ይልቁንስ ብአዴን እንደጀመረው በውስጡ የተሰገሰጉትን ለአገርም ሆነ ለአማራው ሕዝብ ደህንነትና ኅልውና ያልቆሙትን የአመራር አባላትን ለአንዴና ለመጨረሻ ከድርጅቱ ጠራርጎ ሊያስወግድ ይገባል። ይህ ደግሞ የኮሚቴአችን ብቻ ሳይሆን የመላው አማራ ሕዝብ እምነትና ሀሳብ መሆኑ አያጠያይቅም።

ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
ነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ/ም  (September 2, 2018)

በአገራችን በመካሄድ ላይ ያለው ሕዝባዊና አገራዊ ለውጥ በግንባር ቀደምትነት ከመሩት አንዱ የሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን የድንበር ጥያቄ አስመልክቶ ሰሞኑን ያወጣውን መግለጫ የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ በአንክሮ ተመልክቶታል።

የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ባወጣው በዚህ መግለጫ የሱዳን መንግሥት በተለይ “ነብስ ገቢያ አካባቢ ሰፍሮ የነበረውን የሱዳን ወታደር የሰራውን ካምፕ አፍርሶ ከድንበሩ እንዲወጣ” እና የፌዴራል መንግሥቱም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በአስቸኳይ እንዲያስፈጽም ያቀረበው ጥያቄ ወቅታዊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ መሠረታዊና ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ አገራዊ አጀንዳ እንደሆነ ኮሚቴአችን በጽኑ ያምናል።

ሰላም የማስከበር ኃላፊነት የጋራ ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ የሱዳን ወታደሮች ብቻ በድንበሩ አካባቢ እንዲሰፍሩ መደረጉ፤ የኢትዮጵያ ገበሬዎች ለጥቃት ያጋለጠና ለአካባቢው ሰላም እጦት ጠንቅ መሆኑን የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ መገንዘቡን ለመረዳት ችለናል።

ብአዴን የአገራችንን ኅልውና ለማስከበርና የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ከቀደምት አባቶቻችን በወረሰው ወኔና አገራዊ ፍቅር መሠረት ለሚወስዳቸው እርምጃዎች በሙሉ ኮሚቴአችን ከፍተኛ አድናቆት አለው።

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሜቴ ከዛሬ 10 ዓመታት በፊት ሲቋቋም ይዞት የተነሳውና በእጅጉም ያሳስበው ጉዳይ ይህ የአገራችንን ሉዓላዊነት የደፈረ፣ የሕዝብ ተሳትፎ የተነፈገውና የአገርን ጥቅም አሳልፎ የሰጠው “ስምምነት” እንደሆነ ኮሚቴአችን በየጊዜው ባወጣቸው መግለጫዎች ማሳወቁ አይዘነጋም።

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የአገርን ኅልውና ከምንም ባለመቁጠር በተለይም አማራውን ከድንበሩ ለማራቅና ቀጥሎም ድብቅ ዓላማውን በረዥሙ እቅዱ እውን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ የአደባባይ ምስጢር ነው።

ዛሬ ሁኔታው ተለውጦ፤ ይህ አገራዊ አጀንዳ በመንግሥት በተለይም በአማራው ክልላዊ አስተዳደር በከፍተኛ ደረጃ መያዙን እውን ሆኖ ስናየው ኮሚቴው ከፍተኛ ደስታ ያገኘበትና ለብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባላትና ለከፍተኛው አመራር አባላትም ያለንን ልዩ አክብሮት በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን።

የትላንቱ የሕወሓት ሴራ እንደንጋት እየጠራ በመጣበት በአሁኑ ወቅት “ስምምነቱን” አስመልክቶ የብአዴንን አመራር አባላትን ስም ለማጉደፍና ከሕዝቡ ጋር ለማጋጨት ሕወሓት የፈጸመውን ደባ የፌዴራል መንግሥቱ በአስቸኳይ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ያቀረበውን ጥያቄ የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ሙሉ በሙሉ የሚስማማበት ነው።

ለሕዝብ የቆመ መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄ እንደሚቆረቆር ስለምንገነዘብ የድንበር ጉዳይ ኮሜቴ ከመንግሥት ጋር በመሆን የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን እናሳውቃለን።

በዚህ አጋጣሚ ሳንጠቅስ ማለፍ የማንፈልገው ጉዳይ፣ ሰሞኑን አቶ በረከት ስምኦን የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ያወጣውን አቋም መግለጫ በተለይም የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር ጉዳይ አስመልክቶ የወሰደውን አቋምን ከሱዳን ጋር ወደ ጦርነት የሚያስገባ ጸብ አጫሪ ተግባር ነው ሲሉ የሰጡት አስተያየት በእጅጉ የሚያስደንቅና ኃላፊነት የጎደለው አስተያየት ሆኖ አግኝተነዋል። ይህ አባባላቸው የሚጠቁመው ነገር ቢኖር፤ በብአዴን ውስጥ የመሽጉ የሕወሓት ወኪሎች ብአዴንን ላለፉት 25 ዓመታት ያፈኑት አልበቃ ብሏቸው፤ ዛሬ ንቅናቄው በአዲሱ የለውጥ ጓዳና መጓዝ መጀመሩን ማየት ስላልፈለጉና እርምጃውንም ለማደናቀፍ አሁንም ያልተኙ መሆናቸውን ነው።

ትላንት ከደቡብ ሱዳን የተነሱ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባት በጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ ግድያና ዝርፊያ ከፈፀሙ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህፃናት ታፍነው ሲወሰዱ፣ በቤንሻንጉልና ጉሙዝ በኩል የሱዳን ጦር ጥቃት ሲፈጽምና የወገኖቻችን ሕይወት ሲቀጥፍ አንድም ቃል ያልተነፈሰ ሰው ዛሬ ብአዴን የሱዳን ጦር ከኢትዮጵያ ድንበር ለቆ እንዲወጣ እንዲደረግ ፌዴራል መንግሥትን ሲጠይቅ እንዴት ድርጊቱን ፀብ ጫሪ ነው ሊሉ ቻሉ?

የቀድሞው ሕወሓት መራሹ መንግሥት ሥልጣን ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፤ በስሜን ምእራብ የአገራችን ድንበር አካባቢ በተለይም በመተማ ዙርያ በሚገኙ በነፍስ ገቢያና በሌሎች ቦታዎች የሱዳን ወታደሮች በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙ የአማራ ክልል መሪ ነይ ባዩ አቶ በረከት ስምኦን ምን ነው ድምፃቸው እንደዛሬው ነጋ ጠባ በተለያዩ ሚዲያዎች አልተሰማም ? በቅርቡ የሱዳን ጦር በሕወሓት ሚሊሻዎች እየታገዘ በነፍስ ገቢያ አካባቢ ጦርነት ሲከፍትና ታዋቂና ጀግና የሆኑ የአካባቢው ገበሬዎች ውድ ሕይወታቸውን ሲያጡ ምነው አቶ በረከት ይህ በሱዳን በኩል የፀብ አጫሪነት ተግባር ነው አላሉም? ይህን ለመገንዘብ የጠለቀ እውቀት አይጠይቅም። ሕወሓት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መከበር ይልቅ ለሱዳን ጥብቅና የቆመ መሆኑ የ27 ዓመቱ ታሪክ ያሳየው ሀቅ ነው።

ይልቁንስ ብአዴን እንደጀመረው በውስጡ የተሰገሰጉትን ለአገርም ሆነ ለአማራው ሕዝብ ደህንነትና ኅልውና ያልቆሙትን የአመራር አባላትን ለአንዴና ለመጨረሻ ከድርጅቱ ጠራርጎ ሊያስወግድ ይገባል። ይህ ደግሞ የኮሚቴአችን ብቻ ሳይሆን የመላው አማራ ሕዝብ እምነትና ሀሳብ መሆኑ አያጠያይቅም።

የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት በቆራጥ ልጆቿ የከበራል!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *