የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በባህር ዳር ተጀምሯል። ጉባኤውን በንግግር በይፋ ያስጀመሩት የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ድርጅታቸው ለአማራ ህዝብና ለመድረኩ የሚመጥን ቁመና ተላብሶ ለውጡን ለማስቀጠል በየደረጃው በአዳዲስ ትውልድ የተገነባ አመራር መገንባት ይጠይቀዋል ብለዋል። ከዚህም አኳያ ዛሬ የተጀመረው ጉባኤው ሃላፊነት እንዳለበት ነው ያነሱት።
 
ሊቀመንበሩ በመክፈቻ ንግግራቸው ብአዴን የማይታለፉ ይመስሉ የነበሩ የፈተና ጊዜያትን በተለመደው ፅናቱ እየተሻገራቸው ለተሻለ ምእራፍ መነሻ እያደረጋቸው መዝለቁን አንስተዋል።
 
ለአማራና ለመላው የሀገሪቱ ህዝቦች የትግል መነሻ እና መንደርደሪያ በመሆን ክፉውንም በጎውንም በትእግስት፣ በአስተዋይነትና በጥበብ በማለፍ ለአሁኑ የለውጥ የበቃ አንጋፋ ድርጅትም ነው ብለዋል።
 
ብአዴን ኢትዮጵያ ፈተና በገጠማት ጊዜ ሁሉ ከእህት እና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ከራስና ከድርጅት በላይ ሃገርን አስቀድሞና አሻግሮ በማየት ህዝብንና ሃገርን የመታደግ የካበተ ልምድ እንዳለውም ሊቀመንበሩ አቶ ደመቀ ተናግረዋል።
 
አሁን ለበቃንበት የሰላም፣ የይቅርታና የፍቅር እንዲሁም የነፃነት ተስፋ መለምለም የተጫወተው ሚና ጉልህ የነበረ መሆኑን ገልፀዋል።
 
ኢትዮጵያ ስትጀመር አብረን ጀምረናል፤ ስትሰራ ሰርተናል፤ ስትሰለጥን ሰልጥነናል፤ ስታሸንፍ አሸንፈናል፤ በዘመናት በተለያዩ ችግሮች ስትወድቅ አብረን ወድቀናል፤ ከቁልቁለት ጉዞ ለመውጣት ተስፋ ሰንቃ ስትነሳ አብረን በተስፋ ተነስተናልም ነው ያሉት።
 
ቁጭታችን እልህ ወልዶ ይህችን ገናና ሀገር ወደ ክብሯ ለመመለስ ከድህነትና ኋላቀርነት ጋር ትግል በመጀመራችን የተስፋ ፍንጣቂዎችን ማየት ጀምረናል ያሉት አቶ ደመቀ፥ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በስኬቶቻችን ውስጥ ድክመቶች በማሳየታችን ህዝባችንን ቅር አሰኝተን ወደ ግጭት ገብትናል። ግጭቶቹም ዋጋ አስከፍለውናል ብለዋል በንግግራቸው።
 
በህዝቡ ውስጥ ቅሬታ ከፈጠሩና ወደ ችግር ካስገቡ ችግሮች ለመላቀቅ ባደረግነው ትግል ተስፋ ያዘለ ለውጥ ማየት ጀምረናል ያሉት አቶ ደመቀ፥ ይህ ለውጥ የጎደለንን የምንሞላበት፣ ያረጀውን የምናድስበት፣ ያዘመመውን የምናቀናበት፣ የጀመርነውን ዳር የምናደርስበት ስር ነቀል ጉዞ ይሆናል ብለዋል።
 
የለውጡ እንቅስቃሴ መሰረቱ ውስጣዊ መሆኑን እና አንዱን አፍርሶ ሌላ ፍለጋ የሚሄድ ባለመሆኑ ክልሉም ሆነ ሀገሪቱ ፈርሶ መሰራትን እንደማይሹ እና በተግባርም እንደማያስተናግዱ አስታውቀዋል።
 
በሰለጠነው ዘመን አካሄዳችን በኃይል አስገዳጅ ከመሆን ይልቅ በሃሳብ ልዕልና አስረጂና አሳማኝ መሆን ይኖርብታል ያሉት አቶ ደመቀ፥ እያንዳንዱ ወቅትና ዘመን አርበኝነትን ይጠይቃል፤ ለዚህ ትውልድ የ“አርበኝነት” ብያኔ ድህነትን ከልብ መጠየፍ እና በልማት ድል መንሳት እንደሆነ ተናግረዋል።
 
በሀገሪቱ በሁለት ፅንፈኛ ሀይሎች መካከል በተወጠረ ፖለቲካ ውስጥ እንደምትገኝ እና ሁሉን የደፈጠጠና የጨፈለቀ ልሙጥ ሀገራዊ ማንነት ብቻ አንግቦ ጠቅላይና አሃዳዊ አመለካከት የኢትዮጵያን መልከ ብዙ እውነታ በካደ ደረጃ የቆመ ፅንፍ በአንድ በኩል፥ በሌላ በኩል ደግሞ ብሄረሰባዊ ማንነትን ከሌሎች መነጠያና ማግለያ ያደረገና ፅንፈኛ ብሄርተኛ በሚቀነቀንበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
 
የአማራ ህዝብ ሁሉን ደፍጣጩን እና ጨፍላቂውን እንዲሁም ከሌሎች የሚነጥለውንና የሚያገለውን ራስን ከልክ በላይ የሚያወድስ ማንነትን የሚሸከም ትከሻ የሌለው በእኩልነት የሚያምን ከሌሎች ጋር ወዶ እና ፈቅዶ ተሳስሮ የኖረ ህዝብ ነው ብሎ ብአዴን እንደሚያምን አስቀምጠዋል።
 
ብአዴን በእነዚህ ፅንፎች መሃል ሚዛን ሆኖ የመቆም ሀላፊነቱን በብቃት መወጣት የሚጠይቀው ወሳኝ ወቅት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
 
ብዙ ውጣ ውረዶችን ተሻግረን የምናካሂደው ይህ 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የመጣንበትን መንገድ በጥልቀት በማስተዋል የምንማርበት፤ ቀጣዩን ጎዳና በግልፅ የምናመላክትበት ሊሆን ይግባል ብለዋል ሊቀመንበሩ ለጉባኤተኛው።
 
ብአዴን ለአማራ ህዝብና ለመድረኩ የሚመጥን ቁመና ተላብሶ ለውጡን ለማስቀጠል በየደረጃው በአዳዲስ ትውልድ የተገነባ አመራር መገንባት ይጠይቀዋል። ይህም ጉባኤ ከዚህ አኳያ ሃላፊነት ይጠበቅበታልም ነው ያሉት።
 
እዚህም እዚያም የሚታዩ ችግሮች ከአሮጌው ለመላቀቅ እና አዲሱን ለመገንባት በምናደርገው ትግል ውስጥ የተከሰቱ፣ በአሮጌውና በአዲሱ መካከል በተፈጠረ ቅራኔ የተወለዱ መሆናቸውንና አዲሱ ማሸነፉ ግን አይቀሬ መሆኑ ነው አቶ ደመቀ ተናግረዋል።
 
አዲሱ እንዲያሸንፍ፤ ለውጡም ህዝባችን የሚፈልገውን ዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ነፃነትና እኩልነትን እንዲያረጋግጥ ከተፈለገ መወጋገዙን በመተው መተጋገዝ፣ መጠላለፉን በመተው መተቃቀፍ፣ መሰባበሩን በመተው መተባበር መጀመር አለብን ሲሉም መክረዋል።
 
የሚቀረን ብዙ ቢሆንም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያከናወናቸው ተግባራት ጥሩ መነሻ ሆነው የሚወሰዱ እንደሆነው አስታውቀዋል።
 
 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  
 
በዳዊት መስፍን

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *