‹‹የዴሞክራሲ ምኅዳር ማስፋቱ የይስሙላ አይደለም፡፡ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ ምርጫ ቦርድ እና ሌሎችም እንዲጠናከሩ ይደረጋል፡፡››ጠቅላይ ሚንስትር ዶ.ር ዐብይ አህመድ

 ባሕር ዳር፡መስከረም 26/2011 ዓ.ም(አብመድ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር ዶ.ር ዐብይ አህመድ በድጋሜ ፓርቲውን እስከ ቀጣዩ ጉባኤ እንዲመሩ በመመረጣቸው ለግንባሩና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምስጋና አቀረቡ፡፡

ዶ.ር ዐብይ በሐዋሳ ዓለማቀፍ ስታዲዮም በተዘጋጀው የማጠቃለያ መርሀ-ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹ጉባኤው በቀጣይ ኢህአዴግና መንግሥት የሚመሩበት የለውጥ አቅጣጫ የተቀመጠበት ነው፡፡ የተጀመረውን ለውጥ እንዲቀጥልና ይህችን ታላቅ ሀገርና ታላቅ ሕዝብ እንድመራ ዕድል ስለተሰጠኝም እጅግ ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ፤ የተሰጠኝን ኃላፊነትም በአግባቡ እወጣለሁ›› ብለዋል፡፡

በኢህአዴግ ጉባኤ ሰላም ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ መቀመጡንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሰላም በአጠገባችን ያለ ግን የማንገዛው፤ ካልጠበቅነው ግን የሚጠፋ ነው፡፡ በመንግሥት በኩል ትኩረት ሰጥተን ሰላምን ለመጠበቅ እንሠራለን፡፡ ግን ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶች፣ በጋራ ሰላምን እንድንጠብቅ ጥሪየን አቀርባለሁ›› ብለዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት የታዩትን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የተስፋ ጅማሮዎች የከሚያኮላሻቸው የሕግ የበላይነት አለመከበር መሆኑን የገለጹት ዶ.ር ዐብይ ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
‹‹ይቅርታና ምሕረት መቸም ቢሆን የማንለውጣቸው መርሆዎቻችን ናቸው፤ ግን ከዚህ በላይ የሚሆኑ ከየትኛውም ብሔር የተገኙ ከሕግ በታች እንዲሆኑ እንደሠራለን›› ሲሉም በመንግሥትና በኢህአዴግ በኩል ቁርጠኛ አቋም መያዙን ተናግረዋል፡፡ ሕግን ማክበር በማይፈልጉ ሰላም እንዳይደፈርስ ሁሉም ከመንግሥት ጎን ሆኖ ለሕግ የበላይት ዘብ እንዲቆምም ጠይቀዋል፡፡

የተለያዩ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ለሕዝቡ የማይበጁ ሆነው እስከተገኙ ድረስ ለማሻሻል የፍትሕ ተቋሞች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር እንዲያሻሽሉ የአህአዴግ ጉባኤተኞች አቅጣጫ እንዳስቀመጡም ዶ.ር ዐብይ ተናግረዋል፡፡
‹‹የዴሞክራሲ ምኅዳር ማስፋቱ የይስሙላ አይደለም፡፡ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ ምርጫ ቦርድ እና ሌሎችም እንዲጠናከሩ ይደረጋል፡፡›› ያሉት ዶክተር ዐብይ ቀጣዩ ምርጫ የታመነ እንዲሆን አቅጣጫ እንደተቀመጠም በንግግራቸው አንስተዋል፡፡

‹‹ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ይሁን ስንል ኢህአዴግ የሕዝብ ይሁንታ እንዲያገኝ፣ ተፎካካሪዎችም ከመበታተን ወጥታችሁና ጠንክራችሁ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንድናካሂድ በጋራ እንድንሠራ ጥሪ አቀርባለሁ›› ብለዋል፡፡
‹‹አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ወጣቶች፣ ምሁራንና ሴቶችን ወደ አመራር አምጥተናል፤ ይህም የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ በማሰብ ነው፡፡ ኢህአዴግን መገዳደር የምትፈልጉም በወጣትና ምሁራን ካልተደራጃችሁ ፉክክሩ ይከብዳችኋል፡፡ እኛ በአዲስ መንገድና ብልሀት መጥተናልና፤ የሽንፈት ሽታ ከሸተታችሁም ልምድ ልናካፍላችሁ ዝግጁ ነን›› ሲሉም ለተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሚዲያ ተቋማትንም ኢትዮጵያ የሚስፈልጋት ዴሞክራሲ እንደሆነና እሱም በእውነተኛ መረጃ እንደሚገነባ በመግለጽ ‹‹ ለማንም ሳታዳሉ በታማኝነት መረጃ አቅርቡ›› ብለዋል፡፡
በቀጣይ ሁለት ዓመታት ‹‹ኢህአዴጎች ከሕዝባችን ጋር በመሆን ግብርናን ለማዘመን፣ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት፣ … በልዩ ትኩረት እንድንሠራ አቅጣጫ አስቀምጠናል›› ብለዋል ዶ.ር ዐብይ፡፡

‹‹ተዝቆ የማያልቅ ባሕልና ታይቶ የማይጠገብ ቅርስ አለን፤ ትኩረታችን ቱሪዝም ላይም ይሆናል፡፡ ታሪካችን፣ መልክአ ምድራች፣ ባሕላችን፣ .. በማስተዋዎቅ በራችን ለመላው አፍሪካውያ ክፍት ይሆናል፤ በመልካም መስተንግዶ ታግዘን ዘርፉን እሳድጋለን›› በማለት ቱሪዝም በቀጣይ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከተሞቻችን ያደጉ፣ ድኅነትን የቀነሱ፣ የኑሮ ጫና የማያመጡ እንዲሆኑ፣ አዲስ አበባም እንደ ስሟ አበባ እንድትሆን በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል፤ ለወጣቶችም የአብረን እንሥራ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ኢህአዴግ ከአራቱ ድርጅቶች በተጨማሪ ሌሎችም ታክለውበት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት፣ የራሱንና የኢትዮጵያን አንድነት የሚጠብቅ ድርጅት እንዲሆን አቅጣጫ መሰጠቱንም ሊቀ-መንበሩ በመዝጊያ ሥነ-ስርዓቱ ተናግረዋል፡፡
እያንዳንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ከሚከፈለው በላይ እንዲያገለግል ልዩ ክትትል እንደሚደረግም ቃል ገብተዋል፡፡ ለሁሉም የመንግሥት ሠራተኞችም በቅንነት እንዲያገለግሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያን እንደትልቅነቷ፣ እንደ በርካታ የባሕል ባለቤትነቷ፣ ብዙ ሃይማኖቶች እንዳሏት ሀገር፤ ማገልገል ትልቅ ኃላፊነት ነው›› ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር ዐብይ በንግግራቸው፡፡
‹‹ወጣቶች ድንጋይ ሳይሆን መጥረጊያ ይዛችሁ፣ እጃችሁን ጦር ሳትይዙበት ለመተቃቀፍ ከፍታችሁ፣ ለሀገራችሁ ኩራት እንድትሆኑ፣ በፋኖ፣ ዘርማ፣ ቄሮ እና ሌሎችም ስም የተደራጀካችሁ ሕብረታችሁ ለሀገራዊ አንድነት እንዲሆን፤ ለመደጋገፍ እንጅ ለመገፋፋት እንዳይሆን፣ ለመስጠት እንጅ ለመቀማት እንዳይሆን፣ አደራ እላለሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲ፣ በሥራ፣ በተለያዩ ተግባራት ያላችሁ ኃላፊነታችሁን በአግባቡ ተወጡ›› ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

‹‹ምሁራን፣ አርቲስቶች፣ ታዳጊዎች፣ ሴቶች ኢትዮጵያ ለሁላችን ስለምትበቃ ከመላው አፍሪካ ጋር አብረን እንነሳ!›› ብለዋል፡፡
በአብርሀም በእውቀት – ፎቶው ከአቶ ፍጹም አረጋ ገጽ የተወሰደ ነው፡

AMMA

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *