አገራችን በአዲስ የፖለቲካ መንፈስ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ለዚህም በተለይ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በአገሪቱ የተለያዩ አጀንዳዎችን መሰረት በማድረግ ላለፉት ሁለት ዓመታት የዘለቀውን ተቃውሞ ተከትሎ እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎችን በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

ስር እየሰደደ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግርና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት፣ ሙስና እንዲሁም ሥራ አጥነት ህዝቡ ለመንግሥት ጥያቄዎችን እንዲሰነዝር ማድረጋቸውን ተከትሎ መንግሥት እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎችና ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች በፖለቲካው መስክ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርግ ሁኔታ እንዲፈጠር እያደረጉ ናቸው፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ቀደም ሲል የጀመረው ጥረት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ጉልህ ሚና እንዳለው ታምኖበታል፡፡ በድርድሩ በተለይ ሁሉም ህዝብ ሊደመጥ የሚችልበትን ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ላይም ተደርሷል፡፡ ይህም እንደ አንድ ለውጥ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡
ይህ ኢህአዴግ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የጀመረው ድርድር በተያዘው ዓመት ደግሞ በእስር ላይ የሚገኙ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላትና ሌሎችን በመልቀቅ፣ እንዲሁም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የሚገኙትን ደግሞ ክሳቸው እየተቋረጠ እንዲለቀቁ በማድረግ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋቱ ሥራ በእነዚህ እርምጃዎች ብቻ ያቆመ አይደለም፡፡በውጭ አገር የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ መታገል እንደሚችሉ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በውጭ ለሚገኙ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ፓርቲዎች ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ ይህን ተከትሎም የቀድሞው ኦነግ የአሁኑ ኦዴግ መስራቾች ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል፡፡
ኢሳት እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ እንዲሁም የግንቦት ሰባት አመራሮች በሌሉበት የተመሰረተባቸው ክስ እንዲቋረጥ ሆኗል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም አዳዲስ ፓርቲዎች በሚመለከተው አካል እየተመዘገቡ ፈቃድ እየተሰጣቸው ይገኛሉ፡፡
መንግሥት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ተቃውሞችን የጎሪጥ ከማየት በመውጣት ጠያቂ ትወልድ እየተፈጠረ መሆኑን ተከትሎ የተቀሰቀሱ ናቸው በማለት በተቃውሞዎቹ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ተንቀሳቅሷል፡፡ ኢህአዴግ በጥልቅ ተሀድሶ ለበርካታ ቀናት የመከረባቸው ጉዳዮች በኋላም ያሳለፋቸው ውሳኔዎችና ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች አሁን በአገሪቱ ለታየው ለውጥ መሰረት ሆነዋል፡፡
በአገሪቱ የተጠፈሩ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የመፍትሄው አካል ለመሆን እንደሚፈልጉ በማስታወቅ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን በገንዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቻውም በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የተካሄደበት መሆኑም ሌላው የፖለቲካው ድል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ከሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩ ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሰላም ትልቁን ዋጋ በመስጠት የመጀመሪያ የአገር ውስጥ ጉብኝታቸውን በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ስፍራዎች ላይ ከወሰን ጋር በተያያዘ በተቀሰቀሰ በዚህ ግጭት በርካታ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ለሞትና ለአካል መጉደል. ተዳርገዋል፤ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በጉብኝታቸውም ለህዝቡ ንግግር ከማድረግ በተጨማሪ ከህዝብ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡ ተመሳሳይ ጉብኝቶችና ውይይቶች በተለያዩ ክልሎች ተደርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የየክልሉንና አካባቢውን ታሪክ እየጠቀሱ ህዝቡ እንዲፋቀር እንዲተሳሰብ ለውጡን እንዲያስቀጥል የሚያስችል ንግግሮችን በህዝብ ዘንድ አድናቆትን ባተረፈው አንደበታቸው አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚበጃቸው አንድ ሆኖ መጓዝ እንደሆነ አስረድተዋል። ከመካሰስ ይልቅ የይቅርታና ምህረት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡ 
መንግሥት በዚህ ዓመት ብቻ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ብዙ እርምጃ ወደፊት እንዲጓዝ የሚያስችሉ በርካታ እርምጃዎችን ለመውሰዱ የተጠቀሱት በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ህዝቡ በዚህ የመንግሥት እርምጃ ረክቷል፡፡ ይህንንም በተለያዩ መድረኮች እያረጋገጠ ይገኛል፡፡ ሁሉም የተገኘውን ድል እያጣጣመ ቀጣይ ተጨባጭ እርምጃዎችን እየጠበቀ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ከሆነባቸው ወቅቶች መካከል አንዱ ይህ ወቅት ነው ብሎ መናገር የሚያስችል መግባባት ተፈጥሯል ለማለትም ያስደፍራል፡፡ 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን የመጡበት ወቅት በርካታ ፈተናዎች ያሉበትም ነው፡፡ በጥቅምት ወር የተካሄደውን የዶላር ምንዛሬ ማሻሻያ ተከትሎ በሸቀጦች ዋጋ ላይ የተደረገ ጭማሪ ሲያንገበግበው የቆየው ገበያ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ ይበልጥ መንገብገቡን ቀጥሏል፡፡ አጋጣሚው ወትሮውንም ምክንያት እየጠበቁ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ለለመዱ ነጋዴዎች ሰርግና ምላሽ እንዲሆንላቸው አድርጓል፡፡ 
እነዚህ ህገወጥ ነጋዴዎች የምንዛሬ ለውጡ እንደተደረገ መጋዘን ያሉ ሸቀጦችንና የመሳሉትን በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር በፈለጉት ዋጋ ሲሸጡ ቆይተዋል፡፡መንግሥት በእነዚህ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ የወሰደ ቢሆንም፣ እርምጃው ከፈጠሩት ቀውስ ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ ገበያውን መቆጣጠራቸውን አላስተዋቸውም፡፡
በዚህ የተነሳም ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ዋጋ ያልጨመረ ሸቀጥ የለም፡፡ መጀመሪያ በምንዛሬ ለውጡ ሰበብ፣ ቀጥሎ ደግሞ የምንዛሬ ለውጡ በሚያዘው መሰረት፣ ከዚያም የውጭ ምንዛሬ እጥረት በፈጠረው ቀውስ ሳቢያ ዋጋ ሲጭምር ቆይቷል፡፡
የሚገርመው ደግሞ ምንም አይነት ከውጭ የሚመጣ ግብአት የማይጠቀሙ የግብርና ምርቶች ሳይቀሩ ዋጋ አልተጨመረባቸውም ቢባልም ዋጋ ግን ጨምረዋል፡፡ ችግሩ እየባሰ መጥቷል፡፡ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ዓመቱ የግብርና ምርት በከፍተኛ ሁኔታ የተሰበሰበበት ባይሆን ኖር ከፍተኛ ችግር በዚህች አገር ይከሰት እንደነበር መገመት አይከብድም፡፡
በአሁኑ ወቅት አንድ ራስ የበቆሎ እሽት በአዲስ አበባ የተለያዩ መንደሮች አምስት ብር ይሸጣል፡፡ እንቁላል የማይቀመስ ሆኗል፡፡ ወተትን ምን እንዳጠፈው አይታወቅም፡፡ መንግሥት የዳቦ ዱቁት በወቅቱ እያቀረበ አይደለም፡፡ በዚህ የተነሳ ወትሮም በግራሙ አጠያያቂ የሆነው ዳቦ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገበት እየተሸጠ ነው፡፡
የኑሮ ውድነቱ መነሻ ተፈጥሮዋዊም ሰው ሰራሽም ነው፡፡ የምንዛሬ ለውጡ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ተፈጥሮዋዊ ምክንያቶች ቢሆኑም በአመለኛ ህገወጥ ነጋዴዎች የተዘወረ እንደመሆኑ ችግሩ ይበልጥ እንዲገን ተደርጓል፡፡
የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ከእንቅስቃሴ ገትቶታል፡፡ ይህ ሲባል ግንባታ እየተካሄደ አይደለም በማለት አያበቃም፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ሠራተኛ እንደመያዙ ዘርፉ ሥራ አቆመ ማለት ጦሙን የሚያድር በርካታ ዜጋ ተፈጥሯል ማለትም ነው፡፡
መንግሥት በከተሞች የሴፍቲኔት መርሀ ግብር ከዓመት በፊት ባይጀምር ኖሮ ችግሩ ምን ያህል ግዙፍ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡
ይህ ሁሉ የሚያመለክተው በፖለቲካው ዘርፍ ጥሩ ጥሩ ነገሮች ቢታዩም በኢኮኖሚው መስክ በተፈጠረ ችግር ሳቢያ ግን ህዝብ ለኑሮ ውድነት ክፉኛ መጋለጡን ነው፡፡ ተፈጥሯዊ ምክንያቶቹን ህዝብም ተገንዝቦ ቀን እስኪያልፍ ብሎ ችግሩን ሊሸከመው ይችሏል፡፡ 
አሁን መሰረታዊ ችግር እየሆነ ያለው የመንግሥትን እርምጃ እየደገፉ ፣ በሌላ በኩል እርምጃውን የሚሸረሽር ህገወጥ ተግባር በህገወጥ ነጋዴዎች እየተፈጸመ ያለበት ሁኔታ ነው፡፡ ነጋዴ ማተረፍ አለበት፤ ለፅድቅ እንደማይሰራ ይታወቃል፡፡ ይሁንና መንግሥት የህዝብን ጥያቂ ለመመለስ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት እነሱም እርምጃውን እያደነቁ ድጋፍም እንደሚያደርጉ እያረጋገጡ ባለበት ሁኔታ የተለያዩ ምክንያቶችን እያደረጉ የዋጋ መናር የሚያስከትሉ ህገወጥ ነጋዴዎች ጉዳይ ግን በእጅጉ ያሳስባል፡፡ ይህ ድርጊት አገሪቱ ለሚያስፈልጋት ለውጥ ፋይዳ የለውም ፡፡ 
ሁሉም በተሰማራበት መስክ ኃላፊነቱን እየተወጣ መንግሥትን መደገፍ ሲገባው እነዚህ ህገወጥ ነጋዴዎችና ደላላዎች ህዝብ መንግሥትን እንዲያማርር የሚያደረግ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸው በእጅጉ የሚያሳስብ እንደመሆኑ መንግሥትም ለምን እርምጃ ከመውሰድ እንደተቆጠበ ግራ ያጋባል፡፡ አንዳንዶች በማሳሰቢያ ከድርጊታቸው ይታቀባሉ፤ አንዳንዶች ግን ጠንካራ እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ በድርጊታቸው ይቀጥላሉ፡፡ ስለዚህ ነፃ ገበያን ተገን በማድረግ የሚፈፀም ህገወጥ ድርጊትን ማስቆም ይኖርበታል፡፡ 
መንግሥት በአንድ አውደ ውጊያ ድል ማግኘቱ ብቻውን የትም አያደርሰውም፤ ኢኮኖሚው በፖለቲካው እጅ ውስጥ ነው፡፡ የኑሮ ውድነት ሄዶ ሄዶ ህዝብ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ያደርጋል፡፡ በፖለቲካው መስክ እየታዩ ያሉ ለውጦችን ለማስቀጠል የኑሮ ውድነት መፍትሄ ይፈልጋል፡፡ ህገወጦችን መቅጣት አልያም ህዝቡ አማራጭ ገበያ የሚያገኝበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ 
የክረምት ወቅት ገብቷል፡፡ ይህ ወቅት ለአገራችን አርሶ አደርም ሆነ ከተሜ ፈታኝ ነው፡፡ ገበያው የህገወጥ ነጋዴዎችና ደላሎች መጫወቻ ከሆነ ደግሞ ችግሩ ውስብስብ ይሆናል፡፡ ችግሩ የህዝቡን የተለያዩ ጥያቄዎች ለመመለስ በሚንቀሳቀስ መንግሥት ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳርፋልና መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

ዘካርያስ – አዲስ ዘመን

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *