ፈሶሎጂ – እሰይ! ፈሳሁ! ሐሹ! ፈሳሁ! በቃ! ፈሳሁ!  «ፈሶሎጂ» የሚለው ቃል ከሁለት የተለያዩ ቋንቋዎች ከፈለቁ ቃላት የተዋቀረ ነው፡፡ እነዚህም ፈስ የሚለው የአማርኛ ቃልና ሎጂ የሚለው የግሪክ ቃል ነው፡፡ ጥቅል ትርጉሙ ስለ ፈስ የሚያጠና ሳይንስ እንደማለት ነው፡፡

እንግዲህ ምን ይባላል! ከስነ ህይወታዊ (ባዮሎጂካል) አንድምታና ፋይዳው ባሻገር በገጣሚው መነጽር ሳይሆን በገጣሚው ብረት አይን ምናልባትም ጥልቅ በሆነው አይነ ልቦናዊ እይታው ፈስን እንደ አዲስ እያስተዋወቀን ነው፡፡ ሁላችን የሰው ዘሮች ከልጅነት እስከ አዋቂነት በአንድም በሌላም መንገድ የተሳተፍንበትን ተልእኮ እንደ እንግዳ ነገር እያበሰረን ነው፡፡ የሁላችን እውነት ለሁላችን ውሸትና አሳፋሪ ሆኖ እስከመቼ ይኖራል?!
ፈስ መሳቂያና መሳለቂያ እንዲሁም ማፈሪያ በሆነባት ምድር ቃሉም ተግባሩም ማሸማቀቁ የተለመደ ነው፡፡ አሁን ግን መልኩን ቀይሮ በግሩም ቃላት ተሞሽሮ ‹‹ፈሶሎጂ›› በተሰኘ የስንኝ ቋጠሮ ቀርቧል፡፡ ይህ ፈሶሎጂ የተሰኘ ግጥም አንድ ያለበትን ሁኔታ አሜን ብሎ መቀበል ያቃተው ብላቴና ያንጎረጎረው እሮሮ ይመስላል፡፡
ግጥሙን ከዘይቤያዊ አገላለጾች አንጻር ለመተንተን ሰፋ ያለ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም በወፍ በረር ቃኘት ለማድረግ ግን እሞክራለሁ፡፡ የግጥሙን የመጀመሪያ ስንኝ ስናየው ‹‹አይ አዎ›› ዘይቤ ይመስላል፡፡ እኛ የሶስተኛው ዓለም ህዝቦች ለአይናችን፣ ለአፍንጫችን፣ ለጆሮአችን… በስሜት ህዋሳታችን ሁሉ የምንጸየፈውን ነገር ነው፤ ‹‹…ለካስ ፈስም መድኃኒት ነው›› እያለ ደግማችሁ አስተውሉ እያለ የሚመክረን፡፡ ጥያቄው ግን ፈስ መቼ ነው መድኃኒት የሚሆነው የሚለው ነው፡፡ መቼም የመድኃኒት አስፈላጊነት ትርጉም የሚያገኘው ህመም ሲኖር ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የገጣሚው ጥልቅ እውናዊና ምናባዊ እይታ ጎልቶ የሚታየው፡፡
ፈስ መድኃኒት ይሆን ዘንድ በተጨባጭ የሚስተዋሉ (ምናልባትም ነግሰው የበላይነት ያገኙ) ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሳይንሳዊ፣ ማህበራዊ፣ ሰብአዊ፣ ስነልቦናዊ ብልጽግናና ስልጣኔያዊ… የሰው ዘር ይልቁንም የእናት አገር ህማማት ግሩም በሆነ መንገድ ተካትተዋል፡፡
እውነቱን አፈረጥርጦ ለመጻፍ ብእሩን ከሳለ ደራሲ የሚጠቅመውም ይኸው ነው፡፡ ዳሩ ግን ይህ ግጥም ራሱ በራሱ ላይ እየመሰከረ አሊያም ራሱን እየዋሸ ይመስላል፡፡ ታፍኛለሁ መተንፈስ አልችልም እያለ ይህን የመሰለ ግጥም ጀባ ብሎናል፡፡ እዚህ ላይ ድምዳሜ መስጠት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ገጣሚው አሁን በምን ውሳጣዊ ሁኔታ ላይ እንዳለ አይታወቅምና፡፡ ግጥሙ ግን በብሶትና በሰቀቀን የተሞላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹የላይኛው ሲከለከል ምናለ ትንሽ ብንፈታ›› ሲል ፈሳችንንም እንኳን መጥነን መሆን አለበት እያለን ነው፡፡ ይህንኑ ሲያጠናክረው ‹መቼም ነጻነት በራበው ምድር ‹‹ዘረጥን›› ቀድሞም አላውቀው› ይለናል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በገጣሚው እይታ መፍሳት ብዙ አስጨናቂ፣ አስገዳጅና ጨቋኝ ሁኔታዎችን ተከትሎ የሚመጣ የመጨረሻ አማራጭ ሆኖ ነው የቀረበው፡፡
በግጥሙ፤ ‹‹የላይኛው ሲከለከል…›› የሚለው የሚመረጥ እርምጃ ነው፤ ግን የላይኛው ሲከለከል ማለት ምን ማለት ይሆን? ፊት ለፊት ሲያዩት የአንደበት መታሰርን ለይቶ የሚመለከት ቢመስልም የግጥሙ ጠቅላላ እሳቤ አእምሮን አካሎ ከአእምሮ የሚፈልቁ ንግግርና ጽሁፎችን እንዲሁም ድርጊቶችን የሚሸፍን ይመስላል፡፡ እርግጠኛ ሆኖ ደፍሮ ለመተንተን በደራሲው ቦታ መሆንን የሚጠይቅ ቢሆንም፤ ‹‹ፈስ›› የሚለው ቃል ራሱ የተለመደውን ከሆድ የሚወጣ የተቃጠለ አየር የሚል ትርጉም ሊያጣ ይችላል፡፡ ምናልባትም አንዳች ብሶት ሲያይል የሚወልደው አመጽ አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቁም ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ ከሄድን ደራሲው እንደ ነብይ አሊያም መጪውን አሻግሮ እንደሚያይ ባለ ራእይ ሊቆጠር ይችላል፡፡

ፈሶሎጂ
እሰይ! ፈሳሁ!
ሐሹ! ፈሳሁ!
በቃ! ፈሳሁ!
አስተንፋሽ ቦታ ሲጠፋ ለካስ ፈስም መድኃኒት ነው።
የላይኛው ሲከለክል ልሳን ሳንቃው ሲከስም
ለካስ እንዲህ መድኃኒት ነው በታችኛው መተንፈስም።
የሆድ ብሶት ጉርምርምታ -የህሊና አበጥ እምቢልታ
ትንቅንቅ ውስጤ ሲመታ – አፍ ሲከረቸም በቃታ
ምናለ በታች ብፈታ!?
በፈስ አብዮት ድምታ -የማንስ አገር ተፈታ?
ወገኔ ባክህ ተጠየቅ – ፈስ ነፃ ፈቃድ ነው?
ወይስ የሽንት መንቆርቆር ማጀቢያ የፏፏቴው ሙዚቃ ነው?
የላይኛው ሲከለከል ምናለ ትንሽ ብንፈታ
ባሕር ማዶ እኮ ወገኔ አፍ ተከፋፍቶ ተገሳ
እግር ተነስቶ ተፈሳ።
አምቄ ተጠርንቄ አልሞትም እኔስ አጨሰዋለሁ!
ድርግም! አድርጌ እፈሳለሁ
ሆዴ እስኪከሳ ድረስ ድብን! አድርጌ እፈሳለሁ።
ሰው በሌላም ይዋረዳል ለመዋረዱም ግዴለም
ፈስ የዖዞን ማዳበሪያ እንጂ የቃየን መስዋዕት አይደለም።
ውጊያውን አንጀት ተንኩሶ አጅሬ ቁልቁል ሲረግጠው
መቋጠሪያዬ ሽምቀቁን ከዳር ዕዳር ሲያጠብቀው
እንደ ማታ ጎለል ሽብሽቦ በጅማት መቀነትነት ሽንሽኑን ሲጠረንቀው
እንደ ሌጋዎን ሽብዳ ከላይ እታች ሲያጣድፈው
ሆዴን ሽቅብ ገልብጦ እግሬን ሲያንከረፍፈው
ከርሴ ውስጡ ሲዳምን ከብሮ ሲያክል ተነፍቶ
በልቀቅ አትልቀቅ ትግል ደመና ሲዞር አስፋፍቶ
የሐምሌን ሰማይ አድርጎት ሆዴ «ድም»… «ግም»… ሲል
ሆዴ የነሐሴ ኩሬ ሆኖ እንዳፈቀረ እንቁራሪት
ቁርር… ቁርር..ጩርር.. ቧጭ ሲል
እንደጧት የኪዳን ደወል ከላይ እታች ሳቃጭል
ነጭ ላብ ፊቴን ሲያጠምቀው ሽምቀቅ..ጭንቅ.ድቅቅ..
ፉቅቅ… ጥምቅ… ጥልቅ ድብቅ ሲያደርገኝ
ከንፈሬን ስጨረግደው
ወገን ታዲያ ምናለ ምጤን ብገላገለው ?
ድምፁ እንዳይረብሽ አድርጌ ከቋጠሮው በስስ ብፈታው ?
መቼም ነፃነት በራበው ምድር «ዘረጥን» ቀድሞም አላውቀው
አንዴው በትንሽ በትንሹ እ-ሱሱሱሱ… እንጂ በየደቂቃው
ነገር እንዳይበላሽ ድምፁ ከመብረቅ ባርቆ
ያኔ ጥግ ከአድማስ ባሻገር ርቆ
ይሉኝታ ደንበር ተሻግሮ ሀፍረት በቁም ሲረታ
አቤት ያለው የደስደስ አቤት ያለው እፎይታ
የታችኛው ወናፍ ሸምቀቅ ቋጠሮ ውሉ ሲፈታ
አቤት ያለው የደስደስ አቤት ያለው እፎይታ!!
ወገን ታዲያ ምናለ
ያበጠ ጥቁር ሆድ ሁላ ከዚህች ምድረ አፍሪካ
የተገፋ ቀበተት ሁላ ከዚህች ምድረ እንካ ለእንካ
በእከከኝ ልከክህ ታክቲክ ባጉርሰኝ ላጉርስህ ዳካ
በሆድ አብዮት ገፈጠጥ የተነፋ ከርስ ሁላ በተቦካ ባልተቦካ
ወይም በሆድ አብዮት «ሆዱ ካገሩ የሰፋ»
«መድኃኔአለም ያጥብልንና» ሆዱ ካገሩ ሰፍቶበት
የጎረቤት ወሰን የገፋ
ወይም… በብግነት ድማሚት ሆዱ
ጥልቀት ላዕሉ የተነካ
ምናለበት ቢተነፍስ በእሱሱሱ… ድምፅ እየለካ።

የደራሲ ይስማዕከ ወርቁ ግጥም
ይቀጥላል

ፈሶሎጂ የተሰኘው ይህ ግጥም ፍትህና ነጻነት የጠማው ህዝብ (አውዱን እናንተው ድረሱበት) ያለበትን ሁኔታ እና መቃተት በፊት በር ሳይሆን በጓሮ በር ገብቶ ያሳየ፣ የተፈራውን የደፈረ፣ ከእውነታችን ወዴትም ማምለጥ እንደማንችል የጠቆመ፣ ከሁሉም ይልቅ ቻይናውያን ‹‹ካልደፈረሰ አይጠራም›› እንደሚሉት ‹‹ከጭንጋፍ ልጅ ልደት ይልቅ ወደል ፈስ እኮ ግልግል ነው›› በማለት አጉል መሐል ሰፋሪነትን በሚገባ ተችቶታል፡፡ ስለሆነም ግጥሙ ለአብዮተኞች ማጣቀሻ ሊሆን የሚችል ሰነድ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ያም ሆኖ የግጥሙን መሰረታዊ መንፈስ ጠለቅ ብለን ስንመረምር እያደር ብልጭ የሚሉ ፖለቲካ (ለምሳሌ ትንቅንቅ ውስጤ ሲመታ አፍ ሲከረቸም በቃ ሲል በአገሩ ሰፍኖ ስላለ ነጻነት የሚገፍፍ አምባገነናዊ ሥርዓት ያወሳል፡፡) ማህበራዊ የጨቋኝና የተጨቋኝ መደቦች መኖርን ሲያመላክት፤ ‹‹መድኃኔዓለም ያጥብብልንና ሆዱ ከአገሩ ሰፍቶበት የጎረቤት ወሰን የገፋ… ይላል፡፡
ገና ከጅምሩ ‹‹አስተንፋሽ ቦታ ሲጠፋ›› ማለቱ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መነፈግን የሚጠቁም ነው፡፡
‹‹ውጊያውን አንጀት ተንኩሶ አጅሬው ቁልቁል ሲረግጠው›› ሲል፤ አንዳች የጭቆናና የመብት ረገጣ ለመዘከር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
ከፍልስፍና አንጻር ካየነው ሰው መቼም አርፎ እንደማይቀመጥ ያሉትን እድሎች ሁሉ አሟጥጦ እንደሚጠቀም ወደፊትም መሄድ ካቃተው ወደ ኋላ እንደሚሄድ (ቆሞ እንደማይቀር) ነፍስያውም እድሜ ልኳን የኢ-መዋቲነት መሻት እንዳላት ግጥሙ ይጠቁማል፡፡ ለዚህ ጭብጥ አብነት የሚሆኑት ‹‹የላይኛው ሲከለከል…››
‹‹ለካስ መድኃኒት ነው በታችኛው መተንፈስም››
‹‹አምቄ ተጠርንቄ አልሞትም እኔስ አጨሰዋለሁ›› የሚሉት ስንኞች ይመሰክራሉ፡፡
ፈስ የመዋረጃው ብቸኛ መንገድ እንዳልሆነ ምናልባትም ከፈስ የባሱ ውርደትን የሚያስከትሉ የሰው ልጅ ገመናዎችን ሲጠቁም ደግሞ፦
‹‹ሰው በሌላም ይዋረዳል…›› በማለት ጠቀስ አድርጓል፡፡
በሌላ መልኩ የትውልዱን ሆዳምነት እና ለሆዱ ሟችነት ሲገልጽ፦
‹‹በእከክልኝ ልከክልህ ባጉርስ ላጉርስ ዳካ…፣
በሆድ አብዮት ገፈጠጥ… በተቦካ ባልተቦካ›› እያለ ነግሮናል፡፡
የግጥሙ የፊት ለፊት አንድምታ ፈስን ከተፈጥሯዊ ብሎም ባህላዊ እሳቤው ጋር ከአንድ ተራ የጠጅ ቤት ቧልት ባልተለየ መልኩ የቀረበ ነው፡፡ ግጥሙ ከግንባሩ ሲታይ እንደ አንድ አስቂኝ ተራ ግጥም እንዲሁ ስለ ፈስና ተያያዥ የሥርዓተ እንሽርሽሪት ጉዳዮች ቢያትትም፤ እዚህ ላይ ግጥሙ ፈስ መፍሳትን እንደ ነውር የሚቆጥሩ ጨቋኝ ባህሎችን ለመተቸት ያህል የሀበሻን ባህል ባህር ማዶ ካለው የሰለጠነው ህዝብ ባህል ጋር ለማነጻጸርም ሞክሯል፡፡

አዲሱ ገረመው – መዝናኛ addis Zemen

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *