የትግራይ ክልል አሁን የተፈጠረውን አለመረጋጋት አስመልክቶ ስጋቱን ገለጸ። የፌደራልና የክልል መንግስታት ይህ ሁከትና ብጥብጥ በመላው ኣገሪቱ አንዳይሰራጭ ልዩ ትኩረት አንዲሰጡ ኣሳስቧል። ልዩ ትኩረት ያለውን ግን ኣላብራራም። በለውጡ ኣካሄድ ማኩረፉን በተለያዩ አግባቦች ሲያስታውቅ የሰነበተው ህወሃት ያወጣው መግለጫ የአሽሙር ያህል አንደሚቆጠር አስተያየት አየተሰጠበት ነው።
አገሪቱ በጎሳ ተቸርችራ አንደትመራ፣ በአገር ሃብት በጀት መድቦ የጥላቻ ሃውልት ሲያስገነባና ጠላትነትን ሲሰብክ የኖረው ህወሃት ዓላማው አንደሰመረለት ውስጡ አያወቀና የሚታወቁ ደጋፊዎቹም አልቂቱን ተከትለው “እልል” በሚሉበት ወቅት ይህንን መግለጫ ማውጣቱ ብዙዎችን አስገርሟል። በርካቶች አንደሚሉት ህወሃትም ሆነ ደጋፊዎቹ ቀደም ሲል የዘሩት የጥላቻ ዘር ያፈራውን ፍሬ በኩራት አያጣጠመ ወንጀለኞችን ታቅፎ ኣርፎ ቢቀመጥ አንደ ትልቅ ውለታ ይቆጠርለታል።
ከኦነግ ጋር “በርዮተ አለም አንድ ነን” የሚለውና ሰሞኑን ይኸው የኦነግ ፍቅሩ የጋለበት ህወሃት በኦሮሞ ልጆች ላይ የፈጸመውን ግድያ፣ቶርቸር፣ ኣፈና፣ ዘረፋና አይን ያወጣ ግፍ በወራት ውስጥ መዘንጋቱ የፈጠረው ግርምት ሳይደበዝዝ፣ ለዜጎችና ለአገር ተቆርቓሪ መስሎ መቅረቡ አንዳስገረማቸው፣ ድርጅቱም ሆነ ደጋፊዎቹ ሞራል የሚባል ነገር አንዳልፈጠረባቸው ከመግለጫው ኣሰራጮች ግርጌ ከሚነበቡት ኣስተያየቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ከሁሉም በላይ መግለጫው “የዶክተር ኣብይ መንግስት ∕ ኦሮሞ የኣገሪቱን ሰላም ሊያስጠብቅ አይችልም” በሚል የመንግስት ግልበጣ ለማድረግ የነጮቹን ቢሮ ሲሳለም የነበረው ህወሃት መዳረሻ ያሳየ መሆኑንም የገለጹ አሉ። “ህወሃት ሰላም የማስከበር ልምድ አለው። አኛ ካልያዝነው ኣገሪቱ ትናወጣለች” በሚል ለቀረበው የኩዴታ ፈቃድ ሲባል ይህ ሁሉ አንደሚሆን ግልጽ ያደረ ነው የተባለው መግለጫ አንዲህ ይላል።

ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ
—————————————————–
ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ የሃገራችን ኣከባቢዎች በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሳቢያ የዜጎች ሰላምና ደህንነት ኣደጋ ውስጥ እንደገባና በርከት ባሉ ኣከባቢዎች ሰዎች ለስራ በወጡበት በሰላም መመለስ እያቃጣቸው እንደነበረ ይታወቃል፡፡
ዜጎች በተለያዩ የኣገራቸው ኣከባቢዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የመኖር፣ሃብት የማፍራትና የማካበት ሕገ መንግስታዊ መብታቸውና ነፃነታቸው ከመገደቡ ባሻገር በኣገሪትዋ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት ላይ ከባድ የሆነ ጉዳት የሚያደርስና የጥፋት ተግባር በመሆኑ በሆነ መለኪያ ተቀባይነት የሌለውና በኣጭር ግዜ መቆም ያለበትም ነው፡፡
የሃሳብ ልዩነት ያለው ማንኛውም ኣካል ሃሳቡን በነፃነት ማቅረብ የሚችልበት ሕገመንግስታዊ ስርኣት ባለበት ኣገር የብዙሃኑ መብትና ነፃነት በሚቃረን መልኩ ፍላጎቶችን በሃይል ለማስፈፀም የመንቀሳቀስ ውጤት ጥፋት መሆኑን በተግባር እየታየ ያለ ነገር ነው፡፡
የልማትና መልካም ኣስተዳደር ጥያቄ ያለበት ኣካልም ይሁን ኣካባቢ ጥያቄዎቹን ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ ኣገባብ ሊጠይቅና መልስም ሊያገኝ ያለበት ቢሆንም በልማትና መልካም ኣስተዳደር ጥያቄ በማሳበብ በሰዎች ህይወት፣ ንብረትና የልማት ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረስ ለጥያቄዎቹ መልስ ኣያስገኝም ብቻም ሳይሆን በቀጣዩ የኣገራችን ጉዞም ቢሆን በቀላሉ የማይታለፍ መሰናክል የሚፈጥር በመሆኑ መንግስትና ዜጎች እንደዚህ ኣይነቶችን የጥፋት ተግባራት ተሸክመው መሄድ የለባቸውም፡፡
ትናንት በቡራዩና ዛሬም በኣዲስ ኣበባ የደረሰው ጉዳትም በኣስቸኳይ እንዲቆም ጥሪያችንን እያቀረብን በተመሳሳይ ለሚፈጠሩ የጥፋት ተግባራት መሸከም ማለት ችግሩን ወደ ሌሎች የአገራችን ክፍሎች እንዲዛመት መፍቀድና ሁኔታዎች ከግዜ ወደ ግዜ እየተስፋፋና እየከበደ እንዲሄድ ተጨማሪ እድል መስጠት መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የፌዴራልና የክልል መንግስታት በየኣከባቢው እየተፈጠረ ላለው ኣደጋና ጉዳቱ ተገንዝበው የኣገራችንን የሰላም ጉዳይ ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ወንጀለኞችን ወደ ህግ በማቅረብ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ በመደራጀት ሰላሙን እራሱ ለማስጠበቅ የሚያስችለው የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር በላቀ ሃላፊነት መስራት እንዳለበት ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የአገራችን ዜጎችም የኣገራችንን ኣስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ እውን ለማድረግ የእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅበትን ኣስተዋፅኦ እንዲያበረክት የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጥሪ ውን ያቀርባል፡፡
የትግራይ ኮሙኒከሽን ጉዳዮች ቢሮ
መስከረም 07/2011ዓ/ም
ትግራይ
መቐለ
a

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *