‹‹የተቀጣጠለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል የጋራ አቋም መያዝ ባለብን ወቅት የሚካሄድ ጉባኤ ነው›› የደኢሕዴን ሊቀ-መንበር ወ.ሮ ሙፈሪያት ካሚል

ከባሕር ዳር፡መስከረም 18/2011 ዓ.ም(አብመድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሊቀ-መንበር ወ.ሮ ሙፈሪያት ካሚል በደኢሕዴን 10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ‹‹የተቀጣጠለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል የጋራ አቋም መያዝ ባለብን ወቅት የሚካሄድ ጉባኤ ነው›› ብለዋል፡፡ 
‹‹የድርጅታችንን10ኛ መደበኛ ጉባኤ የምናካሂደው በሀገራችንም ሆነ በክልላችን ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት እና ተስፋ በተፈጠረበት ወቅት ነው፡፡ የለውጥ ፍላጎት ወደ ተግባር የሚቀይር ብቁ አመራርን እውን ማድረግ የግድ የሚልበት ጊዜ ላይም እንገኛለን›› ብለዋል ወ.ሮ ሙፈሪያት፡፡

‹‹ዋስትናችን የትናንቱ ውጤታችን ብቻ አይደለም፤ የዛሬም ተግባራችን እንጅ፡፡ ሕዝብ ቃላችንን ጠግቧል፡፡ አሁን የተራበው እና የተጠማው ተግባራዊ ምላሻችንን ነው፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ ‹ላም አለኝ በሰማይ› በሚል ተስፋ አብሮን የሚታገል ሕዝብ እንደማይኖር ተገንዝበናል›› ብለዋል ሊቀ-መንበሯ፡፡ 
‹‹የደረስንበት የትግል ምዕራፍ ከሌሎች ጊዜያ በተለየ አቅምና የዓላማ አንድነት እንደሚጠይቅ ተረድተን ራሳችንን ማዘጋጀት እና ለዚሁ ምዕራፍ የሚመጥን የለውጥ አመራር ማረጋገጥ የነገ የቤት ሥራ ሊሆን አይችልም፡፡ ይልቁንም ከወዲሁ ወገብን ማጥበቅ፣ ትከሻን ማስፋት… የተለየ ቁርጠኝነትን እውን ማድረግ ብቻ የመውጫ መንገድ የሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን›› ሲሉ ጉባኤተኛውን አሳስበዋል ወ.ሮ ሙፈሪያት፡፡

‹‹ድርጅታችን ደኢሕዴን የለውጥ ፋና ወጊ የሆኑ ጓዶችን እንዲያፈራ፣ ለጀመርነው ሀገራዊ ለውጥ በር የከፈተ እና ለሕዝቦች ጥቅም የትኛውንም መሰዕዋት መክፈል እንደሚቻል በተግባር ያረጋገጠ ድርጅት ነው›› በማለትም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የለውጡ አካል ለመሆን ከኃላፊነት በመልቀቅ ያበረከቱትን አስተዋፅዖ አስታውሰዋል፡፡ 
‹‹ይሁን እንጂ በአመራር ግንባታ ስርዓታችን የተሟላ ያለመሆን በምዕራፉ ከሚኖረው የተልኮ ባሕሪ ጋር በተሰናሰለ መንገድ ያልሄድንበት በመሆኑ መሠረታዊ ከሆነው የወገንተኝነት መሸርሸር ወይም ለሕዝብ ያለንን ቅርበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዳከምንና እያጣን በመምጣታችን በክልላችን በርካታ አካባቢዎች ችግሮችን ማስተናገድ ግድ ሆኖ ሰንብቷል›› ብለዋል፡፡

ለውጡን የሚመጥን እና የሚመራ ብቁ አመራር አለመፈጠሩ እና ለሕዘብ ጥያቄ በወቅቱ ምላሽ አለመስጠት ዋጋ ማስከፈሉን የተናሩት ወ.ሮ ሙፈሪያት ‹‹በዚህ ረገድ በጉባኤያችን የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በመምከር ያለንበት ምዕራፍ የድርጅቱን መሪነት፣ የሕዝብን አቅምና የመንግሥትን የማስተባር ሚና አቀናጅቶ እና አዋሕዶ በተስፋ ወደፊት ተስፈንጥረን የምንራመድበትና ቀጣይ የድል ምዕራፍ የምንሸጋገርበት በመሆኑ ለሕዝብ ልብ ቀረብ የምንልበትን አቅጣጫ ጉባኤው ተወያይቶ እና መክሮ እንደሚያስቀምጥ እምነቴ የፀና ነው›› ብለዋል፡፡

ደኢሕዴን የሕዝቦች ትብብር እና ትስስር የጋራ ፍላጎት የወለደው ድርጅት በመሆኑ የሕዝቦችን አንድነትና አብሮነት ማጠናከር የሁል ጊዜ ቀዳሚ አጀንዳው መሆኑን ያስታወሱት ሊቀ-መንበሯ ‹‹ዛሬ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ከድርጀቱ ዓላማ እና ከሕዝቡ እሴት ያፈነገጡ ሕዝብ የማጋጨት ሙከራዎች እየታዩ ይገኛል፡፡ እነዚህ ሙከራዎች በድርጅታችን መርህ ላይ በመቆም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ በፅናት ካልታገልናቸው ነጋችን የምንጠላው ታሪክ ባለቤት ሊያደርጉን ይችላሉ›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

‹‹ለሕግ የበላይነት መከበር እንዲሁም ለሕዝቦቻችን ሰላም እና ደኅንነት የድርጅታችን አመራሮች፣ መላው አባላት፣ ከመላው ሕዝብ ጋር በጋራ ሆነን ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ይህንን ሁኔታ በአስተማማኝ መለወጥ ይገባናል፡፡ በሀገራችን የጀመርነው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በፅኑ መሠረት ላይ ለማኖር የተጀመረው መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን የማይተካ ሚናችንን ልንጫወት ይገባል›› ብለዋል ወ.ሮ ሙፈሪያት፡፡ 
ለሀገራችንም ሆነ ለክልላችን ‹ይጠቅማል› የሚል ሐሳብ ያላቸው አካላት በሙሉ አሁን በተፈጠረው የይቅርታ እና የፍቅር መንፈስ በጋራ ሆነው ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሀሳቦችን በማመንጨት በሰላማዊ መንገድ እየተደረገ ያለውን ዴሞክራሲ እና የዴሞክረሲ ምሕዳርን የማስፋት እንቅስቃሴ ሂደት አካል ሆነው በተደራጀ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ እኛም እንደድርጅት ማሟላት ያለብንን ሁሉ ለማሟላት በድጋሜ ቃል እንገባለንም ብለዋል፡፡

‹‹ድርጅታችን ደኢሕዴን ሕዝባችንን ያማረሩ ችግሮችን ከ2008 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ባደረገው ጥልቅ ታሀድሶ በዝርዝር የለየ ቢሆንም በተግባር ከመፍታት አንፃር ግን ሰፊ ጉድለቶች አሉ፡፡ ይህ ጉድለት ሕዝባችንን ከማማረሩም በላይ በድርጅታችን ላይ የነበረውን ፅኑ እምነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ ያደረገ ነው፡፡ በርግጥም በጀመርነው የለውጥ ማዕቀፍ ፈጥነን ይህንን የመልካም አስተዳደር ችግር መቅረፍ ከቻልን የሕዝባችንን ሙሉ እምነት ማግኘት እንደምንችል አልጠራጠርም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ድርጅታችን ከችግሩ መውጣት ከቻለ ተአምር መሥራት እንደሚችል ያሳለፍነው የትግል ሂደት ለሕዝባችን ትምህርት የሰጠ ስለሆነ ነው፤ ለድርጅታችን ያለውን ፅኑ እመነት ሕዝቡ በቀላሉ ይንዳል የሚል እምነት ስለሌላና መፍትሔውም የእኛ ፈጥኖ መስተካከል ብቻ ነው›› ብለዋል፡፡

‹‹የሕዝብ ውግንናችንን በተግባር ለማረጋገጥ ፈጥነን የመልካም አስተዳደር ችግሮቻችንን ከሕዝቡ ጋር በመሆን ደረጃ በደረጃ መቅረፍ ይኖርብናል፡፡ በሌላ በኩል የጀመርነው ፈጣን ልማት በማስቀጠል ፍትሐዊ የሕዝቦች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዛሬም ለአንድ አፍታ ልንዘነጋው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጥያቄዎች ያለልማት መመለስ አይቻልም፡፡ ፈታን ልማቱን ማስቀጠል ግዴታ ነው፡፡ ከልማቱ ጎን ለጎን ዜጎቻችንን ከዕድገቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው ጎልባቶ በጋራ ማደግ እንዲችሉ ብቃት ያለው አመራር መስጠት ይጠበቅብናል›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡ 
የኢንዱስትሪ ዕድገታችን እንዲፋጠን ከማድረግ ጀምሮ በከተማ የማኒፋክቸሪንግ ዘርፉን በማሳደግ የሥራ አጥ ቁጥርን መቀነስ እና ኢኮኖሚያችንን ማሳደግ በተለየ ትኩረት እና በተለየ መንገድ ተግባራዊ ምላሽ ይሻል፡፡ በማኅበራዊ ዘርፎች ያስመዘገብናቸው ስኬቶችም በጥራት እንዲደገሙ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ የክልላችን ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ የሚያደርጉ አዳዲስ ሐሳቦችን በማመንጨት ወደተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት ይጠበቅብናል፡፡ ከዚህ አኳያ ጉባኤው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እዲሁም የአርብቶ አደር እና የከፊል አርብቶ አደሮች ኑሮ ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ የሚጠናከርበትን ተጨማሪ አቅጣጫ ተወያይቶ ያስቀምጣል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ 
‹‹የበለፀገችና ዴሞክራሰዊት ኢትዮጵያን የመገንባት ጉዳይ ላይ እየገነባነው ከመጣነው ፌደራላዊ ዴሞክራሳዊ ስርዓት አኳያ ይበልጥ ሊጠናከሩ እና ሊሰፉ የሚችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት በማድረግ ቀደም ሲል ያረጋገጥነው ስኬት እንደተጠበቀ ሆኖ በሂደቱ የነበሩ ጉድለቶችን በማረም የሀገራችንን ሕዝቦች ትስስር የበለጠ የሚያጠናክሩ፣ የሚያጎለብቱ፣ የነበሩ የሚዛን ጉድለቶችን በሌላ በኩል ሀገራዊነት ብሔራዊነትን አስተሳስሮ በመገንባት ረገድ የነበሩ እጥረቶችን በማረም፣ ተግባራዊ በማድረግ አንድነታችንን የበለጠ አስተሳስረን ጎልብተን፣ ጠንክረን የምንወጣበት ሁኔታ ላይ ደኢሕዴን የራሱን አወንታዊ ሚና የሚጫወት ይሆናል፡›› ብለዋል ወ.ሮ ሙፈሪያት በመክፈቻ ንግግራቸው፡፡ 
10ኛው ጉባኤ በ9ኛው ጉባኤ የተቀመጡ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ የልማትና መልካም አስተዳደር አቅጣጫዎች ውሳኔዎች አፈጻጸምን ጥልቀት በመገምገም ጉድለቶች የሚያካክስ እንዲሁም የሕዝቦችን የለውጥ ፍላጎት ምላሽ የሚሰጡ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ እምነታቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
‹‹ጉባኤው ያሉ ብዥታዎችን በማጥራት የአስተሳሰብና የዓላማ አንድነታችንን አጠናክረን፣ ለቀጣዩ የትግል ምዕራፍ ብቁ የሚያደርጉንን አቋም የሚያስይዘንና ወቅቱ የሚጠይቀውን ፅናትና ብስለት የተላበሰ የለውጥ አመራር እንደሚያደራጅ እምነቴ የፀና ነው፡፡ የሚደራጀው የለውጥ አመራር ክልሉን ከማሻገር አልፎ ድርጅታችን ሀገራዊ ተልዕኮን በብቃት እንዲወጣ የሚያግዝ ይሆናል የሚል እመነት አለኝ›› ነው ያሉት ሊቀ-መንበሯ፡፡

‹‹ያለንበት ምዕራፍ ባለድርብ ስለት ባሕሪ መሆኑን የተረዳ፣ ወደፊት ሲሄድ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን፣ ፀረ-ዴሞክራሲን የሚያስወግድ፤ የበለጠ ተስፋችንን የሚቀጭጩና የሚያጨል አዝማሚያዎችን ቆርጦ የሚጥል ይልቁኑ ተስፋችንን የሚያለመልም እዲሆን በማድረግ፣ ጊዜው ከግለሰቦች፣ ከቡድኖች ፍላጎት በላይ የሚሻገር ከባድ ሁኔታና እውነታ ውስጥ የምንገኝ መሆኑን በተገቢው በመገንዘብ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ሁሉም በተሠማራበት በብቃት እንዲወጣ እጠይቃለሁ›› ብለዋል፡፡
ኪሩቤል ተሾመ አማራ መገናኛ ብዙሃን

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *