ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ 456 ሰዎችን የያዘ የህዝብ ለህዝብ ቡድን ዛሬ ወደ አስመራ አቀና። የህዝብ ለህዝብ ቡድኑ በሁለት አውሮፕላኖች ዛሬ ረፋድ ላይ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት ጉዞውን ወደ አስመራ አድርጓል።

የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም ወደ ኤርትራ የሚያቀናውን የተጓዦች የልዑካን ቡድን የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። አቶ ሃይለማርያም በሁለቱ ሃገራት መካከል አሁን ላይ የለውጥ ጉዞ መጀመሩን ተናግረዋል።

የሁለቱ ሃገራት ወደ አንድነት መመለስ ከለውጡ እንቅስቃሴ ውስጥ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፥ አሁን ላይ ለመጣው ለውጥም የሁለቱን ሃገራት መሪዎች አመስግነዋል።

በቀደመውና ሃገራቱ ግጭት ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ውስጥ ሃገራቱ ብቻ ሳይሆኑ ምስራቅ አፍሪካ ችግር ውስጥ ገብቶ መቆየቱንም አስታውሰዋል። ይህ ግጭት አብቅቶ አሁን ላይ ወደ ሰላም በመምጣታቸውም በቀጠናው ብሎም በአፍሪካ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል ብለዋል።

አቶ ሃይለማርያም በንግግራቸው የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች በልማትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መካስ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። አሁን ላይ ለተጀመረው ለውጥ ስኬት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ጠቅሰው፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በአጭር ጊዜ እንዲሳካ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በበኩላቸው፥ አየር መንገዱ ለ20 አመታት ተቋርጦ የነበረውን የሁለቱን ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የማስጀመር ሃላፊነቱን በመወጣቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው ዳግም በተጀመረው የሁለቱ ሃገራት የአውሮፕላን በረራ የመጀመሪያ ጉዞም በአየር መንገዱ ታሪክ ሁለት አውሮፕላን መብረሩን ጠቅሰዋል።

አየር መንገዱ በቀጣይ ወደቡን ጨምሮ ወደ ሌሎች የኤርትራ ከተሞች በረራ በማድረግ፥ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ለማጠናከርና የኤርትራን ቱሪዝም ለመደገፍ እንቅስቃሴ ያደርጋልም ነው ያሉት።

በዛሬው እለት የቀጥታ በረራ መጀመሩም ኤርትራውያን ወደ አስመራ ለመሄድ የሚያደርጉትን ጉዞ በማሳጠርና ወጪ በመቀነስ እገዛ ያደርጋልም ብለዋል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመንገደኞች በሚካሄደው ምርጫ የ2018 የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ሽልማትን አሸንፏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያምም ሽልማቱን ለነድን በመገኘት ተረክበዋል። ሽልማቱ መስተንግዶና የመንገደኞችን ምቾት መጠበቅን ጨምሮ አየር መንገዱ በአመቱ በሰጠው አገልግሎት የተበረከተለት ነው።

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)

በፍሬህይዎት ሰፊው

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *