የተከበራችሁ የሕወሓት አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የጥቅም ተጋሪዎች!

በተራ እውነት እንነሳ፡፡ ጦርነት ሁሉ በግድ በጠበንጃ አይካሄድም፡፡ የጦርነት ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ ይህንንም በሀገራችን ሰሞነኛ ክስተቶች እየተገነዘብን እንገኛለን፡፡ በጥይት አረር የሚካሄድ ጦርነት ጊዜያዊ አሸናፊዎችን ይለያል፤ ተዘውትሮ እንደሚጠቀሰው በኃይል ሚዛን በልጦ በመገኘት በጥይት እሩምታ የሚካሄድን አንድ ጦርነት ማሸነፍ ብቻውን ጦርነቱን በአሸናፊነት መውጣትን አያመለክትም – ቀን ጠብቆና ኃይልን አደራጅቶ ጦርነቱ ማገርሸቱ አይቀርምና፡፡ በፍቅር ጦርነት ግን ዘላቂው አሸናፊ ይታወቃል፡፡

እናንት ሕወሓቶች ላለፉት 43 ዓመታት በጥይትና ምናልባትም ከዚሁ ጋር በሚያያዘው የተንኮልና የሸር ትብተባዎች የተዋጣላችሁ ተዋጊዎች ሆናችሁ ዘልቃችኋል፡፡ ባኬሄዳችኋቸው የመሣሪያ ጦርነቶች ሁሉ አመርቂ ውጤት በማስመዝገባችሁ የትጥቅ ትግል ድሎች ከእናንተ ደጅ ሳይጠፉ ይሄውና ከአራት አሠርት ዓመታት በላይ ያሻችሁን ሁሉ አድርጋችኋል፡፡
አሁን ግን ያ የመሣሪያና የአሻጥር ጦርነት ወደ ማክተሚያው ዘመን ደርሷል፡፡ ከፍ ሲል እንደጠቆምኩት የመሣሪያ ትግል ልብንና ኅሊናን ስለማይገዛና ጊዜያዊ አሸናፊነትን ብቻ ስለሚያረጋግጥ የእውነት ዘገር በመጨረሻው ሁሉንም ኃይል መርታቷ አይቀርም፡፡ በሀገራችን እውነተኛዋ የነፃነት ጮራ በመፈንጠቅ ላይ የምትገኘውም ለዚህ ነው፡፡ ለዚህ ቀን ላበቁን ሁሉ ምሥጋናየ ይድረሳቸው፡፡ ባልተወለደ አንጀት እንደዐይጥ የተጨፈጨፉ፣ በእሥር የተንገላቱና አሁን ድረስ እየተንገላቱ የሚገኙ፣ በስደት የሚማቅቁ፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በሰቆቃ ዕንባ የሚነፈርቁ… ሁሉ ለዚህ አንጻራዊ የነጻነትና የሠላም አየር የበኩላቸውን አስተዋፅዖ አበርክተዋልና በያሉበት ፈጣሪ ዋጋቸውን ያብዛልን፡፡
ይህ አሁን እያስተዋልነው የምንገኘው ሕዝባዊ ደስታንና ፈንጠዝያን የፈጠረ እፎይታ እንዲህ በቀላሉ የተገኘ አይደለም፡፡ እናንት ሕወሓቶች ስታፍኑትና ስታሰቃዩት የባጃችሁት ሕዝብ ሲችል በጉልበት ሳይችልና በተጓዳኝ በጸሎትና በዕንባ ሲታገላችሁ ቆይቷል፡፡ የጸሎትን ብትር ደግሞ ማንም አይችለውም፡፡ የጸሎት ጦር ደም መላሽ የለውም፡፡ ትልቁ መፍትሔ እጅ መስጠት ብቻ ነው፡፡ ከማይችሉት ሕዝባዊ ማዕበልና የምሥኪን ዜጎች ዋይታ ከፈጠረው መለኮታዊ የቅጣት ዶፍ ማምለጥ የሚችል ምድራዊ ኃይል የለም፡፡ በቅድሚያ ከራስ ጋር በመታረቅ አካሄድን ማስተካከል ከተጨማሪ የውዝፍ ዕዳ በትር ያድናል፡፡
ላስታውሳችሁ – ደርግ ሲወድቅ አጠገቡ ነበርኩ፡፡ በጦር መሣሪያ ብዛትና ጥራት እንዲሁም በሠራዊት ትልቅነት – የጥራት ችግር ቢኖርበትም – በአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ውስጥ ነበር፡፡ ግን ቀኑ ደረሰና በቅጽበት ውስጥ ተፍረከረከ – ያ ሁሉ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትን ሣይቀር ያስፈራ ጦር እንደጪስ በነነ፡፡ ታንክና መትረየስ የያዘ ሠራዊት ሰባራ ክላሽ ለያዙ ሕጻናት የወያኔ ድኩማን ጀሌዎች እጁን ሰጠ፤ አሥር የማይሞሉ ባላገር ወያኔዎች አንድን ግዙፍ ክፍለ ጦር እያሳደዱ ብዙ ታንክና ባዙቃ ማረኩ፡፡ ቀን ሲጥል እንዲህ ነው፤ ቀን ይሰጣል – ቀን ይነሳል፡፡ በታሪክም እነሮምና ባይዛንታይን ግዛቶች የወደቁት በዚህ መልክ ነው፡፡ ኃይልና ጉልበት፣ ዕውቀትና የመሣሪያ ብዛት ከውድቀት አያድኑም፡፡ አስተውሎት አጣን እንጂ መጽሐፉም “ኢይድኅን ንጉሥ በብዝኃ ሠራዊቱ” ይላል፡፡ ከውድቀት የሚያድነው ብቸኛው መንገድ በጥበብና በእምነት የተገዛ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ለሰው ያዝናል፤ ፍቅር ራስ ወዳድነትን ይጠየፋል፤ ፍቅር ስለራስ ሣይሆን ስለሌሎችና ለሌሎች ይጨነቃል፡፡…

ፍቅር …. (እባክዎ ከግርጌ ያስቀመጥኩትን ዝክረ ፍቅር ይመልከቱ)

አንድ ሰው ትንሣዔና ውድቀቱን ማጤን አለበት፡፡ በመንቻካነት ልጓዝ ቢል ጣሩን ከማብዛቱም በተጨማሪ የገዛ ትውልዱንና ሀገሩን ለከፋ ውድቀት ይዳርጋል፡፡ “ዕወቅ ያለው በዐርባ ቀኑ ያውቃል፤ አትወቅ ያለው ደግሞ በዐርባ ዓመቱም አያውቅም” ይባላል – ለሕወሓት ተለክቶ የተሰፋ ብሂል ይመስላል፡፡ ከስህተት መማር ብልኅነት ነው፡፡ ከታሪክ መማር አስተዋይነት ነው፡፡ በመጀመሪያው ግትርነት እስከመጨረሻ ዘልቆ ወገንንና ሀገርን እንጦርጦስ ለማውረድ መቁረጥ ከጤናማ ሰው የማይጠበቅ የወፈፌነት ምልክት ነው፡፡ ጥላቻና በቀል በዕድሜ መግፋትና በልምድ መዳበር ሊለዝቡ ይገባል፡፡ ዕድሜ እኮ መስተዋት ነው፡፡
ሕወሓት ከእንግዲህ የፈለገውን ዓይነት ተንኮል ቢሸርብ አንድም የሚሣካለት ነገር አይኖርም፡፡ አሁን ሕዝቡ ሁሉንም ነገር ለይቶ አውቋል – ሕይወቱንና ንብረቱን እየገበረ ባሣለፈው ተሞክሮ ምክንያት ዛሬ ላይ ሕዝቡ የማያውቀው ነገር የለም፡፡ ተንኮልም ሸርም ያረጃሉ – ይነቃባቸዋልም፡፡ ብልጠትም ክፋትም አርጅተው ይጃጃሉ፡፡ የክፋት ጀሌም ልብ እየገዛ ይሄድና የሚከዳበት ወቅት አለ፡፡ በክፋት ተባባሪነት የሚሠለፉ ኃይሎችም ይዋል ይደር እንጂ ቀን አይተው ገለል ይላሉ፤ ከሟች ጋር የሚሞት ሞኝ ነው፤ መሠሪዎች የጉዞ መስመራቸውን ለመለወጥ ሞራ አንባቢ እስኪገኝ አይጠብቁም፤ ብልጦች ናቸው፡፡ ስለዚህም ሕወሓት ብቻውን የሚቀርበት አጋጣሚ መኖሩ አይቀርምና ያ አጋጣሚ ደረሰ፡፡ አሁን ሕወሓት እንደዱሮው መስሎት እዚያና እዚህ ቦምብ ላጥምድ ቢል ፋሽኑ አልፏልና አይሠራም – ሕወሓቶች ዝንታለማቸውን “በፋሲካ የተቀጠረች ገረድ” መሆን የለባቸውም፤ ዘመን ተለውጧል፤ የጦርነቱ አቅጣጫና የውጊያ መሣሪያውም እንዲሁ፡፡ ይህ ሕዝብ ዕድሜ ለሕወሓት በችግር መቆራመድንና መታሰር መገረፍን ብቻ ሣይሆን መገደልንና መሞትንም ለምዷል፡፡ ሞትን በፀጋ ለመቀበል የተዘጋጀን ሕዝብ ማሸነፍ ደግሞ አይቻልም፡፡ ይህን አስከፊ ሁኔታ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ተረድተናል – ወዴት ልንሄድ እንደነበር በተለይ በአማራና ኦሮሞ አካባቢዎች የታዩ ጅምር ዐመፆች አመላካች ነበሩ፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያን ትቶ የማይተዋት ፈጣሪ ከምንፈራው የደም ባሕር ሊያወጣን አስቦ ይህን ልጅ – ዶ/ር ዐቢይን – ተመስሎ በሙሤ ፈረስ ከፈርዖኖች ግቢ በመነሣት ገስግሶ በማለዳው የደረሰልን፡፡
ሕወሓቶች ጆሮ ካላቸው ይስሙኝ፡፡ የሚያዋጣው መጸጸትና ከስህተት መንገድ መውጣት ነው – አሁን በአፋጣኝ፡፡ ባረጀ ባፈጀ የመሣሪያ ጦርነትና በማኪያቬላያዊ የተንኮል ቅኝት መጓዝ ለበለጠ መላላጥና ለአስከፊ ጣር ከመዳረግ ባለፈ ሕወሓትንም ሆነ ማንንም አይጠቅምም፡፡ ከስድስት ሚሊዮን ሕዝብ የወጡ እፍኝ የማይሞሉ አሰለጦች መቶ ሚሊዮን የነቃና በመደራጀትም ላይ የሚገኝ ሕዝብ ያሸንፋሉ ብሎ ማሰብ ከመነሻው ዕብደት ነው – ለአፍዝ አደንግዙ ማርከሻው የተገኘለት ይመስላልና ሕወሓት በቶሎ ነቅቶ ወደ ኅሊናው ካልተመለሰና በጥፋት ጎዳናው ልቀጥል ካለ ውጤቱ ተያይዞ ገደል ነው፡፡ እርግጥ ነው – ያ የተለመደው ሕወሓታዊ የቅጥፈት መንገድ ለብዙ ዘመናት ሠርቷል፤ ለዘላለሙ ይሠራል ማለት ግን አይደለም፡፡ ሕወሓት ሕዝብን በዘርና በጎሣ፣ በሃይማኖትና በመሳሰለው ሰውኛ የመከፋፈያ መንገድ አንዱን ከሌላው በማጋጨት ብዙ ተጉዟል፤ ምድራዊና አላፊ ጠፊ ለሆነ የሀብትና የሥልጣን ክምችትም አብቅቶታል፡፡ አሁን ግን በዚህ አሮጌ መንገድ ለተወሰነ ጊዜ መጠነኛ ጉዳት ማድረስ ይቻል እንደሆነ እንጂ እንደ እስካሁኑ ተጉዞ የእስካሁኑን የመሰለ አፓርታዳዊ ሥልጣንንና ሸውራራ የሀብት ክፍፍልን ማስቀጠል አይቻልም፡፡ ሲበቃ ይበቃል፡፡ ለሁሉ ነገር ደግሞ ጊዜ አለው፡፡ የጊዜን ትርጉም ማወቅ አስፈላጊና ግዴታም ነው፡፡ መጽሐፉም እኮ እንዲህ ይላል፡-

ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፤ ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፤ ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤ ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው።መጽሐፈ (መክብብ፣ ምዕራፍ 3 ፣ 1-8)

ስለዚህ ሕወሓት እንዳረጀ አባላቱ ሊረዱና አቋማቸውን ሊያስተካክሉ ይገባቸዋል፡፡ በዱሮ በሬ እያረሱ ራሳቸውንም ሕዝብንም መቅኖ እንዳሳጡ መቅረት የለባቸውም፡፡ ይህ ወጣት ጠ/ሚኒስትር ደግሞ ይበልጥ የሚጠቅመው እነሱን መሆኑን መገንዘብ አለባቸው፡፡ አሁን ላይመስላቸው ይችላል – የዚህን ሰው በዚህን ወቅት ወደ ሥልጣን መውጣት ጠቀሜታውን የሚረዱ ሰዎች ግን የመለኮታዊ ጣልቃ-ገብነት ያህል በአወንታ ይቀበሉታል፡፡
ነገ በሚካሄደው ሕዝባዊ የድጋፍ ሠልፍም ይሁን ከዚያ በኋላ ሕወሓቶች በሀገርና በሕዝብ ላይ ምንም ዓይነት ሸርና ተንኮል ለመፈጸም ባይነሳሱ ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው በተለይ ለነሱ ለራሳቸው ይበጃቸዋል፡፡ “የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም” እንደሚባለው ሌሎቻችን ሁሉንም የክፋት ሥራቸውን ለምደነዋል፡፡ አዲስ ነገር የለም፡፡ በሚሠሩት እያንዳንዱ የክፋት ሥራ ይበልጥ የሚጎዱትና የመቃብር ጉድጓዳቸውን የሚያርቁት እነሱ ራሳቸው ናቸው፡፡ በእልህ ቤት አይገነባም፡፡ በጥላቻ ትርፍ አይገኝም፡፡
ነገ የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድን የለውጥ ጅማሮ ለመደገፍ በሚሊዮን የምንቆጠር የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች ወደ መስቀል አደባባይ እንደምንወጣ ይጠበቃል – ዝግጅቱም በደመቀ ሁኔታ እየተጧጧፈ ነው፡፡ ይህን ሠልፍ ለማደናቀፍና ጠ/ሚኒስትሩን ለማሳጣት ሕወሓት እንደሚሞክር ይገመታል፡፡ ይህን የሕወሓት የክፋት ተግባር መቋቋም ያለበት ሕዝቡ ራሱና ለሕዝብ የሚቆረቆሩ የፀጥታና የደኅንነት አባላት ናቸው፡፡ ለሕወሓት ሸር ምንም ዓይነት ቀዳዳ መክፈት አያስፈልግም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እየገደሉት ለነበሩት ጻፎችና ፈሪሣውያን ያዝንላቸው ነበር፡፡ ምሕረትም እንዲያገኙ “ጌታ ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እያለ ለአባቱ ይጸልይ ነበር፡፡ እነዚህ በኛ ስቃይና ሀዘን የሚደሰቱ ወንድሞቻችንም ጥሎባቸው አሁን ባሉበት አሣዛኝ ሁኔታ ውስጥ የተገኙት ወደው ሣይሆን በአንዳች ጽልመታዊ ኃይል ተገደው ቢሆን ነውና ለነሱም ልናዝንና ከክፋት መንገዳቸው እንዲወጡ ልንጸልይላቸው ይገባናል፡፡ ሕወሓቶች አለተቀናቃኝ ከያዙት የሀገር ሀብትና ሥልጣን እንደሚያቆራርጣቸው በማመን በከፍተኛ ደረጃ የሚፈሩትን ይህን የተጀመረ የለውጥ እንቅስቃሴ በቻሉት ሁሉ ማጨናገፍ ለነገ የሚሉት አይደለምና ደም ለማፋሰስ በሞላ አቅማቸው መራወጣቸው አይቀርም፤ ይህም ፍላጎትንና ጥቅምን ለማስከበር የሚደረግ ጥረት እንደመሆኑ ተፈጥሯዊ ነውና የማይጠበቅ አይደለም – ችግሩ የሚጓዙበት መንገድ ጠማማና እጅግ አሣፋሪም መሆኑ ነው፡፡ አሁንም ታዲያ ትልቁ ኃላፊነት የሚጠበቀው አእምሮውን ይጠቀማል ተብሎ ከሚታሰበው ከተገፊው ሕዝብ ነው – እነሱ በጥቅምና በጎሠኝነት ታውረው ከሰውነት ተራ ሣይወጡ አልቀሩምና በሚያደርጉት ዕኩይ ተግባር ዓለም ብታልፍ ደንታቸው አይደለም፡፡ ፍቅርንና መተሳሰብን ከሚሰብኩ መፈክሮችና አባባሎች ውጪ ጥላቻና ልዩነትን የሚሰብኩ መፈክሮችን ማስተጋባት ታጥቦ ጭቃ ነው – እነሱንም እንደመኮረጅና እንደመሆንም ነው፡፡ ይህ ደግሞ “ዋጮን ቢገለብጡት ያው ዋጮ ነው” እንደሚሉት ተረት ነው፡፡ የእልህና የጥላቻ መንገድ ለሌላ የእልህና የጥላቻ መንገድ ስለሚጋብዝ ብሶትንና በደልን ቻል አድርጎ ወደ ዕርቅና መቻቻል መንገድ መዞር አማራጭ የሌለው የሠላም መንገድ ነው፤ የሚያዋጣን ያ እና ያ ብቻ ነውና፡፡ ሌላውንማ እስኪያንገሸግሸን አየነው፡፡ Yinegal3@gmail.com

✱✱✱
1 በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ።
2 ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።
3 ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።
4 ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤
5 የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም፤
6 ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤
7 ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል።
8 ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል።
9 ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤
10 ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል።
11 ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ።
12 ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ።
13 እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።

የሐዋርያው የጳውሎስ መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ምዕራፍ 13፡ 1 – 13

ethiomedia

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *