አቶ በረከት እጃቸውን ታጥበውና ተለቃልቀው መኖር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። በስማ ባይጠቅሱትም ልክ እንደ ጲላጦስ ማለት ነው። ቢልላቸው ቀሪ ህይወታቸውን ቤትክርስቲያን እያስቀደሱና ንስሃ እየገቡ ሳይሆን መጥፋኦቻቸውን እያገላበጡ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መኖር ይመርጣሉ። ጎንደር እስር ቤት ” ገንዝብ ሲናገር ፍትህ ጭጭ ይላል” በሚል ግድግዳው ላይ በእጅ ጣት ደም ተጽፏል።

“ባድመ የእኛ አይደለችም” በማለት ኢትዮጵያን ወራሪ አድርገው Eritrean Oppositions Arabic Paltalk በሚሰኝ የኤርትራ ተቃዋሚዎች የፓልቶክ መወያያ ክፍል እንግዳ ሆነው ከተናገሩ በሁዋላ በረከትና አገር ወዳዶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መለያየታቸውን በርካቶች ጠቁመው ነበር።

የዳሽን ቢራ የቦርድ ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት በግል አካውንታቸው ገንዘብ እንደገባላቸው የሚያሳይ መረጃ ፣ ከወቅቱ የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ጋር የነበራቸው ትስስርና የግዢ ድራማ በሰራተኛ ማህበሩ አማካይነት በተከታታይ በሪፖርተር ጋዜጣ ይፋ ከሆነ በሁዋላ የተፈጠረውን ለሚያውቁ አቶ በረከት ቢያንስ ዝምታ ሊመርጡ እንደሚገባ አስተያየት እየተሰጠ ነው።

ከምርጫ ፱፯ ቢጀመር እንኳ አቶ በረከት በሚዲያ ብዙ ሊጠየቁ የሚገባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ጥሩ ባለሙያ አላጋጠማቸውም። አገሪቱን እየናጣት ካለው የመንጋ አስተሳሰብ በተመሳሳይ በመንጋ የሚተራመሰው ” የጋዜጠኛነት” ብቃት እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ሊሞገቱና የኢንቨስቲጌቲቭ ስራ ሊሰራባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ድፍረቱና ፍላጎቱ አይታይም።

ለዚህም ይመስላል እንደ አሸን የፈሉትና፣ ሲፈጠሩም ከጀርባቸው ምክንያት፣ ዓላማ፣ ደጋፊና ድጋፍ ለመሆን ታቅደው የተቋቋሙ ሚዲያዎች ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ለመስማት ተገደናል። ውይም ተፈርዶብናል። የቃለ ምልልሱ አካሄድ ስርዓት ማጣት፣ የጥያቄዎቹ እርምጥምጥነት፣ ራሱ ቃለ ምልልሱ የወጌሻ አይነት እየሆነ ወይ ሙያተኛ የሚባለበት ደረጃ ተደርሷል።

አቶ ጉዋንጉል ተሻገር በፌስ ቡክ ገጻቸው በሌላ በኩል አቶ በረከት ትንታግ ጋዜጠኛ አልገጠማቸውም። ሰይፉ እና የዶችቬሌ የአማርኛው ክፍል ጋዜጠኞች የረባ ጥያቄ አላቀረቡላቸውም። ትንታጉ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ኢንተርቪው እንዲሰጡ ሳያውል ሳያድር ሊጠይቃቸው ይገባል። እምቢም ካሉ እምቢ ብለዋል ብሎ ለህዝብ ማሳወቅ ያስፈልጋል።ከአቶ በረከት ጋር የሚደረግ ውይይት የፃፉት የተናገሩት በተለይ 97 በደኖ አርባጉጉ ጉራፈርዳ ሰው ከነህይወቱ ቆዳው የተገፈፈበት፣ የሚያደንቁት መለስ ዜናዊ አማራ እንደ ከብት ሲታረድ ከምስራቅ ጎጃም የሄዱ አማራዎች ናቸው፣ ዛፍ ሲቆርጡ ደን ሲያቃጥሉ ተገኝተው ነው ሲል ሞብን በማበረታታት ያለሀፍረት የተናገረው እየተጠቀሰ እየተጣቀሰ የሚደረግ በእጅ ቦንብ የመወራወር ያህል ከባድ Hardtalk ነው መሆን ያለበት። ሰይፉ እና ዶችቬሌ አንተ ልበልህ ወይስ አንቱ ተባብለው ተፎጋግረው ምንም ቁም ነገር ሳያወሩ ዊኪናኪካ ዋኪናኒካ ተባብለው ጨረሱ። ያሳዝናል። 

ጉዳዩን የአቶ በረከት ነገር ግንባር አደረገው እንጂ ከሁሉም ወገን ራሱ ብአዴንን ጨምሮ አቶ ጉዋንጉል እንዳሉት የከረረ ጥያቄ በማንሳት ሊሞገቱ ይገባቸዋል። በስፋት እንደሚታየው ለሙያው ባዳ የሆኑ የሚያምርባቸውን የጨዋታና የቀደዳ ስራቸውን ትተው በአገራዊ ጉዳይ ላይ አድምተው ላይሰሩ ሲፈተፍቱ ማየት ቅር ያሰኛል።

አቶ በረከትም ሆኑ ማንኛውም ዜጋ የመናገርና መርጃ የማስተላለፍ፣ ብሎም ራስን የመከላከል መብት አላቸው። ሲሆን ሲሆን የአገሪቱ ብሄራዊ ሚዲያ መድረኩ ለህዝብ ክፍት የሆነና ጥያቄ ማቅረብ እንዲቻል የሚፈቅድ ቃለ መጠይቅ አዘጋጅቶ ሁለቱንም አካላት ቢያቀርብ ምንኛ ማለፊያ በሆነ ነበር። ያም ካልተቻለ አንድ ሞጋች ክፍለ ጊዜ ላይ አቶ በረከትን አቅርቦ መከራከር አግባብ ይሆናል። እነ ዶክተር መረራ የሚመሩት ቦርድ ይህንን ካልፈቀደም በግልጽ ሊነገር ይገባል።

አቶ በረከት በተለያዩ ሚዲያዎች ተንፍሰዋል። መባረራቸውን እንደማይቀበሉ ገልጸዋል። ከጥረት ጋር በተያያዘ ችግር እንደሌለባቸውን አመልከተዋ። ህዝባዊ መሆናቸውን፣ ለሕዝብ ሲሉ የተጎዱ እንደሆነ፣ አሁን ያለው ለውጥ የሳቸው ወጤት ሰለመሆኑና በየትኛውም ክልል የመኖር ህገመንግስታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው እንደሚፈልጉ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከሳቸው መነሳት ጋር እጃቸው እንዳለበት ተናገረዋል። ሌላም ሌላም። አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝም ተላላኪ ሆነው ተስለዋል። ይህ ሰፊ ጉዳይ ነውና ከተናገሩ በቁንጽል ሳይሆን በሚሞገቱበት ደረጃ ቢሆን ሙሉ ሰእል ይሰጣልና ይታሰብበት። ምክንያቱም ከላይ እንደተባለው ለእንደዚህ ዓይነት ዓላማ የተፈለፈሉ ሚዲያዎች ገለባ መረጃ እየበተኑ ነገሩን እንዳያዛቡት፤

አቶ ጉዋንጉል ሌላም ነገር አንስተዋል ህግን በተመለከት

አንድ ሰው በፍርድ ቤት ካልተፈረደበት በቀር ንፁህ ሰው ነው ተብሎ ይገመታል። እቶ በረከትም የዚህ የሕግ ግምት Legal presumption ተጠቃሚ ሊሆኑ ይገባል። በብዐዴን ጽ/ቤት ኃላፊና በፓለቲካ ጉዳዮች ተጠሪ አቶ ምግባሩ ከበደ ጨዋነት የተላበሰ አነጋገር መሰርት 3ት ሕጎች አግባብነት ይኖራቸዋል። አንዱ የአስተዳደር ሕግ ሲሆን አቶ በረከት እንዲታገዱ መሰረት የሆነው ህግ ነው። እገዳው ወደመወገድ ሲለወጥ እርምጃው በመባረር ብቻ የሚቆም ሳይሆን በአማራ ክፍለሀገር ፍርድቤት በፍትሐብሔር ገንዘቡን እንዲመልሱ ይከሰሳሉ።እንዲሁም በዚያው በአማራ ክፍለሀገር ፍርድ ቤት በወንጀል ተከሰው ከተፈረድባቸው ዘብጥያ ይወርዳሉ ማለት ነው።

 

በዚሁ መሰረት አቶ በረከትን በህግ ባልተረጋገጠ ጉዳይ መፈረጅም አግባብ አይሆንም። አቶ በረከትም ሆኑ ወዳጆቻቸው ባለስልጣናት በግልና በጋራ የሚጠየቁባቸው እጅግ በርካታ ወንጀሎች በአገራችን ተፈጽመዋል። ብአዴን እንዳለው ጉዳዩ ከፖለቲካ ወሳኔ በሁዋላ ወደ ህግ ያመራልና አቶ በረከትም ራሳቸውን ለመከላከል፣ ቀጪው ክፍልም ውሳኔው አግባብ መሆኑንን ለማሳየት ጊዜ ይኖራል። የሶማሊ ክልል መሪ የነበረው ወሮበላው አብዲሌ ጉዱን ሲያፍረጠርጥ ለመስማት እንደተዘጋጀነው ሁሉ፣

አቶ በረከት እንዳሉት እጃቸውን ታጥበውና ተለቃልቀው የሚቀመጡ ሰው ናቸው ወይስ…. እንደ ጲላጦስ .. ጎንደር እስር ቤት ውስጥ ” ገንዘብ ሲናገር ፍትህ ጭጭ ይላል” በሚል አንድ እስረኛ የእጁን ጣት በመብጣት ጽፏል። ያ ሰው ማን ያሰረውና እንዲት የታሰር ይሆን!!

 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *