገድና ሀብታም መኾን ከፈለጉ ቢሯቸውን እየለቀቁ መሔድ አለባቸው፡፡ ቢሮ ኾኖ፣ የመንግሥት አለቃም ነጋዴ ሀብታም መኾን አይቻልም AT A TIME.

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *