Skip to content

ቀጣይ የፖለቲካ ፓርቲወቻችንና ድርጅቶቻችን – ኃይሉ በላይ

እንደማንኛውም የሰው ልጅ ፍጡር ማህበራዊ እንስሳ በሆኑ ኢትዮጵያውያን የሃገር ግንባታ ታሪክ ውስጥ የተለያየ መልክ ያላቸው ችግሮች እንደነበሩ አሁንም እንደቀጠሉ ግልፅ ነው፡፡ ለዘመናት በዘለቀው ውስብስብ ሃገራዊ ግንባታ ታሪካችን ከተጠቀምንባቸው ያባከናቸው ዕድሎችና አጋጣሚወች ይበዛሉ፡፡ ጥንት ማህበራዊ የሆነውን የሰው ልጅ ተፈጥሮ፣ የገዳ ስርዓትን፣ ዕድርን፣ ዕቁብን፣ ሽምግልናን ክርስትናንና  እስልምናን ለሃገር ግንባታችን በሚገባ አልተጠቀምንባቸውም፡፡ የተቀየርን ቢመስለንም በነበረው መንገድ ስለተቀበልናቸው በዘመናዊት ኢትዮጵያ ሶሻሊዝምን፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲን፣ የብሄር ብሄረሰቦችን መብትና እኩልነትን፣ ምርጫንና ዘመናዊ ሃገር ግንባታን ተጠቅመን የተሻለች ሃገር እና ስርዓት ዕውን ማድረግ ሳንችል ቆይተናል፡፡

በዚህ ወቅት ደግሞ ከተጠቀምንበት የሚታይ ተጨባጭ አጋጣሚና ዕድል ተከስቷል፡፡ ችግር ታክሲ አይደለም በነበረበት ቁሞ አይጠብቅም፡፡ በውቅቱ መታረም ያልቻለ ችግር ከጊዜ ጋር እየገነገነ፣ ዓይነቶችን እየጨመረ፣ እየተወሳሰበ እንደሚቀጥል ታሪካችን ይመሰክራል፡፡ ስለዚህ ወቅታዊው አጋጣሚ እንዳለፉት ጊዜወች ከባከነ የሚጠብቀን ሁኔታ እጅግ የሚያስፈራ ይመስለኛል፡፡

እነዚህ በታሪካችን የዘለቁ የተለያዩ ችግሮች ከመጀመርያው የሃገር ግንባታ ሙከራ ጀምሮ አንድ  መሰረታዊ መነሻ አላቸው፡፡ ብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን በእየአካባቢው ወደ አቅመ ሃገር ሊያድጉ የሚችሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ተቋሞች ቢኖራቸውም የሃገር ግንባታ ታሪካችን የተጀመረው፣ የተስፋፋውና አሁንም የቀጠለው በየጊዜው በነበሩ በውጭ ተፅዕኖወች ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች ለአቅመ ሃገር የበቁት በቀጥታ የቅኝ ግዛት ተፅዕኖ ሲሆን ሃገራችን ደግሞ የዛሬውን መልክ የያዘችው ዜጎቿ በተሳተፉበት፣ የተለያየ መልክ ባለው ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆነ የውጭ ተፅዕኖ ነው፡፡

የተለያዩ መልክ ላላቸው ችግሮች መነሻ የሆነውና አሁንም የቀጠለው ነባራዊ ሁኔታ የሃገር ግንባታ ጥረታችን ከመጀመርያው ጀምሮ ለውጩ ተፅዕኖ ተጋላጭ በነበሩና አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ለቀጠሉ ጥቂት መሪወችና ልሂቃኖቻችን ብቻ መጠቀምያ በመሆኑ ነው፡፡ በእረጅሙ ታሪካችን፣ በሰፊዋና ህብረ ብሄራዊ በሆነችው ሃገራችን ውስጥ እንዳለመታደል ሁኖ ጥቂት የሆኑት መሪወችና ልሂቃን ከሞላ ጎደል እጅ ለእጅ ለመያያዝ፣ ባህሪ ለመወራረስ አልተቸገሩም ነበር፡፡ አሁንም የቀጠለው ተመሳሳይ ነው፡፡

በተቃራኒው ብዙሃኑ ዜጋ የቀርፋፋው የሃገር ግንባታ ሂደት ባዕድ ሁኖ፣ ማግኘትና ማትረፍ የነበረበትን ተጨባጭ ጥቅም ሳያገኝ ለዘመናት ቀይቷል፡፡ ማህበራዊ የሆነው የሰው ልጅ አብሮ መኖርን፣ በጋራ መሻሻልን፣ በፍትሃዊነት መጠቀምን ቢመርጥም ይህን መሰረታዊ ፍላጎት የሚረዳና የሚያጎለብት መሪና ልሂቅ አልታደልንም፡፡ ስለዚህ ኋላ ቀርነት፣ ድህነት፣ እየሰፋ ሳይሆን እየኮሰመነ የሚሄድ የሃገር ግንባታ ሂደት ግዴታ ሁኖብናል፡፡

የሃገር ግንባታ ታሪካችን ችግሮች ከጥንታዊ የሃይማኖትና የሃገር መሪወች ተሻግሮ ወደ ዘመናዊ የየማህበረሳባችንና የሃገራችን ተመሳሳይ የወቅቱ መሪወችና ልሂቃን በተለያየ መልኩ መዛመቱ ግልፅ ነው፡፡ የጋራ የሆነውን ባህሪ አንዳርጋቸው ፅጌ እንደሚጠሩት የጥንታዊውም ይሁን ዘመናዊ መሪወቻችንና ልሂቃኖቻችን የደብተራና የአነብናቢነት ባህሪና ባህል ልንለው እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያ መሪወችና ልሂቃን ሁላችንም ለብዙሃኑ የማናስጨብጠው፣ የማናወርሰው፣ በሆነ ባልሆነው እርስ በእርስ የምንከፋፈልበት፣ ብዙሃኑን ብዥታ ውስጥ በመክተት በጎራ የምንቀራመትበት፣ የምናነበንበው ግን በተግባር ከራሳችን የማንጀምረው፣ የማናሳድገው፤ ግንዛቤ፣ ዕውቀት፣ ባህሪ፣ የጋራ አስተሳሰብና ባህል ባለቤቶች ነን፡፡

በዚህ የጋራ ባህሪ ምክንያት ብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ሰልችቷቸዋል፤ ከአንድ ሃገርና ስርዓት ያተረፉት ነገር እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ከቅኝ ግዛት ጋር ተናንቀው፣ ራሳቸውን ያከበሩ፣ በሰውታቸው የሚኮሩ፣ ጥቁር ሁነው በነጭ የሞቱ፣ ነጭን የገደሉ፣ ያሸነፉ፣ ከአሸነፉ በኋላ እንደ ሰው እኩል መቆም የቻሉ ኢትዮጵያውያን (ኢትዮጵያዊው የሰው ልጅነት አርበኛ ጃገማ ኬሎ ጣልያንን ያሸነፍኩት ሁለት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡ አንደኛው በአምስት አመቱ የአርበኝነት ትግል በማሸነፍ ሲሆን ሁለተኛው ከድሉ በኋላ ሴት ልጄን ለማግባት ለጠየቀኝ ጣልያን ስድርለት ነው ይላሉ፤- በእኩልነት ማለታቸው ነበር፡፡) ዛሬ ከሰው ልጅነት፣ ከአንድ ሃገርና ዜግነት በተወሰነ መልኩ ወደ ጎሳቸውና ቋንቋቸው አፈግፍገዋል፡፡ በብዙሃኑ አይፈረድባቸውም፣ ሁኔታው በታላቋ ሃገር ውስጥ በነበሩና ባሉ በጥቂቶች የሃገሪቱ ልሂቃንና መሪወች ባህሪ ተቀርፀው ላቆጠቆጡ የየጎሳው ልሂቃን ሰርግና ምላሽ ሁኗል፡፡ ለእነዚህ ጥቂት ሃይሎች ጓዳው ሰፊ ሜዳ አዳራሹ ደግሞ ገደልና ጠባብ እንደሆነባቸው መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህ ሰማያዊ ቢሆንም በቀላሉ የሚቀበሉት ሃገራዊ ሃሳብ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ እድሜ ኋላ-ቀር ለነበረው አጠቃላይ ሃገራዊ ጉዞ ይሁንና በእየአካባቢው ምሽጎችን ለማግኘት አልተቸገሩም፡፡

በሌላ መልኩ የትላንትም ይሁን የዛሬ ሃገራዊ  የፖለቲካ ሃይሎች ደግሞ ልዩነትን እንደ አደጋ እየተመለከቱ፣ በአንድ ባንዲራና ታላቅ ሃገር ስም ብቻ እየማሉ፣ የሙጥኝ ብለው በያዙት አቋም ምክንያት ከመሰሎቻቸው ብሄርተኛ ሃይሎች ጋር በሞት የሽረት አውዳሚ ግጭት ውስጥ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ሁሉም አስተዋፅኦ ያደረጉበት ኋላ ቀሩ ሃገራዊ ጉዞ የጋበዘንን የልዩነት ፖለቲካ በመረዳት፣ የነበሩትን የአንድነት ሃይሎች ታሪካዊ ስህተቶች በማረም፣ ሌሎችን በተጨባጭ ለማቀፍ፣ በላቀ ልዩነት አሸናፊ ሁነው ለመውጣት ተቸግረዋል፡፡

ለዘመናት የነበሩንን ታሪካዊ ግንኙነቶች ትተን የሰው ልጅ ማህበራዊ፣ በተጨባጭ የሚጠቀመው አንድ ዓይነት ከሆነው ውስን መንደሩ ሳይሆን በትክክል ከተሰራበት ከሰፊዋና በልዩነት ከደመቀችው ሃገሩ ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያንም ተመሳሳይ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ለዓመታት ጥላቻና ብሄርተኝነት ተዘርቶ በአጭር ጊዜ ኢትዮጵያዊነት የሚያብብ ቢሆንም ዳር መድረስ፣ አሸናፊ መሆን ግን አልተቻለም፡፡ የአንድ ሃገር ስም ይዘው የሚታገሉ ድርጅቶች፣ በስራቸው ወደ ማዶ አይሻገሩም፡፡ የትውውቅ ቡድኖች ናቸው፡፡ አባላቶቻቸውን ሲመለምሉ በተለይ መሪወቻቸውን ሲሾሙና ሲሽሩ የሚያውቁት እነሱ ብቻ ናቸው፡፡ ህዝብ የሚታዘብ አይመስላቸውም፡፡ ብዙሃኑ የሚሰማው ዜና የቡድን፣ የአንጃ ሽኩቻወችን ነው፡፡ በመፈንቅለ ስልጣን፣ በሰርጎ ገብ የድርጅት ዓባል በመከረኛው ምርጫ ቦርድና ውሳኔወቹ ዜና ብዙሃኑ ቢሰለቹ አይገርምም፡፡

ከቅንጅት በኋላ እንኳ መኢአድ፣አንድነት፣ ሰማያዊ ፓርቲ እና የመላው ኢትዮጵያ ንቅናቄ  የተለያዩ ፕሮግራሞች ሳይሆን መሪወችና አባላት ያሏቸው አይደሉም፡፡ ብሄርተኛ ድርጅቶቻችን ከህብረ ብሄራዊነት ያፈገፈጉ ወይም የተገፉና ተገፍተናል የሚሉ መሪወችና አባላት አሏቸው፡፡ በግንባር፣ በቅንጅት ውስጥ የተሻለ ሃሳብ፣ ዕቅድ፣ ስራና አፈፃፀም አይፈለግም፡፡ መድረክ በተሰኘው ግንባርና በሌሎችም የታዘብነው የአባል ድርጅቶችን የግንባር ድርጅት ስልጣን ሽሚያ፣ ቅርምትና ክፍፍል ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት ስልጣንን እንደ ስኳር በእየ ሶስት ወሩ ተረኞች እየላሱት ነበር፡፡ በቅንጅት እንደምናስታውሰው በአንድ ውህደት ውስጥ የነበረ የድርጅት ስም፣ ታሪክ አይፈርስም፣ አይረሳም፣ አይቀየርም፤ ኢዴፓ-መድህን፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት የሚሉት ስሞች ራሳቸው ለዚህ ማስረጃ ናቸው፡፡ (ይህን ፅሁፍ ከፃፍኩ በኋላ የአርበኞች ግንባር ከግንቦት ሰባት የመለየቱን ዜና አንብቤያለሁ፡፡)

ከ 1997 ምርጫ በኋላ በግንቦት ሰባት የፖለቲካ አቋም ልዩነት ቢኖረኝም፣ ላለፉት 13 ዓመታት በድርጅቱ ውስጥ የተከሰቱ ጥቃቅን ሽኩቻወችን የሰማሁና የአዳዲስ አመራሮችን ፊት ባላይም፣   በቀስተ ደመናም ይሁን በግንቦት ሰባት በሀሳባቸው ዜጎችን በማሰባሰብ የተሻሉ መሪወች ባሉት ከኤርትራ በተመለሰው አርበኞች ግንቦት ሰባት ላይ ተስፍ ነበረኝ፡፡  የድርጅቱን የወደፊት ፕሮግራም መነሻ ሃሳብ አንብቤዋለሁ፡፡ ወደፊት ስለምመኛት ሃገር ያላቸው አጠቃላይ መነሻ ሃሳብ በእኔ አቅም እንከን አላገኘሁበትም፡፡

ከዚህ በፊት ግን ሌሎችን ጨምሮ ከላይ የገለፅኳቸውን ሃገራችን ያለችበትን አጠቃላይ ሁኔታ፣ በተለይ ሁላችን የምንጋራውን የመሪወችንና የልሂቃኖችን ባህሪ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ፊት እንዴት ማስተካከል፣ ማረም እና ከተቻለ አብሮ መስራት ካልተቻለም አሸናፊ መሆን እንደሚቻል፣ የተበታተነውን፣ የኮሰመነውን የአንድ ሃገርና የአመለካከት ሰልፍ ከኮሰመነበት በአጭር ጊዜ እንዴት ሊያንሰራራና የበላይ ሊሆን እንደሚችል የተገለፀ ነገር የለም፡፡

እንደ እኔ ዓመለካከት ደግሞ ከሃገሪቱ ነፃና ገለልተኛ ተቋማት ግንባታ ጋር በኢትዮጵያውያን አይን የሚሞላ፣ ለፍላጎታቸውና ለአመለካከታቸው የሚመጥን ድርጅትን መመስረትና ዕውን ማድረግ ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት፡፡ በመነሻ ሃሳቦች ላይ ተመስርቶ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ሁሉንም ዜጎች የሚጋብዝ፣ ከላይ ሳይሆን ከታች መሰረት ያለው፣ በቀጣዩ በዝርዝር መርሃ ግብሮቹ፣ በወደፊቱ የድርጅቱ መሪወች ምርጫ፣ በዕቅዱና በስትራቴጂው ላይ ሁሉም የሚሳተፍበትን ድርጅት በግልፅ ማዋቀር ያስፈልጋል፡፡ ምርጫ ሲደርስ በሆይሆይታ ብቻ የሚመረጥ ሳይሆን ሁልጊዜ ዜጎች የእኔ ነው፣ የተሻለ፣ የተለየ ነው፣ የሚሉት ድርጅት መሆን የመጀመርያውና ለዘለቄታው ጠቃሚ ተግባር ነበር፡፡

ስለዚህ ያሉት አባለትና መሪወች እርሾ ሁነው ቀጣዩ ድርጅት ከላይ የተገለፀው በመሪወችና ልሂቃን፣ በፖለቲካ ፓርቲወቻችን፣ የነበረውን ባህሪ በእራሱ በድርጅቱ ውስጥ የሚያርም፣ ለሌሎች ሃሜት፣ ፍረጃ የማይመች እና እንደውም አርዓያ የሚሆን አዲስ የአደረጃጀት ሂደት ያስፈልጋል፡፡ አርበኞች ግንቦት ሰባትን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች የራሳቸውን ድርጅት ከማደስ በተጨማሪ (የምርጫ ሰርተፍኬት ይዘው) ከቆዩ ሌሎች ድርጅቶች ጋር የሚኖር ግንኙነት ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ የ1997ን መድገም ውርደት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ተመሳሳይ የፓርቲ ፕሮግራም ስላለን ተብሎ ከሚፈፀም ማንኛውም የድርጅት ጋብቻ፣ የወሰደውን ጊዜ ቢወስድም በጋራ አስተሳሰብ፣ በተሻለ ፕሮግራምና በጋራ መልካም የአፈፃፀም ጅምር ከሚገኝ ጥንካሬ ጋር ሊወዳደር አይችልም፡፡

በዚች ሃገር እውነተኛ የፖለቲካ ስራ ስላልተሰራ በአጭር ጊዜ ጥቂቶች አዛዥና ናዛዥ የማይሆኑበት፣ የቡድን ስሜት የማይገንበት፣ ሃሳብና ዓመለካከት የሚፈተኑበት፣ ዕቅድ፣ አፈፃፀም የሚመዘንበት ውጤታማ ድርጅት ዕውን ለማድረግ ቀላል ይመስለኛል፡፡ አጉል የነበረ ጋብቻን በወቅቱ አፍርሶ ከአንድ ሰው መጀመር፣ ሁሉንም መጋበዝና ለመድረስ መሞከር ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡  ማንም ቢሆኑ አንደነበረው ብዙሃኑን አንገት የሚያስደፉ የድርጅቶች ታሪክ ይበቃል፡፡ ይህንን ታሪክ ማድረግ የሚቻለው ከመጀመርያው ጀምሮ በሚኖር የአደረጃጀት፣ የአወቃቀር ሂደት ብቻ እንጅ ለጊዜው በሞዳሞድና በመግባባት አይደለም፡፡

የስልጣን ሽኩቻወች፣ የድርጅት አንጃወች፣ የመፈንቅለ ስልጣን ዜናወች በየድርጅቱ አባላት የሃሳብ ፍጭት፣ በድርጅት መሪወች የሃሳብ፣ የእቅድ፣ የስትራቴጂ፣ የትግል ስልትና …..ወዘተ እውነተኛ የፍክክር ዜናወች መተካት አለባቸው፡፡ በመጨረሻ ቢሆንም በምርጫ ዘጠና ሰባት ቅንጅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሪወችን ለመምረጥ ያደረገው ሙከራ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ምሳሌውን ሂደቱን፣ ባህሪውን በአንድ ድርጅት ውስጥ ከመጀመርያ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች መፈፀም ይገባል፡፡ ያውም ባደባባይ፡፡ የእያንዳንዱን ስስ ስሜት፣ የማንነት ሰልፍ ሳይሆን የብዙሃኑን የጋራ አመለካከትና አመኔታ ለሚፈልጉ ህብረ ብሄራዊና ሃገራዊ ድርጅቶች ውጤታማነት ደግሞ ጉዳዩ የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

Read previous post:
የድሬደዋ ፖሊስ ሕዝብ በማህበራዊ ገጽ በሚለቀቅ መደናገሪያ እንዳይሸበር አሳሰበ፤ ከተማዋን ለማሸበር በሚሞክሩ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቀ

Continue Reading

Close