ስለ ኦነግ ሲወራ፣ ስለ የትኛው ኦነግ እንደሚወራ መረዳት አይቻልም። ኦነግ አጠፋ ከተባለ የትኛው ኦነግ እንደሆነ ልይቶ መኮንነ አዳጋች ነው። ኦነግ ደግ ስራ ሰራ ቢባልም ለማመስገን እንዲሁ ችግር ነው። ኦነግ ዞሮበት እንዳዞረብን ይኸው ግማሽ ምዕተ ዓመት ሞላን።  ኦነግ / የትኛው እንደሆነ ለመለየት ቢያስቸግርም ዛሬ በሰላም ለመታገል መግባቱን አስታውቆ ሳለ ደድንገት አቋሙን በመንግስት ሚዲያ ሲነገረን ከማዞርም በላይ አጥወልውሎኛል። 

“ኦነግ ወደ ሀገር ቤት የገባው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ትጥቁን ፈትቶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ነው ተብሎ የሚነገረው መሰረት ቢስ ወሬ ነው ። እኛ ትጥቅ እንድንፈታ የተስማማንበት ስምምነት የለም ። የታጠቀው አካል ትጥቅ ይዞ እያለ እኛ ትጥቅ የምንፈታበት ምክንያት አይኖርም … ትጥቅ ፈቺም አስፈችም የለም  ” አቶ ዳውድ ኢብሳ ለዋልታ የተናገሩት

እንዳለው አቀንቃኝ ኦነግ ከታገተበት ኤርትራ በሰላም አገር ቤት ሲገባ፣  የታሰበውና “መሪ” የተባሉት ይፋ እንዳደረጉት በአዲሱ እሳቤ በሰላማዊ መንገድ የተጀመረውን ለውጥ በማገዝ ለመስራት ነበር። አሁን ግን ብረት ይዞ ከወዲህ ወዲያ እያለ መሆኑንን ቀውስ ከተፈጠረበት አካባቢ ያሉ አመራሮች ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ አቶ ዳውድ ኢብሳ የሰጡት ምላሽ ነገሩን ሁሉ ታጥቦ ጭቃ አድርጎታል። አቀንቃኙ እንዳሉት ” ከእንቅልፌ ስነቃ — እዛው ነኝ ለካ” አይነት ሆኗል። እኔም ለመሆኑ ኦነግን ማን አስታጠቀው? የሚለውን ጥያቄና የእሳቸውን መልስ ሳሰላስል April 2, 2013 ጎልጉል የተባለ የድረ ገጽ ጋዜጣ ያተመው ታወሰኝ። እናም አቶ ዳውድም ይሁኑ ሌሎች ያ – ዘመን ትዝ ብሏቸው ይሆን ስል ጠየኩ።

የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት በኦነግ ታጣቂ ሃይሎችና በኢህአዴግ ሰራዊት መካከል እኩል ሊባል በሚችል ደረጃ የጡንቻ  መፈታተን ነበር። ደርግ ሲበታተን ኦነግን የተቀላቀሉ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት አካላት ወያኔን የማዳፋት አቅሙ ነበራቸው። በወቅቱ የንስር ያህል ጉልበት ቢኖራቸውም ራሳቸውን ጫጩት አድርገው ተመለከቱ። አዲስ አበባ ሲገቡ በመክለፍለፍ ላይ ስለነበሩ ማስተዋል ተሳናቸው። በዚሁ ጡዘት ሲጋልቡ የወያኔ ስልት ሰላባ ሆኑና የነበራቸውን የህዝብ ድጋፍ አራግፈው ጣሉት። በስሜት እየተነዱ ከሚወዷቸው ሁሉ ተቀያየሙ። ህወሃት አጋጣሚውን ለቅስቀሳና ለስም ማቆሸሻ ሰራበት። በስተመጨረሻ ኦነግ ሃይሉንና አቅሙን ዘንግቶ በአመራር ችግርና በአቋም ሸውራራነት ሃይሉን በሙሉ ወደ ካምፕ በማስገባት የኢህአዴግን የእርቅ ጥያቄ ተቀበለ። ሰራዊቱን እየነዳ በፈቃደኛት ካምፕ አማርጦ አሳሰራቸው። 

በሻዕቢያ አደራዳሪነት ሁርሶ፣ ደዴሳና መስኖ የገባው ሰራዊት “በደባ” ተከቦ ትጥቁን እንዲፈታ ተደረገ። አብጦ የነበረው የኦነግ ጡንቻ በቅጽበት ሟሟ፤ ሰለለ። ኦነግ ሲቆጣጠራቸው የነበሩትን ቦታዎች ለማስተዳደርና በኦህዴድ ለመተካት ኢህአዴግ እንደ እባብ ተሹለክልኮ ዓላማውን አሳካ። ሻዕቢያም በዚሁ ውለታው ኢትዮጵያንና ኢኮኖሚዋን ብሎም የኢትዮጵያን ስነልቦና እንዳሻው እንዲጋልብበት ተፈቀደለት። ብዙ አሻጥር ተሰራ፤ ተፈጸመም። ደንዳና ቆዳ ያላት ኢትዮጵያና ህዝቧ ተቦጠቦጡ። ተዘረፉ። አንድ እግር የቡና ተክል የሌላት ኤርትራ ቡና ላኪ ከሚባሉት ቀዳሚ አገራት ዝርዝር ውስጥ መሰለፏን ግብር የምንከፍለለት የአገራችን ሚዲያ ሳይቀር አበሰረልን። እድሜ ለመለስ ዜናዊና አጫፋሪዎቻቸው አፈርን። ነደድን!! እነ መለስ ግን ዛሬ ድረስ ባለ ” ራዕይ” ይባላሉ። 

“አገሬን ከወራሪ አጸዳሁ” በማለት ከበሮ እየመታ ጦርነት አልቋል ብለው እጅ የሰጡ የወገን ወታደሮችን የረሸነው ሻዕቢያ ኢትዮጵያንም ያስተዳድር ጀመር። ዛሬ የሚማልባቸውና “ውርሳቸውን ሳናዛባ እናስጠብቃለን” የሚባልላቸው አቶ መለስ እንደ ባዕድ መሪ የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም ለሻዕቢያ አሳልፈው ሰጡ። የሻዕቢያ ታጣቂዎችና ኢትዮጵያ አብልታ ያሳደገቻቸው ጎረቤቶቻችን ሳይቀሩ ናጠጡብን። በየደጃቸው መሳሪያ ወደላይ እየተኮሱ በደስታ ውለታ ባስቀመጠችላቸው አገር ላይ ተሳለቁ። በጥጋብ ፋነው በባሩድ አገራቸንን ደረት ደረቷን እየነረቷት ዘለሉብን። ይህ ሁሉ የሆነው ከሌላኛው ጨዋታና የመለስ ቅዠት በተጨማሪ ኦነግን በአደራዳሪነት ስም አስከብበው ስላስተነፈሱት ነበር። 

በዚህ መነሻ ከሆነና ስጋት ከሆነ አቶ ዳውድ ኢብሳ ጉዳዩ ” ሴንሲቲቭ” ነው ሲሉ መሳሪያ አስፈቺና ፈቺ እንደሌለ የነገሩን ” አይቼሽ ነው ባይኔ ወይስ በቴሌቪዥን” የሚለውን ዘፈን ከመጋበዝ ያለፈ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። ማንገራገራቸውም ልክ አይሆንም። ሌላ ከጀርባ የተያዘ ጉዳይ ከለኤለ። ዛሬ፣ የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት አይደለም። ዛሬ በሰላም ወደ አገር ቤት መመለስ የተቻለው በንጹሃን ደምና በኢህአዴግ ውስጥ በተነሱ የለውጥ ሃይሎች ትግል ነውና፣ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ በማስተዋል መጓዝ እንጂ ሌላው ዓይነት ሩጫ መጀመር በራሳቸው በኦሮሞ አክቲቪስቶችና ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም።

“አክራሪ” የሚባሉት አቶ ጸጋዬ አራርሳ እንኳን  ” … መንግሥት የታጠቁትን ትጥቅ ማስፈታት መጀመር አለበት። እየታጠቁና እያስታጠቁ ያሉትን ሁሉ ማስቆም አለበት። የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ፖለቲካዊ ኃይሎች ሁሉ ለሰላም መተባበር አለባቸው። የሰላም ፍላጎታቸውንም በግልፅ ለሕዝብ እየገለፁ ተጠያቂነትን መሸከም መጀመር አለባቸው።… ከመብት ያለፈ የፖለቲካ ምኞትን ለማሟላት በማሰብ ብቻ እራስን በማስታጠቅ ያልተገባ የፖለቲካ ፍላጎትን በመሳሪያ በመመካት ሌሎች ላይ ለመጫን የሚንቀሳቀሱ የእብሪት ኃይሎችን ያለምንም እሹሩሩ በሕግ አግባብ በገሃድ ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል።

ዳውድ ኢብሳ የሚመሩትም ኦነግ ይሁን ሌላ ማንኛውም ድርጅት እንዲህ ባለው የነፍጥ ቁማር ውስጥ ሊገባ የሚያስችለው አንድም ምክንያት ለጊዜው በሌለበት ሁኔታ፣ አካሄድን ማበላሸት ከቀድሞው አለመማር ብቻ ሳይሆን፣ ከስርና ከስደት ወደ ቤታችሁ እንድትመለሱ፣ ነጻ ያወጧችሁን አካላት በሙሉ ውለታና መርሳት ነው። ታሪክንም ማበላሸት ነው። ጸጋዬ አራርሳ እንዳሉት ” አጉል ፍርሃት ” ነው።

ከዚህ በዘለለ ግን እሱ ሰራዊት ከሆነ፣ በአዲግራት አድርጎ አገሩ የገባው ሰራዊት እንዴት በየመንደሩ ሊበትን ቻለ? የሚል ጥያቄና አሁን በተለያዩ ወገኖች የሚሰራጨው የመሳሪያ ማስታጠቅ ዘመቻ መሪ ማን ነው ? ለሚሉት ጥያቄዎች ዜጎች መልስ ይሻሉ። በጋምቤላ በኩል የደቡብ ሱዳንን መንግስት የሚወጉ ሽፍቶች መሳሪያ በገፍ እንዲያስገቡ እንደሚደረግ መርጃዎች አሉ። እነዚህ አማጺዎች ከጋምቤላ አመራሮች ጋር ግንኙነት አላቸው። እነዚህ አመራሮች ደግሞ ” አንደመርም” በሚል አፈንጋጭ ከሆኑት ወገኖች መሆናቸውን የሚያውቁ ሚስጢር እያወጡ ነው። 

እናም በዚህ መመዘና መሰረት አሁን የቤኒሻንጉል ክልል አመራሮች የሚከሷቸው ህጻናት የኦነግ ወታደሮችን ማን ነው መሳሪያ እየገዛላቸው ያለው? ለምንስ ዓላማ ነው ነፍጥ ይዘው ንጹሃንን እያፈናቀሉ ያሉት? ለምንስ ነጹሃንን ይገላሉ? ትርፉስ ምንድን ነው? ከማፈናቀሉ በሁዋላ ቀጣዩ ተግባር ምን እንዲሆን ይጠበቃል? ነው በኦነግ ስም የማይታወቁ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች የሚያደርጉት ዘመቻ ነው? አለያም እንዲሁ ዜጎችን በማፈናቀልና በመግደል የሚከሰሰው የቤኒሻንጉል ክልል አማካሪዎች የሚያሴሩት ድርጊትነው? እኒህን ጉዳዮች መንግስት ሳይውል ሳያድር ግልጽ ሊያደርግ ይገባል። 

አቶ ዳውድ ኢብሳ ለዋልታ ከተናገሩት ቅንጫቢ እንደሰማሁት እሳቸው ለጉዳዩ ባዳ መሆናቸውን ነው። እንደውም እንዲጣራ ይጠይቃሉ። ጉዳዩ በዚህ ደረጃ ህዝብ ፊት ማስተባበያ የሚቀርብበት ከሆነ፣ አሁንም ምን እየሆነ ነው? የሚለው ድምጽ ይበርክታል። ለሁሉም ግን የዳውድ ኢብሳን ሙሉ ንግግር እንስማ!!

ዋልታ የበደኖውን የኢንቁፍቱ ገደል ድራማ ለአቶ ዳውድ ኢብሳ አንስቶባቸዋል። ጠያቂው ምን ያህል እንደሞገታቸውና የት ድረስ እንደሚዘልቅበት ይፋ ባይሆንም፣ አቶ ዳውድ በገልተኛ ወገን እንዲጣራ ያኔውኑ መጠየቃቸውን። አሁንም በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ፍላጎታቸው መሆኑንን አመላክተዋል። ታዲያ በጋረሙለታው የበደኖ ዘግናኝ እልቂት ኦነግ በተለያዩ አመራሮቹ እጁ እንደሌለበት ካስታወቀ፣ ማን ነው? የሚለውን ጉዳይ ለማጣራት ገለልተኛ ወገን እንዲሰየም፣ አለያም የአገር ውስጥ የመብት ተሟጋቾች ለምን ታሪክ እትሰሩም?

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *