የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትስያስ የመስቀሉ አስተምህሮ ፍቅር፣ ይቅርባይነት እና አንድነት ብቻ መሆኑን ገለጹ።

አቡነ ማትስያስ ይህንን ያሉት የደመራ በዓልን በማስመልከት በመስቀል አደባባይ ተገኝተው ለምዕመናኑ ቡረኬያቸውን ባስተላለፉበት ወቅት ነው። መስቀሉ ላይ ያለው አስተምህሮ እየተበደሉ ይቅርታ ማድረግ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ክርስቶስ የሰው ጥፋትና በደል በምልዓት የሚያውቅ ሆኖ ሳለ በመዋዕለ ስጋዌ በመገለጥ ይቅር ተብላችኋል ከማለት በስተቀር አንድም ሰው ላይ አልፈረደም ብለዋል አቡነ ማትያስ።

ስለመስቀል በዓል ታሪካዊ ዳራ ያነሱት አቡነ ማትያስ ንግስት እሌኒ የፍቅር ጉዞ ተሳክቶ መስከረም 17 በለኮሰችው እሳት ጢስ ተመርታ መጋቢት 10 ቀን መስቀሉን ማግኝቷን አስታውሰዋል።

በመጨረሻም በጎሎጎታ ባስገነባቸው ቤተመቅደስም በድጋሚ መስከረም 17 ማሳረፏንም አንስተዋል። መስቀሉ ላይ የተገነባው የይቅርታና የፍቅር ግንባታ በአድናቆትና በተመስጦ እንድናየው ያስገድደናል ብለዋል።

ደመራ የተበታተኑ እንጨቶችን አንድ ማድረግ መሆኑን የጠቀሱት አቡነ ማትያስ ምዕመናኑም ከመስቀል በተገኘው አስተምህሮ መሰረት በአንድነት መሰባሰብ እንሚገባቸው አንስተዋል።

መስቀል ከወዳጅ ጋር ብቻ ሳይሆን ከባላጋራ ጋርም ተቻችሎ መኖር መሆኑን ያነሱት ፓትርያርኩ፥ ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለበዳይም ጭምር ይቅርታን መጠየቅ ነው ብለዋል።  አቡነ ማትያስ ቅዱስ መስቀል ያወረሰውን ይህን ባህል እናክብረው፤ እንመራበት ሲሉ ቡራኬያቸውን አስተላልፈዋል።

አቡነ ማትያስ በኢትዮጵያ አሁን ስላለው ሁኔታ በማንሳትም ገና ያልሰከነ የሚመስል የጥላቻ፣ የመጠራጠር፣ ያለመተማመን እና እራስን የመውደድ ዝንባሌዎች እንዲገቱ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ አንድነት ከሁሉም ነገር በላይ መሆኑን ጠቅሰው የትኛውም ነገር በአንድነት ብቻ እንደሚገኝ አሳስበዋል። ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮችም በዓለ መስቀሉ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት በዓል እንዲሆንም ተመኝተዋል።

fana B.C

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *