መስከረም 11 ቀን፣ 2011 አም
በወቅቱ የአትዮጵያ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ ረጅም ታሪከ ያላት፣ በአለም ላይ በጥንታዊ ስልጣንያቸው ከሚታወቁ አገሮች አንዷ ነች፡፡ የአውሮፓ ሀያላን አፍሪካን ስለሚቀራመቱበት ሁኔታ በ 1876 አም በርሊን ላይ ይፋ ጉባኤ ተቀምጠው ከመከሩ በኋላ፣ ባለ ድርሻ የሆነችው ጣልያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ በ 1888 አም ያካሄደችውን ወረራ አድዋ ላይ ድል በመምታት ከመላው አፍሪካ አህጉር ነጻነቷን አስከብራ የኖረች ብቸኛ ሀገር ሆና ቀጠለች፡፡

ሆኖም፣ ይህ ባእድ ወራሪን መክቶ አገርን በነጻነት የማቆየት ወደር የሌለው ጀግንነት በዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ለውጥ፣ በኢኮኖሚ እድገትና በሀገራዊ ብልጽግና የታጀበ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ በፊውዳል ስርአተ ማህበር ላይ በቆመ፣ ፈላጭ ቆራጭ የዘውድ አገዛዝ ስር የምትማቅቅ፣ ምንም አይነት የፖለቲካ ነጻነት የማይታወቅባት፣ ኢኮኖሚዋ ኋላ ቀር የሆነ፣ በምድር ላይ እጅግ ደሀ ከተባሉት ተርታ የተሰለፈች ሀገር ነበረች፡፡ ይህም ሆኖ፣ የንጉሰ ነገስቱ መንግስት ለሰላማዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለወጥ በሩን ዘግቶ መቀመጥን መረጠ፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ኋላ ቀርነትና ድህነት እረፍት የነሳቸው አገር ወዳዶቹ ጀነራል መንግስቱ ነዋይ፣ ወንድማቸው ገርማሜ ነዋይና ተባባሪዎቻቸው በታህሳስ ወር 1953 አም የመንግስት ለውጥ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡

ታህሳሳዊያን የቆሙለት አትዮጵያን የማዘመን አላማ ግን ከነርሱ ጋር አልተቀበረም፡፡ የኢትዮጵያን ተማሪዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ለመሰረታዊ ለውጥ እንዲታገሉ ቀሰቀሰ እንጂ፡፡ በተለይም በ1957፣ የታህሳሳዊያን ሙከራ በተቀጨ በአራተኛው አመት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ዝነኛውን የመሬት ላራሹ መፈክር አንግበው በአዲስ አበባ ጎዳናዊች ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ታህሳስ 1953 የተለኮሰውን የለውጥ ችቦ ከዘጠኝ አመት በኋላ ለፈነዳው ለየካቲት 1966 ህዝባዊ አመጽ አሸጋገሩ፡፡ የየካቲት አብዮት የኢትዮጵያን አራሽ ገበሬ እጅ ከወርች ጠፍሮ ለከፊል ባርነት ዳርጎት የኖረውን የመሬት ስሪት ሲያፈርስ ግፈኛው የባለርስትና ጭሰኛ ግንኙነትም አበሮት ተቋረጠ፡፡ ፈላጭ ቆራጭ የዘውድ አገዛዝም አከተመ፡፡

ይሁን እንጂ፣ የዘውድ አገዛዝ ቢወገድም በቦታው ዴሞክራሲያዊ ስርአት አልተተካም፡፡ አራሹ የኢትዮጵያ ገበሬም የመሬቱ ባለቤት ሊሆን አልቻለም፡፡ ህገ ወጥ ግድያ፣ የፖለቲካ አፈና፣ ረሀብ፣ ድህነት፣ የኢኮኖሚ ድቀትና የማያቋረጥ ጦርነት የደርግ አገዛዝ መለያዎች ሆኑ፡፡ ደርግን ጥሎ ስልጣን የያዘው ኢህአዴግ እንኳንስ የኢትዮጵያን ህዝብ ከድህነት ሊታደግና ዴሞክራሲን ሊያሰፍን፣ የህዝቦቿን የጋራ እሴቶች በማጣጣል፣ ልዩነቶቻቸውን በማጉላትና ከፋፍሎ በማጋጨት የኢትዮጵያን ሀገራዊ ህልውና አደጋ ላይ እስከመጣል ደረሰ፡፡

ከሶስት አመት ወዲህ፣ የኢህአዴግን አፈናና ጭቆና በመቃወም፣ በመሀላቸው አህአዴግ ያቆመውን ከፋፋይ አጥር በመስበር፣ በኦሮሚያና በአማራ ወጣቶች ግንባር ቀደምነት ህዝባዊ አመጽ በያለበት ሲቀጣጠል በህወሃት የበላይነት ሲዘወር የኖረው የኢህአዴግ ድርጅታዊ መዋቅር ከመሰረቱ ተናጋ፡፡ በውስጡ ሆኖ ሲታገል የቆየው የለውጥ ሃይል በድርጅቱ ውስጥ የበላይነትን ያዘ፡፡ በመሆኑም፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊ ራእይ ያለው፣ ለአንድነት፣ ለፍትህ፣ ለህግ የበላይነት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሰላምና ለልማት የቆመ፣ የእነ ለማ መገርሳ፣ ዶክተር አብይ አህመድና ገዱ አንዳርጋቸው የለውጥ ሀይል በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ጥልቅ የለውጥ እንቅስቃሴ እየመራ ይገኛል፡፡ በተለይም፣ ዶክተር አብይ አህመድ የመሪነቱን ሃላፊነት ከተረከቡ ወዲህ ያራመዱት ጥበብና አርቆ አስተዋይነት የተሞላበት የይቅርታ፣ የፍቅርና የአንድነት ፖሊሲ የኢትዮጵያን ህዝቦች በጋራ ሀገራዊ ራእይ ዙሪያ እንዲሰባሰቡ፣ ሰላም እንዲሰፍንና ህዝብም መጪውን ጊዜ በተስፋ እንዲመለከት አድርጓል፡፡

የፍትህ ስርአቱን እንደገና በማደራጀት ነጻ ፍርድ ቤቶች ለማደራጀት፣ የህግ የበላይነት ለማስፈን፣ የመደራጀት ነጻነት እንዲከበር፣ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ ማህበራዊ እርቅ እነዲወርድ እየተወሰዱ ያሉትን እርምጃዎች እናደንቀለን፡፡ የነዚህ አብይ የማሻሻያ እርምጃች አካል የሆነው ከገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ነጻና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ የማዋቀሩ ስራም በቅርቡ የጀመራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ከኤርትራ ጋር የነበረውን አደገኛ የጦር ፍጥጫ በማርገብ፣ የሰላምና የፍቅር እጅ በመዘርጋት የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት በአዲስ የሰላም ስምምነት እንዲቋጭ ተደርጓል፡፡ በአምስት የስራ ወራት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያከናወኑት የለውጥ እርምጃ፣ ኢትዮጵያ ባለፉት 27 አመታት ካሳለፈቻቸው የፈተና ዘመናት ጋር ሲነጻጸር፣ በመንፈሱም ሆነ በይዘቱ ታሪካዊ ነው፡፡

እረግጥ ነው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰላምን የሚያደፈርሱና የህዝብን ተስፋ ለማጨለም የታቀዱ የዝርፍያና የግድያ ተግባሮች በአዲስ አበባና በአካባቢዋ ተከስተዋል፡፡ ሰዎች ተገድለዋል፣ ተደብድበዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል፡፡ ዜጎች በሰላም በሚኖሩበት ቀያቸው የተፈጸመባቸውን ጭካኔ የተሞላበት አረመንያዊ ተግባር መኢሶን ያወግዛል፣ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ሀዘኑን ይገልጣል፣ መጽናናትን ይመኛል፡፡ ድረጊቱ ባስቸኳይ ተጣርቶ ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ይጠይቃል፡፡ ከዘህ ሌላ፣ በታሪካችን የሌለ፣ መጤ የመንጋ ፍትህ፣ ሴትን መድፈርና ሌሎች አሰቃቂ ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡  ሸማቹ ህብረተሰብ በዋጋ ንረት ተማሯል፡፡ ቀላል የማይባል አሉባልታ በማህበራዊ ሚድያ ይለቀቃል፡፡ የመንግስት አስፈጻሚ አካሎችም ልግም  ህዝብን ለአደጋ ሲያጋልጥ ይታያል፡፡  ይህ ሁሉ በአንድነት ህዝብን ማስመረሩና ማስደንገጡ ሀቅ ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን፣ እንደነዚህ አይነት እርኩስ ተግባሮች ወደ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ ሽግግር በሚደረግበት ወቅት የሚያጋጥሙ፣ መታለፍ ያለባቸው ፈተናዎች መሆናቸውን ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል፡፡ የህግ የበላይነት ወደ ሰፈነበት ስርአተ ማህበር ለመሸጋገር ከተፈለገ፣ ወንጀለኛን በህግ ከመዳኘት ዉጭ ወደ ቀደመው መንግስታዊ ግድያ፣ አፈናና ህገ ወጥ አሰራር መመለስ የሚታሰብ አይደለም፡፡  በመሆኑም፣ ሰላማዊ ለውጡ ዳር እንዲደርስና በሀገራችን ተጠያቂነት ያለበት መንግስት እንዲቆም የምንፈልግ አትዮጵያዊያን በለውጡ ጉዞ ወቅት አልፎ አልፎ የሚገጥሙ እንደነዚህ ያሉ እንቅፋቶችን ተሻግረን፣ የለውጡ ግንባር ቀደም መሪ ከሆኑት ከጠቅላይ ሚነኒስትር አብይ አህመድና ከሚመሩት መንግስት ጎን በጽናት መቆም ይጠበቅብናል፡፡

መኢሶን ከ1980 አም ጀምሮ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ቅንጅት (ኢዴሃቅ) ምስረታ፣ የፓሪስ አንድና ሁለት ጉባኤዎችን በማደራጀት፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ህብረት (ኢተፖድህ)  እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ህብረት (ህብረት) ምስረታ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ዛሬም በዚህ የለውጥ ዘመን፣ መኢሶን በህብረት ትግል አስፈላጊነት ያምናል፡፡ በተለይም ሰባና ሰማንያ የሚጠጉ የፖለቲካ ድርጅቶች ባሉበት የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገር-አቀፍ አማራጭ የፖለቲካ ሃይል ሀኖ መውጣት ምን ያህል አዳጋች እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ ተቀራራቢ የፖለቲካ ጥሮግራምና የጋራ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አመለካከት ያላቸው ድርጅቶች ተሰባስበው አብረው ቢሰሩ ይበልጥ ፍርያማ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለው፡፡ በመሆኑም፣ መኢሶን የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማቀራረብና የጋራ መድረክ በመፍጠር ከሌሎች ጋር አብሮ የመስራት ፍላጎት ያለው መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ይገልጣል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *