ጸጋዬ አራርሳ አስቀድመው የቦታውንና የብሄሮችን ስም ጠርተው መቀሰቀሳቸውን የሚገልጹ ለተፈጠረው ችግር ሁሉ በግንባር ቀደም ይከሷቸዋል። በሌላም በኩል “የሚከፈላቸውና በጀት የተቆረጠላቸው ዘራፊዎችና አውዳሚዎች አሉ” ሲሉ የሚናገሩ በርካታ ናቸው። ይህ ሁሉ የሚሆነው የተጀመረውን ለውጥ የሚመሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ኦህዴድና ካቢኔያቸው የአገርን ሰላም ማስጠበቅ አልቻሉም በሚል በሕዝብ ያላቸው ተቀባይነት ለመሸርሸር ስለመሆኑ ጥርጥር የለም።

ኦነግና ሆነ ግንቦት ሰባት እንዲሁም በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ዝርፊያና ማውደምን ማዕከል ላደረገው የውንብድና ተግባር ጅርባቸውን እንደሚሰጡ፣ እንደማይቀበሉትና ከድርጅቶቻቸው ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው በይፋ አስታውቀዋል። ይህንን ተከትሎ ነው ” እነማን ናቸው ይህንን የወንበዴ ቡድን በገንዘብ እየደጎሙ የሚመሩት፣ የሚያደራጁት ” የሚለው ጉዳይ ገሃድ እንዲወጣ የህዝብ ፍላጎት ነው።

በቡራዩ ይህ አሳዛኝ ድርጊት ከመፈጸሙ በፊት ዛጎል ያናገረው አንድ ወጣት ” ሁሉም ነገር ያስጠላል። በወሬ ደረጃ የሚሰማው ደስ አይልም። ሁሉም ታጥቋል። ኦህዴድ መዋቅሩ እስከ ቀበሌ አልወረደም። ስጋት አለኝ። ህዝብ በጠቅላላ የለማን ቲም ነው የሚደግፈው። ግን ምን እንደሚፈልጉ በግልጽ የማያስረዱ ቡድኖች አሉ። ህዝብ በዚህ ጉዳይ ደስተኛ አይደለም ” ሲል ተናግሮ ነበር።

ምስል – በቡራዩና አካባቢው ጥቃት ፈጽመው እንደ ጀግና ምስላቸውን የሚለጥፉት ወረቦሎች መካከል

፩

ከዚህ ወጣት ንግግር መረዳት እንደሚቻለው በየአካባቢው በታችኛው መዋቅር ላይ የበላይ የሆነ የተደራጀ የዘራፊና የሁከት ቡድን ሴል መኖሩን ነው። ይህ ሴል ለውጡ ባስከፋቸው ክፍሎች የሚደገፍ እንደሆነ ይነገራል። አክቲቪስት የሚባሉት ወገኖችም ይህንኑ ነው የሚያረጋግጡት። 

አቶ ዳውድ ኢብሳ እግራቸው አዲስ አበባን እንደረገጠ ” ለውጡን እንደግፋለን፤ አብረን ከመንግስት ጋር ለመስራት ነው የመጣነው” ብለዋል። በዋና ንግግራቸው ላይ ” እኛ እናልፋለን። ሕዝብና አገር ግን ይቀጥላሉ” ሲሉ ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎች የምትመች አገር እንድትሆን ለመስራት ጽኑ እምነት እንዳላቸው፣ ከዚህም በላይ አባሎቻቸውን የማሰልጠንና የማስተማር፣ ሰራዊታቸውንም መልሰው የማንቃት ስራ እንደሚሰሩ በግልጽ ነው የተናገሩት።

በዛላንበሳ አቀባበል የተደረገለት የኦነግ ሰራዊት ወኪልም ” …ኦነግ የሚታገለው ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ ነው የሚል የተሳሳተ አመልከካከት አለ። እኛ የምንታገለው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው” ሲል ተደምጧል። ቄሮ ይሚባለው ሃይል በዲሲፒሊን እንደሚመራና ይህንን አይነት የውንብድና ተግባር እንደማይፈጽም አመራሮቹ ይናገራሉ። እንግዲህ እንደ እነሱ ገለጻ ኦሮምኛ እየተናገሩ የሚዘርፉትን ወንበዴዎች ማንነት ያማጣራት ጉዳይ የመንግስት ብሎም የክልሉ ጉዳይ ይሆናል።

ለምርመራው አሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት ከሰባ በላይ ዘራፊዎች በቂ ናቸው። አስገራሚው ጉዳይ እነዚህ በህቡዕ የተደራጁ ወንበዴዎች በቡራዩ አሸዋ ሜዳ፣ አንፎ ከታና የተለያዩ አካባቢዎች ሲዘርፉ፣ አካል ሲያጎድሉ፣ ንብረት ሲያወድሙ የሚያሳይ ምስላቸውን ይፋ እያደረጉ መሆኑ ነው።

አገሪቱ ላይ በተጠና መንገድ ስራ አጥነትን ለመቅረፍ ከመስራት ይልቅ የጎሳ ፖለቲካን በማራመድ ህዝብ እርስ በእርሱ እንዳይተማመን፣ ቤተሰብ አንዱ አንዱን እንዲሰልለው በጀት ሲከሰክስ የኖረው የመለስ አስተዳደር ያፈራቸውን ስራ አጥ ወጣቶች እየደለሉ ለጥፋትና አገር ለማተራመስ ተግባር ያደራጇቸው ክፍሎች የህቡዕ አደረጃጀት እስካልተገለጠ ድረስ ችግሩ ቦታና ጊዜ እየለዋወጠ እንደሚቀጥል ጥርጥር የለውም። 

በሶማሌ ክልል የተለኮሰው እሳት ነብስ በልቶ፣ ንብረት አውድሞ፣ የሃይማኖት ተቋማትን አንድዶ፣ በሚሊዮን አፈናቅሎ ዛሬ በቁጥጥር ስር ቢውልም፣ ያንን ሁሉ ወንጀል የፈጸመውና እንዲፈጸም መመሪያ ተቀብሎ ሲያሰራጭ የነበረው አብዲ ኢሌ ” ለምን ታሰረ” በሚል ዘራፍ ሲሉ የነበሩትን ወገኖችን ህዝብ በምን ያህል ደረጃ እንደታዘበ ልቡ ያውቀዋል። “ታዋቂ ነን” የሚሉት አፍቃሪ አብዲ ኢሌዎች ” አብዲ መብቱ ተጣሰም” እያሉ እየተከራከሩ ነው።

በድሬ ደዋ፣ በሶዶና በሃዋሳ በተመሳሳይ የተፈጸመውና ሰፍቶ የከፋ መተራመስ ይፈጥራል የተባለው ቀውስ እንዲቆም ሲደረግ አሁን አዲስ አበባንና አዲስ አበባ ዙሪያ የተጀመረው ነውጥን የመዝራት፣ ዝርፊያን የማራባት፣ ቅርሶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃትና ይህንኑ ተከትሎ ህዝብ ከሕብ እንዲጫረስ ገጀራና ጦር ማሰለፍ የተመረጠበት ደረጃ ተደርሷል። አብዛኞች እንደሚሉት ነገሩ ረገበ እንጂ አዝማሚያው ቀላል አልነበረም።

በቡራዩ አሸዋ ሜዳ፣ አንፎ ከታና የተለያዩ አካባቢዎች የተፍጠረውን ጸያፍ ድርጊት እያለቀሱ የገለጹ አባት ” ምን አደርግናቸው…. ደጎች ሸሽገውን ከልጆቼ ጋር አተረፉን። ንብረቴ ድርና ማግ ነው አውጥተው አቃጠሉት” አሉ። አንድ እናት ” አይታወቁም” አለች። ” ከመቶ በላይ ሆነው በየቤቱ እየገቡ ይዘርፋሉ…” ሌላኛው ከፖሊስ ጋር በኦሮሚኛ ይነጋገሩና በጀርባ ዞረው እንደሚመጡ ይናገራሉ። ህዝብ ይሸሽጋል። የተደራጁ ሌቦች ይዘርፋሉ። የገርፋሉ።ንብረት ያወድማሉ። በዚህ መልኩ እንዴት መቀጠል ይቻላል?

2222.jpg

ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ጣታቸውን የሚቀስሩባቸው ለውጡ ካስከፋቸው አካላት ጋር የሚሰሩ ከውጭ የገቡና ደጋፊ መስለው የሚሮጡ አሉ። ይህ የህቡዕ አካል በውጪ የሚገኙ ተባባሪዎችም እንዳሉት ይጠቁማሉ። እነዚህ በሁለት ቢላ እየበሉ ያሉ ወገኖች በቅርቡ ራሳቸውን እንደሚያረክሱና ውዳቂ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። እነዚህ ክፍሎች እቅድ ነድፈው የሚሰሩ፣ ኮድ የሚልኩ፣ ላያቸው ለውጡን የሚደግፍ፣ እጅግ ሰፊ ተከታትይ ያላቸው፣ ነገር ግን በግልጽ ፍላጎታቸው የማይታወቅ ናቸው። የአቶ ኢብሳ አገር ቤት መግባትና አስመራ ላይ ኢትዮጵያን ለመገንባት ስምምነት የደረሱ መሆናቸው፣ ካላይ በተገለጹት ሃይሎች ” አስመራ ተቀምጦ ጊዜውን እና እድሜውን የፈጀ ጡረተኛ” በሚል ሲወገዙ መኖራቸው ጉዳዩን ወደ ፍጻሜ እንደሚያቀርበው ይጠበቃል።

ዳውድ ኢብሳ ቄሮ የሳቸው አደረጃጀት መሆኑን በድጋሚ መግለጻቸው አሁን ነገሮች የሚጠሩበት ጊዜ መቃረቡን አመላካች እንደሆነ በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ ምልክትም ታይቷል። ፋና ከታች ያለውን ዘግቧል

በቡራዩና አካባቢው ለንጹሀን ሞትና ጉዳት እንዲሁም ለንብረት ውድመት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ከ70 በላይ የተደራጁ ዘራፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

በቡራዩ አሸዋ ሜዳ፣ አንፎ ከታና የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት 2 ቀናት ለንጹሀን ሞትና ጉዳት እንዲሁም ለንብረት ውድመት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ከ70 በላይ የተደራጁ ዘራፊዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለማየሁ እጅጉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፣ በአካባቢዎቹ የተደራጁ ዘራፊዎች በፈጸሙት ድርጊት በሰዎች ህይወትና አካል ላይ ጉዳት ደርሷል።

በርካታ ህብረተሰብም ከመኖሮያው የተፈናቀለ ሲሆን፥ ከፍተኛ ንብረትም ወድሟል።

በአሁኑ ሰአትም አካባቢዎቹ ሙሉ በሙሉ የተረጋጉ መሆናቸውንም ነው ኮሚሽነር አለማየሁ የገለጹት።

የክልሉ ፖሊስ አካባቢዎቹን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ዳግም ድርጊቱ እንዳይፈጸም ጥበቃ እያደረገ መሆኑንም ነው የተገለጸው።

የአካባቢው ሽማግሌዎችም ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች በማወያየት ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹ በሁለት ዙር ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት ባቀረቡት ቅሬታ ፖሊስ ጥበቃ እንዲያደርግላቸውና ወንጀኞችን በአፋጣኝ ለህግ እንዲያቀርቡላቸው ጠይቃዋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *