‹የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድም የአገሩ ህዝቦች የተለየ/የበለጠ ጥቅም አይፈልግም!!!› እውነት ነው! የትግራይን ህዝብ ጨምሮ የተለየ ጥቅም የሚፈልግ ህዝብ የለም፤ ሊኖርም አይገባም — አይችልምም፡፡ የተለየ ጥቅም የሚያገኝ የአንድ ስብስብ አካል የሆነ ሌላ ስብስብ አለ ማለት በውጤቱ በዝያ ስብስብ ውስጥ አንደኛና ሁሉተኛ ወይም ልጅና እንጀራ ልጅ አልያ እሳቸውም እንዳሉት ለማኝና ተለማኝ የሚባል ኢፍትሃዊ አደረጃጀት/አሰላለፍ ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ የዚህን አደረጃጀት ተከትሎ የሚከሰተው ደግሞ አለጥርጥር ስርዓት፣ ህግ፣ ወይም መርህ አልበኝነት ይሆናል፡፡

እንሆ መቀሌ ተሰልፋለች! በታሪኳ እንዲህ አይነት ሰልፎች ስለማስተናገዷ አላውቅም፡፡ እርግጥ እንኳን ሰልፍ የግል ጋዜጣ ይሸጥባት እደሆነም ሰምቼ አላውቅም፡፡ የሆነው ሆኖ መቀሌ ተሰልፋለች፤ ለሁለት አላማዎች ‹ከመድረኩ ንግግሮች እንዳስተዋልኩት›፤ 1ኛ የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ አቻው ጋር ያወረደውን ሰላም በተመለከተ “የተሰማትን ደስታ” ለመግለጽና 2ኛ የደ/ር አብይን/የፌደራሉን መንግሰት ስለ አንዳንድ ጉዳዮች ለማስጠንቀቅ፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ዶ/ር ደብረ-ጽዮን ገ/ሚካዔል የትግራይ ህዝብ ከወንድም የኤርትራ ህዝብ ጋር በሳህል፣ በናቅፋ፣ በባርካና ወ.ዘ.ተ በርሃዎች በአንድ ግንባር ተሰልፎ መታገሉን፣ መሞቱንና በአንድ ጉድጓድ መቀበሩን ያስታወሱ ሲሆን ባለፉት 20 የባከኑ የጸብና ኩርፊያ አመታት የተቆጩ ስለመሆኑና ጸንቶ በቆየው የአይንህን/ሽን ላፈር ኩነት ሁለቱም አገሮች መክሰራቸውን አስረድተዋል፡፡ እርግጥ ነው ከ20 አመታት በላይ እርሳቸውና ድርጅታቸው ሕውሀት በፌደራሉ መንግስት ወንበር ላይ ተቀምጠው ሳለ ዛሬ የተደሰቱበትን የእርቅና ሰላም እርምጃ ላለመውሰድ የከለከላቸው ነገር ምን እንደነበር አልተናገሩም፤ ወይም ሲናገሩ አምልጦኛል ማለት ነው – አልሰማሁም፡፡ ዶ/ሩ ለኤርትራ ህዝብ ከየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ህዝብ የበለጠ ድርጅታቸው የሚመራው ህዝብ እንደሚቀርብ ለማስገንዘብ የመሰለ ንግግራቸውን ስሰማ ከዚህ ቀደም አቦይ ስብሃት ነጋ ኤርትራዊያን ትግሉን ሊያቋርጡ ሲሉ አይገባም ከማለታችንም ባሻገር 400 ገጾች ያሉት ስለትግሉ አስፈላጊነት የሚያትት መጽሓፍ አሳትመን አጀግነናቸዋል ያሉበትና የኤርትራ መንግስት ላይ ጥቃት የሚሰነዝር አካል ከመጣ እኛ ከጎናቸው ሆነን የምንታገል መሆኑን ሊያውቅ ይገባል ያሉባቸውን ንግግሮቻቸውን እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ ዳዊት ገ/እግዚኣብሄር የተባሉ ሰው የባድመ ጉዳይ የትግራይና ኤርትራ ህዝቦች ጉዳይ ነው! ሌላው ኢትዮጵያዊም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት በሁለተኛ ደረጃ ካልሆነ አያገባውም!!! ያሉትን አስታወሰኝ፤ ክፉ ትውስታ ነው፤ በተለይ መጨረሻ የጠቀስኩት ንግግር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሌላ ጊዜ ብመለስበት ይሻላል መሰለኝ፡፡

ደ/ር ደበድረ-ጽዮን ብዙዉን በገደምዳሜ፣ አንዳንዱን ደግሞ በቀጥቃ ለፌደራሉ መንግስት ያስተላለፏቸው መልዕክቶችን በገረፍ ገረፍ ስንመለከት ደግሞ ቅድሚያ ወስዶ የምናገኘው የ‹እንፈራርሳለን› ማስጠንቀቂያቸው ይሆናል፡፡ ም/ርዕሰ-መስተዳድሩ ፍትሓዊ ተጠቀሚነት የማይረጋገጥ ከሆነ፣ ህዝቦች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መስራት/ሀብት ማፍራት የማይችሉ ከሆነና መከባበር ከጠፋ አገር ትበታተናለች ሲሉ እንደቀደሙት የድርጅታቸው (ሕውሀት) ፊት አውራሪዎች ሁሉ አስጠንቅቀዋል፤ ዝተዋል፤ አስፈራርተውማል፡፡ ድርጅታቸውና ዶ/ሩ ላለፉት 27 አመታት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጡ በሚመስል ሁኔታ ያሰሙት ይህ ንግግር ለብዙዎች ቃር ቃር የሚል የቸከ ዲስኩር እንደሚሆንባቸው እረዳለሁ፡፡ ላለፉት 3 አመታትና ከዝያ በላይ በመላው አገሪቱ ሰፍኖ የቆየው አመጽና ተቃውሞ ዋነኛ ጥያቄውም ይሄው የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ እንደሆነ እኔም፣ ዶ/ሩም፣ ሌላውም የሚያውቀው ጸሃይ ላይ የተሰጣ ሀቅ ነው፡፡ የአገሪቱን አንድ አራተኛ ሲደመር ኢኮኖሚ የተቆጣጠረው ኤፈርት የተባለው የድርጅታቸው ድርጅት እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ድርጅት ህገ-ወጥነትና ባለቤትነት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለጊዜው ምንም ማለት አልፈልግም፤ አሁን ለማለት የምፈልገው ዶ/ሩና ድርጅታቸው ባለፈው የአንድ ትውልድ እድሜን የሚያህል ዘመን ላላረጋገጡት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ኡኡ! ብሎ መጮህ አልያም እበተናለሁ! ብሎ ማስፈራራትም ካለበት ሊያደርገው የሞራል ልዕልና ያለው የእርሳቸው ድርጅት አለመሆኑን ነው፡፡

ለመሆኑ ድርጅታቸው ክልሉን ይዞ ቢገነጠል የሚጠቀመው፤ የሚጎዳውስ ማን ነው? ‹‹በነገራችን ላይ ድርጅቱ ብዬ የምጽፈው መላው የትግራይ ተወላጅን በጅምላ መጥቀስ ወይም የአንድ ድርጅት አባል እደሆነ መውሰድ ተገቢ ነው ብዬ ባለማመኔ ነው፡፡ ተሳስቼ ቢሆን እንኳ ያንኑ ማድረግ እመርጣለሁ፡፡››

በድንበር ጉዳይ ያልተቋጩ፤ በአጭር ጊዜም የሚቃጩ የማይመስሉ ጉዳዮች በዶ/ሩ የቢሮ ጤረጴዛ ላይ አልያም ማስታዎሻ ደብተራቸው ላይ በጉልህ የተቀመጠ ላለመሆኑ ማስረጃ የለም፡፡ በተለያየ ወቅት እርሳቸውና ድርጅታቸው እያጣጣሉ ቢሆንም እንኳ ያወሩን ከአማራና አፋር ክልሎች እንዲሁም ከኤርትራ ጋር የድንበር ውዝግብ ውስጥ መሆናቸውን ነው፡፡ ከዝያም አልፎ የተፈታ የድንበር ውዝግብ ስለመኖሩም ከወራት በፊት ነግረውናል፡፡ በተጻራሪው እንደምናየው ‹‹ተፈታ!›› የተባለውም የድንበር ውዝግብ ካልተፈታው በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ክልሉ “በተበተነ”/በተገነጠለ ማግስት የማያባራ ጦርነት ውስጥ ቢያንስ ከአንደኛው የድንበር ባለጉዳይ ጋር ይገባል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል የክልሉ ኢኮኖሚያዊ ትስስርም ቢሆን በተለይም ንግድና ግብግርናን በሚመለከት ከቀሪው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጋር እንጂ ከሱዳን ወይም ከ20 አመታት “ጠላት” ኤርትራ ጋር አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ላለፉት በርካታ አመታት ከተለያዩ የአለም መንግስታትና ተቋማት የተወሰደውን በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ብድር ለሁለት (ክልሉና ኢትዮጵያ) ተካፍለው የሚከፍሉ መሆኑና ይህንንም መሸከም ለክልሉ ህዝብ ምን እንደሚያተርፍለት ለመገመት በማይከብድ ደረጃ ያለ ንቅ አደጋ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ የአካባቢው ጂዖፖለቲክስም ይሁን ፖለቲካል ኢኮኖሚ እንደማይፈቅድ እየታወቀ ለምን “እንበተናለን” እያሉ ማስፈራራት እንዳስፈለገ አይገባኝም!፡፡ እንደኔ እንደኔ ድርጅቱ ይህን ጉዳይ ከዚህ በላይ ባይገፋው እመኛለሁ፤ ከአፍ ሲያመልጥ ራስ ሲመለጥ… እንዳይሆን፡፡

በመጨረሻ ም/ርዕሰ-መስተዳድሩ ከጠ/ሚሩ ተውሰው የተጠቀሙትን የንግግራቸውን አንድ ፍሬ-ጉዳይ ላንሳ፤ ‹የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድም የአገሩ ህዝቦች የተለየ/የበለጠ ጥቅም አይፈልግም!!!› እውነት ነው! የትግራይን ህዝብ ጨምሮ የተለየ ጥቅም የሚፈልግ ህዝብ የለም፤ ሊኖርም አይገባም — አይችልምም፡፡ የተለየ ጥቅም የሚያገኝ የአንድ ስብስብ አካል የሆነ ሌላ ስብስብ አለ ማለት በውጤቱ በዝያ ስብስብ ውስጥ አንደኛና ሁሉተኛ ወይም ልጅና እንጀራ ልጅ አልያ እሳቸውም እንዳሉት ለማኝና ተለማኝ የሚባል ኢፍትሃዊ አደረጃጀት/አሰላለፍ ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ የዚህን አደረጃጀት ተከትሎ የሚከሰተው ደግሞ አለጥርጥር ስርዓት፣ ህግ፣ ወይም መርህ አልበኝነት ይሆናል፡፡ ይህን ተከትሎ የሚመጣው አንድም መጠፋፋት ነው አለበለዝያም የቀውሱ ምንጭ የሆነውን ኢፍትሃዊነት አስወግዶ አስተማማኝ፤ በእጅጉ አስተማማኝ በሆነ መንገድ ፍትሃዊነትን ያረጋገጠ በህግና ህግ ብቻ የሚመራ ስብስብን መገንባት ነው፡፡ እንደኔ እምነት ከመጀመሪያው ምርጫ የሚያተርፍ ካለ መጀመሪያውኑ የስብስቡ አካል ያልነበረ ይበልጡንም በስብስቡ መፍረስ የሚቀዳጀው አስቀድሞ የታቀደ ስኬት ያለው ባዕድ ሀይል ብቻ ነው፡፡ ምክኒያቱም የአህያ ሞት ፍስሃ የሚሆነው ለጅብ ነው እንጂ ለተቀሩት ሌሎች አህዮች መርዶ ነው፤ ተጨማሪ ሸክም እየመጣ መሆኑን የሚገልጽ መርዶ፡፡

በነገራችን ላይ ዶ/ር ደብረ-ጽዮን በነካ እጃቸው የትግራይ ህዝብ ማለት ሕውሀት ማለት አይደለም ብለው በነበረና ህዝቡን ነጻ ባወጡት ኖሮ ብዬ መመኘቴን ሳልጽፍ ማለፍ አልፈልግም፤ መቼም “የዋህ!” ላለመባል ብዬ መመኘቴን አልተው ነገር…፡፡

ቸር ያሰማን!
አንድ ሰው ከአዲስ አበባ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *