• ህዝቡ አብሮ አደጎቹን ከ20 ዓመታት መለያየት በኋላ ተቀብሏል፡፡

‹‹ደብረ ማርቆስ ለቅሶ፣ ሳቅ እና ጭፈራን አስተናገደች፡፡›› ይህ አንድ የዓይን እማኝ በስፍራው ተገኝቶ የታዘበውን ስሜት የገለጸበት መንገድ ነው፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ከ20 ዓመታት በፊት ወደ ኤርትራ ሄደው የነበሩ አብሮ አደጎቻቸውን ትናንት ተቀበሏቸው፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት ኑሯቸውን በደብረ ማርቆስ ከተማ አድርገው ነበር፤የወቅቱ አስከፊ የፖለቲካ ውሳኔ ግን በአካል እንጂ በመንፈስ ካልተለዩት ህዝብ ጋር ሳይፈልጉ ተገደው እንዲለዩ አደረጋቸው፡፡

ዛሬ ታሪክ ተቀይሯል፤መለያየት በአብሮነት፤ጥላቻ በፍቅር ድል ተነስተዋል፡፡ እናም አቶ ተስፋ ሚካኤል ግደይና አቶ መድሃኔ ግደይ ወደ ቀድሞ ከተማቸው ተመልሰዋል፡፡ ደብረ ማርቆስም የትናንት ልጆቿን የዛሬ እንግዶቿን እልል…! ብላ ተቀብላለች፡፡ ነዋሪዎቹ ወንድሞቻቸውን ‹‹ለቅሶ፣ደስታ እና ጭፈራ በተቀላቀለበት ስሜት›› እንደተቀበሏቸው ነበር በስፍራው ተገኝቶ ትዕይንቱን የታዘበ አንድ የዓይን እማኝ የነገረን፡፡

ከአቀባበሉ በኋላ ደግሞ የህዝቡን ቃል አክባሪነት እና ታማኝነት ያስመሰከረ አንድ አስገራሚ ዕውነታ ተገለጠ፡፡ ወደ ኤርትራ በሄዱበት ወቅት ትተውት የሄዱት ቤት ተጠብቆ ቆይቶላቸው ነበርና ዛሬ ህዝቡ ለባለቤቶቹ አስረክቧል፡፡

የኢትዮጵዊነት እሴትም በተግባር ታየ፡፡ ህዝቡ ለኤርትራዊያኑ ወንድሞቹ የጋቢ ስጦታም አበርክቶላቸዋል።

በአስማማው በቀለ
ፎቶ እና መረጃውን ያደረሰንን ጋሻየ ጌታሁንን እናመሰግናለን፡፡  

Amhara Mass Media Agency

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *