ተጠርጣሪዎቹ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ሰኞ ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ሲቀርቡ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳን ጨምሮ አሥር የኮሚሽኑ አባላትና ‹‹ለድጋፍ ነው የወጣነው›› ያሉ 16 ግለሰቦች ተካተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረቦች ኮማንደር ገብረ ኪዳን፣ ኮማንደር ገብረ ሥላሴ፣ ኮማንደር ግርማዬ በርሄ፣ ኮማንደር አንተነህ፣ ምክትል ኮማንደር አባቡ ዳምጤ፣ ኮማንደር ገመቹ ታፈረ፣ ምክትል ኮማንደር አብዲሳ ባይሳ፣ ምክትል ኢንስፔክተር ነገሪ ፈይሳና ዋና ሳጅን ከድር ዓሊ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የምርመራ ቡድን ነው፡፡

ዲያቆን መሆኑን ለችሎት የገለጸውን አቶ በጽሃ ቦቸራንና የቤት ሠራተኛ መሆኗን የገለጸችው ወ/ሪት ሸጊቱ አዋሽን ጨምሮ 16 ግለሰቦችን ከቦምብ ፍንዳታው ጋር በተገናኘ እንደጠረጠራቸው ገልጾ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው ደግሞ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቡድን ነው፡፡

በሁለት የወንጀል ምርመራ መዝገብ ተካተው ፍርድ ቤት ስለቀረቡት 26 ተጠርጣሪዎች ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ እንዲያስረዳ ተጠይቆ እንደገለጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በተሾሙ አጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገቡትንና ያሳዩትን የአመራር ብቃትና ለውጥ ለመደገፍ፣ ሕዝቡ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ ተገኝቶ ነበር፡፡ ለድጋፍ ሰላማዊ ሠልፍ የሚወጣውን ሕዝብ ከማንኛውም ጉዳት ፖሊስ ጥበቃ እንዲያደርግ ከመንግሥት የሥራ አቅጣጫ የተሰጠ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪ የፖሊስ አባላት በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ባለመቻላቸው፣ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ ከ100 በላይ ሰዎች ጉዳት ሊደርስባቸው መቻሉን መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ባለመቻላቸውና ለደረሰው ጉዳትም ተጠያቂ በመሆናቸው፣ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቡድንም በ16 ተጠርጣሪዎች ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ ለድጋፍ በወጡ በግምት አራት ሚሊዮን በሚሆኑ ሰዎች ላይ ቦምብ በማፈንዳት ከ100 በላይ ሰዎች ላይ አደጋ አድርሰዋል በማለት እንደጠረጠራቸውና ቀሪ ምርመራ እንደሚቀረው በመግለጽ፣ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ መርማሪ ቡድኑ ባቀረበው የክስ አቤቱታ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ጠይቋቸው፣ ሁለት ጠበቆች ይዘው የቀረቡት ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው አቤቱታ ጥቅል ነው፡፡ የእያንዳንዱን ተጠርጣሪ የግል ተሳትፎና የወንጀሉን ባህሪ አልገለጸም ብለዋል፡፡ ‹‹ኃላፊነታቸውን አልተወጡም›› የሚለው አነጋገር ጅምላና ጥቅል መሆኑን፣ ከያዛቸው በኋላም ምን እንደሠራና ምን እንደቀረው አለማስረዳቱን፣ ምክትል ኮሚሽነሩ ምርመራው እንዳይቀጥል የሚያደናቅፉት አለመሆናቸውን፣ ለምርመራውም ተባባሪ እንደሆኑ፣ ሁሉም ነገር በመንግሥት ተቋም ውስጥ በመሆኑና የሚፈለገው ነገር እዚያው ስለሚገኝ እሳቸው በዋስ ቢወጡ የሚያሸሹትም ሆነ የሚያጠፉት ነገር ስለሌለ፣ በበቂ ዋስ ሆነው በውጭ እንዲከታተሉ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡

ሌሎቹም የፖሊስ ኮማንደሮች ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣታቸውን፣ እንደየደረጃቸው በተሰጣቸው መግለጫ መሠረት በሥራቸው ለሚገኙ ፖሊስ አባላት በቂ መግለጫ ሰጥተው፣ ከንጋቱ 10፡30 ሰዓት ጀምሮ ሠልፉ እስከሚበተን ድረስ ግዳጃቸውን መወጣታቸውን አስረድተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ስምንት፣ ሌሎቹም ከሦስት እስከ አራት የሚደርሱ ቤተሰቦቸውን የሚያስተዳድሩት እነሱ መሆናቸውን ጠቁመው፣ እነሱ ለእስር የሚዳረጉ ከሆነ ቤተሰቦቻቸው በቤት ኪራይና ችግርና በቀለብ ችግር ወደ ጎዳና ሊወጡ ስለሚችሉ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

ሌሎች 16 ተጠርጣሪዎችም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ዲያቆን መሆኑንና አስቀድሶ ሲመለስ ሰላማዊ ሠልፉን ተቀላቅሎ በመጨፈር ላይ እያለ መያዙን፣ ሌላው ደግሞ ከኤግዚቢሽን አካባቢ ተሰቅሎ የነበረ ፊኛ አውርዶ በእጁ ይዞ እየጨፈረ ሲሄድ መንገድ ላይ ፊኛው በመፈንዳቱ መያዙን፣ አንዱ ደግሞ ዝም ብሎ ከመሀል ያለ ምክንያት መያዙን፣ ቦምብ በፈነዳበት ቦታ ላይ የተገኘን ሸራ፣ ቦርሳና ሹራብ ሊያቃጥሉ ሲሉ ‹‹ለምን ታቀጥላላችሁ? ለማስረጃ ይሆናል ለፖሊስ ይሰጥ፤›› ስትል ተይዛ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዷን፣ በማያውቁትና ባልሠሩት ሥራ ዝም ብለው የታሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከቡራዩ፣ ከአዳማ፣ ከሱሉልታና ከአዲስ አበባ ከተለያዩ ሥፍራዎች የመጡ መሆናቸውን አስረድተው፣ የተወሰኑት በነፃ እንዲሰናበቱ ቀሪዎቹ ደግሞ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድኑን የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል፡፡ የፖሊስ ኃላፊዎቹን በሚመለከት፣ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል አልተወጡም የሚለውን ገና በምርመራ እንደሚያረጋግጥ፣ የምስክሮችን ቃል ስላልተቀበለና ምስክሮቹ የእነሱ የበታች ሠራተኞች በመሆናቸው ሊያስፈራሯቸው ስለሚችሉ ዋስትናው ውድቅ ተደርጎ የተጠየቀው 14 ቀናት ጊዜ እንዲፈቀድላቸው በድጋሚ ጠይቋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም መርማሪ ቡድንም 16ቱ ተጠርጣሪዎች ላቀረቡት የዋስትና ጥያቄ የተቃውሞ ምክንያቱን አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ ላይ ተሳታፊ እንደነበሩ ጥቆማ ደርሶት እንደያዛቸው ጠቁሞ፣ የተሳትፎ ዓይነቱን አጣርቶና የምስክሮችን ቃል ተቀብሎ ስላልጨረሰ ዋስትናውን እንደሚቃወም ገልጿል፡፡ በምርመራው ሒደትም ውሳኔ እየሰጠ እንደሚሄድ ገልጾ፣ የጠየቀው 14 ቀናት እንዲፈቀድለት በድጋሚ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ተጠርጣሪዎቹ የተያዙበት ጊዜ አጭር ቀን በመሆኑና ፖሊስ በዚህ ጊዜ ውስጥ ምርመራውን አጠናቋል ተብሎ ስለማይገመት፣ የተጠየቀውን 14 ቀናት መፍቀዱን በመግለጽ የዋስትናውን ጥያቄ ውደቅ አድርጎታል፡፡

ፖሊስ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ ያለውን የወንጀል ተሳትፎ ለየብቻው ዘርዝሮ ከእነ መዝገቡ ለሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ታምሩ ጽጌ ሪፖርተር

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *