• የፍትህ ተቋማት ገለልተኛነታቸው እንዲረጋገጥ፣ በጀቱም ሳይቀር ከመንግስት ውጪ መሆን አለበት
  • ወደ ሃገር ቤት የተመለሱ ሃይሎች ከአብዮት ቅዠት ወጥተው ሪፎርሙን መቀበል አለባቸው
  • በነፃ አውጪነት የተደራጁ የፖለቲካ ሃይሎችን ምርጫ ቦርድ ሊመዘግባቸው አይገባም
  • ማንኛውም የፖለቲካ ቡድን በመጀመሪያ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አለች ብሎ መቀበል አለበት
  • የቀይ ሽብር የክስ ሂደት በአሸናፊዎች የተቀነባበረና በአሸናፊዎች የተዳኘ ነበር

   በ2009 ዓ.ም “ሪፎርም ወይስ አብዮት” በሚል ባወጡት መጽሐፍ በምህረት አዋጅ አተገባበር፣ በውጭ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር ቤት ስለሚመለሱበት ሁኔታ ያነሱት አንጋፋው የህግ ባለሙያና ተንታኝ አቶ ሞላ ዘገየ፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በለውጡ ሂደት፣ ከአብዮት መንፈስ አልወጡም በሚሏቸው የፖለቲካ ሃይሎች፣በቀይ ሽብር የፍርድ ሂደትና ሌሎች አወዛጋቢ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚከተለው ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ እነሆ፡

   አሁን በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥ እርስዎ “ሪፎርም ወይስ አብዮት” በሚል ርዕስ ባወጡት መጽሐፍ ካነሱት ሃሳብ አንፃር እንዴት ይገመግሙታል? 
መጽሐፉን ስጽፍ ከፍተኛ ስጋት ነበረኝ። ብዙ ሰዎች የፀደይ ወይም የአረብ አብዮት አይነት አብዮት ኢትዮጵያም ያስፈልጋታል ሲሉ ነበር። በአደባባይም ሆነ በሚስጥር ለዚህ አይነቱ አብዮት ቅስቀሳ ይካሄድ ነበር፡፡ እኔ በወቅቱ ሁኔታው ስላሰጋኝ ነው በመጽሐፌ ነገሩን ለመገምገም የሞከርኩት፡፡ የአረብ አብዮት ምን ውጤት አመጣ? በግብፅ፣ ሊቢያ፣ የመን የተነሳው አብዮት ምን በጐ ውጤት አመጣ? ምናልባት የአረብ አብዮት ጥሩ ውጤት አመጣ ልንል የምንችለው በቱኒዚያ ብቻ ነው፡፡ የግብጽ አብዮት ወታደራዊ መንግስት ነው የፈጠረው። ሊቢያ ያው የምናያት ናት። በዚህ መነሻነት ነው አብዮት ወይስ ሪፎርም ነው የሚያስፈልገን የሚል ሃሳብ ያነሳሁት፡፡ እኔ በመጽሐፌ እንደ አማራጭ ያቀረብኩት ሪፎርም ነው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ የተረዱ ወገኖች፣ በህብረተሰቡ ውስጥ እየተቀጣጠለ የመጣውን የለውጥ ፍላጐት እንዲመሩት ነበር በመጽሐፌ ጥሪ ያቀረብኩት። ከዚህ አንፃር ተሳክቶልኛል ማለት እችላለሁ፡፡ ኢህአዴግ በወቅቱ የነበረው አማራጭ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ለውጥ በመገንዘብ፣ ራሱን ከፍላጐቱ ጋር አስማምቶ፣ ለውጡን መምራት ወይም መበላት ብቻ ነው ብዬም ተናግሬያለሁ፡፡ በኋላ ከውስጡ የለውጥ ሃይሎች መፈጠራቸው እንደ ትልቅ ክስተት አድርጌ እወስደዋል፡፡ 
ለውጡ በዚህ መልክ እውን እንዲሆን እስረኞችን ያለ ቅድመ ሁኔታ መፍታት፣ በሀገር ቤትም በውጪም ለሚገኙ የፖለቲካ ሃይሎች ጥሪ ማቅረብ፣ ከዚያም ብሔራዊ ንግግር  ማድረግ እንደሚገባ ለማስገንዘብ ሞክሬአለሁ፡፡ አብዛኞቹ ተደርገዋል፡፡ የሚቀረው ብሔራዊ ንግግር ማድረግ ነው፡፡ አሁን የማየው ነገር አብዛኞቹ በውጭ የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎች ከለውጡ ጋር ራሳቸውን በሚገባ አለማስማማታቸውን ነው። እነዚህ ሃይሎች ጥሪ ሲያደርጉ የነበረው ለአብዮት እንጂ ለሪፎርም አልነበረም፡፡ አንድም የፖለቲካ ቡድን ሪፎርም መደረግ አለበት ብሎ የተናገረው ነገር የለም፡፡ ሁሉም ስለ አብዮት ነበር ሲናገሩ የቆዩት፡፡ አሁን ችግር የተፈጠረው ለምንድን ነው ከተባለ፣ አብዮት ሲጠብቁ የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎች፣ ሪፎርም ቀደማቸው፡፡ ያውም ባላሰቡት መንገድ፣ ካላሰቡት አቅጣጫ፡፡ አሁን ይሄን እውነታ መዋጥ አቅቷቸዋል፡፡ ይሄን መቀበል ተስኗቸዋል፡፡ መጨረሻ ላይ ጥሪ ተደርጐላቸው ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ፤ “እኔ ነኝ የለውጡ ባለቤት” በሚል የባለቤትነት ሽሚያ ውስጥ መግባታቸውን በግልጽ ታዝበናል፡፡ ሁሉም ሲናገሩት ሰምተናል። እነዚህ ሀይሎች አስተዋጽኦ አላበረከቱም ማለት አይደለም፡፡ በተለያየ አቅጣጫ የሚደረጉ ትግሎች ተጠረቃቅመው ነው ለውጥን የሚያመጡት። ከዚህ አንፃር አስተዋጽኦ አላበረከቱም እያልኩ አይደለም፡፡ ሁሉም ለለውጥ ያግዛል ያለውን የየራሱን ጨዋታ ተጫውቷል፡፡ ነገር ግን ጐሉን ያስገቡት ኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠሩት የለውጥ ሃይሎች ናቸው፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይ፣ እነ አቶ ለማ፣ እነ አቶ ገዱ ናቸው፣ ተጨባጭ ለውጥ ያመጡት። በኛ ሀገር አብዮት እንጂ ሪፎርም ተደርጐ አያውቅም፤ ይሄ የመጀመሪያው ነው፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ሪፎርም አልቀበልም ብለው አብዮት ነው የጋበዙት፡፡ ደርግ ሪፎርም አልቀበልም ብሎ አብዮት ነው የጋበዘው። በኢህአዴግ ውስጥ ግን ለህይወታቸው ሳይሳሱ የታገሉ ሪፎርመሮች ተፈጥረው ነው፣ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ሪፎርም የተፈጠረው። እነዚህ ሃይሎችም የአብዮት አስተሳሰባቸውን ትተው፣ ከሪፎርሙ ጋር ራሳቸውን ማስማማት አለባቸው፡፡ ችግር እየፈጠረ ያለው፣ አሁንም ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ሃይሎች፣ ሪፎርሙን ባለመቀበል፣ በአብዮት መንፈስ ውስጥ በመሆናቸው ነው፡፡ 
ከውጭ የመጡ የፖለቲካ ሃይሎች፣ አብዮት የመፈለግ ዝንባሌ፣ በተጨባጭ በሀገሪቱ ላይ የፈጠረው ችግር አለ?     
አዎ! በነገራችን ላይ ጥንቃቄም መደረግ ነበረበት። ለምሣሌ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግን) ወስደን እንመልከት፡፡ ኦነግን እኔ እንኳ ሳውቀው 45 አመቱ ነው፡፡ ብዙዎቹን መሪዎች በቅርብም በሩቅም አውቃቸዋለሁ። የተወሰኑ ሰዎች አስተሳሰባቸውን አሻሽለው፣ ከቀድሞ ኦነግ ወጥተው፣ የየራሳቸውን ድርጅት ፈጥረው የመጡ አሉ፡፡ አሁን መጨረሻ ላይ የመጣው ቡድን ደግሞ “ኦሮሚያ ነፃ መውጣት አለባት” የሚለው ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር በአጽንኦት መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ሁለት ነገር አንድ ላይ አይሄድም። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት በእርግጠኝነት ለለውጡ ሃይሎች ማረጋገጥም ግዴታም መግባት የነበረበት ነገር አለ፡፡ “እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ከአሁን በፊት በነበረው ሁኔታ ኦሮሞ በደል ስለደረሰበት መፍትሔ ነው ያልኩትን ፕሮግራም ቀርጬ ነበር፡፡ አባላቶቼንም በዚህ ፕሮግራም ነበር አስተምርና አደራጅ የነበረው። አሁን ግን በኢትዮጵያ ውስጥ በኢትዮጵያዊነት መታገል እፈልጋለሁ” ማለት ነበረበት፡፡ ይሄን መሪው በተለያዩ ሚዲያዎች ተናግረውታል፤ ነገር ግን ስለ መለያየት  ሲሰብኳቸው ለኖሩት ተከታዮቻቸውና አባሎቻቸው በአደባባይ ማወጅ ነበረባቸው። አመለካከታቸውን በዚህ እንዲቀይሩ መምከር ነበረባቸው፡፡ “አዲስ አበባ ያንተ ነው፣ ፊንፊኔ ነው ስሙ፣ የማንም አይደለም ያንተ ነው” እየተባለ ሲሰበክ የኖረ ሰው፣ ዛሬ “አዲስ አበባ የኔ ነው” እያለ ረብሻ ቢያስነሳ ከዚህ አንፃር አይደንቅም፡፡ የፖለቲካ ትርኢቱ ምናልባት ለዚያ ዘመን ሠርቶ ሊሆን ይችላል፤ በአሁን ዘመን ግን አይሠራም። ሁኔታዎች ተለውጠዋል። ለተለወጠው ሁኔታ ተስማሚ የሆነ የፖለቲካ ትርኢት አስቀድሞ መፍጠር ነበረበት። አባላቱንም በዚህ መቃኘት ነበረበት፡፡ ይሄ ባልተረጋገጠበትና ባልሆነበት ሁኔታ ነው ወደ ሀገር ቤት የገባው። ይሄ ባለመሆኑ ብዙ ችግር ተፈጥሮ አይተናል፡፡ ለምሣሌ በባንዲራ የተነሳውን ውዝግብ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኦነግ የራሱ አርማ አለው፡፡ አርማውን ይዞ ማውለብለብ መብት ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ኦነግ የሚንቀሳቀሰው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው። የዚያ ክልል መለያ ባንዲራ አለ፡፡ ባንዲራው በክልሉ ህጋዊ ነው፤ እሱን መያዝ ነበረበት። ሦስተኛ ኦነግም የሚንቀሳቀስበት፣ ኦሮሚያ የሚባለው ክልልም የሚኖርባት ኢትዮጵያ አለች፡፡ የኢትዮጵያን ህጋዊ ባንዲራ መውለበለብ ነበረበት፡፡ ለወደፊትም ማንኛውም የፖለቲካ ቡድን የህግን የበላይነት አስከብራለሁ የሚል ከሆነ በመጀመሪያ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አለች ብሎ መቀበል አለበት፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ የተመሠረተው፣ ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር በጋራ እንገንባ በሚል ነው፡፡ ለዚህ ጥሪ ምላሽ ሰጥቶ እመጣለሁ የሚል ሃይል፣ ግልጽ እና ጥርት ባለ መልኩ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አለችን ብሎ ማወጅ አለበት። ኢትዮጵያ ደግሞ ሰንደቅ አላማ አላት፡፡ በህገ መንግስት የተደነገገ፡፡ ምናልባት በህግ የተደነገገው ሰንደቅ አላማ ላይ ላያስማሙ ይችላሉ። ነገር ግን ህገ መንግስቱን ተቀብዬ፣ በሱ ጥላ ስር ሆኜ ለመንቀሳቀስ መጥቻለሁ የሚል ሃይል፤ ባንዲራው ባይስማማውም ማውለብለብ አለበት፡፡ ያንን እያውለበለበለ እንዲቀየር ይጠይቃል፡፡ በህግ የሚያምን ወይም በህግ የበላይነት ስር እሆናለሁ የሚል አካል፤ መጀመሪያ የሚያደርገው ይሄንን ነው፡፡ ምክንያቱም ህገ መንግሥቱን ተቀብለው ነው የመጡት፡፡ 
ለ”አርበኞች ግንቦት 7” በተደረገው አቀባበል ላይ የቀድሞ ሰንደቅ አላማ መውለብለቡን በተመለከተ ምን ይላሉ? 
ትክክል አይደለም፡፡ ግንቦት 7 ተሳስቷል፡፡ እሱም እንደ ኦነግ ህግ ጥሶ ነው የተንቀሳቀሰው። በህገ መንግስት የተደነገገውን ሰንደቅ አላማ ግንቦት 7 ላያምንበት ይችላል፡፡ ሰንደቅ አላማው እንዲለወጥ ትግል ሲደረግ፣ ህግ በመጣስ ሳይሆን ህግን እያከበሩ ነው፡፡ እኔ አሁን ያለውን የፌደራል ባንዲራ አምኜበት አይደለም ይሄን የምለው፤ የህግ ልዕልና ስለሚያስገድደኝ ነው፡፡ ግንቦት 7 ወደ ሀገር ቤት ሲመጣ፣ ከአርማው ጐን ለጐን ህጋዊውን ባንዲራ ማውለብለብ ነበረበት። ወይም እንዲውለበለብ ማበረታት ነበረበት፡፡ ህግን ይዞ ነው ለህግ መለወጥ መታገል ያለበት፡፡ የህግ የበላይነትን ማስከበር ማለት ይሄ ነው፡፡ ይሄ ባንዲራ በዶ/ር ዐቢይ ወይም በሌላ ሰው ውሣኔ የፀና አይደለም፤ በህግ የተደነገገ ነው፡፡ 
ከፖለቲካ ሃይሎች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ሌላው ጉዳይ አለ። አብዛኞቹ በውጭ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ አመራሮች የውጭ ሃገር ዜግነት ያላቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የጥምር ዜግነት መብት የላትም፡፡ ስለዚህ የውጭ ሀገር ዜጋ ሆኖ ለዚህ ሃገር የፖለቲካ ስልጣን መታገል አይቻልም ማለት ነው፡፡ ከአሁን በፊት በደርግ ጊዜም፣ በኢህአዴግ ዘመንም ይሄን ነገር እታዘባለሁ፡፡ ይሄ መሆን የለበትም። አንድ ነገር ሲፈጠር ዜግነት ወደሰጣቸው ሀገር ይሄዳሉ፡፡ የውጭ ሀገር ዜጋ መሆናቸውን እንኳን የምናውቀው ችግር ሲያጋጥማቸው ነው፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች የሲቪክ ተቋማትን ሊያቋቁሙ ይችላሉ፣ ሊመሩ ይችላሉ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁመው ግን የስልጣን ውድድር ውስጥ ሊገቡ አይችሉም። በህግ ክልክል ነው፡፡ የህግ የበላይነት ይከበር ስንል ይሄን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ኢትዮጵያ የጥምር ዜግነት ህግ የላትም። ይህ መሆን የሚችለው የጥምር ዜግነት መብት በህግ ሲደነገግ ብቻ ነው። በዚህም የህግ ጥሰት አለ። ምክክር ሊደረግበት ይገባል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ታሣቢ ሳይደረጉ ነው ማናቸውም የፖለቲካ ሀይሎች ወደ ሀገር ቤት የተጠሩት፡፡ ሌላው ከፖለቲካ ሃይሎች ጋር በተያያዘ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ደግሞ በነፃ አውጪነት የተደራጁ የፖለቲካ ሃይሎችን ምርጫ ቦርድ ሊመዘግባቸው አይገባም፡፡
ለምን?
ምክንያቱም ምርጫ ቦርድ “የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ነው” ስያሜው፡፡ ስለዚህ ነፃ አውጪዎች ከማን ነው ነፃ የምትወጡት ተብለው ሊጠየቁ ይገባል። መቼም ከጅቡቲ ነፃ ለመውጣት አይታገሉም። ታዲያ ከማን ነው ነፃ የሚያወጡት? ከኢትዮጵያ ነው፡፡ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ከማን ነው ነፃ የሚያወጣው? ከኢትዮጵያ ነው። የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ከማን ነው ነፃ የሚያወጣው? ከኢትዮጵያ ነው። ሌሎችም በነፃ አውጪነት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ነፃ ለመውጣት የሚፈልጉት ከኢትዮጵያ ነው፡፡ በዚህ አኳኋን የተደራጁ የፖለቲካ ቡድኖች እንዴት ሆኖ ነው “የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ” ነፃ በሚያወጡበት ሀገር ህጋዊ የሚያደርጋቸው፡፡
ታዲያ ምን ይደረግ ይላሉ?
ግልጽ ነው፡፡ ሊመዘገቡ አይገባም፡፡ የተመዘገቡም ካሉ ስማቸውን እስኪያስተካክሉ ድረስ ሊሰረዙ ይገባል፡፡ ህገ መንግስቱ በብሔር መደራጀት የተፈቀደ ነው አይልም፡፡ በብሔር መደራጀት፣ በነፃ አውጪነት መደራጀት በህግ አልተፈቀደም፡፡ 
በብሔር ወይም በነፃ አውጪነት መደራጀትንም በግልጽ አይከለክልም፡፡ በህግ ያልተደነገገ እንደተፈቀደ ይቆጠራል የሚል ሃሳብም አለ–
አሁን ወደ ህግ የበላይነት እንግባ እያልን እኮ ነው። በህግ ያልተደነገገ እንደተፈቀደ ይቆጠራል የሚለው አንተ እንዳልከው፣ በህግ የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ፖለቲካዊ መረጋጋት ለመፍጠር መስመር ለማስያዝ፣ ህግን ለችግር መፍቻ  መጠቀም ይቻላል፡፡ ህግ ችግር መፍቻ ነው እንጂ ችግር መፍጠርያ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳት አለው ካልን፣ ህግን ለችግር መፍቺያ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ 
በነፃ አውጪነት የተደራጁ የፖለቲካ ሃይሎች መመዝገብ የለባቸውም ብለዋል፡፡ ነፃ አውጪ የሚል ስም ይዘው ሃገሪቱን የሚመሩ ድርጅቶች  አሉ፡፡ እነሱንም ይጨምራል?
ምዝገባ መከልከል መጀመር ያለበት ከእነሱ ነው። ህወሓት የትግራይ ነፃ አውጪ ነው፡፡ ትግራይን ከማን ነው ነፃ የሚያወጣው? መቼም ከጅቡቲ አይሆንም፤ ያው ከኢትዮጵያ ነው። ስለዚህ ህወሓት ስሙን እስኪቀይር ድረስ ከምዝገባ መሠረዝ አለበት። እያንዳንዱ ነፃ አውጪ ከማን ነው ነፃ የምትወጣው ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ከኢትዮጵያ ነፃ እወጣለሁ የሚል ሃይል “በኢትዮጵያ” ምርጫ ቦርድ በምንም አይነት መመዝገብ የለበትም፡፡ 
በመጽሐፍዎ ላይ ስለ ምህረት ያቀረቡት ሃሳብ አለ። ከዚህ አንጻር በቅርቡ የታወጀውን የምህረት አዋጅና ያስገኘውን ጥቅም እንዴት ይመለከቱታል?
የምህረት አዋጅ ያለ ቅድመ ሁኔታና በቅድመ ሁኔታ ሊታወጅ ይችላል፡፡ እኔ የምህረት አዋጅ መታወጅ አለበት ስል የነበረው ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሚደነገገውን ነበር፡፡ በቅርቡ የታወጀው የምህረት አዋጅ ግን ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣል። አንድን የህዝብ ስብስብ ያገለለ አዋጅ ነው። በኢትዮጵያ አብዮት ውስጥ ተጋድሎ ያደርግ የነበረ አንድ የትውልድ አካልን ያገለለ ነው፡፡ በዘር ማጥፋት (ጂኖሣይድ) የተከሰሰ ሰው ምህረት አያገኝም ይላል፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? እርግጥ ነው ነጭ ሽብር ቀይ ሽብር በሚል፣ በፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ፍጅት መፈጠሩ ይታወቃል፡፡ አንድ ድርጊት ሲፈፀም፣ ድርጊቱን ለመፈፀም ምን አነሳሳህ የሚል ነገር በህግ መታየት አለበት፡፡ የነጭ ሽብር ቀይ ሽብር የእርስ በእርስ መተላለቅ ሲፈፀም፣ ገፊ ምክንያቱ ዘር አይደለም፤ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ነው፡፡ የተደራጁም ያልተደራጁም ሀይሎች ናቸው ለፖለቲካ አላማቸው የተገዳደሉት እንጂ የዘር ፍጅት አልተፈፀመም፡፡ ድርጊቱን የጂኖሣይድ ድርጊት ነው ያሉት በፖለቲካዊ መነሳሳት ነው እንጂ በህግ ትርጓሜ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚያን ጊዜ የዘር ማጥፋት አልተፈፀመም፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተብሎ በተመሠረተው ክስ ተፈፀሙ የተባሉት ድርጊቶች፣ በአለማቀፍ ህግ ስለ ዘር ማጥፋት ወንጀል ከተደነገገው ጋር ይለያያል፡፡ ከ1948 (እኤአ) የጄኖሣይድ ኮንቬንሽን ፍሬ ነገር ጋር በጭራሽ የማይገናኝ ነው፡፡ 
የኛ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 281፣ የ1948 የጄኖሣይድ ኮንቬንሽንን መሠረት ያደረገ ህግ ነው። ነገር ግን በኛ ህግ ላይ የፖለቲካ ቡድኖችን መግደል ጄኖሣይድ ነው ይላል፡፡ ይሄ ከኮንቬንሽኑ የተቃረነ ነው። ብዙ መከራከሪያም የሚቀርብበት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እኔም 9 አመት ታስሬያለሁ። ተከራክሬያቸው በነፃ ነው የተሠናበትኩት፡፡ ብዙ ወገኖቼ ግን በዚህ የጨነገፈ ፍትህ ብዙ መከራ አይተዋል፡፡ አሁን የወጣው የምህረት አዋጅ፣ “ጄኖሣይድ የፈፀሙ ምህረት አያገኙም” ያለው፣ ያንን የጨነገፈ ፍትህ መነሻ አድርጐ ነው፡፡ በወቅቱ ክሱ ሲቀርብብን ደግሞ ፈጽሞ የፍትህ ባህሪ የሌለው፣ የአሸናፊዎች ፍርድ ነው የተላለፈው። “ከኢህአፓ መጣን፣ ሥልጣንም ያዝን” በሚሉ ግለሰቦች አቀናባሪነት፣ የፀረ ቀይ ሽብር ኮሚቴ ነበር የተቋቋመው፡፡ በሌላ በኩል የደርግ ጥላቻ የነበራቸው ጋዜጠኞች እየተመረጡ፣ የደርግን ጉዳይ ባለ በሌለ አቅማቸው እንዲያስጮኹት ተደረጉ፡፡ በዚህም ከድርጊቱ ይልቅ ድርጊቱን ለመግለጽ የተሠራው ፕሮፓጋንዳ የምር ድርጊቱን ደበቀው፡፡ እንዴት እንደተደረገ፣ ማን እንዳደረገው፣ መቼ እንደተደረገ፣ ምን እንደተደረገ በግልጽ ማወቅ አልተቻለም፡፡ በደርግ ዘመን የተፈፀመው ቀይ ሽብር ብቻ አይደለም፤ነጭ ሽብርም አለ፡፡ ኢህአፓዎች በምልክት ትዕዛዝ እየተሠጣቸው ሰው ሲገድሉ ነው የነበረው፡፡ ነገር ግን በኋላም ከአሣሪዎች አንዱ እነሱ ነበሩ። በወቅቱ ልዩ አቃቤ ህግ የሚባልም ተቋቋመ፡፡ ይሄ ልዩ አቃቤ ህግ የተቋቋመው ደግሞ “ኢህአፓ ነበርን፤ ወንድሜ እህት ሞተውብናል፣ እኔም ታስሬያለሁ፣ ተገርፌያለሁ” በሚሉ ሰዎች ነበር፡፡ ታዲያ ያ ልዩ አቃቤ ህግ እንዴት ፍትህ ሊያስገኝ ይችላል? ያ ልዩ አቃቤ ህግ የተቋቋመው ፍትህ ሊያስገኝ ሳይሆን ሊበቀል ነው፡፡ ዳኞች ደግሞ የተመለመሉት ፀረ ደርግ መሆናቸው ተለይቶ ነበር። “ደርግ ወንድሜንና እህቴን ገድሎብኛል፣ እኔም ታስሬያለሁ” የሚሉ ተለይተው ነበር በዳኝነት ወንበር ላይ የተሰየሙት፡፡ አልፎ ተርፎ የከፍተኛው ፍ/ቤት የወንጀል ችሎት ሰብሳቢ የነበሩት የህወሓት ታጋይ የነበሩ ናቸው። የሚገርመውና የሚያሳዝነው በወቅቱ ክስ ሳይመሠረት ሲቀር፣ አንድ ሰው አካሉን ነፃ ማድረግ የሚችልበትን ህግ ለ6 ወር ሠርዘውታል፡፡ ይሄን ሰርዘው ያስኬዱት ምርመራ ፍትህ ተብሎ ነው የተጠራው፡፡ ፍ/ቤት ቀርበን ዳኛ ሳይመለከተን፣ እነሱ ይሄንን ነው ፍትህ የሚሉት እንግዲህ፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙዎቻችን ፍ/ቤት ቀርበን እንኳን በእስር ያጋጠመንን ችግር መናገር አንችልም ነበር፡፡ ክስ ሲመሠረት ደግሞ “ባልታወቀ መሣሪያ፣ ባልታወቀ ቀን፣ ባልታወቀ ሰው ተገደለ” የሚል ነበር፡፡ ይሄ ማንም የነበረውን ሂደት ማጥናት የሚፈልግ አካል፣ ዛሬም መዝገቦቹን ተመልክቶ የሚመሰክረው ነው፡፡ አካሄዱ ስህተት ነው ስንል እንኳ የሚሠማን አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የክስ ሂደቱ በአሸናፊዎች የተቀነባበረ፣ በአሸናፊዎች የተዳኘ ነበር፡፡ ለሙያቸው ክብር ባልነበራቸው አቃቤ ህጐችና ዳኞች ተቀነባብሮ፣ ፖለቲካዊ ውግንናን መሠረት ያደረገ ክስ ቀርቦ ነው ጉዳዩ የዘር ማጥፋት ነው የተባለው፡፡ ይሄ የጨነገፈ የበቀል ፍትህ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ በተላለፈ ፍርድና ብያኔ ምክንያት ዛሬ የዘር ማጥፋት ተከሳሾች የምህረት አዋጁ አያስፈልጋቸውም ማለት ሌላ በደልና ሌላ ወንጀል ነው፡፡ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ለበቀል ፍትህ፣ ለአሸናፊዎች ፍትህ ነው በዚህ ውሣኔ ድጋፍና እውቅና የተሠጠው። በዚህ ሁኔታ ወደ 23 ሺህ የኢሠፓ አባላት የክብር መኮንኖች፣ የአየር ሃይልና ባህር ሃይል መኮንኖች ወደ ሃገራቸው መግባት አልቻሉም፡፡ በዚህ ሁኔታ ጣሊያን ኤምባሲ የታሠሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት የምህረት አዋጅ ሲጠብቁ፣ ነገ ዛሬ እንፈታለን ብለው ሲጠብቁ ቅስማቸው እንዲሰበር ነው የሆነው፡፡ አንዳንድ ወገኖች፣ እኔ ይሄን ስል፤ “አንተ የነበርክበት መንግስት በየሜዳው ነበር ሰው የሚገድለው፤ ይሄን እንኳ ለማድረግ አልፈለገም” ይላሉ፡፡ አዎ ደርግ ያንን ፈጽሟል፤ ነገር ግን ያ ግድያ የዘር ማጥፋት አልነበረም። ኢህአፓ፣ ኢዲዩ፣ ወያኔ፣ ኦነግ — እየተባለ ሰው ተገድሏል። ይሄ እውነት ነው፤ ደርግ እንደ ኢህአዴግ አላስመሰለም፡፡ ሁሉንም ፊት ለፊት ነው ያደረገው፡፡ የመደብ ትግል፣ የአይዲኦሎጂ ትግል፣ የፖለቲካ ትግል ግድያ ነው፡፡ ይሄ አይካድም፡፡ መሆን ያልነበረበት ሆኗል፡፡ የዘር ማጥፋት ካልን ግን እኔ እንደውም “ደርግ ሳይሆን ህወሓት የዘር ማጥፋት ፈጽሟል” ብዬ መሟገት የምችልበት በቂ ማስረጃ አለኝ፡፡ የህወሓት ማኒፌስቶ ያነጣጠረው እኮ አማራ የሚባል ዘር ላይ ነው፡፡ የገዥ መደብ ነው ያልነው ይላሉ፤ ይሄ ለኔ አሳማኝ አይደለም። በግልጽና በማያሻማ ቋንቋ “አማራው” ነው ያሉት። ይሄ ለጄኖሳይድ በቂ ነው፡፡ የኢህአፓን አባሎች ገድለዋል። የኢህአፓን አባላት ህወሓት ሲገድል ፍትሃዊ፣ ደርግ ሲገድል የዘር ማጥፋት። ይሄ እንዴት ይሆናል? ኦነግን ህወሓት ሲገድል ፍትሃዊ፣ ደርግ ሲገድል  የዘር ማጥፋት፡፡ ይሄ እንዴት ይሆናል? ትክክል አይደለም፡፡ 
ሌላው በዚህ የጨነገፈ ፍትህ ላይ ያለው ጉድለት ደግሞ የህገ መንግስቱና የሂደቱ ግንኙነት ነው፡፡ አሁን ያለው ህገ መንግስት በህግ ከመጽናቱ በፊት ነው ክስ የተመሠረተው፡፡ ስለዚህ ክሱ ከህገ መንግስቱ ጋር የተገናዘበ አልነበረም፡፡ የዘር ማጥፋት ፍርደኞች ናቸው ከተባለ ኢህአፓም ነጭ ሽብር እያለ ነው የገደለው፣ የሚቃወሙትን ገድሏል፡፡ ስለዚህ በነሱ አተረጓጐም፣ ኢህአፓም የዘር ማጥፋት ፈጽሟል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የኢህአፓ መሪዎች ለዚህ ድርጊታቸው ፍ/ቤት ቀርበው መጠየቅ አለባቸው፡፡ ምህረት አያስፈልጋቸውም ማለት ነው፡፡ ይሄ ጉዳዩ እንዴት እንደሚወሳሰብ ነው የሚያሳየው፡፡ ነጭ ሽብርና ቀይ ሽብር፤ የፖለቲካ ልዩነት የፈጠረው ግድያ ነው እንጂ የዘር ማጥፋት አይደለም፡፡ በዚህ መልኩ ነው መበየን ያለበት፡፡ አሁን የተሠጠው ብያኔ በአሸናፊዎች የተሠጠ ነው፡፡ በጊዜው የዘር ማጥፋት የሚለውን የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግሥታት አልተቀበሉትም ነበር፡፡ 
እኔ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የማመለክተው፣ “የደርግ ሰዎች ጄኖሳይድ ፈጽመዋል ምህረት አይገባቸውም” መባሉ ትክክል አይደለም በማለት ነው፡፡ ፍትህ የሌለው የአሸናፊዎችን የበቀል ፍርድ ተንተርሶ፣ “የዘር ማጥፋት የፈፀሙ” መባል የለበትም፡፡ በወቅቱ “እንደ ደርግ ገደሉ እንዳንባል አስፈርደን እንሰራቸው” የሚል የማስመሰል እርምጃ ነው፡፡ እርዳታ እንዳይቋረጥባቸው ያደረጉት ማስመሰልና ማጭበርበር ነው፡፡ አለምን ያታለለ ድርጊት ነው፡፡ ይሄን የጨነገፈ ፍትህ መነሻ አድርጐ ዛሬ  ደግሞ  ምህረት አይገባችሁም ማለት የበደል በደል ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን የጨነገፈ ፍትህ ማረቅ ያስፈልጋል፡፡ 
እርስዎ ጉዳዩን ወደ ኋላ ተመልሶ መመርመር ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ? 
እርቅ ለሁሉም አይሆንም፣ ምህረቱም ለሁሉም እኩል አይሠራም ከተባለና ልዩ አቃቤ ህጉ የመሠረተው ክስ ህጋዊ ክስ ነው ተብሎ ከተወሰደ፣ ሁሉም ነገር እንደገና ይታይ፡፡ በዚህ ፀንቼ እታገላለሁ፡፡ አንድን ድርጊት ሌላው ሲያደርገው ህጋዊ፣ አንዱ ሲያደርገው የዘር ማጥፋት ከሆነ፣ ጉዳዩ በጥልቀት ይመርመር፣ ለውይይት ይቅረብ፡፡ ሌላው በዚህ የፖለቲካ ትርክት ውስጥ መስተካከል አለበት ብዬ የማምነው፣ እዚህ መስቀል አደባባይ አካባቢ የተገነባው ሃውልት ጉዳይ ነው፡፡ የቀይ ሽብር ሰማዕታት ነው የሚለው፡፡ ኢህአፓ በነጭ ሽብር የገደለውስ ሰው አይደለም? ደሙ የተለየ ነው? ለአንዲት ልጇ ለሞተባት እናት፣ ደርግ ገደለው ኢህአፓ ገደለው ትርጉም የለውም፡፡ ስለዚህ ያ ሃውልት የነጭ እና ቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ መባል አለበት፡፡ አለበለዚያ መፍረስ አለበት፡፡ “ለለውጥ የተሰው ወገንተኞች መታሰቢያ ሃውልት” ሊባልም ይችላል፡፡ ኢህአፓ ሰው ስለመግደሉ እኮ ኢህአፓዎችም በሚጽፏቸው መጽሐፍት ላይ ራሳቸው መስክረውታል፡፡ የደርግ ሰዎች ሶስት አራት ጊዜ እንዴት ይበደላሉ? 
የኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ጉዳይስ እንዴት መታየት አለበት ይላሉ?
ከኢሣያስ አፈወርቂ ጋር ከተጨባበጡ በኋላ እንዴት ለመንግስቱ ምህረት አይሰጥም። መንግሥቱ ኃ/ማርያም እኮ የሀገሩን አንድነትና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በመሰላቸው መንገድ ከኢሣያስ አፈወርቂ ጋር ነው የተጋደሉት፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት እኮ ለሀገር አንድነት ነው ከሻዕቢያ ጋር የተዋደቀው፡፡ መንግስቱ ኃ/ማርያም እኮ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ በዘመኑ በመሠላቸው መንገድ ከሱማሌ፣ ከሻዕቢያ፣ ከወያኔ ጋር ነው የታገሉት፡፡ ይሄን ሁሉ ያደረጉት ለሀገራቸው ብለው ነው፡፡ አላጠፉም እያልኩ አይደለም፡፡ እኔ በግሌ መንግስቱ ኃ/ማርያም ይቅር የማልላቸው ድርጊት ፈጽመዋል የምለው፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት በቀበሮ ጉድጓድ እየተፋለመ ጥለውት መሄዳቸው ነው፡፡ የፈለጋቸውን ምክንያት ቢደረድሩ፣ አንድ የጦር አዛዥ ያሠማራውን ሃይል ቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ጥሎ አይሸሽም፡፡ በዚህ በግሌ ይቅር አልላቸውም፡፡ እዚሁ ሲዋጉ መሞት ነበረባቸው፡፡ የጦር መሪ የሚያዝዘውን ሠራዊት ጥሎ አይሸሽም፡፡ ነገር ግን እንደ ማንኛውም ዜጋ በምህረት ለሀገራቸው መብቃት አለባቸው፡፡ 
ለውጡን ከማካሄድ ጐን ለጐን የህግ የበላይነትን ለማስከበር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
እነዚህ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱ ሃይሎች ታግለዋል፣ ለለውጡ ብዙ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ ነገር ግን አንድ ማወቅ ያለባቸው ነገር አሁን ኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን የለውጥ ሃይል መቀበል አለባቸው፡፡ ሙሉ እውቅና መስጠት አለባቸው፡፡ ከአብዮት ቅዠት መውጣት አለባቸው፡፡ ሪፎርሙን መቀበል አለባቸው። ጥሩ ሊጫወቱ ይችላሉ፤ ጐሉን ግን ያስቆጠሩት እነ ዶ/ር ዐቢይ ናቸው፡፡ ዋናው ደግሞ ግብ መቆጠሩ ነው። ለዚህም ሙሉ እውቅና መስጠት አለባቸው። አንዳንዶች እነ ዶ/ር ዐቢይን እኛ ነን የፈጠርናቸው ሲሉ እሠማለሁ፡፡ እኔ ይሄን አልቀበልም። ቄሮ ፈጠራቸው የሚሉም አሉ፡፡ ይሄንንም አልቀበልም፡፡ ራሣቸውን የፈጠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ራሣቸውን ፈጥረው፣ ከነበረው የደህንነት መዋቅር ራሣቸውን ደብቀው ታግለው፣ ለድል የበቁ ሰዎች ናቸው፡፡ ለትግላቸው ምናልባት የቄሮ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ አበርክቶ ሊሆን ይችላል። እነ ዶ/ር ዐቢይ ራሣቸውን የለውጥ ሃይል አድርገው፣ በብርቱ ትግል ለድል የበቁ ሰዎች ናቸው፡፡ ይሄን ሁሉም ሃይል መቀበል አለበት፡፡ 
የህግ የበላይነት ማለት የህግ ድንጋጌን ማክበር ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እንዴት እንደሚቻል የተቀመጠ ህግ አለ፡፡ ያንን ማክበር ማለት ነው። ከውጭ የመጡት ሃይሎች ለአባሎቻቸው የህግ ገለፃ ማድረግ አለባቸው። ህግ አስከባሪው ሃይልም ከለውጡ ጋር የተስማማ በቂ ስልጠና አግኝቶ ነው ወደ ህግ ማስከበር መግባት ያለበት። የህግ የበላይነት የሚከበረው በፖሊስ፣ በአቃቤ ህግ፣ በፍ/ቤትና በማረሚያ ቤቶች ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ደግሞ ሳይውል ሳያድር መጽዳት አለባቸው። በህዝብ ተሳትፎ እንደገና መዋቀር አለባቸው፡፡ ይሄ ቅድሚያ ተሰጥቶት ዛሬውኑ መሠራት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ እድል ሆኖ መጥፎ የህግ ሰው ይበዛል፡፡ ህግን የፖለቲካ መሣሪያ የሚያደርግ፣ ትዕዛዝ ተቀባይ ሆኖ ህዝብ የሚያንገላታ መጥፎ የህግ ሰው ነው፡፡ ጐበዝ የህግ ሰው ግን ለህግ የበላይነት የሚቆም፣ የፖለቲካ ቡድን መሣሪያ አለመሆኑን የሚያስመሰክር፣ ህግ የፍትህ መሣሪያ ነው ብሎ የሚያምን ነው። ለምሣሌ የፀረ ሽብር፣ የፕሬስ አዋጅ የመሳሰሉት መጥፎ የህግ ባለሙያዎች የሠሩት ነው፡፡ የእነሱ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ እኔ ትልቁ ቅሬታዬ፣ አሁንም ከገዢው ፓርቲ ሣጥን ውስጥ አለመወጣቱ  ነው፡፡ ዛሬም ዳኞች፣ አቃቤ ህጐች በፖለቲካ ውግንናቸው  እየተመረጡ ነው፡፡ የፍትህ ተቋማት ገለልተኛነታቸው እንዲረጋገጥ ከተፈለገ፣ በተቻለ መጠን በጀቱም ሳይቀር ከመንግስት ውጪ መሆን አለበት፡፡ 
ራሱን የቻለ ተቋም ነው መሆን ያለበት። ለዳኝነት የሚመለመሉ ሰዎች ህዝብ ተችቷቸው፣ በጥንቃቄ የተመረጡ መሆን አለባቸው። ከኢህአዴግና ለኢህአዴግ ውግንና ካላቸው ሰዎች ውጪ መመልመል አለበት፡፡ ፖሊስም፣ አቃቤ ህግም መመልመል ያለበት በዚህ መልኩ ነው፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ነው የሚሠሩት ብለን ስለምናምናቸው ልንረዳቸው ዝግጁ ነን፡፡ ኢትዮጵያን ሊገነቡ የተነሱ ሰው ናቸው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ወደ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ማህበራዊ ግንባታ ለመምጣት ማሠሪያው የህግ የበላይነት ስለሆነ፣ ይሄ ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ አይደለም፡፡ 

addisadmassnews

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *