አቶ ንጉሡ ጥላሁን በጅማ ከተማ በመካሄድ ላይ ባለው የኦህዴድ 9ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ያስተላለፉት ሙሉ የአጋርነት መልዕክት 

ጓድ ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዴግ እና ኦህዴድ ሊቀመንበር እና የኢፌድሪ ጠ/ሚንስትር፤
ጓድ ለማ መገርሳ የኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር እና የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር፤
ውድ የኦህዴድ አመራሮች እና አባላት፤
የተከበራችሁ የዚህ ታላቅና ታሪካዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ፤
ከሁሉ በማስቀደም በጥንታዊቷ፤የአባ ጅፋር መናገሻ፤ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መነኸሪያ በሆነችው ጅማ ከተማ በዚህ ታሪካዊ የሽግግር ወቅት በምታካሂዱት 9ኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችሁ ላይ ተገኝቼ የብሄረ-አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴንን/ የአጋርነት መልዕክት ለማስተላለፍ በመታደለ ላቅ ያለ ክብር የተሰማኝ መሆኑን ስገልፅ ጉባኤያችሁም በስኬት የጀመርነውን የለውጥ ተስፋ እውን ለማድረግ የሚያስችሉና ወቅቱን የሚመጥኑ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ በመመኘት ነው፡፡
ይህ ድርጅታዊ ጉባኤ የሚካሄደው ድርጅታችን ኢህአዴግ እና አገራችን ኢትዮጵያ ከጥፋት አደጋ ወጥተው በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገራችን ህዝቦች ብሩህ ተስፋ በሰነቁበት ወቅት በመሆኑ በየትኛውም ጊዜ ከተካሄዱ ጉባኤዎች የተለየ እና ታሪካዊ እንደሆነ ለማናችንም ግልፅ ነውና በድጋሜ እንኳን ደስ አለን ፤
እንኳን ለዚህ ታሪካዊ ጉባኤ በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ!!! 
በገ ነጋን ጌሰን ፤በገ ገመደን
==============================================
የተከበራችሁ ጉባኤተኞች እና ታዳሚዎች 
ኦህዴድ 9ኛውን ድርጅታዊ ጉባኤውን የሚያደርግበት ወቅት ሁላችንም እንደምንገነዘበው ድርጅታችን ኢህአዴግ መላ የአገራችንን ህዝቦች የልማት፣የሰላም እና የዴሞክራሲ ትሩፋቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሰራው ስራና ያስመዘገበው ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ የፈፀመው ስህተት በህዝቡ ላይ ቅሬታ በመፍጠሩ ያለፉት ሦስት እና አራት አመታት ሀገራችን አመጽ፣ብጥብጥ እና ቀውስ ስታስተናድግ ቆይታለች፡፡ ይህንን ተከትሎ ድርጅታችን ኢህአዴግ በውስጡ ትግል በመለኮስ ከባድ ውጣ ውረድ ታልፎ እና ከፍተኛ ዋጋ ተከፍሎ በመላ አገራችን ሁለንተናዊ ነፃነት፣እኩልነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በድምሩ የለውጥ ተስፋ እንዲለመልም አድርጓል፡፡ ይህ ለውጥ እንዲመጣ ኦህዴድ ያበረከተው አስተዋፅኦ እና የተጫወተው ሚና በእጅጉ ትልቅና ታሪክ ሊረሳው የማይችል ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ መላው የድርጅታችን አባላት እና የአማራ ክልል ህዝብ ኦህዴድ በለውጡ ሂደት ለተጫወተው ሚና እና ላበረከተለት መሪ ከልቡ እውቅና በመስጠት በመላ ክልሉ ወረዳዎች ድጋፉን መስጠቱን ሳስታውስ በታላቅ ኩራት እና ደስታ መሆኑን ልገልፅላችሁ እወዳለሁ፡፡
============================================
የተከበራችሁ ጉባኤተኞና የጉባኤው ታዳሚዎች
የጀመርነው ለውጥ በመላ አገራችን የነፃነት፣የእኩልነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ተስፋ የታየበት ፤ ቂም በቀል፤ጥላቻና ቁርሾ ተወግደው ሰላም፤ ይቅርታና ፍቅር እንዲነግሱ መሰረት የጣለ እና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ፤ የሀገራችንን ህዝቦች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ንቃት ከፍ ያደረገ ለውጥ ነው፡፡ 
ኦህዴድ ይህ አዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ከጋራ ግምባራችን ኢህዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶች እንዲሁም መላ የአገራችን ህዝቦች ጋር የተጫወተው አኩሪ ሚና ድርጅቱን ሀገር በመለወጥ ሂደት ውስጥ በታሪክ ርዝመት የማይደበዝዝ ሀገር እና ህዝብ ያዳነ የትግል አሻራ ባለቤት ያደርገዋል፡፡
ኦህዴድ ከእህት እና አጋር ድርጅቶቹ ጋር በመሆን በመራው ለውጥ ምክንያት ሰላም፤ ይቅርታ እና ፍቅር እንዲያሸንፉ በር በመክፈት፤ የታሰረው ተፍትቶ ፤ ከሃገር የወጣው ገብቶ አዲሱን አመት በአንድ ማዕድ እንዲቆርስ ፤የአብሮነት፤የመቻቻል እና የአንድነት መንፈስ እንዲነግስ አድርጓል፡፡ ለውጡ የተጣላን ያስታረቀ፤የራቀን ያቀረበ፤ ወንድማማቾችን በአንድነት የሰበሰበ በመሆኑ የእርቅ፤የሰላም፤የይቅርታ፤የፍቅር ልብስም አልብሶናል፡፡ 
============================================
የተከበራችሁ ጉባኤተኞና የጉባኤው ታዳሚዎች

ለውጡ ይዞት የመጣው የነፃነት፣የሰላም፣የቅርታና የፍቅር ተስፋ ብቻ ሳይሆን ፈተናም ጭምር ነው፡፡ ፈተናው በአንዳንድ አካባቢዎች በግጭት እና ወድመትም ጭምር የሚገለፅ ሲሆን የንጹሀን ዜጎቻች ህይወት መቀጠፍ እና መፈናቀል ማጋጠሙም አልቀረም፡፡ “ሊነጋ ሲል ይጨልማል” እንደሚባለው በለውጥ ሂደት ውስጥ እንዲህ አይነት ፈተና ማጋጠሙ አይቀርም ፡፡ ዋናው ቁም ነገር ይህ ፈተና ሌላ ጉዳት ሳያደርስና ለውጡን ሳይቀለብስ መታረም ያለበት በመላ ኢትጵያዊያን ትከሻ ላይ የወደቀ ፈተና በመሆኑ በተናጠል ሳይሆን በጋራ መረባረብን ፤እንዲሁም ትዕግስትንና አስተዋይነትን መጠየቁ ነው፡፡ 
ምንም እንኳን እዚህም እዚያም ፈተናዎች ቢያገጥሙንም ፈተናዎቹ ለውጡን ከቀሰቀሰው የኢትዮጵያ ህዝብ ማዕበል እና ለውጡን ከሚመራው አመራር በላይ ሆነው ማሸነፍ እንማይችሉ ቅንጣትም ታክል አልጠረጠረም ፡፡
በዚህ አጋጣሚ ሰሞኑን በአዲስ አበባ፤ ቡራዩ እና አካባቢው እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን አልመሃል በተባለ አካባቢ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው ጉዳት ብአዴን ከፍተኛ ሃዘን የተሰማው ሲሆን መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያደርገውን ማንኛውም እንቅስቃሴ በመደገፍ የሚጠበቅበትን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን እንገልፃለን፡፡ 
አንዳንድ ወገኖች ይህንን የለውጥ አጋጣሚ በመጠቀም በህዝቦች መካከል በተለይም በኦሮሞ እና በአማራ ህዝቦች መካከል ግጭት በመፍጠር፤ ጥርጣሬን በማንገስ እንዲሁም ቁርሾን በመንቀሳቀስ የቤት ስራ ሊሰጡን ይሯሯጣሉ፡፡ ኢህዴድና ብአዴን የኦሮሞንና የአማራን ህዝቦች እንዲሁም መላ የሀገራችንን ህዝቦች ለሰላም፤ ለይቅርታና ለፍቅር የማንቀሳቀስ ትልቅ አገራዊ አደራ የተሸከሙ ወንድማማች ህዝብ ድርጅቶች በመሆናቸው እነዚህን እኩይ ተግባራት የማምከን ታካቅ ሀገራዊ አደራም ተሸክመዋል፡፡ 
======================================
የተከበራችሁ ጉባኤተኞና የጉባኤው ታዳሚዎች

ኦሮሚያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ለዘመናት ከኦሮሞ ወንድሞቻቸው ጋር ተዋደውና ተዛምደው ፤በደምና በስጋ ተሳስረው የሚኖሩበት ክልል ነው፡፡ በሀገራችን ውስጥ የአማራ ህዝብ ከአማራ ክልል በመቀጠል በብዛት የሚኖራው በኦሮሚያ ነው፡፡ በግልባጩ የኦሮሞ ተወላጆች በአማራ ብሔራዊ ክልል በብሔረሰብ አስተዳደር የራሳቸውን ምክር ቤት አቋቁመው ራሳቸውን በራሳቸው እያሰተዳደሩ በሰላም እና በፍቅር ይኖራሉ፡፡ ሁለቱ ህዝቦች ጠንካራ የአካልና የመንፈስ ትስስር ፈጥረው የኖሩ ህዝቦች ሆነው ሳለ በታሪካቸው ከነበራቸው የአንድነት፤ የፍቅርና የአብሮነት ትውስታዎች ይልቅ የጥርጣሬ ፤የቁርሾ እና የቂም በቀል ትርክቶች ላይ እንዲያተኩሩ በመሰራቱ ለበርካታ አመታት ጉዳቶች መድረሳቸው የሚታወስ ቢሆንም በዚህ የይቅርታ፤ የፍቅርና የመደመር ዘመንም አዳዲስ የጥፋት ምዕራፎች እንዲከፈቱ ስውር ዳባዎች ሲፈፀሙ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ የጥላቻ፤ የቂም በቀል እና የመጠፋፋት መርዞች በኦህዴድና በብአዴን መሪነት፤ በኦሮሞና አማራ ህዝቦች እንዲሁም በመላ ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የማርከሻ መድሃኒት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ 
የእነዚህ የጥላቻ ፣የቂም በቀልና የመጠፋፋት መርዞች ማርከሻ ፍቅር፣ ይቅር ባይነትና ወንድማማችነት በመሆናቸው ኦህዴድና ብአዴን ከሌሎች እህትና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ሰላምን፣ፍቅርንና ይቅርታን በማንገስ እንዲሁም የህግ የበላይነትን በማስፈን የሀገራችን ሰላም እንዳይናጋ ህዝቡን በአንድ ልብ ማንቀሳቀስ የወቅቱ የአንድነት እና አብሮነት ደወል ነው፡፡
ያለፈው ዓመት ቦረና በድርቅ ምክንያት ጉዳት ደርሶበት በተቸገረበት ጊዜ የአማራ ህዝብ ያለውን ያጋራበት፤ የኦሮሞ ወጣቶች ጣናን ኬኛ ብለው እንቦጭን ለመንቀል ወደ ባህር ዳር የተመሙበት፤ቡኖ በደሌና አካባቢው የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆምና የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር በጋራ መስራታችን የአማራንና የኦሮሞን ህዝቦች ከያሉበት በእምባ ያራጨው የጋራ መድረካችን ለሁለቱ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵዊያን የአንድነትና አብሮነት ተስፋ የጫሩ የኦህዴድንና የብአዴንን በመርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነትና ወንድማማችነት ያጠናከሩ፤ ለቀጣይ የአንድነትና አብሮነት ጉዟችን አዲስ ምዕራፍ የከፈቱ የለውጥ ማፋጠኛና መጣፈጫ ቅመሞች ነበሩ፡፡ 
==================================== 
የተከበራችሁ ጉባኤተኞና የጉባኤው ታዳሚዎች

የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች በሁለቱም ክልሎች ለዘመናት ተዋህደውና ተሳስረው ፤ተዋለደውና ተዛምደው የሚኖሩ ከመሆናቸውም ባሻገር ትብብራቸውና ጠንካራ ግንኙነታቸው በኢኮኖሚ የዳበረች ህብረ-ብሄራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ጉልበት የሚሰጡ ሃያል ክንዶች ናቸው፡፡ 
ይህን በመገንዘብ እኛ የዘመኑ ፖለቲከኞችና መሪዎች እንዲሁም ባለሀብቶች፤ ፤ምሁራን፤ወጣቶች እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለማጠናከር እውቀታችንን፣ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ገንዘባችንን ልናረባርብ ይገባል፡፡
በዚህ ዘመን የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ለማጎልበት ከምንሰራው ስራ በላይ የአንድነታችንን ድርና ማግ ለመበጣጠስ ከፀአዳው ግንኙነታችን ይልቅ ጥላሸቱ እንዲጎላ ፤ከይቅርታና ፍቅር ይልቅ ጥላቻና ቂም በቀል ቦታቸው እንዲሰፋ ሲደረግና አልፎ አልፎም ይሄው እኩይ ተግባር ፍሬ ሲያፈራ ይታያል ፡፡ በመሆኑም በዓላማ የተሳሰሩት ግን ደግሞ በራሳቸው የቆሙ ድርጅቶች የሆኑት ብአዴንና ኦህዴድ ከሌሎች አህትና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ለዜጎች ህይወት መጥፋት፣ ስደትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ግጭቶችን በማስወገድ ማንም በብሄሩ በሃይማኖቱ ወይም በሌላ ማንነቱ ምክንያት የማይሞትባት እና የማይሰደድባት ሀገር እንድትሆን በታላቅ ሃላፊት መስራት ይጠበቅብናል ፡፡ 
ሁለቱን ህዝቦች እርስ በእርሳቸው፤እንዲሁም ከሌሎች ህዝቦች ጋር ለማጋጨት ፍላጎት ያላቸው ወገኖች እሳት ሲጭሩ ብአዴን እና ኦህዴድ፤እንዲሁም የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦች ከመላው የአገራችን ህዝቦች ጋር በመተባበር የሰላም፤የይቅርታ እና የፍቅር ውሀ በመርጨት እሳቱን ሊያጠፉባቸው ይገባል፡፡
የሃይማኖት ድርሳናት ቢታዩ፣የታሪክ ማህደሮች ቢፈተሹ ሁሉም ቅርሶቻችን ቢዳሰሱ የአማራንና የኦሮሞን ህዝቦች አንድ የሚያደርጉን እና የሚያስተሳስሩን የጋራ እሴቶቻችን ይበዛሉ፡፡ የሚያለያዩን ጉድለቶች ጥቂት ከመሆናቸውም በላይ እነዚህ ጉድለቶቻችን እኛን የመለያየት ምንም አቅም የላቸውም፡፡ 
ያለፉትን የአንድ ወጣት ዕድሜ የሚሆኑ አመታት የኦሮሞን እና የአማራን ህዝብ በሚለያዩ ጉደለቶች ላይ አመዝነን በመስራታችን እንዲሁም የሚያሰተሳስሩንን ገመዶች በመጉዳታችን ትልቅ አገራዊ ጉዳት አድረሰናል፡፡ በአሁኑ ወቅት እኛን የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች እንዲሁም መላው ኢትዮጵያዊያን ያለን ብቸኛ አማራጭ ሊለያዩን የሚችሉ ነገሮችን በመቀነስ አንድ ሊያደርጉን እና ተከባብረን፤ ተቻችለንና ተዋደን ለመኖር የሚያስችሉን ጉዳዮች ላይ ጠንክረን መስራት ነው፡፡ 
ያለን ብቸኛ አማራጭ ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችንን ፤ከጥላቻችን ይልቅ ፍቅራችንን፤ ከቂማችን ይልቅ ይቅር ባይነታችንን የሚያጠናክሩትን ድልድዮች በመገንባትና በማጠናከር የሚያለያዩንን የአስተሳሰብና የተግባር ግንቦች ማፍረስ ነው፡፡ ይህንን ስናደርግ ደግሞ ሰላም፤ፍቅርና ይቅርታ እንደሚያሸንፉ ማሰተማር እንችላለን፡፡ 
አንድ ስንሆን ፤ስንፋቀር እና ይቅር ስንባባል እንኳን ለእኛ ለጎረቤተሰቦቻችን እንዲሁም ለመላው ዓለም ሞልቶ የሚተርፍ ሰላም ማጎናፀፍ የምንችል ብርቱና ጠንካራ ህዝቦች መሆናችንን ባለፉት አራት እና አምስት ወራት ብቻ በተግባር አሳይተናል፡፡ ሀገራችንም የብዙ ብሄር-ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር በመሆኗም አስደማሚ ህብር ያለው ውበትና መታደል እንጂ መርገምት አለመሆኑን ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈናል፡፡
=========================================
የተከበራችሁ ጉባኤተኞና የጉባኤው ታዳሚዎች

ብአዴን የኦህዴድ ጥንካሬና ስኬት የራሱ ጥንከሬና ስኬት መሆኑን፤ ድክመቱንና ፈተናዎቹንም እንዲሁ የራሱ አድርጎ በማየት ጥንካሬዎቹ ይበልጥ እንዲጎለብቱ፤ፈተናዎቹ እንዲታለፉ የበኩሉን ሁሉ ለማድረግ ከጎናችሁ የሚቆም መሆኑን ማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡ 
ኦህዴድ በዘመናት የትግል ታሪኩ በርካታ ወጣ ውረዶችን አልፎ ዛሬ ላለበት ደረጃ የበቃ ጠንካራ ድርጅት በመሆኑ ወቅቱ የወለዳቸውን ፈተናዎች በተለመደው ጥንካሬው እና ፅናቱ እንደሚያልፋቸው ሙሉ እምነት ያለኝ መሆኑን ስገልፅ በስኬታችሁም ይሁን በፈተናችሁ ጊዜ ሁሉ ከጎናችሁ ቆመን በጋራ የምንሻገር መሆናችንን በማረጋገጥ ነው፡፡
በመጨረሻም ይህ ታሪካዊ ጉባኤ ለመላው የኦሮሞ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ የምትመክሩበት ኦህዴድንና ኢህአዴግን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግሩ አቅጣጫዎች የምታሰቀምጡበት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡
==== የላቀ ሀሳብ፤ለበለጠ ድል====
Yaada Mo”ataa Injifannoo caalmaaf
አመሠግናለሁ 
========== Galatomaa ============

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *