ምንም እንኳን ፈጣንና ተከታታይ እድገት እየተመዘገበ ቢሆንም፣ ዛሬም ድረስ ግብርና መር የሆነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚፈለገውን ውጤት ያመጣ ዘንድ የግብርናው ትራንስፎርሜሽን እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ የግብርና ትራንስፎርሜሽን እውን እንዲሆን ደግሞ የግብርና ሜካናይዜሽን እጅጉን ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት ላለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ሲተገበር ቆይቷል፡፡


ለመሆኑ የትግበራው ሂደት ምን ይመስላል፣ በሂደቱ የነበሩ ችግሮችና የታዩ ለውጦች እንዴት ይገለጻሉ፣ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣስ በቀጣይ ምን መሰራት ይኖርበታል፤ በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ በግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የግብርና ሜካናይዜሽን ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ሃብቴ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ለንባብ በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ 

የግብርና ሜካናይዜሽን
የግብርና ሜካናይዜሽን በርካታ ነገሮችን የሚይዝ አንድ ትልቅ የአሰራር ሥርዓት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በሰብል ልማት ውስጥ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ መዝራትን፣ መንከባከብን፣ ማጨድን፣ መውቃትን፣ ማከማቸትን ጨምሮ መጓጓዝንና እስከ መለስተኛ ማቀነባበር ድረስ የሚዘልቅ ስራን ይመለከታል፡፡ በመስኖ ረገድ፣ የመስኖ ልማት መሳሪያዎችን ከመለየትና ከመፈተሽ ጀምሮ የሚገለጽ ሲሆን፤ ከእንስሳት ልማት ጋር ሲታይ ደግሞ የእንስሳት መኖና መጠለያን ከማዘጋጀት ጀምሮ የእንስሳት ውጤቶችን እስከከማቀነባበር ያሉ ተግባራትን የሚመለከት ነው፡፡
ስለዚህ የግብርና ሜካናይዜሽን አቅርቦትን ይመለከታል፤ አጠቃቀምን ይመለከታል፤ በአጠቃቀም ሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ እንደ ጥገና አይነት ነገሮችንም የሚመለከትና በውስጡም ከፍተኛ የስራ እድል የሚፈጥር፤ ስራውን ለመስራትም የተለየ ክህሎት የሚጠይቅ ነው፡፡ በግልም ሆነ በሽርክና የማምረት፣ የማከፋፈል፣ ተጠቃሚዎችም አገልግሎቱን በኪራይ የሚያገኙበት፤ አገልግሎት ሰጪዎችም የተሰማሩበት ዘርፍ በዚህ ውስጥ የተካተተ ነው፡፡ 
ለግብርናው ትራንስፎርሜሽን አጋዥ እንዲሆን
በአገሪቱ እየተመዘገቡ ባሉ ለውጦች ውስጥ ግብርናው ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ የኮንስትራክሽን፣ የአገልግሎት፣ የጤናው፣ ወዘተ ዘርፎች ከግብርናው ባገኙት ጥሪት ወደፊት እየተራመዱ ነው፡፡ በዚህም ግብርናው ኢኮኖሚውን ትራንስፎርም ለማድረግ እድል እየሰጠ ሲሆን፤ ይህ ግን ሊቀጥል የሚችለው ግብርናው በራሱ ውስጥ ትራንስፎርም ሲያደርግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በግብርናው ውስጥ ምንም አይነት መዋቅራዊ ለውጥ ባልመጣበት፤ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ በተለምዶ በሆነበት፣ በገጠር በግብርና ስራ ላይ የተሰማራው ህዝብ እየተማረና ወጣቱም በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ እየገባ፣ አሁንም ድረስ በቀድሞው መንገድ እየሰሩ ያሉ አርሶ አደሮች እድሜያቸ ውም እየገፋ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነው አገሪቱ ያለችው፡፡
ከዚህ በኋላ ግን ግብርናው በራሱ ውስጥ ለውጥ ካላመጣና ራሱን ትራንስፎርም ካላደረገ አሁን ያለውን የአገሪቱን ፍላጎት ለማሳካት ይቸገራል፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ በቀን በብዙ ሺህ የሚቆጠር የግብርና ምርት በግብዓትነት የሚጠቀሙ አግሮ ኢንዱስትሪዎች እየተቋቋሙ ነው፤ ሆኖም ግብርናው እነዚህ የአግሮ ኢንዱስትሪዎችን ሊመግብ በሚችልበት ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ በመሆኑም ግብርናው ራሱን ትራንስፎርም ካደረገ፣ ኢኮኖሚውም የበለጠ ትራንስፎርም ያደርጋል፤ ግብርናው ግን ባለበት ከቆመ፣ ተሸክሞ እዚህ ያደረሳቸው ዘርፎች ሁሉ ወደኋላ የሚመለሱበትና የሚወድቁበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

Related image
አሁን ባለው ሁኔታም ግብርናው መዋቅራዊ ለውጥ ካላደረገ አቅሙን እያሟጠጠ ይገኛል፡፡ ድሮ በሚሰራው ባህላዊ ግብርናም ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ መሸጋገር አይቻልም፡፡ ይሄን መሰረት በማድረግም የግብርና ሜካናይዜሽን ስትራቴጂ ወጥቶ እየተተገበረ ሲሆን፤ ከምርምር ጀምሮ በአጠቃቀም፣ በጥገናና በሽያጭና ከዚህ በኋላ ባሉ አገልግሎቶች ዙሪያ እየተሰራ ነው፡፡ ይህም ግብርናው ራሱን ትራንስፎርም እንዲያደርግ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውም ቀጣይነት እንዲኖረው የጎላ ድርሻ እንዲያበረክት የሚያስችለው ነው፡፡
የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን በነፍስ ወከፍ ወይም በተደራጁ ማህበር መጠቀም የሚያስችል ቢሆንም፤ አገልግሎቱን ገዝቶ መጠቀሙ አዋጪ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ አርሶ አደር አንድ ትራክተር ቢገዛና ያለችው መሬት ሁለት ሄክታር ብትሆን፣ ትራክተሩ መሬቷን በአንድ ሰዓት ተኩል ውስጥ አርሶ ይጨርሳል፡፡ እናም ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላ የዚህ አርሶ አደር ትራክተር ምንም ስራ አይኖረውም፡፡ ይህ ከሚሆን አርሶ አደሩ በሄክታር አገልግሎቱን ቢገዛ የበለጠ ያዋጣዋል፤ በዚህ ስራ ላይ ለሚሰማሩም ሰፊ የስራ እድል እየፈጠረ ይሄዳል፡፡
በመሆኑም ይሄን መሰረት በማድረግ አገልግሎት ሰጪዎች በስፋት እንዲሳተፉና ከማሳ ዝግጅት እስከ አጨዳና ውቂያ ባሉ የተለያዩ ደረጃዎች አገልግሎት ሰጪዎች በኪራይ አገልግሎቱን እንዲሰጡ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም የመንግስታዊ ድርጅትም ያለ ሲሆን፤ በአብዛኛው ግን የግል ባለሀብቶች ናቸው፡፡ የተደራጁ ወጣቶችም አሉ፡፡ የህብረት ስራ ዩኒየኖችም አሁን ከሚሰጡት የግብይትና ማዳበሪያ ከማቅረብ ውጪ ትራክተርና ኮምፓይነሮችን እየገዙ ለአባሎቻቸው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡
ፈታኝ ሁኔታዎችና የታዩ ውጤቶች
የግብርና ሜካናይዜሽንን ከመተግበር አኳያ በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ቴክኖሎጂውን የማግኘት ሁኔታ ሲሆን፤ በአገር ውስጥ የሚመረቱ የተወሰኑ ቴክኖሎጂዎች ቢኖሩም የእነሱ አካሎች ደግሞ ከውጭ ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በቆሎ መፈልፈያ፣ ስንዴና ገብስ መውቂያ አገር ውስጥ ቢመረት፤ ሞተሩ ግን ከውጭ ነው የሚመጣው፡፡ በተመሳሳይ ትራክተር ሙሉ አካሉ ተከፋፍሎ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ነው የሚገጣጠመው፡፡ እነዚህ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ደግሞ የውጭ ምንዛሬና አቅም ይፈልጋሉ፡፡ ሆኖም ከፋይናንስ ብድር ተደራሽነት አኳያ ለሌሎች ዘርፎች የተሰጠውን ትኩረት ያክል ለግብርና ሜካናይዜሽን አልተሰጠም፡፡ የብድር አቅርቦቱም ሆነ የውጭ ምንዛሬ የማግኘት ሂደቱም አለ በማይባልበት ደረጃ ነው ያለው፡፡
ለአብነት፣ በቅርቡ የማሽነሪ ሊዝ ፋይናንስ ተጀምሯል፡፡ ሲሰጥ የነበረው ግን ማኑፋክቸሪንክ፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች ሲሆን፤ ለግብርና ዘርፍ ግን ፈጽሞ አይሰጥም ነበር፡፡ በዚህ ዓመት በቅርብ ጊዜ ነው የተጀመረው፡፡ አጀማመሩም ቢሆን ቀደም ብሎ በነበረው ልምድ ውስጥ ተውጦ ያለ ስለሆነ፤ እስካሁን ድረስ ለዚህ ዘርፍ ተጨባጭ የሆነ እንቅስቃሴ እያደረገ አይደለም፡፡ ማሽኖችና መሳሪያዎችን ለመጠቀምም ጥሩ ክህሎትና እውቀት ያላቸውን ኦፕሬተሮች ማዘጋጀትና ማሰልጠን የሚችል መንግስታዊ ድርጅት አለመኖር ተደማሪ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡
እንዲህ ሆኖ ምን ተሰራ ሲባል፤ ቁጥሮችን ማስቀመጥ የሚቻልበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ ያህል፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ሲጀመር ወደ 200 ሺ ያህል ተጠቃሚዎች ነበሩ፡፡ አሁን ግን በተያዩ አገልግሎቶች ወደ ሦስት ሚሊዮን ገደማ የግብርና ሜካናይዜሽን ተጠቃሚዎች አሉ፡፡ ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥም ጥሩ ስራ ተሰርቶ መሰረት ተጥሏል ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ በዚህ ስራ ውስጥ እማ ወራዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፤ የተደራጁ ወጣቶችም በግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ተሰማርተው በተለያየ መልኩ እየተጠቀሙ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ዘርፉ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ያለና ጥሩ ጅምር የታየበት ነው፡፡
ቀጣይ አቅጣጫዎች
ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ጉዞ ውስጥ እነዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች በደንብ ተፈትሸዋል፡፡ በዙሪያቸው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተደረጉ ሙከራዎችም ያመጧቸው ለውጦች ታይተዋል፡፡ ችግሮቹም የንዑስ ዘርፉን ጉዞ ሰንገው እንደያዙ መረዳት ተችሏል፡፡ በመሆኑም ይሄንን መሰረት ያደረገ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል፡፡ ለአብነት፣ አሁን ላይ በአገሪቱ ከ60 ሺ በላይ የልማት ሰራተኞች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ግን አንድም የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኒሺያን የለም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ይህ ስልጠና አልነበረም፡፡ አሁን ግን ስልጠናው ተጀምሮ 200 (100 አንደኛ ዓመት፣ 100 ሁለተኛ ዓመት) ኦፕሬተሮች ስልጠናውን በብቸኝነት በሚሰጠው አላጌ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ውስጥ በደረጃ አራት በመሰልጠን ላይ ይገኛሉ፡፡ በቀጣይም ስልጠናውን በአጋርፋና በሌሎች ኮሌጆች ለመስጠት ታስቧል፡፡
የመሳሪያ ሊዝ አቅርቦቱን በተመለከተም የሌሎች አገሮችን ልምድ በማየት መሳሪያዎቹ በሊዝ ፋይናንስ በስፋት እንዲቀርቡ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ከአጋር ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆንም የማሽነሪ ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲገኝም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ተስማሚ ፕሮጀክቶች ተሞክረው ውጤት ያመጡት በአገር ውስጥ እንዲመረቱ የተጀመረው እንቅስቃሴም በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በቆላማ አካባቢዎችም ሜካናይዜሽንን በቀላሉ ማስፋት እንዲቻል በቂ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በእነዚህና መሰል እርምጃዎችም የዘርፉን ማነቆ እየፈቱ መሄድ ይቻላል፡፡
መልዕክት
በአገሪቱ ካሉ ኮምባይነሮች አብዛኞቹ በግል ባለሀብቱ የተያዙ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹ ባሌና አርሲ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ እና የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንኮች ለግብርና ሜካናይዜሽን ድጋፍ ስለሚሰጡ ነው፡፡ ልማት ባንክ በጣም በተወሰነ ደረጃ ይሰጥ እንደሁ እንጂ፣ ንግድ ባንክን ጨምሮ ሌሎቹ የፋይናንስ ድርጅቶች አይሰጡም፡፡ በመሆኑም አሁን የሚደግፏቸው ዘርፎች ግብርናው ባመነጨው ጥሪት በተገኘ ፋይናንስ መሆኑን በመረዳትና ግብርናው ከወደቀ እነርሱም ተያይዘው የሚሄዱበት ሁኔታ መኖሩን ተገንዝበው የፋይናንስ ድርጅቶች በዘርፉ ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በተወሰኑ ክልሎች ብቻ ያለው የግብርና ሜካናይዜሽን አደረጃጀት በየክልሉ እንዲፈጠር፤ ሁሉም የህብረት ስራ ዩኒዬኖችም በዘርፉ እንዲሰማሩ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መልኩ የግብርና ሜካናይዜሽኑን ውጤታማ በማድረግ የኢኮኖሚውን ቀጣይነት ማረጋገጥ ይገባል፡፡

“አሁን አየ አይኔ” የሚል ርዕስ በመስጠት አንባቢ ከአዲስ ዘመን ቀድተው የላኩት

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *