የቄሮ ሊቀመንበር እኔ ነኝ በማለት ራሱን በመሰየም መታወቂያ በማዘጋጀት እና የቅርብ ተጠሪውን የከተማዋን ፖሊስ አዛዥ ስም በመፃፍ የተለያዩ ተቋማት ስፖንሰር እንዲያደርጉት ሲያስገድድ የነበረ፤ እንዲሁም በቄሮ ስም ቲተር እና ማህተም በማስቀረፅ የቄሮ መታወቂያ በማሳተም ሲሸጥ የነበረ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሏል


 በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የህግ የበላይነትን ለማስከበር በተወሰደ እርምጃ እስካሁን 171 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ።

የኦህዴድ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እንዳስታወቁት፥ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በተለያዩ ህግ ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው ሲንቀሳቀሱ ነው።

በዚህ መሰረትም ሱሉምታ ከተማ በቄሮ ስም በመንቀሳቀስ የግለሰብ ሰዎችን ቤት በማፍረስ የቤት ክዳን ቆርቆሮ በመስወድ ላይ እያሉ 4 ሰዎች እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል ብለዋል አቶ አዲሱ።

በሻሸመኔ ከተማም ባለፈው ሳምንት በከተማዋ ከተፈፀመው ወንጀል ጋር ተያያዥነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 7 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቀዋል።

በቡራዩ ከተማ በቄሮ ስም ሲነግድ የነበረና የቄሮ ሊቀመንበር እኔ ነኝ በማለት ራሱን በመሰየም መታወቂያ በማዘጋጀት እና የቅርብ ተጠሪውን የከተማዋን ፖሊስ አዛዥ ስም በመፃፍ የተለያዩ ተቋማት ስፖንሰር እንዲያደርጉት ሲያስገድድ የነበረ፤ እንዲሁም በቄሮ ስም ቲተር እና ማህተም በማስቀረፅ የቄሮ መታወቂያ በማሳተም ሲሸጥ የነበረ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል አቶ አዲሱ።

በለገ ጣፎ ለገ ዳዲ ከተማ የ62 ወጣቶችን በማዘጋጀት እና ፎቶ ግራፋቸውን ወረቀት ላይ በማሳተም፤ ይህ የቄሮ አደረጃጀት ከቀበሌ እስከ ክልል ድረስ እውቅና ማግኘት አለበት በማለት ወጣቶችን ሲያነሳሱ እና ሲያሳስቱ የነበሩ 2 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በጅማ ከተማም በህገ ወጥ ስራ ላይ የተሰማሩ፣ ህገ ወጥ ግንባታ የገነቡ እና ያስገነቡ እንዲሁም የመንግስትን ስራ ሲያደናቅፉ የነበሩ 42 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ያሉት አቶ አዲሱ፥ ከእነዚህ ውስጥ 8 ሰዎች ላይ ማስረጃ ተደራጅቶ ክስ ሊመሰረትባቸው በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም ሁለት ሽጉጦች እና ከ180 በላይ ህገ ወጥ ጥይቶች መያዛቸውን አስታውቀዋል።

በአዳማ ከተማም በከተማዋ በቅርቡ ተፈጥሮ ከነበረው ግጭት ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ግንኙነት ነበራቸው ተብለው የተጠረጠሩ 8 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በሞጆ ከተማም ጨለማን ተገን በማድረግ ፋብሪካ ለመዝረፍ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 2 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል አቶ አዲሱ።

በሰበታ ከተማ ደግሞ ህገ ወጥ ግንባታ ያካሄዱ፣  ምግብ ቤት ገብተው ተጠቅመው አንከፍልም የሚሉ፣ ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ህግ አስከባሪ አካላት ሲናገሯቸው ሲደበድቡ የነበሩ 14 ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለዋል ሲሉ አቶ አዲሱ ገልፀዋል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ በቄሮ ስም በመሬት ወረራ ላይ የረሳተፉ 32 ተጠርጣሪዎች በቁጠጥር ስር የዋሉ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ 2 ተጠርጣሪዎች የአዳማ ከተማ መሃንዲሶች የነበሩ እና በስነ ምግባር ችግር የተባረሩ ናቸው።

በተመሳሳይ በፈንታሌ ወረዳ የብሄር ግጭት እንዲቀሰቀስ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ እና ከዚህም በማለፍ የመንግስት መስሪያ ቤት ድረስ በመሄድ የስራ ሀላፊዎችን የደበደቡ 4 ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በተጨማሪም በቦረና ወረዳ መንገድ በመዝጋት አመፅ ለማነሳሳት ሞክረዋል የተባሉ 55 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስው ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑንም አቶ አዲሱ አክለው ገልፀዋል።

በተያያዘ ዜና በኢሉ አባ ቦራ ዞን ሁሩሙ መረዳ ጨማሪ በተባለ ቀበሌ በህገ ወጥ ተግባር የተሰማሩ እና ብሄር ብሄረሰቦች ላይ ያተኮረ ጥቃት የፈፀሙ 7 ተከሳሾችም ከ2 እስከ 7 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጥተዋል።

በዚህም መሰረት አለቶ ዘላለም አለበል፤ አቶ ተካ ጥሩነህ፣ ወጋሪ ልጃለም በ7 ዓመት ጽኑ እስራት፣ አቶ ተካልኝ ሽመልስ በ2 ዓመት ከ6 ወር፣ አቶ ወንድሙ በቀለ በ1 ዓመት ከ8 ወር እንዲሁም አቶ ጌታቸው በቀለ በ1 ዓመት ከ2 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል ብለዋል አቶ አዲሱ።

በሙለታ መንገሻ አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 14፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የትህነግ "ውሮ ወሸባዬ" - የመንግስት ሩጫ - የሃላኑ የኢትዮጵያን ቋንጃ የመበጠስ የእባብ አካሄድና ባንዳዎች!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *