የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት ለሁለት አስርት አመታት ገደማ በሁለቱ አገራት መካከል ሰፍኖ የቆየው ውጥረት ማብቂያ እንደሆነ የጠቅላይ ምኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ፍጹም አረጋ በትዊተር ገፃቸው ጽፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የኤርትራ ልዑካን ቡድን ጉብኝት ለተሻለ መፃኢ ጊዜ መሠረት እንደሚጥል ተስፋ እንዳላቸው አቶ ፍጹም አረጋ ገልጸዋል።

በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልሕና የፕሬዝዳንቱ አማካሪ በሆኑት የማነ ገብረ አብ የሚመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገቡ በቅርቡ ጥቅላይ ሚኒስትር አብይና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እንደሚገናኙ ተሰማ።

ለልኡካን ቡድኑ በቦሌ አየር ማረፊያ በመገኘት አቀባበል ያደረጉላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ፣ ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ፣ የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት አቶ አህመድ ሽዴና አቶ አርከበ ዕቁባይ ናቸው።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ባካሄደው ስብሰባ የኢትዮ- ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በመገምገም፥ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ለመተግበር መስማማቷን መግለጹ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረቡም የሚታወስ ነው።

የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ዑስማን ሳልሕ

ወደ ትጥቅ ትግሉ ከመቀላቀላቸው በፊት መምህር የነበሩት የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ዑስማን ሳልሕ በ 1978 ወደ ትግል ሜዳ ከወጡም በኋላም በመምህርነት አገልግለዋል።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተለየች በኋላ እአአ ከ1993-2007 የትምህርት ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። ከ2007 እስከ ዛሬ ድረስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙ ናቸው።

ለ20 ዓመታት ያክል ተቋርጦ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሃላፊነት የሚመሩትም እኝህ ሚኒስትር ናቸው።

የፕሬዚደንቱ አማካሪ አቶ የማነ ገብረኣብ

የፕሬዚደንቱ አማካሪና የፖለቲካ ፓርቲው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑት የማነ ገብረኣብ በ1977 ከአሜሪካ ነበር የትጥቅ ትግሉን የተቀላቀሉት። በትግሉ ግዜ በዜና ክፍል፣ በ ‘ድምፂ ሃፋሽ’ ሬድዮ ጋዜጠኛም ሆነው አገልግለዋል። ከኤርትራ ነፃነት በኋላም በተለያዩ ሓላፊነቶች ላይ አገልግለዋል። ከ 1994 ጀምሮ እስካ አሁን ድረስ የድርጅታቸው የፖለቲካዊ ጉዳዮች ሓላፊ ናቸው።

2017 ላይ አቶ ዑስማን ሳልሕ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ አቶ የማነ ገብረኣብ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሚያደርጓቸው ዲፕሎማሲያዊ ጉዞዎች ላይ አብረው ይጓዛሉ።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ቁልፍ ክንውኖች- የጊዜ ሰሌዳ

ግንቦት 16፣ 1985 ኤርትራ ከኢትዮጵያ ነጻ መውጣቷን በሕዝበ ውሳኔ አሳወቀች

ሚያዚያ 28፣ 1990- ደም አፋሳሹ የድንበር ጦርነት ተጀመረ።

ከ1990-1992- ሁለቱ አገራት ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት አደረጉ። ከሰባ ሺ በላይ ዜጎች ሞቱ።

ሰኔ፣ 11 1992- ሁለቱ አገራት በጠላትነት ላለመተያየት ሰነድ ፈረሙ

ታኅሳስ 03/1993 የአልጀርስ የሰላም ስምምነት ተፈረመ

ሚያዚያ 05/1994 የኢትዮ-የኤርትራ ድንበር ኮሚሽን ይግባኝ የሌለውን ውሳኔ አሳወቀ።

ጥር፣ 1994- የኤርትራ ብሔራዊ ሸንጎ ማንኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ ምዝገባ እንዳይካሄድ አገደ።

ኅዳር 1998 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁለቱ አገራት ወደ ሰላም ካልተመለሱ ማዕቀብ እንደሚጥል አሳወቀ።

ኅዳር 1998- ኤርትራ አሜሪካዊያንን አውሮፓዊያንና ራሻዊያን ያሉበትን የሰላም አስከባሪ ከድንበር አባረረች።

መጋቢት 1999-ኤርትራ ራሷን ከምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አገለለች።

ኅዳር 2002-የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤርትራ በሶማሊያ አክራሪዎችን ታስታጥቃለች በሚል ማዕቀበል ጣለ።

መጋቢት 2003- ኢትዮጵያ ለኢሳያስ መንግስት ተቀናቃኞች እርዳታ እንደምትሰጥ አሳወቀች

ታኅሳስ 2004- ኢትዯጵያ ኤርትራ አፋር ድንበር ላይ ቱሪስቶችን ገድላለች ስትል ከሰሰች

የካቲት፣ 2004 ኤርትራ የኢትዮጵያ አማጽዮችን ለማሰልጠን ኤርትራ ትጠቀምበታለች የሚባለውንና በደቡብ ምዕራብ ኤርትራ የሚገኘውን ወታደራዊ ካምፕ አጠቃች።

ነሐሴ፣ 2004- መለስ ዜናዊ ከሃያ ሁለት ዓመታት የሥልጣን ቆይታ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ታኅሳስ፣ 2005- የተቃዋሚ ወታደሮች በአስመራ የሚገኘውን የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ሕንፃ ተቆጣጠሩ።

ግንቦት 2007- የኤርትራ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽማል ሲል የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት ወቀሰ።

ሰኔ፣ 2008- ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማሪያም ደሳለኝ ኤርትራ የምታደርገውን የወታደራዊ ቆስቋሽነት እንድታስታግስ፥ ይህ ካልሆነ ግን ወታደራዊ ጥቃት እንደሚሰነዘሩ አሳሰቡ።

ነሐሴ፣ 2008- ኢትዮጵያና ኤርትራ በፆረና ግምባር ጦርነት አደረጉ፤ አንድ መቶ ወታደሮች ተገደሉ።

ግንቦት፣ 2009- የኳታር ሰላም ጠባቂዎች ከድንበር አካባቢ መውጣታቸውን ተከትሎ በጅቡቲና ኤርትራ መሐል ውጥረት እንዲነግስ ሆነ።

መስከረም፣ 2010- የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሊህ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ከጦርነቱ መልስ ለመጀመርያ ጊዜ አግኝተው ተወያዩ።

መጋቢት 24፣ 2010- ዐብይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሐላ ፈጸሙ።

በተመሳሳይ ዜና የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአንድ መካከለኛ አገር ፣ አለያም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከተሰማሙ እሳቸው ኤርትራ መመሄድ እንደሚገናኙና ህዝብ በጉጉት የሚጠብቀውን የኢኮኖሚ ጉዳዮች ያካተተ ውይይትና የስምምነት መነሻ ላይ እንደሚደርሱ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ጠቁመዋል።

ዜናው ከቢቢሲና ፋና የተጠናቀረ ነው
ፎቶ ፋና
 
 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *