“እንበታተናለን” የሚለው ማስፈራሪያ ሰልችቶናል። ” አገር አልባ ትሆናላችሁ” የሚለው ቀረርቶ አታካች ነው። ” እንደ አገር አንቀጥልም” የሚለው ማላዘንም አንገሽግሾናል። ከሁሉም በላይ እንዲህ ያሉት ጩኸቶች ማብራሪያ አልባ፣ መሰረት የሌላቸው ሲሆኑብን ያጥወለውለናል። ዛሬ ዛሬ ብታምኑም ባታምኑም እንዲህ ያለው ግልብ አስተሳሰብ የሚገለማ ሆኗል።

ኮተት ሳላበዛ በአጭሩ ሃሳቤን ላፍታታ። የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ ህወሃት ደስተኛ አለመሆኑንን በይፋ አመላክቷል። ለዚህ ኩርፊያው አጃቢ ይሆኑት ዘንደ የሶማሌ ፣ የቤኒሻንጉል፣ የአፋር፣ የሃረሪና የጋምቤላ ክልል ህዝብ፣ እንዲሁም አብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ ከዶክተር አብይ ጋር የመጓዝ ፍላጎት እንደሌላቸው እየነገረን ነው።

ከኤርትራ ጋር  የተጀመረው የሰላም ንግግር ዓለምን ጉድ ያሰኘና ድጋፍ ያስቸረ፣ በተለይም የሁለቱንም አገር ህዝብ ጮቤ ያስረገጠ ሆኖ ሳለ ” የትግራይ ህዝብን ያላካተተ የሰላም ሂደት የትም አይደርስም፤ ይጨናገፋል” እያለን ነው። የአፋርንም ህዝብ በማንሳት የማጨናገፊያው ምሶሶ ለማድረግ እየሞከረ ነው።

በአገሪቱ ለውጥ እንዲካሄድ የተወሰነው ህዝብ ከጥይት ጋር ተናንቆ የኢህአዴግን እጅ በመጠምዘዙ ብቻ ነው። እናም ይህ ህዝብ አስገድዶ ያመጣው የለውጥ ሂደት ዶክተር አብይን ወደ ሃላፊነት አምጥቷቸዋል። እናም እሳቸው የህዝብ አደራ አለባቸው። በህዝብ ካልተመረጠ ፓርቲ ቢወከሉም በደም መስዋዕትነት የተገኘው ድል ፍሬ ናቸውና ለሕዝብ ስሜት ቢያደሉ አልክ ነው። አግባብም ይሆናል።

በተጀመረው የለውጥ ሂደት ውስጥ ቅር የተሰኘው ህወሃት ምን ጉዳዮች ቅር አንዳሰኙት ብትን አድርጎ ማስረዳት አልቻለም። በጅምላ ህገመንግስት ተጣሰ፣ ያልተለመደ ሹም ሽር ተካሄደ፣ ህወሃት እየተገለለ ነው፣ ወዘተ ከሚሉት ጥቅል ሃሳቦች ውጪ  ለሰሚው በሚገባ መልኩ የቅሬታውን መጠንና ይዘት ሲያብራራ አይስተዋልም።

ነባርና ጉምቱ አባሎቹ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ እንዲሁም አምርረው እንደሚታገሉ እየወተወቱ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስም በመጥቀስ ህግና ደንብን ያልተከተለ ቃታ የመጎትት ያህል አንደበታቸውን ሲስሉ መስማት ተለምዷል። እንደውም በየትኛውም መድረክና አግባብ ስሙ በክፉ ያልተነሳውን የትግራይን ህዝብ እንደ ምሽግ በመቁጠር ለዚሁ ህዝብና ለድረጅታቸው መስዋዕት ለመሆን ካሁኑ ዝግጅት ላይ መሆናቸውንም እያስታወቁና ክትት እያወጁ ያሉ አሉ።

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

ከኤርትራ ጋር እየተካሄደ ያለው የሰላም ሂደት ምኑ እንዳልተመቸው አሁንም ግልጽ ያልተናገረው የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር / ህወሃት ባወጣው መግለጫ ሰላም እንኳን ቢደረሰ ድንበር ላይ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ስፍራውን እንደማይለቅ ይፋ አድርጓል። አንድ ነጻ አውጪ ግንባር እንዴት ብሎ ነው ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የተውጣታን የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ እስከመወሰን ደርሶ መግለጫ የሚያወጣው የሚለው ጉዳይ ህገ መንግስታዊ ስለመሆኑ ግን ማስረጃ የላቸውም።

ይህ ሰራዊት ቤተሰብ ያለው፣ ወገን ያለው፣ ስሜት ያለው። የሚሆነውንና እየሆነ ያለውን የሚረዳ፣ ለህገው መንግስቱ ታማኝ የሆነ፣ ለህዝብ ክብር የሚሰጥ እና በዚሁ አግባብ አለቃው በህገ መንግስቱ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ መሆናቸውን የሚያውቅ ነው። ከዚህም በላይ ለማይረባ ዓላማ የከፈለው ዋጋና አሁን ድረስ በረሃ ምሽግ ውስጥ የሚኖርበት ሚስጢር በወጉ የማይገባው ጭምር ነው። በተጨማሪም እሱ ድንበር ሲጠብቅ ወገኖቹ፣ ቤተሰቦቹ፣ ምን አልባትም ልጆቹ በአልሞ ተኳሾች ሲገደሉበት እንደነበር፣ በየቶርቸር ቤቱ ሲሰቃቱ እንደነበር የሚረዳ ነው። ባጭሩ ይህ ውድ የአገራችን ሰራዊት ስሜት አልባ እንደሆነ አድርጎ በብጣሽ ወረቀት ሊማማሉበት ለሚወዱ ምላሽ ይኖረዋልና ረጋ ማለት ደግ ነው።

ሌላው ጉዳይ እስካሁን በተደረገው ድርድር ኢትዮጵያና ኤርትራ የትግራይን ህዝብ የሚጎዳ ምን ስምምነት አደረጉ የሚለውን ጥያቄ ህወሃት ማስረጃ ጠቅሶ ሊመልስ አይችልም። በግልጽ እንደተሰማው በድንበር አካባቢ ያሉት ችግሮች በህዝብ ፈቃድ አማካይነት እልባት የሚበጅላቸው መሆናቸውን ነው። የተቀሩት ጉዳዮች በፌደራል ደረጃ የሚታዩ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳዮች ስምምነቶች መደረጋቸው የህወሃትን ዓይን እንዴት ሊያቀላው እንደቻለና የተወሳሰበ ሚስጢር እንዲሆንበት ያደረገው ጉዳይ ለሰሚው ግራ ነው።

Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

በዚሁ ጭንቀት በወለደው እሳቤ፣ በግራ መጋባት ውስጥ የተዘፈቀው ህወሃት አሁን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ እንዳልወደደው ለማስረዳት መሞከሩ ደግሞ አስቂኝና የድርጅቱን ተላላነት የሚያሳይ ይሆናል። አሁን ህወሃትን የተኛው የኦሮሞ ህዝብ ነው የሚሰማው፤ የሚያምነው፤ የአገሪቱ እስር ቤት ሁሉ መግባቢያ ቋንቋው ኦሮምኛ መሆኑንን መርሳት የአስተሳሰብ መዛል ካልሆነ ምን ሊባል ነው፤

ህወሃት እንደ ድርጅት ብቻ ሳይሆን ቅርንጫፍ ሆነው የሚያገለግሉት ወዳጆቹ “የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት በኦነግ እንጂ በኦህዴድ አይደለም” ሲሉ መስማት የአመለካከት መገሸብ እና የህሊና መድረቅ ከማሆን የሚዘል አይመስለኝም። እንኳን ዛሬ በወራት ልዩነት በዓመታት ውስጥም ቢሆን ህወሃት ኦሮሚያ ላይ የሚሰማው ሊያገኝ እንደማይችል ለማመን አለመሞከራቸው ተራ ተስፈኛ ከሚያስብል  በቀር ሌላ የሚሰጠው ስም የለም።

ጋምቤላ በተመለከት መሬቱን የወረረ፣ የቸረቸረ፣ በምስኪን ሰላማዊ የአኝዋክ ልጆች ላይ ጂኖሳይድ ያከናወነ፣ ደናቸውን የመነጠረና ህዝባቸውን በኢንቨስትመንት ማን እንዳፈናቀለ ስውር የሚመስለው የህወሃት አመራርም ሆነ ደጋፊ ካለ ጅል ብቻ ነው። እናም በደም አበላ የተጨማለቀና ክልሉን ሲያልቡ የኖሩ ዛሬ ለውጥ ለማደናቀፍ የጋምቤላ ህዝብ ምሽግ ለማድርገ ሲዳክሩ ማየት አሁንም የህሊና መኮሰስና መድረቅ ከመሆን አያልፍም።

የሶማሌ ክልልም ሆነ የቤኒሻንጉልን አስተዳደር ተብትቦ በመያዝ መንቀሳቀስና የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመግታት መሞከር ብዙም የሚያስኬድ አይደለምና ለውጡን ሚዛኑንን ሳያስቱ ተባባሪ በመሆን መንቀሳቀሱ ለምስኪኑ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲና ነጻነትን ማጎናጽፍ ይሆናል።

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

ህወሃት እስከዛሬ በአገሪቱ ላይ የፈጸመው ሳያንሰው ዛሬ በሞተ ጉዳይ አጉል መዳከሩ ብዙም እንደማይጠቅመው አዋቂዎች እየመከሩ ነው። በዚሁ እምነት እርቅን ተቀብሎ ከህዝብ ጋር የተጀመረውን መንገድ ማስቀጠል ግድና ግድ ነው። ከዚህ ውጪ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት የጅል ጨዋታ መጫወት መጨረሻው ጥሩ አይሆንም።

ትጥቅ፣ ሎጂስቲክ፣ ሃብት፣ አንድ ላይ ተዳምረው የሚፈጥሩት እብሪት ከፍርሃት ጋር ሲዳመር አደጋው የከፋ ነውና አዲሱ ትውልድ ጭልጥ ብሎ ከመነዳት ይልቅ ቆሞ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ሚዛኑንን ሊጠብቅ ይገባል ባይ ነኝ። ህወሃት ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ስላጣን በገፍ ተቆጣጥሮ ሲገዛ ነበር። ዛሬ ደግሞ የስላጣን ክፍፍሉ ፍትሃዊ ሊሆን ይገባል በሚል ሁሉንም እንደሚወክሉት ህዝብ ብዛት የማዳረስ ስራ ሲጀመር አጉል መቅበዝበዝ ፍትሃዊም አይሆንም።

በመጨረሻ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እንደተረዳው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረው የሰላም ውይይትና የተደረሱት ስምምነቶች አንዳቸውን ሚስጢር አይደሉም። አንዳቸውም የትግራይን ህዝብ አይጎዱም። አንዳቸውም የአገርና ህዝብን ጥቅም አሳልፈው አይሰጡም። አሁን የተጀምረው ኖርማላይዝ የማድረግ ተግባር ሲሆን ድንበር በማፍረስ አብሮ የመዝለቅ እሳቤ ስላለው በዚህ ግንኙነት ውስጥ የተበላሸውን ማስቀጠል ብልጥነት ይሆናል። ይህ አያዋጣኝም በሚል ቅሬታ ካለ እንደ መለስ ንግግር ” መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ ” መንፈራገጥ ይሆን ካልሆነ ህዝብን ማሸነፍ አይቻልም!! አንበታተነም!!

እስከዳር ዮሐንስ
ዝግጅት ክፍሉ- ይህ ጽሁፍ የጸሃፊው እምነት ብቻ ነው። ምላሽ ለሚጽፉ እናስተናግዳለን

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *