(አያሌው መንበር)

በተረፈ ውስጠ ሚስጥሩ ሳይገባችሁ በግልብ መረጃ እየተነሱ የሚቃወሙትን ስም ለማውጣት የምትሞክሩ ሰዎች አደብ ግዙ።

ትናንት እነ ገዱንና ደመቀን የተሻሉ ብለን ስንናገር ምን ስትሉን እንደነበር እናውቃለን።ዛሬ ለአምባቸውም ስንከራከር ስም ለማውጣት የምትሮጡ ድኩማኖች ገፍተን ሌላ ነገር እንድንጨምር ታደርጉናላችሁ።

እንኳን ከሁለተኛ ወገን የሚሰማ መረጃ ከራሥ ከባለቤት የሚሰማ እንኳን ሰምና ወርቅ አለው።ፖለቲካ ሁልጊዜም ከግምትና ሰም የራቀ ነው።

ይልቁንም የተሻለው የሚያቆጠቁጡ ሴራዎችን በግልፅ እየታገሉ የለውጥ ቡድኑ ቲም ጠንክሮ እንዲወጣ ማድረግ ነው መፍትሄው።

አዴፓ ከአበልዥነት፣ ከቅቤና ማር ጫኝ ኔትወርክና፣ ከትውውቅ ደረጃ እድገትና ምደባ ባህሉ ከሆነው ብአዴን መሻል አለበት። የኢሳቱ ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም የድርጅቱ ቁልፍ ሰው ነገረኝ በሚል የፃፈውና በኢሳትም የወጣው የዶ/ር አምባቸው ጉዳይ እኔም (ምናልባትም ከተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ምንጭ) ተመሳሳይ ነገር ደርሶኛል።በግሌ የሚጠቅመኝን ብቻ ወስጃለው፤ እኔ ግን ወሬው ላይ ሳይሆን መፍትሄው ላይ አተኩራለው።

ፋሲል ሲፅፍ እንዲህ ይላል :-

“የድርጅቱ ቁልፍ ሰው ጋር ውይይት አድርጌ ነበር። የነገረኝን እንደወረደ አቀርበዋለሁ:-

“ዶ/ር አምባቸው ፕሬዚዳንት ለመሆን ጥያቄውን ያቀረቡት ራሳቸው ናቸው። ጥያቄውን እንዳቀረቡ አቶ ገዱና አቶ ደመቀ በጽኑ ተቃውመዋቸዋል። አንተም ልትከዳን ነው በሚል ማንገራገሪያ ሳይቀር ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑት ለምነዋቸዋል። ዶ/ር አምባቸው፣ ‘በዚሁ ቦታ ብሆን፣ ትንሽ ጊዜ ወስጄ ለማንበብና ለሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ራሴን ለማዘጋጀት ይጠቅመኛል’ የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል። ይህም ተቀባይነት ባለማግኘቱ ‘ እንደሱ ከሆነ የፕሬዚዳንቱ ስልጣን በአዋጅ ትንሽ ከፍ ይደረግና ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና በዲፕሎማሲው ስራ በስፋት የምሳተፍበት ሁኔታዎች ይመቻቹልኝ’ ብለው ሃሳብ በማቅረባቸው በዚህ መሰረት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል። ምናልባትም ሰኞ ፕሬዚዳንት ሆነው በይፋ ሊሾሙ ይችላሉ። በአቶ ገዱና አቶ ደመቀ ላይ ሲዘንብ የነበረው ትችት ተገቢ ያልሆነና በመረጃ ላይ ያልተደገፈ ነው።”……..የሚል ነው

ከላይ የተፃፈው ፅሁፍን አንድምታ ለፖለቲከኞች የምተወው ሁኖ ይህንን መሰል ነገር ግን ይመስለኛል እነ ቹቹ አለባቸው፣ እነ ውብሸት ሙላት፣እና ሌሎችም ተቀራራቢ ነገር እንደደረሳቸው የሚጠቁም መረጃዎችም ተመልክቻለው።

እኔ ደግሞ ጥሎብኝ የፖለቲካ መረጃ ላይ ተጠራጣሪ ነኝ።ብዙ ርቀት እጓዛለው።እናም ብዙ ጊዜ ለነገ የምለውን እየተውኩ፣ ለዛሬ አስፈላጊነው የምለውን የራሴን እምነት እየጨመርኩ ነው የምፅፈው።እናም እውነታነት ያለው ትንሽ ቢሆንም ብዙ ጥያቄ ይጭርብኛል።

ለምሳሌ የእነ ደመቀና ዶ/ር አብይን አፈና በተመለከተ ከመከላከያ፣ከቦታው አብሮ ከነበረና ከእነ ደመቀም ጋር ከነበረ ከሶስት ወገን ሰምቻለው።ለኢሳት ያለፈውን መረጃም የማግኘት እድል ነበረኝ።

ነገር ግን የወሰድኩት አቋም የደመወዝ ጥያቄ አይደለም የሚል ነበር።በወቅቱ ብዙ ሰው ሰድቦኛል። ዶ/ር አብይ እና ሰዓረ ግን ውለው አድረው እውነታውን አውጥተውታል።አለመሳሳቴንም ብዙዎች የተረዱት ይመስለኛል።

በተመሳሳይ ዶ/ር አምባቸውን በተመለከተም በውጭ ያለን ሰዎች በይሆናልና ይመስለኛል የምንፅፋቸው አሉ፣ ለፕሮፖጋንዳ እና የሰውን ስሜት ለመለካት የሚለቀቁ አሉ፤ እንዲሁም በቀናነት እውነተኛ ተደርገው እዛው ውስጥም የተለቀቁ መረጃዎች ያሉ ይመስለኛል። ሁሉንም በሚዛናቸው አያለው።ይህ እንደተጠበቀ ሁኖ በይደር የምተወውም የራሴ መረጃ ይኖራል።

ልክ እንደ ዶ/ር አብይ ሁሉ ምናልባት ራሱ ዶ/ር አምባቸውም ወይም የሚቀርቡት ሰዎች መረጃውን በግልፅ ያወጡታል ብየ አስባለው።ይህንን እስካልሰማው ድረስ ውስጤ አይሽርም።ትክክልም አይደለም።እናም የፋሲል የኔአለም መረጃ ግልቡ (ገብስ ገብሱ) ትክክል ነው።በእኔ እምነት ሌላ ነገር ያለው ይመስለኛል።ደግሞም ለበጎም ይሀን ከተንኮል የተሰራ ስህተት አለ።

አሁን ግን ለጊዜው መፍትሄው ላይ እናተኩር የሚለውን እመርጣለው።እናሳ? ካላችሁን መፍትሄው ፕሬዝዳንትነቱን ውድቅ ማድረግ አልያም አዴፓን ጥሎ መውጣት ነው።ሁለተኛው አስደንጋጭ ይሆናል።ነገር ግን የታሰረች ዶሮ ጠባቂ ከመሆን ሜዳ ላይ ያለ እንስሳን በማገት ቢያንስ ህሊናህ እረፍት ያገኛል።ተፈጥሮውን ታያለህ።ስፖርት ትሰራለህ።ደግሞ ከአቻ ሰው ጋር ታወራለህ።
ችግር የሚመስለኝ የዶ/ር አምባቸው ጉዳይ የፌደራል ካቢኔ ከመወሰኑ በፊት ወይም በዚያው ሰዓት ይመስለ ለፕሬዝዳንትነት የተወሰነው።ስለዚህ ምደባው ላይ አልተካተተም።በወቅቱ በአምባቸው ጉዳይ የብአዴን የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ እለት ከተሳታፊዌች ውስጥ በተለያየ ምክንያት የተቃወሙ፣በልዩነት የወጡ፣ዝም ያሉ፣የደገፉ እያልን ልንዘረዝር እንችላለን።ግን ያ አልፏል።ስለሆነም አሁን ሹመት ሁሉ ስለተጠናቀቀ ዶ/ር አምባቸው ፕሬዝዳንትነቱን ይተው የሚለው የፀና አቋሜ ቢሆንም ክፍት የሚኒስትር ቦታ የለውም።በሌላ አባባል መዋቅር ሲሰራ ተንሳፋፊ ነው ማለት ነው።

ስለዚህ ዶ/ሩ ማረፊያው ምን ይሆናል? የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው።አምባሳደር?አማካሪ? ጽ/ቤት ሀላፊ?ወይስ ወደ ባህር ዳር ሂዶ የሆነ ቢሮ መምራት? ብቻ መጀመሪያ የተሰራው ጥቃቅን ስህተት ምስቅልቅል ያደረገው ይመስላል።ስለዚህ እንደተዳፈነ ፕሬዝዳንትነቱን እስከ ችግሩ ይዞ ከፖለቲካ ውሳኔ ርቆ ቢቀጥል ይሻላልን? የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው።በግሌ አይሻልም ነው።ፕሬዝዳንትነቱም ይተወውና ድርጅቱ በመደበው ይስራ ነው የምለው። እንደሚተወውም አምናለው።

በእኔ እምነት ዋናው አምባቸውን የምፈልግበት ዋና ምክንያት አምባቸው መድረክ ላይ መከራከርና ሀሳብ ማብላላት ስለሚችል ምናልባት የፖለቲካ ውይይቶች ግለታቸውን የጠበቁና ፍፃሚያቻውም የአማራን ጥቅም ያስከበሩ እንዲሆኑ ይታገላል ከሚል ቀናነት ነው።ከዚህ በፊት በነበሩ አንዳንድ ጉዳዮች በልዩነት እንደወጣ ሁሉ እናስታውሳለን።ለምሳሌ በግጨው ጉዳይ ስህተት ውሳኔ ነው ብሎ በልዩነት መውጣቱንና ኢሳት መዘገቡን አስታውሳለው።የእኔ እምነት እንዲህ አይነት ለጊዜው ፈታኝ/ቀላል የሚመስሉ ኪሳራቸው ግን አደገኛ የሚሆኑ ጉዳዮች ላይ መድረኩን በመጋፈጥ አብሮ ይታገል እንደሆን በሚል ነው።በ2008 ዓ.ም በአማራ ላይ በተፈፀመ ጭፍጨፋ አምርሮ የተቃወመ እንደሆነም ይታወቃል።

የሆነው ሁኖ አሁን ሌላ ምዕራፍ ነው።አምባቸው ልክ እንደ እነ ገዱና ደመቀ ሁሉ በመሰረታዊ የፖለቲካ ውሳኔዎች ለአማራ ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ።በነገራችን ላይ ደመቀን ባለበት እንዲቀጥል በብአዴን ጉባኤ ምሽትና ጠዋት በእጅጉ ያግባቡ ባለሀብቶችና ወጣቶች የአምባቸውንስ ጉዳይ ምነው መፈፀም አልቻሉም? የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው።

መደምደሚያ:-

አምባቸው ፕሬዝዳንት አይሆንም ብየ አምናለው፤ከሆነም ክህደት ነው፤ተገፍቶ ከተደረገም ተመሳሳይ ሴረኛ ክህደት ነው።እናም ፖለቲካው ውስጥ መቆየት አለበት።ከዚያ ማረፊያው ምን ይሁን? የሚለውን ድርጅቱ ይወስን።

የማዕከላዊ ኮሚቴው ልክ በጉባኤው ወቅት የደመቀን ጉዳይ እንደተመለከተው ሁሉ (እንደ ፓርቲ አካሄድ ትክክል ነው አይደለም ጊዜ የሚፈታው ሁኖ) የአምባቸውን የፕሬዝዳንትነት ጉዳይም በጥንቃቄ ተመልክቶ (ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን) በጥቅምት 13 ውይይቱ ውድቅ ማድረግ እና አምባቸውም በፖለቲካ ትግሉ እንዲቀጥል ማድረግ አለበት ብየ በፅኑ አምናለው።መልዕክቴንም ለምታውቋቸው አመራሮች ሁሉ በInbox and በShare ታድርሱ ዘንድ እጠይቃለው።

ከዚህ ባለፈ አንዳንድ መረጃዎችን እያወጡ የሰዎችን የልብ ትርታና ስሜት ለመለካት የሚደረግ ጨዋታ አይጠቅምምና ብንቀንሰው ደስ ይለኛል። ለምሳሌ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነ ተብሎ የተወራው ፍላጎት ካልሆነ በስተቀር ፍፁም ስህተት ነው።ምናልባት ይህም ስሜትን ለመለካት ይሆናል።በእኔ እምነት ክልሉ በገዱ፣መላኩ፣ላቀና ምግባሩ ቅንጅት ቢመራ እመርጣለው።ያም ሆነ ይህ የሚሆነውን ከሳምንት በኋላ እናያለን።ግምቶች አሉ። መላኩ አለበልና (ከሚኒስትርነት የተነሳው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ) እና ላቀ አያሌው (የብአዴን ስራ አስፈፃሚ) የገዱ ምክትል ይሆናሉ ተብሎ ጭምጭምታ አለ።እንዲሁም ምግባሩ ከበደ በምክትል ር/መስተዳደር ማዕረግ የብአዴን ፅ/ቤት ሀላፊ ሁኖ ሹመት ፀድቆለታል።ቲሙ ጥሩ ይመስለኛል።

(N.B አምባቸው ፕሬዝዳንት ለመሆን ፈለገ ካልን ለምን? የሚለውን ከብዙ ወገን እናጣራ።ቁልፉ እዛ ጋር ነው።ከዚያ በመለስ ያለው ትርፍ ነውነው።እንደወረደ አይፃፍም))

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *