ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የደቡብ ሱዳን ባላንጣዎች የእርስ በርስ ጦርነቱን ለማቆም ሰላማዊ ድርድር አድርገዋል፡፡ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ባለፉት ዓመታት በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ብዙ ሰዎች ሞተዋል፤ ከአራት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል፡፡ ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር በካርቱም የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽርም በስምምነቱ ላይ በመገኘት ሁለቱ መሪዎች ሰላም እንዲያወርዱ ድርድሩን መርተዋል፡፡


በተደረሰው የተኩስ አቁሙ ስምምነትም ሁለቱ መሪዎች የአፍሪካ ህብረት አገራትና በአካባቢው የሚገኙ አገራትን በማስፈቀድ ወደ ደቡብ ሱዳን ሰላም አስከባሪ ኃይል ማሰማራት የሚቻልበት ሂደት ተካቶበታል፡፡ በተጨማሪም አገር አቀፍ ምርጫ እስኪካሄድ በጋራ ሆነው የሽግግር መንግሥት በማቋቋም አገሪቱን ለመምራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ከሱዳን ጋርም በነዳጅ ገበያው አካባቢ ያሉ ችግሮች በመፍታት የነዳጅ ምርት ለማሳደግ እቅድ ይዘዋል፡፡ በሁለቱ መሪዎች መካከል የተወሰደው እርምጃ በአካባቢው ሰላም ከማምጣት ባለፈ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እገዛ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ስምምነቱ ሳምንት ሳይሞላው አደጋ የተጋረጠበት ይመስላል፡፡
በተያዘው ወር መጀመሪያ የተኩስ አቁም ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ ቢደርሱም በሰዓታት ውስጥ ስምምነቱም የሚጥስ ተግባር ተፈፅሟል፡፡ የመንግሥትና የተቃዋሚው ኃይል በንግድ እንቅስቃሴዎች የእርስበርስ ክስ ጀምረዋል፡፡ ከቀናት በኋላ የደቡብ ሱዳን መንግሥት የሳልቫኪርን የስልጣን ዘመን እስከ 2021 ድረስ ሊያራዝም የሚችል ማሻሻያ አዋጅ ለፓርላማው አቅርቧል፡፡ ይህንን አዋጅ ተቃዋሚው ፓርቲ ያልተቀበለ ሲሆን፣ ሁኔታው በአገሪቱ የተጀመረውን የሰላም ስምምነት የሚያፈርስ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የደቡብ ሱዳን መንግሥትና ተቃዋሚው የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረጋቸው ላይ ጥርጣሬ አሳድሯል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ትልቅ ጥያቄ እየሆነ የሚገኘው ድርድሩን ያመቻቹትና የመሩት ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር መሆናቸው ነበር፡፡
የበሽር መንግሥት ደቡብ ሱዳን እ.አ.አ 2011 ላይ ነፃነቷን ካወጀች በኋላ የእርስ በርስ ጦርነቶች እንዲነሱ እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ለዚህ ነው በደቡብ ሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ አልበሽር ሲያደራድሩ አግራሞት የፈጠረው፡፡ በተያያዘም በበሽር አማካኝነት የተደረገው የሰላም ስምምነት ዘላቂነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች መካከል የተደረገው ዘላቂነት ያለው የተኩስ አቁም ስምምነት የተጀመረው በካርቱም ሳይሆን አዲስ አበባ ላይ ነበር፡፡ እ.አ.አ 2018 ሰኔ 21 ቀን ላይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሳልቫኪርንና ሪክ ማቻርን በቤተመንግሥቱ የእራት ግብዣ አድርገውላቸው ነበር፡፡ በዛ ምሽት ሁለቱ መሪዎች ከእ.አ.አ 2016 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኙበት ወቅትም ነበር፡፡ በእራት ግብዣው ላይ ስለ ሰላም ስምምነት የተደረገ እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ 
በአዲስ አበባ የተደረገው የሰላም ስምምነት ከከሸፈ በኋላ እ.አ.አ ሰኔ 25 ቀን 2018 የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ሁለቱ መሪዎች በካርቱም እንደሚደራደሩ አስታወቀ፡፡ የሰላም ስምምነት ድርድሩን የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ከአዲስ አበባ ወደ ካርቱም የወሰደው ዓለም አቀፍ አገራት ማለትም አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ኖርዌይ አልበሽር ትክክለኛው አደራዳሪ ባይሆንም ሁለቱን መሪዎች ግን ወደ ሰላም እንዲመጡ ግፊት ያደርጋል ብለው በማመናቸው ነበር፡፡ 
አልበሽር የማቻርን ቡድንና ሌሎች በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ተቃዋሚዎችን በማበረታታት ሲሰራ የቆየ በመሆኑ ተቃዋሚዎቹ ወደ ሰላም እንዲመጡ ማሳመን ይችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ በሌላ በኩል በሽር ከደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት የተለያዩ አላማዎቹን ማሳካት ይፈልጋል፡፡ ከአላማዎቹ መካከል በሽር ሱዳን ያለባትን የኢኮኖሚ ችግር ለመፍታት ከገልፍ አገራት የጠበቀውን ያክል እርዳታ ባለማግኘቱ በደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚገኘውን ነዳጅ ለመጠቀምና የደቡብ ሱዳንን ኢኮኖሚ በመታደግ ጥቅም ለማግኘት ዕድሉን እየሞከረ ይገኛል፡፡
በመጀመሪያ ኦማር አልበሽር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል ከአሜሪካ እየተሰጠው ያለውን እርዳታ እንዲቆም በማድረግ የትራምፕ አስተዳደርን ቀልብ ለመሳብ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ሰላም እንዲመጣ ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ሁለተኛ በሱዳን ያለውን የፖለቲካና ኢኮኖሚ ችግር ለማስቀየስ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ በመጨረሻም የሰላም ድርድሩን በአሸናፊነት መንፈስ በማጠናቀቅ በቀጣናው ሰላማዊ የሆነች ሱዳንን ለመመስረት ዕቅድ አለው፡፡
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና ተባባሪ አገራትም ሃሳባቸውን ያሳኩ ይመስላል፡፡ በሽር በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለውን ችግር እና በእሱ ድጋፍ እየተዋጉ የሚገኙ ተቃዋሚ ቡድኖች የሰላም ፍላጎት ተረድቷል፡፡ የሆነው ሆኖ በሽር በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች መካከል በተደረገው የሰላምና የተኩስ አቁም ስምምነት ሁሉንም ምስጋና አይወስድም፡፡ የዓለም አቀፉ አገራት በደቡብ ሱዳን ያለው የርስበርስ ጦርነት እንዲቆም እያደረገ ያለውን ጥረት ተከትሎ በካርቱም የተካሄደው የሰላም ድርድር ሰዓቱን ጠብቆ የተካሄደ ነው፡፡
ይህንንም ጉዳይ በደቡብ ሱዳን ያሉት ተቃዋሚና መንግሥትም ተረድተውታል፡፡ በዚህም ውጤት ከበፊቱ የበለጠ አንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ላይ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በተኩስ አቁም ስምምነቱ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና ተባባሪ አገራት በአገሪቱ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ በማድረግ የበሽር የእርቅ እቅድ እንዲሳካ ጥረት አድርገዋል፡፡
የዩጋንዳው መሪ ዩዎሪ ሙሴቬኒ በካርቱም በመገኘት በደቡብ ሱዳን ውስጥ ተኩስ አቁም እንዲደረግና ሁለቱ መሪዎች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የጎላ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ዩጋንዳ በደቡብ ሱዳን በፀጥታና በኢኮኖሚ ጉዳይ የራሷ አላማ ያላት በመሆኑ በደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ትፈልጋለች፡፡ ሙሴቬኒ ለደቡብ ሱዳን መንግሥት ፖለቲካዊ የሆነና በተለያዩ መንገዶች የሳልቫኪርን ወታደሮች ይደግፉ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከተቀናቃኙ ሪክ ማቻር ጋር የሚደረጉ የሰላም ድርድሮችን እየደገፈ በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲመጣ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ 
በሽርና ሙሴቬኒ በመጨረሻ ሰዓት በደቡብ ሱዳን ውስጥ ሰላምና መረጋጋት መምጣት እንዳለበት የተረዱ ይመስላሉ፡፡ ለዚህም በሁለቱ መሪዎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈረም የበኩላቸውን ግፊት አድገዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለተኩስ አቁሙ መፈረም ከፍተኛ ሚና የተወጡ በሽርም ይሁን ሙሴቬኒ ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ጥቅም የለውም፡፡ ህዝቡ የሚፈልገው በአካባቢው ያለው ግጭት እንዲቆም ብቻ ነው፡፡
በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለውን ሰላምና መረጋጋት ዘላቂ ለማድረግ የህግ የበላይነት እንዲከበር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የተደረገው ስምምነት ከተወሰኑ ሰዎች እንደ ሽልማት የተሰጠ ማድረግና ለራሳቸው ጥቅም በአገሪቱ ሰላም እንዲመጣ ላደረጉ አገራት ምስጋና ማቅረቢያ ማድረግ አያስፈልግም፡፡ በደቡብ ሱዳን የመጣውን ሰላም የህዝቦች ሰላም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ምክንያቱም የተደረገው የሰላም ስምምነት በአገሪቱ ለብቻው የህግ የበላይነትን አያመጣም፡፡ በዋናነት በደቡብ ሱዳን በትክክለኛ መንገድ ህዝቡን መምራት የሚያስችል አሰራር ያስፈልጋል፡፡ በአገሪቱ ሰላም ለማጣት ፍትህ፣ ተጠያቂነት እንዲሁም እርቅ ዋነኛ ቁልፍ ሆነው አገሪቱን በመገንባት ሁኔታዎች ላይ የጎላ ሚና ይጫወታሉ፡፡ የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና ሌሎች ዓለም አቀፍ አገራት ሁለቱ መሪዎች የሰላም ስምምነቱን እንዲያከብሩ በማድረግ የለውጥ አጀንዳ እንዲያራምዱ ግፊት ሊያደርጉ ይገባል፡፡ 
ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ቢሆንም እንደ በሽር ያሉት በደቡብ ሱዳን ሁሉን አቀፍ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ያስፈልጋሉ፡፡ ደቡብ ሱዳን በእርስበርስ ጦርነትና በጎሳ ትርምስ ውስጥ ነበረች፡፡ ቀድሞም ነፃነቷን ለማግኘት ከሱዳን ጋር እረጅም ዓመታት ጦርነት ስታካሂድ ቆይታለች፡፡ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ሱዳንና ዩጋንዳ የራሳቸውን ክልል በማበጀት የሰላም ሁኔታው በራሳቸው ፍላጎት እንዲመሰረት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ምንጭ፡- አልጀዚራ ድረገፅ – አዲስ ዘመን

መርድ ክፍሉ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *