የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች አደራጃጀት፣ ስልጣንና የስራ ድርሻ ለመወሰን የወጣው አዋጅ  በክልሉ የዳኝነት ስራ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ አለው ተብሏል።

አዋጁ ፍርድ ቤቶች ተጠሪነታቸውን እና ሀላፊነታቸውን የለየ እና ያለማንም ጣልቃ ገብነት ስራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያደርግ የህግ ማእቀፍም አስቀምጧል።

እንዲሁም ከዚህ ቀደም የነበረውን አዋጅ የቀየረ በሚባል ደረጃ የተዋቀረ ነው የተባለ ሲሆን፥ በተለይም የዳኝነት ስራን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ለውጥ ተደርጎበታል።

አዋጁ ህብረተሰቡ ከወረዳ እስከ ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመመላለስ የሚያባክነውን ጊዜ እና ገንዘብ በመቆጠብ ከወቅቱ ጋር እንዲራመድ እንደሚያደርገው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኮሙዩኒኬሽን ዳሬክተር አቶ ጎንፋ ቱማ ገልፀዋል።

ከዚህም ባሻገር በየጊዜው ከዳኝነት አሰጣጥ መዛባት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ቅሬታ ለመፍታት በወረዳ ደረጃ በአንድ ዳኛ ብቻ የሚተላለፈው ወሳኔ ወደ ሶስት እንዲያድግ መደረጉን ዳሬክተሩ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአዋጁ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተልእኮዋቸውን እና ተጠያቂነታቸውን የለየ አደረጃጀት መዘርጋቱንም አቶ ጎንፋ አስታውቀዋል።

የፍርድ ቤቶች ተጠሪነትም የወረዳ ለከፍተኛ፤ ከፍተኛው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሆኖ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ለጨፌው እንዲሆን ያስቀምጣል።

የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች ተጠሪነትም በዚሁ የሚመራ ሆኖ በተለይ ከዚህ ቀደም የምክትል ከዚህ ቀደም በግልፅ ያልተቀመጠው የምክትል ፕሬዚዳንቶች የስራ ድርሻም ሆነ ተጠሪነት የአሁኑ አዋጅ በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑን ገልፀዋል።

የዳኝነት ነጻነት በተመለከተም በአዲሱ አዋጅ የህግ ማእቀፍ ተበጅቶለት የዳኝነት ስራ ላይ ጣልቃ የሚገባ እና ተጽኖ የሚያደርግ አካል እስከ 5 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ አስቀምጧል። ይህም ዳኞች ህጉ በሚፈቅድላቸው እና  ሙያዊ ስነ ምግባር በተላበሰ መልኩ ፍትህ ለማስፈን እንዲሰራ ያስችላቸዋል ነው የተባለው።

በሰርካለም ጌታቸው    (ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *