አብዲ ኢሌይ ማለት ተስፋ የቆረጠ ሰው ነው፤ ስለዚሀ አሁን የፈለገውን ለማለት ይችላል፤ ግን ተጠያቂ ከመሆን አያመልጥም። ፍትህን መጋፈጥ አለበት፤ በእጆቹ ላይ ደም አለበት፤ በጦር ወንጀለኛነትና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በሚፈጸም ወንጀሎች መከሰስ የሚገባው ሰው ነው – ፊሊክስ ሆርን

ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት (ሂውማን ራይትስ ዎች) በቅርቡ በሶማሊ ክልል ስለሚፈጸመው እጅግ አሰቃቂየሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች አዲስ ዘገባ ማውጣቱ ይታወቃል። የክልሉ ርዕስ መስተዳድር የሆነውን አብዲ ኢሌይን በቀጥታ ተጠያቂ የሚያደርገው ይህ ዘገባ ከወጣ በኋላ አብዲ የተለያዩ “ዕርምጃዎችን” ሲወስድ ተስተውሏል።እነዚህም “ዕርምጃዎች” እስረኞችን ሁሉ መፍታት፣ በክልሉ የሚፈጸመውን ስቅየት ማቆም፣ … ያካተቱ ናቸው ቢባልላቸውም ለምሳሌ በኦጋዴን እስርቤት የነበሩትን የመፍታት ሳይሆን ወደ ሌላ ቦታ የማዛወር ተግባር ነው የተፈጸመው በማለት “ዕርምጃዎቹን” ውድቅ የሚያደርጉ ጥቂቶች አይደሉም።

ከዚህ ሌላ አብዲ ኢሌይ በክልል ምክርቤቱ ስብሰባ ላይ እስካሁን በክልሉ ለተፈጸሙት ወንጀሎች ህወሓትን በቀጥታ ተጠያቂ ሲያደርግ መስማታቸውን የክልሉ አክቲቪስቶች አረጋግጠዋል። አብዲ ይህንን በተናገረ ምሽት የተወሰኑ የሚዲያ ሰዎችን ጠርቶ የህወሓት አመራሮች በተለይም የደኅንነት ኃላፊ የነበረው ጌታቸው አሰፋ በርካታ ወንጀሎችን አስገድዶ ያስፈጽመው እንደነበር፣ በክልሉ ሥራ ጣልቃ በመግባት ከፍተኛ ችግር ይፈጥርበት እንደነበር ተናግሯል። ከዚህ ጋር አያይዞም እስካሁን ስህተቶች መፈጸማቸውን በማመን እነዚህ ስህተቶችን በይቅርታ በማለፍ፣ በመደመር ወደፊት አዲሱን የዐቢይ አሕመድን አስተዳደር እየደገፉ መሔድ ተገቢ እንደሆነ ተናግሯል። ሆኖም ግን አብዲ በክልሉ በከፍተኛ ወታደራዊ ሥልጣን ላይ ያሉትን የህወሓት ጄኔራሎች ላይ ግን ምንም የተናገረው አልነበረም።

አብዲ ኢሌይ ይህንን የተናገረው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ ዘገባ ከወጣ ጥቂት ቀናት በመሆኑ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የዘገባው ዋና አቀናባሪ የሆኑትንና በድርጅቱ የኢትዮጵያና የኤርትራ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑትን ፊሊክስ ሆርን አነጋግሯል። ይህ በስልክ በተደረገ አጭር ቃለ ምልልስ ዋና ተመራማሪው አብዲ ኤሌይ ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ በአጽዕኖት ተናግረዋል። ፊልክስ ሆርን በተለይ ለጎልጉል የሰጡትን አጭር ቃለምልልስ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

ጎልጉል፤ የድርጅታችሁ መግለጫ ከወጣ በኋላ አብዲ ኢሌይ የተናገረውን የሰሞኑን ንግግር ሰምተውታል?
ፊሊክስ፤ አዎ ሰምቼዋለሁ፤ ባለፉት ሁለት ቀናት ከኢትዮጵያ ሶማሊዎች በኢሜል እና በስልክ መልዕክቶች “ስደበደብ” ነው የቆየሁት፤ ሁሉም በመልዕክቶቻቸው በጣም ተናድደዋል፤ በጣም ተቆጥተዋል፤ አብዲ ነጻ እንዳልሆነ ነው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፤ ስለዚህ አብዲ ኢሌይ የፈለገውን ቢልም ከኃላፊነት አያመልጥም።

ጎልጉል፤ አብዲ ኢሌይ በቪዲዮውም ሆነ በምክርቤት ንግግሩ ይህንን ወንጀል ያሠሩን የህወሓት ሰዎች ናቸው በማለት እነ ጌታቸው አሰፋን ተጠያቂ ለማድረግ ሞክሯል፤ ይህንን እንዴት ተመለከቱት?

ፊሊክስ፤ አብዲ ኢሌይ ማለት ተስፋ የቆረጠ ሰው ነው፤ ስለዚሀ አሁን የፈለገውን ለማለት ይችላል፤ ግን ተጠያቂ ከመሆን አያመልጥም። ፍትህን መጋፈጥ አለበት፤ በእጆቹ ላይ ደም አለበት፤ በጦር ወንጀለኛነትና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በሚፈጸም ወንጀሎች መከሰስ የሚገባው ሰው ነው፤ ጠ/ሚ/ሩ በኃላፊነት ሊጠይቁት ይገባል፤ ምክንያቱም እርሳቸው የጀመሩት አስተዳደር ግልጽነትኛ ተጠያቂነት ይኖረዋል ብለዋል። ይህንን በተግባር ሲፈጽሙ መታየት አለባቸው።

ጎልጉል፤ ዘመኑ የይቅርታ ነው ለሠራነው ጥፋት ይቅርታ ተደርጎልን ወደፊት እንሂድ፤ ያለፈውን እንተወዉ ብሏል፤ ስለዚህስ ምን ይላሉ?
ፊሊክስ፤ በጣፋጭ የብስኩት ማሰሮ ውስጥ እጁን አስገብቶ ተያዘ እንደሚባለው የእንግሊዝኛ አገላለጽ ነው የአብዲ ኢሌይ የአሁኑ ሁኔታ፤ (ሲሰርቅ ስለተያዘ ነው እንደማለት ነው) እጅ ከፍንጅ ተይዟል ስለዚህ ነው ይህንን ያለው። የኢትዮጵያ ሶማሊዎች ፍትህ ማግኘት ይገባቸዋል።

ጎልጉል፤ የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ይሆን ይህንን እንዲል ያደረገው?
ፊሊክስ፤ (በእንግሊዝኛ የሚነገረውን አባባል በመጥቀስ በግርድፍ ትርጉሙ) የመጨረሻው ገለባ ወይም የሣር ሰበዝ ነው የግመሏን ጀርባ የሚሰብረው እንደሚባለው ብዙጊዜ የድርጅታችን ዘገባ ከወጣ በኋላ ተጠያቂ የምናደርጋቸው ሰዎች ጉዳይ ያከትማል፤ የሒውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ብዙውን ጊዜ የብዙዎችን ነገሮች ፍጻሜ መምጫ ሲሆን ተመልክተናል እና ይህ ሪፖርት የእርሱን ፍጻሜ የሚያመጣው ሊሆን ይችላል ብለን እንገምታለን።

ጎልጉል፤ ከአብዲ ኢሌይ በቀጥታ ምላሽ ሰምታችኋል? ወይም ለእርስዎ በቀጥታ መልስ ሰጥቷል?
ፊሊክስ፤ የተለያዩ ምላሾች ከማንበብ በስተቀር ለእኔ በቀጥታ ምንም የተላከ መልዕክት ወይም ምላሽ የለም።

goolgule

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *