የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ፣ አቋሙ የክልላቸው መሆኑንና ባለፈው ቅዳሜ የተሞከረውን ግድያ አጥብቀው እንደሚኮንኑ አስታወቁ። ድርጊቱን የፈጸሙት ለውጡ ያልተዋጠላቸው ወገኖች እንደሚሆኑ በመግለጽ ድርጊቱ ተቀባይነት የሌለውና ለውጡም የሚቀጥል መሆኑንን አስታወቀዋል።

አቶ ደሴ በሆስፒታል ተገኝተው በቦንብ የቆሰሉትን ወገኖች ከጎበኙ በሁዋላ በተሌቪዥን እንደተናገሩት እሳቸው የሚመሩት የክልሉ መንግስት በተፈጸመው ድርጊት ማዘኑንን ተናግረዋል። ከለውጥ ሂደቱ ጎን መሆናቸውንም የ” መንግስቴ” አቋም ሲሉ ይፋ አድርገዋል። የአቶ ደሴ ንግግር የደቡብ ክልል አሁን ካለው አዲሱ የለውጥ ሃይል ጋር ሙሉ በሙሉ መቀላቀሉን አመልካች እንደሆነ አሳይቷል።

አቶ ሽፈራው ሽጉጤና አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ በሕዝብ ግፊትና ጥያቄ በግምገማ ራሳቸውን ከሃላፊነት ማግለላቸውን ተከትሎ በክልሉ በየደረጃው የማስተካከያ ለውጥ እንደሚካሄድ እየተገለጸ ባለበት በአሁኑ ሰዓት፣ ሪፖርተር ምንጭ ሳይጠቅስ በደፈናው ” ታወቀ ” ሲል አቶ ደሴ እንደሚነሱና አቶ ሲራጅ ፈርጌሳን ተክተው የደህዴን ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ የክልሉ መሪ እንደሚሆኑ ዘግቧል።

በተመሳሳይ ዜና የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል  በመስቀል አደባባይ የቦምብ ፍንዳታ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመገኘት ነው ጠይቀዋቸዋል። 

በተመሳሳይ በዛሬው እለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚልና የምክር ቤቱ አባላት በቅዱስ ጴጥሮስና በየካቲት 12 ሆስፒታሎች በመገኘት በመስቀል አደባባይ የቦምብ ፍንዳታ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ጎብኝተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የክልሉ የካቢኔ አባላት በመስቀል አደባባዩ የቦምብ ፍንዳታ ጎዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በሚኒልክ ሆስፒታል በመገኘት ጠይቀዋቸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮችም በተመሳሳይ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኝተው የህክምና ክትትል ላይ ያሉትን ተጎጂዎች በመጎኝት ደም መለገሳቸው ታውቋል።

በተጨማሪም የሀይማኖት አባቶች እና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም በመስቀል አደባባይ የቦምብ ፍንዳታ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ተጎጂዎችን ጎብኝተዋል። ድርጊቱንም ሁሉም ወገኖች አውግዘዋል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *