ኦሮሚያን አስመልክተው የሚሰሩ ሚዲያዎች ከግለሰብ ማንነትና ድጋፍ ያልተላቀቁ፣ ሚዛናቸው ግለሰብን መደገፍና ማስተዋወቅ እንደሆነ ኦቦ ቃሉ ይናገራሉ። “ነጻና ከግለሰብ ዝና አቀንቃኝነት የተላቀቀ ሚዲያ ቢኖር ህዝብ ስለ ፖለቲካ መሪዎቹ ጥሩ ስዕል ይኖረው ነበር”  ሲሉም ያክላሉ። ማናቸውም ሚዲያዎች ግለሰቦችን የመንጠልጠልና የመካብ ስራ ላይ ካተኮሩ ዋናው መስፈሪያ ሚናቸውን እንዳይዘነጉ ይሰጋሉ። 

ኦቦ ቃሉ ኦነግን በተለዩ ጊዜያት በተለያዩ ሃላፊነቶች  በአገር ቤትና በስደት ሆነው  አገልግለዋል። ከላይ የተጠቀሰውን አስተያየት የሰጡት በዲስምበር ፳ /፳፩፭ ለጎልጉል ጋዜጣ ነው። ወቅቱ የኦሮሚያ ትግል የተፋፋመበትና ወደማይመለስ የሕዝብ ዓመጽ የተሸጋገረበት ሲሆን፣ በተመሳሳይ ከአመጹ ጀርባ ” እኔ እኔ” የሚል የባለቤትነት ላይሰንስ ለመውሰድ ድምጽ የሚሰማበት ነበር። አመጹን በጉልህ ሽፋን በመስጠጥ የሚዘግበው የኦሮሚያ ኔት ዎርክና የዚሁ ሚዲያ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆነው ጃዋር መሐመድ ነበር።

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ሲቋቋም በትግሉ ዙሪያ ያሉና የተለያየ አቋም በሚያራምዱ ዘንድ ያለ ነቀፌታ ድጋፍ የተደረገለት፣ በዚያው መጠን ደግሞ በኦሮሚያ ዙሪያ የሚታገሉትን ሁሉ እኩል ለማስተናገድ የማለ እንደነበር ስለ አመሰራረቱ የሚያውቁ ያስረዳሉ። በዚሁ እምነት ስራውን የጀመረው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ ከትግሉ ስኬት አንጻር ጉልህ ሚና መጫወቱን በርካቶች ” ዓላማውን ያሳካ” በሚል ይገመግሙታል። ግን ኦቦ ቃሉ ያሉት ስጋት ዛሬ ላይ ሊከሰት እንደሚችል አስተያየት እየተሰጠ ነው።

ሚዲያው ከሚያቀርባቸው ዝግጅቶች አቶ ጃዋር መሐመድን ከማስተዋወቅና ለማናቸውም ጉዳዮች አመራር ሰጪ አድርጎ የማቅረቡ ጉዳይ ሊሎችን የመዋጥ ስሜት እንዲሰማቸው ማድረጉን፣ ይህ ቅሬታም ውስጥ ውስጡን እንዳለ ይልማ ታመነ ይናገራል። ኦሎንኮሚ ተወልዶ ያደገው ይልማ እንደሚለው አሁን አሁን በኦሮሞ ትግል ዙሪያ በርካታ ዋጋ የከፈሉ የፖለቲካ መሪዎችና ድርጅቶቻቸው እኩል መድረክ አያገኙም። እነሱን በሚመለከትም ጉዳይ አስተያየት ለመስጠት ቀዳሚ አይደረጉም። አልፎ አልፎ በውይይት ከመጋበዝ የዘለለ ሚናም የላቸውም።

አቶ ጃዋር የሚዲያ መሪ፣ የለውጥ አቀንቃኝና አውራ አክቲቪስት፣ መሁርና ተንታኝ፣ የፖለቲካ ስልጣን የማይከጅላቸው እየተደረጉ በተጠቀሱት ማዕረጎች ሁሉ የተገነባላቸው ስብዕና የሚያሳስባቸው ጥቂት እንዳልሆኑ የሚናገረው ታመነ፣ የለማ መገርሳ ፓርቲም ቢሆን እያደር ስጋቱ እንደሚጨምር ምልክት መኖሩን ይናገራል።

ተደጋግሞ እንደተባለው ቄሮ የሚባለውን አደረጃጀት በዋናነት ማን ፈጠረው? ማንስ ፈቀደለት? እነማንስ ተባበሩት? አሁን በበላይነት የሚመራው ማን ነው? የሚሉና ሌሎች ጉዳዮች ሲነሱ ታመነም ሆነ ስማቸውን እንዳይተቀስ የጠየቁ የኦዴፓ ሰው የሚናገሩት ይስማማል። 

እንደ ታመነ ገለጻ ቄሮን የወለዱት አቶ በቀለ ገርባ ናቸው። ይኸው ጉዳይም ለዳግም እስር እንደዳረጋቸው በእርገጠኛነት ያወሳል። አቶ በቀለ ከእስር ከተፈቱ በሁዋላ የአቋም ለውጥ ያደረጉም በዚሁ መነሻ መሆኑን ይናገራል። በሌላ በኩል ቄሮ አደረጃጀት ውስጥ የኦህዴድ እጅ አለ። የገጠርና የቀበሌ መዋቅር ውስጥ ይህ አደረጃጀት የኢህአዴግን የአንድ ለአምስት አደረጃጀት ወደ ራሱ ገልብጦ እንዲሰራበት ቁልፉን ያስረከበው የዛሬው ኦዴፓ ነው። 

አቶ ዳውድ ኢብሳም አስመራ ሆነው ይህ ቄሮ የሚባለው አደረጃጀት እሳቸው የሚመሩት ኦነግ ያደራጀው እንደሆነ በቪዲዮ በላኩት መልዕክት አስታወቀዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ ቄሮ የኦነግ የአገር ቤት አደረጃጀት ነው። እናም ቄሮ ባለቤቱ ብዙ ነው።

ኦቦ ቃሉ ለጎልጉል እንዳስረዱት ከተበታተኑ በሁዋላ በወቅቱ ህብረት ለመፍጠር ይሰሩ የነበሩት በኦነግ ስም የሚጠሩ ድርጅቶች ከአምስት አያንሱም። በአቶ ቦንሳ ተባ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር [ሸሌ]፣ በአቶ ድሪባ ሆርዶፋ የሚመራው ጊዜያዊ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ህብረት፣ በአቶ አብደታ ኢሸኬ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ታጋዮች ጥምር፣ ከእነ ጀነራል ከማል ገልቹ የተገነጠለውና በአቶ ኑሮ ደደፎ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር [ቼንጅ] የሚባሉት የተለያዩ የኦነግ አካሎች የፈጠሩት ህብረት ነው። ኦነግ ከሚለው መጠሪያው ጎን [ዩናይትድ] በሚል ተቀጽላ ራሱን የሚለየው ኦነግ ኦቦ ነጋ ጃራን ሊቀመንበር፣ ጄኔራል ኃይሉ ጎንፋን ምክትል ሊቀ መንበር አድርጎ የሰየመ ነው። ኦቦ ቃሉ በወቅቱ እንዳሉ መንገድ ላይ የነበረው ውህደት ተግባራዊ ይሁን አይሁን እስካሁን አለየም።

አገር ቤት በምርጫ ቦርድ ፈቃድ አግኝተው ከሚንቀሳቀሱት እና በቅርቡ ውህደት ከፈጸሙት ጋር ሲዳመር በርካታ የኦሮሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መገናኛ ይፈልጋሉ። የመሪዎቻቸውን ስብዕናና የደጋፊዎቻቸውን ቀልብ ለማግኘት ያቅዳሉ። በዚሁ መነሻ ያላቸውን የሚዲያ ጥማት ጃዋር የሚመሩት ኦ ኤም ኤን ያረካላቸዋል? ወይስ ሌላ አማራጭ ያፈላልጋሉ? ወደ ሌላ አማራጭ ካመሩ ማረፊያቸው አብይ አሕመድ የሚመሩት ክልል ሚዲያና ፓርቲያቸው ይሆናል። 

እነዚህ በተለያዩ ደረጃ የጃዋርን ሚዲያ ሲደግፉ የኖሩ ኦዴፓን ጨመሮ በሚፈልጉት ደረጃ የሚዲያ ሽፋን ከተከለከሉ በዝምታ ይቀበሉታል? ወይስ ሚዲያውን ወደ ተቋቋመለት ዓላማ ለመመለስ ትግል ይጀምራሉ? የችግሩና የቀጣዩ አለመግባባት ቁልፍ ጉዳይ እዚህ ላይ መሆኑንን ታመነ ይናገራል።

አሁን ያለው ኦዴፓ እንደቀድሞው አይነት አይደለም። አዲሶቹ የኦዴፓ አባላት ህወሃት ላይ እጃቸውን ያነሱና ቅድመ ታሪካቸው ኦነግ፣ ኦፌኮ፣ ኦፌድን የሆነ፣ በተወለዱበትና ባደጉበት አካባቢ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። ታመነ እንደሚለው ለምሳሌ ከንቲባ ታከለ ኡማን ጉደር ላይ ማንም ቢመጣ አይረታቸውም። ሌሎችም አሉ። 

የኦሮሞ ሚዲያ ኔት ዎርክ ቦርድ ስፍራ ለጊዜው ባይታወቅም፣ እነ በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸው ሚዲያው ከገለሰቦች አምልኮ እንዲወጣ ፍላጎት አላቸው። አለያም ሂሳቡን አወራርዶ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ እንዲሆን የሚጠየቅበት ወቅት እሩቅ እንደማይሆን ታመነ ቅድመ ትንቢቱን ያስቀምጣል።

” ማንም ሊፈርደው በሚችል መልኩ ሚዲያው በሕዝብ ገንዘብ በውል ሃሳቡና አካሄዱ ያልታወቀን ሰው እያጎላ መሆኑ ሰክነው የሚያስቡትን በሙሉ ጥያቄ ውስጥ ጥሏቸዋል” የሚለው ታመነ ፣ አንድ ሰው በባዶ እግሩ ሄደ፣ መደብ ላይ ተቀመጠ … የሚሉ ዘገባዎችን ልዩ ትኩረት በመስጠት መዘገብ ጥርጣሬ ብቻ ሳይሆን ፍርሃቻም ያመጣል።

በውስን ተዋንያኖች አጃቢነት ሰፊ ጊዜውን የሚያሳልፈው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ በኦሮሚያ ውስጥ የተለየ ሃሳብና ዓላማ የሚያራምዱ አካላትን ሲያነጋግርና ሲያወያይ ሰምቶ እንደማያውቅ የሚናገረው ታመነ፣ ኦሮሚያ ኦሮምኛ የማይናገሩትን ጨመሮ በርካታ የሰለጠነ አመላካከት ያላቸው አባቶች፣ እናቶች፣ አዛውንቶች፣ ወጣቶች እንዳሉበት ሊያስብ እንደሚገባም መክሯል። በርግጥ በምርጫ ወቅት ሁሉም ድምጹ በጁ ቢሆንም፣ እንደ አንድ ዴሞክራሲን ላስፋፋ ተነሳሁ የሚል ሚዲያ ቀዳሚ ተግባሩ የተለያዩ ሃሳቦችን ማስተናገድ እንጂ አንድን ሰው የነገር ሁሉ ሊቅ አድርጎ መሳል ሊሆን እንደማይገባም አስተያየት ሰጥቷል።

የአራትና የሶስት ሰዎች ተመሳሳይ አስተሳሰብ በተደጋጋሚ መጫን አሁን ሊያቆም እንደሚገባና የተለያዩ ፕሮግራሞች ተነድፈው የሃሳብ ገበያ እድሉን እንዲሰጠው ይደረግ ዘነድ የሚመለክታቸው የሚዲያው ባለ ድርሻ አካላት እንዲሰሩም ጠይቋል። 

በዚህና በሌሎች ፖለቲካዊ መነሻዎች፣ የአቶ ጃዋር ተጽዕኖ ያሳሰባቸው፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋጋ የከፈሉ ወገኖች፣ መሪዎችና ህዝብ የሚያከብራቸውን ታጋዮች ወደ ጎን እንዲገፉ መደረጉ አድሮም ቢሆን በልዩነት ደረጃ ገሃድ እንደሚወጣ በርካቶች ይስማማሉ። ጃዋር በተደጋጋሚ እንደሚለው ግን ካሁን በሁዋላ ኦሮሚያ ላይ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በኦሮሚያ ቁልፍ ጉዳዮች ልዩነት የላቸውም። አንድ ናቸው። እሱ እንደሚለው ጉዳዩ እውነት ቢሆን እንኳን አንድነታቸውን የሚናገሩት ራሳቸው ድርጅቶቹና መሪዎቻቸው እንጂ ሌሎች አይደሉም። አቶ ጃዋር ቃል አቀባይ አይደሉምና!! 

በኦሮሚያ የተካሄደው ትግል ለሰው ልጆች መብት መከበርና ለዴሞክራሲ ልዕልና እንጂ ጽንፍ ይዞ ” ተራው የእኔ ነው” በሚል እሳቤ ሊሆን እንደማይገባ፣ በዛሬው እውነታ አሸናፊና ተሸኛፊ እንደሌለ፣ ሁሉም አሸናፊ እንደሆኑ አቶ ለማ መገርሳም ሆኑ አብይ አሕመድ በተደጋጋሚ መናገራቸው አይዘነጋም።

አሁን በኦሮሚያ እየገነነ የመጣው አስተሳሰብና አካሄድ፣ ኦዴፓ የሚያራምደው ፖለቲካ፣ በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች የትግል እርከንና ተሚክሮ፣ ከሌሎች ⶒርቲዎች ጋር የሚደረጉ ውህደቶች ኦሮሚያ ላይ ያለውን የከረረ አካሄድ እንደሚያስተነፍሱት ይገመታል። ይሁን እንጂ መድረኩ መዘጋቱ አሳሳቢ ይሆናል። መድረኩ ሲዘጋ በተመሳሳይ የህቀሃትን የበላይነት ለማስቆም እንደተጀመረው አይነት ትግል ይጀመራል። የዛኔ ሁሉም ጉዳይ ግልጽ ይሆናል የሚለው የታመነ የመደምደሚያ አስተያየት ነው።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *