Ermias Tokuma –  አለማችን ላይ እጅግ አሳፋሪ እና አስቂኝ በሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች ጦርነቶች ተቀስቅሰዋል። በ1925 ግሪክና ቡልጋሪያ በአንድ ውሻ የተነሳ ወደጦርነት ገብተው በርካታ ወታደሮች ሞተዋል፤ በ1969 የኤልሳልቫዶር ብሔራዊ ቡድን በሆንዱራስ መሸነፉን ተከትሎ የኤልሳልቫዶር መንግሥት በንዴት ሆንዱራስ ላይ ጦርነት አውጀው በርካታ እልቂት ተፈጥሯል፤ The Pastry War ተብሎ የሚጠራው በሜክሲኮ እና በፈረንሣይ መካከል የተካሄደውም ጦርነት በአንድ ግለሰብ ካፍቴሪያ ላይ በጎረምሶች በደረሰ ጥቃት ምክንያት የተነሳና በርካታ እልቂት ያስከተለ ነበረ።

ኢትዮጵያ ውስጥም በጎሳዎች መካከል በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ ግጭቶች መንስኤያቸው አሳፋሪም አስቂም ናቸው። በተለይም በፖለቲከኞቻችን ምክንያት የሚነሱ የህዝቦች ግጭት ያስቀኛል፤ የተወሰኑትን ግጭቶች እንመልከትና ፖለቲከኞቻችን ምን እንደሚሰሩና ምን ያህል ኋላቀር እንደሆንን እንመልከት።

በአንድ ወቅት ሃላባ ቁሊቶ ላይ በተደረገ የብሄረሰቦች የባህላዊ አልባሳት ትርኢት ሀላባ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ጎሳዎች ተመሳሳይ የሰሌን ኮፍያ ለባህላዊ ትርኢቱ ይዘው በመቅረባቸው ኮፍያው የኔ ነው የሚል ንትርክ በፖለቲከኞች መካከል ይነሳና ሁለቱ ጎሳዎች ተጣልተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ስለሰሌኑ ኮፍያ ሲባል ህይወታቸውን አጥተዋል።

በጉራጌዎችና በወለኔ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረውም ግጭት ምክንያቱ እጅግ አስገራሚ ነበረ። የወለኔ ህዝብ ከህብረተሰቡ በተዋጣ ገንዘብ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገነባሉ ስሙንም “አበሩስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ሲሉ ይሰይሙታል። ከጥቂት አመታት በዃላም የጉራጌ ህዝብ ትምህርት ቤት ገንብቶ የትምህርት ቤቱን ስም “አበሩስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ብለው ይሰይሙታል፤ ጉራጌዎች አበሩስ የሚል ትምህርት ቤት እንደከፈቱ የሰሙት የወለኔ ፖለቲከኞች ስማችንን ተቀማን ብለው የወለኔ ህዝብ በጉራጌ ላይ እንዲዘምት የክተት ጥሪ ያውጃሉ ጥሪውን ተከትሎ በተነሳ ግጭት ከወለኔውም ከጉራጌም በርካታ ሰው ከሞተ በዃላ ግጭቱ በሽማግሌዎች በቀረበ ሃሳብ እንዲቆም ይደረጋል። ሽማግሌዎቹ ያቀረቡት ሃሳብ ጉራጌዎች የከፈቱት ትምህርት ቤት ስሙን ከአበሩስ ወደአበሩዬ እንዲቀየር ማድረግ ነበረ። የሽማግሌዎቹ ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ “ዬ” የተሰኘችው ፊደል የህዝቦችን ግጭት አስቁማለች። በደርግ ጊዜም እናሸንፋለን በሚልና እናቸንፋለን በሚሉ ቃላት የተነሳ በርካታ ሰው ህይወቱን ማጣቱ ይታወሳል።

እንዲሁ በተመሳሳይ በኦሮሞዎችና በሱማሌዎች መካከል በርካታ ጊዜ ግጭቶች ተፈጥረዋል የግጭቶቹ ምንጮች የከብቶች የግጦሽ ሳር ነው። እንሰሳት የኦሮሞ ሳር የሱማሌ ሳር ብለው መርጠው እንዲበሉ ይጠበቅ ይመስል የሱማሌ በሬ የኦሮሞን ሳር ጋጠ የኦሮሞ ፍየል የሱማሌን ቅጠል በላች ተብሎ የበርካታ ሰው ህይወት ጠፍቷል። ምክንያቱ የግጦሽ መሬት ሆነ እንጂ አንድ የኦሮሞ በሬ የሱማሌን ላም አጥቅቶ ቢሆን ኖሮ የሚፈጠረውን አስቡት።

በአጠቃላይ በህዝቦች መካከል የሚነሱ ግጭቶች ሁሉ መንስኤያቸው ፖለቲከኞች ናቸው፤ በአሁን ዘመን የሚገኙ ፖለቲከኞች ደግሞ ስልጣናቸውን ለማራዘምም ሆነ ስልጣን ለመያዝ ህዝቦችን ከማጋጨት ወደዃላ የሚሉ አይደሉም ህዝቡም ቢሆን መሳሪያውን በጎረቤቱ ላይ ከማንሳቱ በፊት ማመዛዘን አለበት ሁሌም እንደምለው የአንድ ጎሳ አባል ሆኖ መገኘት የጥረት ውጤት አይደለም ማንኛውም ግለሰብ ጎሳውንና ብሄሩን ለፍቶ ጥሮ ግሮ በላቡ አላገኘውም፤ በድካምህ ላላገኘኸው ጎሳህ ህይወት ልትከፍልለት አይገባም፤ ሁላችንም ሰው መሆናችንን አምነን መቀበል አለብን ሰው መሆን ደግሞ በትልቁ ማሰብን ይጠይቃል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *