ለዜጎች ሕይወት መጥፋትም ሆነ ለአገሪቱ አንድነት አደጋ የሆኑ የሕገ ወጦችን እርምጃ መንግስት ሊቆጣጠር ግዴታ አለበት፡፡

ፓርቲያችን ሰኔ 9/2010 ዓም በሰጠዉ መግለጫ “ለዘላቂ ሠላምና ብሔራዊ መግባባት የፖለቲካና የሕሊና እስረኞችን መፍታት፣ ግጭት፣ ግድያና መፈናቀል ሊቆም ይገባል፡፡” ብለናል፡፡ ይህንን መግለጫ የሰጠነዉ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ በአገሪቱ የድንበር ከተሞችና አዋሳኝ ክልሎች ዉስጥ ማለትም ከሞያሌ፣ ከጭናቅሰን፣ ከወሎ ባቲ፣ ከመዳ ወላቡ፣ አከባቢዎች በግጭት ምክንያት ሕይወት እየጠፋ፣ ንብረት እየወደመ፣ ዜጎች እየተፈናቀሉ ስለሚገኙ ነበር፡፡ በተጨማሪም መንግስት ግጭቶችን ለማስቆም ባለመቻሉ በሐረርጌ፣ በጉጂ፣ በጌድኦ፣ በማናስቡ፣ በሐዋሳ፣ በወላይታ፣ በወልቂጤና በሌሎች አከባቢዎች ግድያና መፈናቀሉ በእጅጉ አሳስቦን ስለነበረ ነዉ፡፡

የኢፌዲሪ መንግስት ለግጭት መነሻ የሆነ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ አካል ባለማቅረቡና በየቦታዉ የሚከሰቱ ግጭቶችን ባለማስቆሙ ከላይ የተጠቀሰዉ መግለጫችን ከተሰጠ ወዲህ እንኳን በቤኔሻንጉል ጉሙዝና በጎንደር አከባቢዎች በነዋሪዎችና በሱዳን ድንበር አከባቢ ግጭት ተከስቷል።

በያዝነዉ ሳምንት ዉስጥ ደግሞ መንግስት ሊቆጣጠር ያልቻለ ወይም ሊቆጣጠር ያልፈለገ የሚመስለዉ በምስራቅ ሐረርጌ ባቢሌ ወረዳ ገብቶ በማንአለብኝነት የሰዉ ሕይወት አጥፍቷል፣ መኖሪያ መንደሮችን አቃጥሏል፣ ንብረት አወድሟል፤ እንስሳት በቤት ወይም ማደሪያ ጎሮኖአቸዉ ዉስጥ እንዳሉ አቃጥሏል፡፡ በዘመናት ሊፋቅ የማይችል ጠባሳ ለዘመናት አብረዉ በኖሩና የቋንቋም ሆነ የባህል
ትስስር ባላቸዉ ሕዝቦች መሀከል ፈጥሯል፡፡

የዚህን ወንጀል አስከፊ ገጽታን አስመልክቶ መንግስት ማብራሪያ ሊሰጥበት ይገባል፡፡ ይህንንና ተመሳሳይ የሕገ ወጥ ኃይሎችን እርምጃ መንግስት ሊቆጣጠረዉ ካልቻለ ለሕዝቦች አብሮነትም ሆነ ለአገሪቱ አንድነት አደጋ እንደሆነ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ አበክሮ ያሳስባል፡፡ መንግስትም ሊቆጣጠረዉ ግዴታ እንዳለበት በብርቱ እናሳስባለን፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ
ፊንፊኔ፤ ሰኔ 28/2010 ዓም

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *